ሱር ኮንስትራክሽን ዋና ቢሮውን ትግራይ ክልል አዘዋወረ

Views: 527

ከ30 በላይ ፕሮጀክቶች በመኖራቸው ነው አንዳንድ የሥራ አባላት ወደ ትግራይ የሄዱት (ታደሰ የማነ)

በሕዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ ባለቤትነት ስር የሚተዳደረው እና በርካታ የልማት ድርጅቶችን አቅፎ በያዘው ትግራይ መልሶ ማቋቋም (ኤፈርት) ተብሎ በሚጠራው ድርጅት ውስጥ ከሚገኙ ድርጅቶች አንዱ የሆነው ሱር ኮንስትራክሽን ዋና ቢሮውን ወደ መቀሌ ማዘዋወሩ ተገለፀ።

ምንጮች ለአዲስ ማለዳ እንዳስታወቁት የኮንስትራክሽን ድርጅቱ በቦሌ ሸዋ ዳቦ አፍሪካ ጎዳና ተብሎ በሚጠራው ስፍራ ባስገነባው የራሱ ግዙ ሕንጻ አገልግሎት ይሰጥ የነበረ ሲሆን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ወደ ትግራይ ክልል መዲና መቐለ ማዘዋወሩን ለማወቅ ተችሏል።

ሱር ኮንስትራክሽን ዋና ቢሮውን ወደ ትግራይ ያዘዋወረው ኮቪድ 19 ከገባ ከወራቶች በኋላ መሆኑን ለዚህም ደብዳቤ እንደደረሳቸው በድርጅቱ ውስጥ የሚሰሩ ማንነታቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ የአዲስ ማለዳ ምንጮች ተናግረዋል።

ሱር ኮንስትራክሽን ውስጥ ከሚሰሩ ሰራተኞች መሀል የሆኑት አዲስ ማለዳ ምንጭ እንደተናገሩት ከሆነ ኮቪድ 19 ከገባ በጥቂት ቀናት በኋላ ዋና ቢሮው ትግራይ ክልል መቀሌ ከተማ ማድረጉን የገለፁ ሲሆን በዚህም አፍሪካ ጎዳና ሜጋ ሕንጻ አጠገብ ዋና ቢሮው የነበረው ሱር ኮንስትራክሽን አዲስ አበባ የሚገኙ ሰራተኞቹን ፈቃድ እንደሰጠ እና ምክንያቱ ደግሞ ኮሮና ኢትዮጵያ መግባቱን ተከትሎ እንደሆነ እንደተገለፀላቸው ጠቅሰዋል።

ድርጅቱ ይህን ይበል እንጂ ከቀናት በኋላ በአዲስ አበባ ለሚገኙ ሰራተኞች የተገለፀው ፈቃደኛ ሆነው ትግራይ ክልል መቀሌ ገብተው መስራት ከፈለጉ እንደሚችሉ እና ካልሆነ ግን በገዛ ፈቃዳቸው ስራቸውን እንደለቀቁ እንደሚወሰድ እንደተነገራቸው አዲስ ማለዳ ከምንጮቿ አረጋግጣለች።

ከዚህ ጉዳይ ጋር ያነጋገርናቸው የሱር ኮንስትራክሽን ዋና ስራ አስኪያጅ የሆኑት ታደሰ የማነ ለአዲስ ማለዳ እንደተናገሩት ከሆነ በኮንስትራክሽን ዘርፍ ላይ ተሰማርቶ ያለው ሱር ኮንትራክሽን ከዚህ ቀደም የነበረውን ዋናውን ቢሮ አለመልቀቁን እና ቅሬታውም ከእውነት የራቀ ነው በማለት ተናግረዋል።

ዋና ስራ አስኪያጁ እንደሚሉት ከዚህ ቀደም የሱር ኮንስትራክሽን ዋና ቢሮ የሚገኝበት ደምበል አካባቢ ከሜጋ ህንፃ ጎን እንደሆነ እና አሁንም እዛው እንዳለ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።
ታደሰ ጨምረውም አሁን ደምበል አካባቢ የሚገኘው ቢሯቸው አገልግሎት እየሰጠ ያልሆነበት ምክንትን ሲጠቅሱ፤ በትግራይ ክልል ከ30 በላይ ፕሮጀክቶች በመጀመራቸው እና ሱር ኮንስትራክሽንም ለስራው ቅርብ መሆን ስላለበት አንዳንድ ዋና ዋና የስራ ኃላፊዎች ወደዛው መቅረብ ስላለባቸው መሆኑን ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

ነገር ግን ይላሉ በፕሮጀክቱ ላይ ለመሳተፍ ምን ያህል ሰራተኞች እንደሄዱ በቁጥር እንደማያውቁ እና አዲስ አበባ ከሚገኘው ዋናው ቢሮም ምንም አይነት ሰራተኛ በእረፍት ላይ አይገኝም ሲሉ አስተባብለዋል።

ሱር ኮንስትራክሽን በኤፈርት ስር ከሚገኙ ወደ 14 የሚጠጉ ድርጅቶች ውስጥ አንዱ ሲሆን በአሁኑ ወቅት ከሦስት ሺሕ በላይ ቋሚ እና ከሰባት ሺሕ በላይ ደግሞ ቀን ሰራተኞችን በስሩ ሚያስተዳደር ግዙፍ ኩባንያ እንደሆነም ለማወቅ ተችሏል።

ከ20 ዓመታት በፊት በ108 ሚሊዮን ብር ካፒታል የተመሰረተው ሱር ኮንስትራክሽን በሕወሓት ባለቤትነት በሚመራው ኤፈርት ኩባንያዎች አንዱ አካል እንደሆነም ይታወቃል።
ሱር ኮንስትራክሽን በአገር ውስጥ ካሉ ኮንስትራክሽኖች ደረጃ አንድ ግንባታ ድርጅት ሲሆን፤ ሀይድሮፓወር ፕሮጀክቶች እና የመኖሪያ ቤት ግንነባታዎችም ላይ በስፋት እንደሚሳተፍም ይታወቃል።

ከተሳተፈባቸው ፕሮጀክቶችም መካከል በከፍተኛ ወጪ እየተገነባ የሚገኘው የዛሬማ ሜይዴይ ግድብ አንዱ ሲሆን በአገር በቀል ድርጅቶች ይህን የሚያክል ከፍተኛ በጀት ያላቸውን ፕሮጀክቶች በዋና ተቋራጭነት በመሳተፍ ሱር ቀዳሚው ድርጅት ነው። በተመሳሳይም በመቐለ ከተማ መኖሪያ መንደርም በመገንባት ስራ ላይም ተሰመራርቷል።

ቅጽ 2 ቁጥር 96 ነሐሴ 30 2012

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com