የአዲስ ዓመት ጉራማይሌ ስሜቶች

Views: 104

በአዲስ ዓመት ማግስት ላይ ሆነን እንዲሁም አሁን አምና በምንለው በ2012 ማገባደጃ ቀኖች፥ ከመልካም ምኞት መግለጫው ጎን ለጎን የብዙዎች ጭንቀት ኢትዮጵያ በ2013 ምን ዓይነት ጊዜ ታሳልፍ ይሆን የሚለው መልስ አልባ ጥያቄ ነው። ጥያቄው መነሳቱ ብቻ ሳይሆን ከ2012 ሰቀቀን አለመላቀቁ የጉዳዩን ክብደት አመላካች ነው።

እርግጥ ነው! 2012 ለኢትዮጵያ ከባድ ዓመት ነበር። የኢትዮጵያ የፖለቲካ ልኂቃን ቁጭ ብለው ተረጋግቶ ለመነጋጋር፣ ለመደማማጥ፣ አንዱ ሌላውን ለመረዳት፣ ሰጥቶ መቀበል፣ ለመደራደር ዝግጁ አልነበሩም። የፖለቲካ ባህላችን በእንፉቅቅ እንኳን መሄድ አልቻላም፤ ግራ ቀኝ ብሎ ወደ ኋላ የተመለሰበት ዓመት ነበር ቢባል ያስደፍራል። በአጭሩ ኋላ ቀር የፖለቲካ ባህላችን ብሶበት ነበር ማለት ይቻላል።

ባለፈው ዓመት ታዋቂው ፖለቲከኛ ጃዋር መሐመድ አንድ ምሽት በማኅበራዊ ገጹ ላይ ተከብቢያለሁ የሚል ኡኡታ ባሰማበት ቅጽበት፥ የእሱ ደጋፊ የሆኑ ወጣቶች ቦሌ ወደሚገኘው መኖሪያ ቤቱ ከለላ ሊሰጡት ተምመዋል። በማግስቱና በተከታታይ ቀናት በተከሰተ ኹከትና ብጥብጥ በአዲስ አበባ ዙሪያ በሚገኙ የኦሮሚያ ክልሎች በተለይም በቡራዮ በአጠቃለይ ለ197 ሰዎች ሕይወት መቀጠፍ እና ለበርካቶች የአካል ጉዳት መድረስ ሰበብ ሆኗል።

እንዲሁም ኦሮሚያን ጨምሮ አማራ፣ ደቡብ ክልል እና ሌሎች ክልሎች በ2012 በተለያዩ ጊዜያት ኹከት አስተናግደዋል። ይሁንና የዓመቱ አሳዛኝ ግድያ በታዋቂው የአፋን ኦሮሞ ድምፃዊ ሃጫሉ ሁንዴሳ ላይ መፈጸሙን ተከትሎ በኦሮሚያ ክልል በተለይ በሻሸመኔ፣ ዝዋይ፣ አርሲ እና ምሥራቅ ሐረርጌ ብሔርና ሃይማኖትን የለዩ አሰቃቂ ግድያዎች፣ የአካል ጉዳት፣ መፈናቀሎች እና ከፍተኛ የንብረት ውድመት ደርሷል። ይህ ሁሉ ሲፈጸም ሰላምና ደኀንነት ማስጠበቅ ዋና ተግባራቸው የሆኑ የፖሊስ፣ የደኅንነት እና የመከላከያ ሠራዊት አባላት ቀድመው ተገቢውን ሥራ ባለመውሰዳቸው ከ160 በላይ ሰዎች ተገድለዋል፣ በርካቶች ቆስለዋል፣ ሌሎች ተፈናቅለዋል፣ ከተሞችም ወድመዋል። በዚህም ምክንያት ታዋቂ ፖለቲከኞችን ጨምሮ ብዙ ሺ ሰዎች ታስረዋል።

ከሃጫሉ ግድያ በመለስ በደቡብ ክልል የወላይታ የክልል እንሁን ጥያቄ እንዲሁም በጸጥታ ኀይሎች በተወሰደ እርምጃ የሰዎች ሕይወት እንዲሁ ተቀጥፏል።
መጋቢት 2012 ዓለም ዐቀፉ የኮሮና ወረርሽኝ ኢትዮጵያ ውስጥ ከተከሰተ ጀምሮ በዐሥር ሺዎች በበሽታው ተይዘወል፤ ከአንድ ሺሕ በላይ ሰዎች ሕይወትም ቀጥፏል።
በአዲስ አበባ ደግሞ ውስጥ ውስጡን ይነገሩ የነበሩት የጋራ ቤቶችን ለማይገባቸው ሰዎች መታደል እና በስፋት የተካሄደው ሕገ ወጥ የመሬት ወረራ በኢዜማ በማስረጃ መጋለጥ የብዙኀን መነጋገሪያ ብቻ ሳይሆን የዓመቱን መጨረሻ ቀናት ካጠየሙት መካከል ግንባር ቀደም ተጠቃሽ ሆኖ አልፏል። እርግጥ ነው የኋላ ኋላ አዲሲቱ የከተማ ከንቲባ አዳነች አበቤ ድርጊቱ መፈጸሙን አምነው ሕዝቡ ከአስተዳደሩ ጋር በመሆን በጋራ እንሥራ የሚል ጥሪ አቅርበዋል።

እነዚህ እና ሌሎች አስፈሪ፣ አሳዛኝ፣ አሳፋሪም ድርጊቶች ያስተናገደው 2012 ሙሉ በሙለ ጨለማ ነበር ማለት ግን አይቻልም። በርካታ መልካም አጋጣሚዎች ተፈጥረዋል። ምን ፈታኝ ጊዜ ቢያልፍ ለሰው ልጅ መድኀኒቱ ሰው ነው የሚለው ወርቃማ አባባል ከቃል በላይ በተግባር ተተግብሯል።

ከግድያው፣ ከአካል ጉዳቱና ከንብረት ውድመቱ ጋር በተያያዘ ሰለባዎች እርዳታ እንዲያገኙ ከፍተኛ ርብብር ተደርጓል። የኮሮና ወረርሽን ብዙ እንቅስቃሴ በገደበበት ሁኔታ የዕለት ኑሯቸውን በዕለት ሥራ የሚሸፍኑና የኢኮኖሚ አቅማቸው ዝቅተኛ ለሆኑ የኅብረተሰብ ክፍሎች ምግብ ነክ እርዳታዎች ከዚህ ቀደም ባልታየ መልኩ ተበርክቷል። የበጎ አድርጎት ተነሳሽነት እና ልገሳ በከፍተኛ ደረጃ ጨምሯል።

የሕዳሴ ግድብ የመጀመሪያ የውሃ ሙሌት በተሳካ ሁኔታ መሄድ እንዲሁም በአዲስ አበባም በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ቁርጠኛ ውሳኔና ርዕይ የሸገር ማስዋብ ፕሮጀክቶች እና የእንጦጦ ፓርክ ግንባታ በመጨረሻ ምዕራፍ ላይ መገኘት እና የሸገር ዳቦ ፍብሪካ ተጠናቆ ወደ ሥራ መግባቱ ኢትዮጵያ ተስፋ የማይቆረጥባት አገር እንደሆነች ማሳያ ተደርጎ በብዙዎች ይታመናል።

በተለያዩ የአገራችን ክፍሎች ተደጋጋሚ ተስፍ አስቆራጭ እና ተስፋ ፈንጣቂ ሁነቶች መከሰት አዲሱን ዓመት ብዙዎች በተስፋና ስጋት ገራማይሌ ስሜቶች እንዲቀበሉት ሆኗል። መልካም አዲስ ዓመት!

ቅጽ 2 ቁጥር 97 መስከረም 2 2012

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com