2012 በጥበብ ዘርፎች ዕይታ

Views: 88

ቀን ቀንን እንደሚያድስ፣ በተመሳሳይ ሰማይና ፀሐይ ነገር ግን ሌሊትን በተሻገረ ቁጥር አዲስ ቀን እንደሚገኝ፣ አዲስ ዓመትም እነሆ መጥቷል። ከ365 ቀናት በፊት አዲስ የነበረውና በወረት የተቀበልነው 2012 አሁን አሮጌ ተብሏል። ክፉውም ደጉም አልፎበት፣ መሠረት ግን ሆኖ፣ በሌላ ተስፋ፣ በሌላ ስጋት 2013 ዘልቋል። አዲስ ማለዳ እንደ ወትሮው 2012 በጥበብ ዘርፍ ልትቃኝ ወዳለች።

ቴአትር
የቴያትር ጥበብ የሰው ልጅ ሕይወት፣ የአኗኗር ዘይቤ፣ ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ እሳቤውን በመድረክ ላይ የሚገለፅበት አንዱ የኪነ ጥበብ ዘርፍ ነው። ታዲያ ይሄ ዘርፍ ባሳለፍነው የ2012 ከመቼውም ጊዜ በበለጠ በከፍተኛ ሁኔታ ተጎድቶና ተቀዛቅዞ ነበር።

ቴአትር የመድረክ ሥራዎቹ የብዙ ሰዎችን ቅንጅት የሚጠይቁ፤ ተመልካቹም በአንድ አዳራሽ ውስጥ ተሰብስቦ የሚታደማቸው ናቸው። በአገራችን ብሎም በዓለም ዙሪያ ከፍተኛ ስጋት ሆኖ የተከሰተው የኮቪድ 19 ኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ለዘርፉ ከፍተኛ የሆነ ተግዳሮትን ፈጥሯል።

‹‹2012 እንኳን ሄደልን የሚባል ዓመት ነው›› የሚለው የአገር ፍቅር ቴአትር ተዋናይ እና በብዙ የፊልም ሥራዎቹ የምናውቀው ተሾመ ወርቁ ነው። ተሾመ ከአዲስ ማለዳ ጋር በነበረው ቆይታ ያለፈው ዓመት በአገራችን ብቻ ሳይሆን በዓለም ደረጃ ማለፉ ደስ የሚያሰኝ ዓመት ነው ብሎታል።

ከመጋቢት ወር በኋላ በቴአትር ቤቶች የነበሩ ቴአትሮች ቆመው ቴአትር ቤቶቹም ተዘግው እንደከረሙ ያስታውሳል። ‹‹እንደውም በአገር ፍቅር አብዛኞቹ ይታዩ የነበሩት ቴአትሮች ከ2012 በፊት የወጡ ናቸው።›› የሚለው ተሾመ፣ ከመጋቢት በኋላ በኮሮና ወረርሽኝ ላይ ትኩረት ያደረጉ የቴሌቭዥንና የሬዲዮ ሥራዎችን በመሥራት ላይ እንደነበሩ ይናገራል።

‹‹ያሳለፍነው 2012 በቴአትር ቤትና በቴያትረኛው ላይ መጥፎ ጥላ ያጠላ ዓመት ነበር።›› በማለት የሚገልፀው ተሾመ፣ ‹‹አዳዲስ ሥራዎችን ለመሥራት የማትነሳሳበት ነበር። ተመችቶህ እንኳን ልሥራ ብትል የምታየውና የምትሰማው ነገር ሥራህን እንድትሠራ የሚገፋፋ አይደለም። ለዚህም ነው እንኳንም ሄደልን ያልኩት።›› ሲል ዓመቱ በዘርፉ ያሳደረውን ጫና በምሬት ይገልፃል።

በአገር ፍቅር ቴያትር ቤት በ2012 ‹አሉ› የተሰኘ ቴአትር ተሠርቶ ለታዳሚዎች ቀርቦ የነበረ ሲሆን፣ ከዛ ውጪ ልምምድ ላይ የነበሩ ቴአትሮች በኮቪድ 19 ምክንያት ልምምዱ መቆም ስለነበረበት እንዲቆሙ ተደርገዋል። በተመሳሳይም በሌሎች ቴአትር ቤቶችም መሰል ሁኔታዎች በመከሰታቸው ያለፈው 2012 አሮጌ ዓመት ላይ ብዙም የመድረክ የጥበብ ሥራዎች አልተሠሩም።

በአሁን ሰዓት አራቱ ቴአትር ቤቶች በጋራ በመሆን ታዳሚ አልባ የሙዚቃ ሥራን ለሕዝቡ ለማስተላለፍ በአገር ፍቅር ቴአትር ቤት እየተቀረፁ እንደሚገኙ የገለፀው ተሾመ፣ በቀጣይም አስፈላጊውን ጥንቃቄ በማድረግ እንቅስቃሴ የሚጀመር እና የመድረክ ትርኢቶችም ይኖራሉ ብሎ እንደሚያስብ ይናገራል።

በ2012 ከፊልም ሥራ እንዳልራቀ ያወሳ ሲሆን፣ ከወረርሽኙ በፊት ‹81› የተሰኘ ፊልም ላይ በተዋናይነት ሠርቷል። በመቀጠልም ከኮሮና ወረርሽኝ በኋላ የተለያዩ በዩ-ቲዩብ ላይ ለእይታ የቀረቡ ኹለት ፊልሞችን እንደሠራ ጠቅሷል። አሁን ደግሞ ራሱ በድርሰት፣ በትወናና በዳይሬክቲንግ የተሳተፈበት ‹ኳራይንታይን› የተሰኘ ፊልም በዩ-ቲዩብ ለእይታ እንዲበቃ ሠርቻለሁ ብሏል።

በ2013 ሁሉ ነገር መልካም ከሆነና ወደ ቀድሞው ቦታው ከተመለሰ ቀጣይ ሥራዎችን እሠራለሁ ብሎ አቅዷል። እንደ አገርም ‹‹ምንጊዜም የአገራችንን ነገር ሁሌ ለፈጣሪ ነው የምሰጠው። መጸለይ ነው፤ ሌላ ምንም መፍትሄ የለውም።›› በማለት በአዲሱ ዓመት በኢትዮጵያ ላይ ያለውን ተስፋ በፈጣሪ ላይ መጣሉን ያስረዳል።

ፊልም
አሁን አሁን የፊልም ቴክኖሎጂው ተራቋል። የተለየ ጥራትና ብቃት ያላቸው ካሜራዎችም ወደ አገራችን እየገቡ ነው። ነገር ግን የካሜራ ጥራት ብቻ አንድን ፊልም ፊልም ሊያስብለው አይችልም። የደራሲው ብቃት፣ የዳይሬክተሩ ችሎታ፣ የተዋናዩ መሰጠትና መሰል በፊልም ሥራ ውስጥ የሚያስፈልጉ ግብአቶች ሁሉ ሲሟሉ ያኔ ልክ ይሆናል። ለወትሮውም የዘውግና የተዋናዮች ተመሳሳይነት ‹እድገቱ›ን ሙግት ውስጥ ያስገባው የአገራችን የፊልም ኢንዱስትሪ፣ ባሳለፍነው ዓመት በኮሮና በወረርሽኝ ሳቢያ ጭራሹኑ መውደቁን ብዙዎች ይገልፃሉ።

‹‹ከሕዝቡ ጋር አብሬ እንደ መኖሬ አብዛኛው ማኅበረሰብ እንደ ሆነው ሁሉ መጀመሪያ አካባቢ በጣም ደንግጫለሁ። ከቤት መውጣትም አልነበረም።›› የሚለው በተለያዩ ፊልሞች ላይ በአዘጋጅነትና በተዋናይነት ሲሠራ የሚታወቀው ሰለሞን ሙሄ ነው። ሰለሞን ያሳለፍነውን 2012 ወደኋላ መለስ ብሎ በማስታወስ ከአዲስ ማለዳ ጋር ባደረገው ቆይታ፣ ኮሮና በአገራችን ከተከሰተበት ወቅት አንስቶ አብዛኛውን ጊዜውን ከስለእናት የበጎ አድራጎት ድርጅት ጋር አብሮ በመሥራት እንዳሳለፈ ያስረዳል።
‹‹ድርጅቱ ያለፈውን ዓመት ያሳለፈበት ሁኔታ አሳሳቢና እስከመዘጋት የሚያደርስ ችግር ላይ ነበር። ስለዚህ እነሱን የመርዳትና ግንዛቤ የመፍጠር ሥራ ላይ ትኩረት ሰጥቼ እየሠራሁ ነው ያሳለፍኩት። አሁን ደግሞ ወደሥራ ገብቻለሁ።›› በማለት በግሉ ኮሮና ከፊልሙ ሥራ ቢያርቀውም በበጎ አድራጎቱ ላይ በመሳተፍ የራሱን አስተዋፅዖ ሲጫወት መቆየቱን ይገልፃል።

‹‹የዩ ትዩብ ሥራዎች ናቸው በብዛት እየተሠሩ የነበሩት።›› የሚለው ሰለሞን፣ የፊልም ባለሞያዎች ያለውን አማራጭ መጠቀማቸውን የሚደግፈው ጉዳይ እንደሆነ ያወሳል። ‹‹ልክ ነው! ሰዎች መሞት የለባቸውም። የቤት ኪራይ አለባቸው፤ በልተው ማደር አለባቸው። ስለዚህ የሲኒማው አማራጭ ሲዘጋ ፊታቸውን ወደ ዩ ትዩብ በማዞር ሲሠሩ ነበር።›› በማለት ጠቅሷል።

በግሉ ያሳለፈውን ሲያወሳም፤ ‹‹እንደ አጋጣሚ እኔ ኮሮናው ከመግባቱ በፊት የተለያዩ የሲኒማ ፊልሞችን ለመሥራት ቀብዶችን ተቀብዬ ነበር። ያው ሥራውን መቀጠላችን ስለማይቀር እርሱን እየተጠቀምኩ ቆይቻለሁ። የተቋረጡትንም የሲኒማ ፊልሞችም አሁን ከጀመርናቸው ሦስት ወራት ተቆጥረዋል፤ እየሠራናቸው እንገኛለን። ኮሮናው በሚፈቅደው መንገድ የዩ ትዩብ ሥራዎችንም በማዘጋጀት ረገድ ፊልሙ ላይ ያለው ማሕበረሰብ ሲሠራ ነበር። ምክንያቱም መኖር አለበት።›› ብሏል።

እንደ ሰለሞን ገለጻ በአጠቃላይ በኮሮና ምክንያት ተጀምረው የተቋረጡ ፊልሞች አሉ። አሁን እነሱን መቀጠል በጣም ከባድ እንደሚሆን ነው የሚያስረዳው። ምክንያቱ ደግሞ ከኮንቲኒቲ ጀምሮ ፊልሙ ተጀምሮባቸው የነበሩ የቀረፃ ቦታዎች ሁሉ መልካቸውን ስለሚቀይሩ፣ ታሪኮቹም ከወቅታዊነት አንጻር አሁን ላይ ላይፈለጉ መቻላቸው እና ሌሎች የተለያዩ ተያያዥ ጉዳዮች ናቸው።

አክሎም ወጪ አውጥተው ጀምረው የከሰሩ ያሉ ሰዎች እንዳሉ ጠቁሟል። አብዛኞቹ ፕሮድዩሰሮች ገንዘብ በማገላበጥ ነበር የሚሠሩት ያለ ሲሆን፣ የጊዜው ሁኔታ የሚያሠራ ባለመሆኑ ምክንያት ነገ ወይም ወደፊት ፊልም የሚያዘጋጁበት (ፕሮድዩስ የሚያደርጉበት)ን ገንዘብ በልተው ጨርሰዋል።

‹‹ስለዚህ ኮሮና ቢጠፋና ችግሩ ሁሉ ቢቀረፍም እንኳን በፊልሙ ኢንዱስትሪ ላይ ወደፊትም የሚቀጥል ተፅዕኖን አርፏል። ወደፊት ልናገኛቸው የማንችላቸው ሰዎች አሉ። ወደ ገበያው አሳምነን ያመጣናቸው፣ የተሻለ ዘርፉን ሊረዱ ይችላሉ ያልናቸውን ጥሩ ጥሩ ሰዎች አጥተናል።›› ሲል አክሏል።

‹‹እኔ በግሌ እንደ ግለሰብ ምንም ያህል ኃጢአተኛ ብሆንም በየትኛውም መንገድ በፈጣሪ በጣም እተማመናለሁ። ፊልሙ ቀጠለ አልቀጠለ እኖራለሁ፤ ለምን? ፈጣሪ ስለሚያኖር ብቻ።›› ይላል ሰለሞን፤ በ2013 ምን ተስፋ ይታይሃል ለሚለው ጥያቄ ሐሳቡን መስጠት ሲጀምር።

‹‹ሲኒማ ቤት ተከፈተ አልተከፈተ ባናውቅም፤ የተጀመሩ ፊልሞችን እየጨረስን አዳዲሶቹንም እየጀመርን እንገኛለን። እዚህ አገር ላይ ሕግ ይወጣልለ ቶሎ ቶሎ ይቀየራል። ምንም ለማቀድ አይመችም። ዝም ብሎ መሥራት ነው።›› ብሏል።

እንደ አገር በ2012 የታዩ መልካም ያልሆኑ ክስተቶችን ያነሳው ሰለሞን፣ ወንድሙን የሚገድል፣ የአገር ንብረት የሚያወድም ‹ማኅበረሰብ› ተፈጥሮብናል ይላል። በቀጣዩ አዲስ ዓመት 2013ም ዳግም እንዲያ ያለ ነገር ባያጋጥም ደስ እንደሚሰኝ፤ ምኞቱን ገልጿል። ‹‹ያ ማለት ግን እውነት ተደብቆ ይለፍ ማለት አይደለም። ታሪክ ተድበስብሶ መቅረት የለበትም። እኔ ያጠፋ ተቀጥቶ የተበደለ ደግሞ ተክሶ ማየት እፈልጋለሁ።›› ሲል መሻቱንም ተናግሯል።

ስዕል
2012 ከብዙ አቅጣጫዎች በጣም ብዙ ውጣውረዶች እና ፈተናዎች የነበሩበት ነው ያለው የስዕል አውደ ርዕዮች አዘጋጅ ፍጹም ጥላዬ፤ በየቦታው ያሉ ባለሙያዎች አሁን በከፍተኛ ሁኔታ ተጎድተዋል። ገቢ እያጡ ነው። ሥራቸውን የሚያይላችውም ሆነ የሚገዛቸው ሰው አያገኙም ሲል ያክላል።

በኢትዮጵያ የተከሰተው አለመረጋጋት ከኮሮና ወረርሽኝ ጋር ተዳምሮ የስዕል ጥበቡን በከፍተኛ ሁኔታ ጫና ውስጥ እንዲቆይ አድርጎታል። እንዲህ ባለ ጊዜ ሥራዎችን ወደ ዲጂታል ቀይሮ መሥራት የሚቻልበትን ሁኔታ በማጥናት ላይ እንደሚገኝ ያነሳው ፍጹም፣ ባለው ወቅታዊ ሁኔታ ሳቢያ የስዕል አውደርዕይም ይሁን ሽያጭ በዲጂታል ሥራ መሠራ አለበት ብሎ በማመኑ ሥራውን ለመጀመር እየሠራ እንደሆነ ጠቅሷል።

‹‹ነገሮች ቀስ እያሉ ያሻሻላሉ፤ ባሳለፍነው ዓመት በነበሩት አስቸጋሪ ቆይታዎች ሰው ወደ እራሱ እንዲመለከትና እራሱን እንዲጠይቅ ይሆናል ብዬ አስባለሁ።›› ያለው ፍጹም፤ ሰው ወደራሱ ሲመለስ ደረስኩበት የሚለው ነገር ሁሉ በጣም በትንሽ ነገር መቆም የሚችል መሆኑን ስለሚያውቅ፣ ደግሞም ከብር ለሰው ሕይወት እንዲሁም ለዛሬ እንዲሰጥ ያደርገዋል የሚል እምነት እንዳለው ያነሳል። ‹‹ስለዚህ አርቲስቶችም ብዙ ራሳቸውን ያዩበትና የገመገሙበት ወቅት ነበር። በዚህ በአዲሱ ዓመት በጣም ብዙ የፈጠራ ሥራዎች ይኖራሉ ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ›› ሲል ተስፋውን ገልጿል።
በአሁኑ ሰዓት በጣም ድብልቅልቅ ያለ ነገር እንደሚታየውም አልሸሸገም። ሆኖም ከሚወራውና ከሚታየው ባሻገር መሬት ላይ የወረደውን ነገር ሲያይ ተስፋ

እንደሚታየው ጠቅሷል። ‹‹በአገራችን በጣም ትልልቅ ፕሮጀክቶች በብዙ ቦታዎች ላይ አሉ። እነሱ አልቀው የምናይበት ዓመት ስለሚሆን ለእኔ ተስፋ ነው የሚታየኝ።›› ብሏል።

ሁሉም ጊዜና ተራ አለው የሚለው ፍጹም፣ ‹‹ሁልጊዜም እንደዛ ነው የሚሆነው፤ አንድ አካባቢ ላይ አንድ ውጥረት ወይም ጭንቀት ከነበረ፣ በኋላ የግድ ተራውን ደግሞ ለሌላው መልቀቅ አለበት። ስለዚህ በአገር ደረጃም በጣም ብዙ የተሻሉ ነገሮች የሚመጡ ይመስለኛል።›› ሲል አክሏል።

‹‹መንግሥትም እየሠራቸው የሚገኙት ፕሮጀክቶች በጣም ብዙ ሰዐሊዎች እና ለሌሎችም የኪነጥበብ ሰዎች የሚሆኑ ቦታዎች ተፈጥረዋል። እና ያንን የሚጠቀም ማኅበረሰብ መፍጠር ይገባናል። እነዚህ ቦታዎች ላይ እነዚህ የኪነ ጥበብ ሰዎች ቦታ ተሰጥቷቸው ከማኅበረሰቡ ጋር የሚገናኙበት የኪነ ጥበብንም ፋይዳ የሚገልጹበት፣ መንግሥት ላይ ተቃውሞ ቢኖርህ ድጋፍ ቢኖርህ አንድ መንገድ ብቻ አይደለም መግለፅ የሚቻለው። በተለያዩ የኪነ-ጥበብ ዘርፎችም ማኅበረሰቡ ሐሳቦቹን፣ ስሜቶቹን፣ ለአገሩ ያለውን ተስፋ ለቀጣዩ ትውልድ ያለውን ምኞት እና መልዕክት ማስተላለፍ የሚችሉበትን መድረክ መፍጠር ይገባል።›› በማለትም በሰፊው አስረድቷል።

ይህ እንዲሆን ታዲያ ሰላም እና አገር ወሳኝ ነው ያለው ፍጹም፣ ይህንን ደግሞ የሚደግፉ በመንግሥት ደረጃ ያሉ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶችና አካላት እንደሚያስፈልጉ አሳስቧል።

‹‹ድህነት በሁሉ መልኩ ይገለፃል። ከዛ ለመውጣት የምናስብ ከሆነ ሥነጥበብን የቅንጦት ነገር ሳይሆን ሰዎች አዲስ ዕይታን እንዲያስቡ፣ ያልተጨበጠ ያልታየን ነገር ቀድሞ በማየት ያንን ወደመመኘት፣ ቀጥለው ደግሞ በተሳካ የፕሮጀክት አፈፃፀም ወደ እውነታ ለመተግበር፣ ለመኖር፣ ለማየት፣ ለመቅመስና ለመዳሰስ ወደሚያስችል ደረጃ ማድረስ አለብን። የሚታየኝም ብሩህ ነገር ነው።›› ሲልም ተስፋውን አካፍሏል።

መጽሐፍ
ዓለማየሁ ገላጋይ በየዓመቱ አንድ አንድ የመጽሐፍ ሥራዎችን ለአንባብያን ማድረሱን የተያያዘው ብርቱ ደራሲ ነው። በ2012ም ‹ሐሰተኛው በእውነት ሥም› የተሰኘ መጽሐፍ ለአንባብያን አድርሷል። ይህን መጽሐፍም በዛው 2012 ጀምሮ ጨረሰውም በዛው ዓመት ነው። የሙሉ ጊዜ ጸሐፊ በመሆኑም በተረፈ ጊዜውን በማንበብ፣ ሰው በማግኘት መሰል እንቅስቃሴዎ ዓመቱን ማሳለፉን ከአዲስ ማለዳ ጋር ባደረገው ቆይታ አንስቷል።

በሕትመት ዘርፍ እንደቀደመው ጊዜ ሁሉ በየወሩና በየኹለት ወሩ ወረቀት እየጨመረ እንደሚመጣ ያወሳል። ‹‹ወደፊት ምናልባት ለህትመት ሁሉ መክፈል ሊከብድ ይችላል። ማሳተሙ ራሱ ትልቅ ፕሮጀክት እየሆነ ነው። በግለሰብ ደረጃ የማይቻል እየሆነ መጥቷል።›› ሲልም ያለፈውን ጊዜ የህትመት ሁኔታ ያነሳል።

በዚህ ሐሳቡ ላይ በመጨመርም ‹‹አሳታሚ ድርጅቶች አሁን በጣም ጥቂትና ኹለት ወይ ሦስት ናቸው። የነበሩትም አሳታሚዎች በሙሉ ተዘግተዋል። ስለዚህ ወደፊት ምናልባት የሆነ ተአምር መጥቶ የወረቀት ጉዳይ አደብ ካልገዛ በስተቀር አስፈሪ ነው የሚሆነው።›› ብሏል።

አንድ መጽሐፍ ታትሞ ሲደገም እንደገና የማሳተሚያ ዋጋው ላይ ተጨማሪ ይደረጋል። ቢያንስ በሳምንት ወይ በአስራ አምስት ቀን ልዩነት ነው ዋጋው ላይ ጭማሪ የሚያሳየው። በተጨማሪም የሚፈለገውን አይነት ወረቀት ላይገኝ ይችላል ወይም አይገኝም። ይህን ነጥብ ዓለማየሁ ሲያስረዳም አለ፤

‹‹አሁን የወረቀቱ ቅርፅ ኤ5 የሚባለው ብቻ ነው ያለው፤ አጭሩ የለም። አጭሩን ከፈለክ ያ ኤ5 የተባለው ተከርክሞ ነው የሚሠራው። ያ ደግሞ የመጽሐፉን ውበት ይቀንሰዋል። አገር ውስጥ የሚመረተው አንድ አይነት ወረቀት ነው። እሱንም አሟልተው ቶሎ አያደርሱትም። አንድ መጽሐፍ ለማሳተም ራሱ ከወር ከአስራ አምስት ቀን በላይ ጠብቀናል።››

በዚህ ጊዜ ደግሞ የወረቀት አምራቾች ካርቶን፣ ደብተር እንዲሁም ፖስት ካርድ መሰል ምርቶችን ቢሠሩ ነው የሚያዋጣቸው። ይህም ነገሩ የበለጠ እየተወሳሰበ የመጽሐፍ ጉዳይን አስፈሪ ያደርገዋል ሲል ስጋቱን ያነሳል። ‹‹ከዚህ በፊት ብዙ ስንታገል የነበረው አንባቢውን ለመጨመር ነበር። አሁን ላይ ከበፊት ጊዜያት የተሻለ የአንባቢ ቁጥር ላይ ብንደርስም፣ የማተሚያ ቤት ዋጋ እየጨመረ መሄዱ እጅግ አስፈሪ እየሆነ ነው የመጣው።›› የዓለማየሁ አስተያየት ነው።

በቀጣይ ጊዜና በዘለቀው 2013 አዲስ ዓመት ዓለማየሁ እቅዱና ዓላማው በተረጋጋ ሁኔታ ውስጥ አንብቦና ጽፎ የጻፈውን ማሳተም ነው። ያነበቡትን ወደ ጽሑፍ ግብአት ማስተላለፍና ያንን ጽሑፍ ደግሞ እንደገና ወደ ማተሚያ ቤት መውሰድ ነው።

‹‹በሚቀጥለው ዓመት አጋማሽ ላይ አንድ መጽሐፍ ይወጣል ብዬ አስባለሁ። ነገር ግን ቀድሞ ያነሳኋቸው ነገሮች ላይ ትኩረት ማድረግ ያለበት አካል ትኩረት ቢያደርግ ጥሩ ነው። እውቀት ማለት የአገር ጭንቅላት ነው። እውቀት አይቀረጥም ቢባልም በተዘዋዋሪ በወረቀቱ፣ በፕሌቱ፣ በኮላው እንዲሁም በሌሎች የህትመት ግብአቶች ላይ ዞሮ ዞሮ ያገኙታል። ቀረጠም እዛ ላይ ከጨመረ መጽሐፍ ላይ ነው እንደገና መጥቶ የሚያርፈው።›› ሲል ከግል እቅዱ በተጓዳኝ ያለውን ውጣ ውረድ አንስቷል።
በአገር ሰላምና መረጋጋት ዙሪያም ሐሳቡን ሲያካፍል እንዲህ አለ፤ ‹‹አሁን የተሻለ ሰከን ማለት ይታያል። የበለጠ ሰክኖ በአንድነት እየተወያየን ይህቺን አገር የምናስቀጥልበት እድል እንዲኖር ነው የምመኘው። ሌላው ሁሉ ከዚህ በኋላ ያለ ነው።

ይሄ ካልተሳካና መጥፎ ደረጃ ላይ ከደረስን፣ ሁሉም እቅዳችን ከንቱ ነው። ከማኅበረሰብ ጀምሮ እስከ ግለሰብ ድረስ ምንም ብናቅድ ምንም አይሆንም። እነ ሶሪያን ዐይተናል። ሁሉንም ነገራቸውን ጥለው ነው በየአገራቱ ተሰደው የሚኖሩት። ያንን እንዴት መማሪያ ማድረግ እንዳቃተን አይገባኝም።›› በማለት በአዲሱ ዓመት ቢሆን ብሎ የሚጠብቀውን ሁኔታ ተናግሯል።

በንግግሩና ከአዲስ ማለዳ ጋር በነበረው ቆይታ በመጨረሻ እንዲህ ሲል መልዕክትና ተስፋውን አስተላለፈ፤ ‹‹በማኅበረሰብ ደረጃ ልክ እንደ ዳንቴል ተወስውሰን የተሰባጠረ ባህል ነው ያለን። የተሰባጠረ ሃይማኖት ነው ያለን። እነዚህ ነገሮች በሙሉ ለጥቅም ብቻ ሳይሆን ለክፋትም ቢሆን መጥፎና ለማረም የሚከብድ ነው የሚሆነው። እና ይሄንን አስበን ከወዲሁ ልቦና ሰጥቶን በጉዳዮች ላይ እየተወያየን የማይገባንን ሳይሆን የሚገባንን ብቻ እየጠየቅን እንድንኖር ተስፋ አደርጋለሁ።››

ቅጽ 2 ቁጥር 97 መስከረም 2 2012

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com