የአዳማ ኢንደስትሪያል ፓርክ ሰራተኞችን ቅጥር መንገድ ይፋ አደረገ

Views: 323

በኦሮሚያ ክልል አዳማ ከተማ የሚገኘው የአዳማ ኢንደስትሪያል ፓርክ ከዚህ ቀደም አዳዲስ ሰራተኞችን ይቀጥርበት የነበረውን መንገድ በአዲስ መተካቱን ፓርኩ ለአዲስ ማለዳ አስታወቀ።

ከዚህ ቀደም ፓርኩ ሰራተኞችን ለመቅጠር ማስታወቂያ በመለጠፍ እና ስራ ፈላጊዎችም በግንባር በመምጣት ይመዘገቡ እንደነበረ የሚታወቅ ሲሆን፤ አሁን ግን በአዲስ መልክ ስራ ፈላጊዎች በክልሉ የሰራተኛና መኅበራዊ ቢሮ ሔደው በመመዝገብ እና በጥቃቅን እና አነስተኛ በመደራጀት በፓርኩ ተቀጥረው ለመስራት ፍላጎት ያላቸው ሰዎች መቀጠር የሚችሉበት መንገድ መጀመሩን ይፋ አድርጓል።

ሰራተኞችን ለመቅጠር በተመረጡ አራት ዞኖች ላይ የሚገኙ ሰራተኞችን በመለየት ብሪጅ ከተባለ ግብረ ሠናይ ድርጅት ጋር ስልጠና እንዲያገኙ በማድረግ ወደ ስራ እንደሚገቡ የአዳማ ኢንደስትሪያል ፓርክ ለአዲስ ማለዳ አስታውቋል።

በፓርኩ ውስጥ የኢንዱስትሪ ሠላማዊ ግንኙነት ዋና ዳይሬክተር የሆኑት ሽመልስ ታዩ ለአዲስ ማለዳ እንዳስታወቁት ከሆነም ለኢንቨስትመንት መሬታቸውን የሠጡ ሰዎች ልጆቻቸው ቅድሚያ ተሰጥቷቸው ወደ ሥራው እንዲገቡ ለማረግ እየተሰራ እንደሆነም ለማወቅ ተችሏል።

የቅጥሩን ሁኔታ በክልሉ ውስጥ ከሚገኙ የሠራተኛ ማህበራዊ ጉዳይ ጽሕፈት ቤት እና ከጥቃቅን እና አነስተኛ ኢንትርፕራይዝ ጋር በተፈጠረው የሥራ ትስስር መሆኑንም ሽመልስ ገለጸዋል።

የሥራ ትስስሩን በጋራ መሥራት ያስፈለገበትን ምክንያት ለአዲስ ማለዳ ያስረዱት ሽመልስ፤ የሥራ አጡን ቁጥር ለመቀነስ ብሎም ወደ ስራ ለመግባት በተቀመጠለት መንገድ ወይም መስፈርት መሠረት በቃሉ ወደ ሥራ እንዲገቡ ለማድረግ ያለመ እንደሆነ ገልጸዋል።

ሌላው ደግሞ ይላሉ ዋና ዳይሬክተሩ ሽመለስ፤ በኢንደስትሪያል ፓርክ ውስጥ የሚገኙት ድርጅቶች የሚፈልጉት የሰለጠነ እና ስለ ሥራው በቂ ግንዛቤ ያለው ሠራተኛ በቀላሉ እንዲያገኙ ለማድረግ የታሰበ እደሆነም አስታውቀዋል፡፡

እንዲሁም ቀደም ሲል የተጠቀሰው መሬታቸውን ለኢንደስትሪያል ፓርኩ ግንባታ የሰጡ ሰዎች ልጆች በቅድሚያ የሥራ እድሉን አግኝተው ወደ ስራ እንዲገቡ ለማድረግ ያለመ እንደሆነው ነው የፓርኩ የኢንደስትሪ ሠላማዊ ግንኙነት ዋና ዳይሬክተር ተናግረዋል።

በኢንደስትሪያል ፓርክ የሚገኙ ድርጅቶች ሠራተኞችን መቅጠር ሲፈልጉ ለፓርኩ የኢንደስትሪ ሠላማዊ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት ፍላጎታቸውን በማሳወቅ ሰራተኞች መቀጠር እንደሚችሉ ለማወቅ ተችሏል።

በክልሉ ከሚገኙት አራት ዞኖች ማለትም የምስራቅ ሸዋ ዞን፣ የምስራቅ አርሲ ዞን፣የምዕራብ ሀረርጌ ዞን እና አዳማ ከተማ ውስጥ የሚገኙ ወጣቶች የእድሉ ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ሽመልስ ለአዲስ ማለዳ አስረድተዋል።

በፓርኩ ውስጥ ያሉ ድርጅቶች ምን ያህል ሰራተኞችን እንደሚፈልግ ካሳወቁን በኋላ የሚፈለገውን የሰው ኃይል ቁጥር እንዲያገኙ ለማድረግ ከስምምነት ላይ መደረሱንም እንዲሁም አስታውቀዋል፡፡

ዋና ዳይሬክተሩ ለአዲስ ማለዳ እንደገጹት ከሆነም በኦሮሚያ ክልል የሚገኙት ከላይ የተጠቀሱት አራቱ ዞኖች ትስስር የተፈጠረላቸው ለአዳማ ኢንዱስትሪያል ፓርክ ቅርብ በመሆናቸው ነው ብለዋል።

በቀጣይም ከኢንዱስትያል ፓርኩ ውጭ ላሉ እና ፍላጎት ላላቸው ድርጅቶች ሰራተኞችን በትስስር ለማቅረብ የሚቻልበትን ሁኔታ እንዲመቻች ይደረጋል ነውያሉት።
በተማጨሪም በአዳማ ኢንደስትሪያል ፓርክ የኢንደስትሪ ሠላማዊ ግንኙነት በዳይሬክተሬት ክፍል ውስጥ የስራ እድል እንዲኖር ከመስራት በተጨማሪም በሚሠጠቸው ስልጠና የሥራ ባህሪ እና የስራ ባህላቸውን እንደሚቀይርላቸውም ገልጸዋል።
በዚህ ድርጅቶቹም ቢሆን ብቃት ያላቸውን ባለሙያ ለማግኘት እደሚረዳቸው ነው ሽመልስ ያመላከቱት።

በአጠቃላ በኢንዱስትሪ ሠላማዊ ግንኙነት ዳይሮክቶሬት ክፍል ውሰጥ ሰላማዊ የሥራ አካባቢ እንዲፈጠር ለማድረግ እንደሚሰራም ሽመልስ ገልጸዋል።
ከተቋቋመ ሦስት ዓመታትን ያቆጠረው የአዳማ ኢንደስትሪያል ፓርክ በአሁን ወቅት 4ሺህ 861 ሠራተኞች እንዳሉት ከፓርኩ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

ቅጽ 2 ቁጥር 97 መስከረም 2 2012

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com