የ 2012 የአንደበት ትውስታ

Views: 25

2012 ዓመት አዲስነቱን ጀምሮ በአሮጌ መዝገብ ሰፍሮ እነሆ ተሸኝቷል። ባለፉት 365 ቀናት የነበሩትን ኹነቶችና በየጊዜው የሚሰሙ ክስተቶችን በመዘገብ የምትታወቀው አዲስ ማለዳም፣ ለተከታታይ 52 ሳምንታት በተለያዩ አምዶቿ በርካታ ጉዳዮችን ዳስሳለች። ከእነዚህ አምዶች መካከል ‹አንደበት› በተሰኘውና የተለያዩ እንግዶቿን በምታስተናግድበት አውድም ከሃምሳ በላይ እንግዶችን ቃለመጠይቅ አቅርባለች።

አነጋጋሪ የነበረ ቆይታን ከፖለቲከኛ ጃዋር መሐመድ ጋር አድርጋለች። ከሰብአዊ መብት ኮሚሽን ኮሚሽነር ዳንኤል በቀለ (ዶ/ር) እንዲሁም ከአምነስቲ ኢንተርናሽናል አፍሪካ ቀንድ የሰብአዊ መብት ጉዳዮች አጥኚ ፍስኃ ተክሌንም እንግዳ አድርጋለች። በዚህም በኢትዮጵያ በተለያየ ጊዜ ስለተነሱ የሰብአዊ መብት አያያዝ ጉዳዮች፣ ስለታገቱ ሴት ልጆች እንዲሁም ተቋማቱ ጊዜ ጠብቀው ባወጡት ዘገባ ዙሪያ ጥያቄና መልሶች ቀርበዋል።

ከብርቱ ሴቶች መካከል ዘሚ የኑስ ‹የሳሞራ የኑስ እህት ነዎት ወይ?› ከሚለው ጥያቄ ጀምሮ በኦቲዝም ዙሪያ የሠሩትን ሥራ ከአንደበታቸው አካፍላለች። ሴታዊት ንቅናቄም ከኢዜማ ጋር ያላትን ግንኙነት ከመሥራቾቿ መካከል ከስኂን ተፈራ (ፒኤችዲ) ጋር ባደረገችው ቆይታ አውቃ አሳውቃለች።

ታሪክን በማንሳት ኢብራሂም ሙሉሸዋን፣ ከመገናኛ ብዙኀን ባለሞያዎች አንጋፋውን ጋዜጠኛ ጥበቡ በለጠን፣ በአረብኛ ቋንቋ መምህሩን ዑመር መኮንንን በአንደበት አምድ ተስተናግደዋል። ግብረሰዶምን በሚመለከት ከመምህር ደረጄ ነጋሽ ጋርም ቆይታ ነበራት። በቅርቡም በአዲስ ትውልድ ከመጣው ኢሕአፓ አመራር ቴዎድሮስ ዘርፉን አናግራለች። ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያምም የአዲስ ማለዳ እንግዳ ነበሩ። በዚህ የ2013 መግቢያም ከእነዚህ ትውስታዎች ከፍላ ልታጋራችሁ ወዳለች፤

መስፍን ወልደማርያም (ፕሮፌሰር)
በማንበብና በመጻፍ ነው፣ ሌላ ሥራ የለኝም። ማኅበረሰቡን፣ ኢትዮጵያን አልተለየሁም። እናም ባለኝ አቅም፣ በተቻለኝ መጠን ባለው ሁኔታ መሳተፍ እፈልጋለሁ።
[የፖለቲካ ባህል] የለምኮ! ወሬ ነው። ፖለቲካ የሚባል ነገር ኢትዮጵያ ውስጥ ገና ነው። አገዛዝ እስካለ ድረስ ፖለቲካ የለም። አገዛዝ ሲጠፋ ነው ፖለቲካ የሚመጣው። አገዛዝ ጠፍቶ እያንዳንዱ ሰው ሰው ሆኖ፣ ዜጋ ሆኖ ለነጻነቱ ለመብቱ ሲቆም ነው ፖለቲካ የሚመጣው። እዛ ጋር ገና አልደረስንም። አሁን ያለው እንደው ዝም ብሎ የጎሳ ትርምስ ነው ፖየቱ ብሔር የቱን ጨቆነ ብዬ መናገር ያስቸግረኛል።

የብዙ ሰዎችን ዘር አናውቅም። አሁን አሁን አንዳንድ ነገር አወቅን። ለምሳሌ የአፄ ኃይለሥላሴን ብሔር አሁን ከለውጡ በኋላ ነው ያወቅነው፣ በፊት አናውቅም። ከእርሳቸው በኋላ የመጡትን ስንመለከት፣ የተፈሪ በንቲ ዘር ይሁኑ፣ የጄኔራል አማን አምዶም ዘር ወይስ የመለስ ዘር ነው [የጨቆነው] … ይህን ማሰብ ያስፈልጋል።ለቲካ የሚባለው።

ፖለቲካ የለም አልኩኝ`ኮ። የጎሳ ነገር ፖለቲካ አይደለም። በአገዛዝ ውስጥ ያለ ለሥልጣን፣ ለወፍራም እንጀራ መቆራቆዝ ፖለቲካ አይደለም። አሜሪካና እንግሊዝ የሚደረገውን ነገር እያየን አይደለም እንዴ? እሱን አይተን እኛ ጋር እንምጣ። እኛ ጋር ፖለቲካ አልተጀመረም፣ ሥሙ ብቻ ነው የመጣው።

ፕሮፌሰር ጥሩሰው ተፈራ(የትምህርት ሎሬት)
በኢትዮጵያ ደረጃ ትምህርት ቤት ከመከፈቱ በፊት እና ከተከፈተ በኋላ በሦስት መልኩ ዝግጅት መደረግ አለበት።
የትምህርት ሚኒስቴር ራሱን የቻለ ከሚኒስቴር መሥሪያ ቤት ጀምሮ እስከ ትምህርት ቤት ድረስ የሚወርድ ግብረ ኃይል ማቋቋም ይኖርበታል። በግብረ ኃይሉ ውስጥም የትምህርት፣ የጤና፣ የመረጃ ቴክኖሎጂ (ICT) ባለሙያዎች እንዲሁም የሥነልቦና ባለሞያዎችን ያካተተ መሆን ይኖርበታል።

በመጀመሪያው ደረጃ ምንም አይነት ተግባር ከመጀመሩ በፊት አስቀድሞ በአገር ዐቀፍ ደረጃ የዳሰሳ ጥናት መካሄድ ይኖርበታል። ሁሉም ትምህርት ቤቶች ንፁህ የመጠጥ ውሃ፣ መፀዳጃ ቤት እና የመማሪያ ክፍሎች ዝግጁነት ጨምሮ መምህራን ሌሎች የድጋፍ ሰጪ ሠራተኞችንም አካቶ በጤናም፣ በሥነልቦናም መዘጋጀት ይገባል።

በ‹ኒው ኖርማል› እንደዚህ ቀደሙ ተማሪዎች መቀበል ሳይሆን በእንክብካቤ ሁሉን አካታች በሆነ መልኩ መሆን አለበት።ይህን አይነት ዝግጁነት ከሌለ ወላጆችም ልጆቻቸውን ወደ ትምህርት ቤት ለመላክ ሊቸገሩ ይችላሉ። ልጆችም ትምህርት ቤት መሄድ ለመሄድ እንዲሁ።

ጥበቡ በለጠ(አሐዱ ሬዲዮ ዋና ስራ አስኪያጅ)
በጣም አፈናዎች፣ ግድያና ስደቶች፣ በፖሊስ ጸጥታ ኃይል የመንገላታትና መሰል የኢትዮጵያ ጋዜጠኞች የከፈሉት ዋጋ በጣም ከባድ ነው። ያለፉት ኹለት ዓመት ግን በስኬትና በጥሩ ሁኔታ አልፏል። ይህ ማለት ግን ችግሮች የሉም ማለት አይደለም። አሐዱ በዚህ ስርዓት የመጀመሪያው ተከሳሽ ነው። ለኹለት ወር ያህል እስከ ሰንዳፋ ተመላልሰን በፍርድ ቤት ክስ ተመስርቶብን፣ ከሳሽም ዳኛም ያው ፍርድ ቤት ሆኖ፣ የፍትሕ ሂደቱ ችግር የሞላበት እንደነበር እናስታውሳለን።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገብተውበት ነው ይህ ጉዳይ የቆመው። ምክንያቱም እርሳቸው የዓለም የፕሬስ ቀን ኢትዮጵያ እንዲከበር አድርገው፣ በዛ ማግስት ነው አሐዱ የተከሰሰው። የአገሪቱን ገጽታ በእጅጉ የሚያቆሽሽ ስለነበር፣ ወዲያው ያንን ሊያጸዱት ችለዋል። በአንድ ሚድያ ጉዳይ ገብተው ያንን መፍትሔ በመስጠታቸው፤ በዚህ አጋጣሚ እርሳቸውንም ላመሰግን እወዳለሁ።
የብሔር ሚድያዎች የዛን ብሔር ቋንቋውን፣ ባህሉን፣ ማንነቱንና ፍልስፍናውን ከመናገር ይልቅ የፖለቲካ አጀንዳ ውስጥ ገቡ። አንዱ ሌላውን ጨቋኝ ነው ሲል የነበረውን ትርክትና ግለቱን ሚድያዎች እያባባሱ መምጣታቸው ነው ትልቁ ችግር።

ኢዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) የገንዘብ ሚንስትር ዲኤታ
በዓለም ዐቀፍ ደረጃ ግን ኹለት መልእክት ያለው ነው። በአንድ በኩል ምን ያህል እንደተሳሰርን ያሳየ ነው። አንዱ ጋር የሚፈጠረ ችግር እዛው አንዱ ጋር ብቻ ታፍኖ የማይቀር መሆኑን ያሳየ ነው። አሁን ሁሉም ሰው ስጋት ላይ ነው ያለው። አገራትም ሕይወት ማዳን ሥራ ላይ ነው ያተኮሩት። ስለዚህ በጣም ወደ ውስጥ የማየት ነገር ይኖራል።
ይህ ነገር ሲያበቃ ግን፣ የሚቀጥለው ወረርሽኝ ይህን እንዳያመጣ እንዴት በተሻለ ትስስር መሠራት አለበት የሚለው መታሰብ አለበት ብዬ ነው የማስበው።
የመንግሥት ሚና በኢኮኖሚ ውስጥ የሚለውን ጥያቄ እያነሳህ ከሆነ፣ ድሮም ቢሆን ከወሬ ባለፈ በተግባር የትኛውም አገር የኢኮኖሚ እድገት ከምጣኔ ሀብት ታሪክ ብታይ፣ መንግሥታት በጣም ትርጉም ያለው ሚና ነው በምጣኔ ሀብት ውስጥ የተጫወቱት።
የመንግሥት የአመራር ድርሻ ኢኮኖሚውን አንድ ላይ የማንቀሳቀስ ጠንካራ ሚና ሊጫወት ይገባል የሚል ጠንካራ እምነት አለኝ። መንግሥትም ይህ እምነት አለው። የዓለም ተሞክሮም ይህን ነው የሚያሳየው።

ሙሴ ምንዳዬ
(ንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የመልቲላተራል ንግድ ግንኙነት ዳይሬክተር)
የሕግ ባለሞያ የሆኑት ሙሴ፣ ከሉላዊነት አንጻር አፍሪካ በምጣኔ ሀብት ትንሣኤዋ የሚሆንበት ዋዜማ ላይ ናት ሲሉ፣ ብቸኛው በዚህ ተስፋ ላይ ያጠላው ጥላ የኮቪድ 19 ኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ መሆኑን በማጠየቅ ነው።
የኢትዮጵያ ማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ተወዳዳሪ መሆን አለበት። ያለምንም ጥርጥር የአፍሪካ ነጻ ገበያ ስምምነት የጉምሩክ ገቢን መቀነሱ አይቀርም። የኢትዮጵያ ከአፍሪካ አገራ ጋር የምታደርገው የንግድ ግንኙነት እዚህ ግባ የሚባል አይደለም።
በእኛ ጥናት መሠረት ኢትዮጵያ ከአፍሪካ አገራት ጋር በምታደርገው ከቀረጥ ነጻ የሆነ ግብይት፣ በዓመት 920 ሚሊዮን ብር የቀረጥ ገቢ ስታጣ ኖራለች። 10 በመቶ ከቀረጥ ነጻ አገልግሎትንም ለኮሜሳ ሰጥታለች። ሆኖም ግን ይህ ኪሳራ ለገበያ በሚቀርቡ ምርቶች ብዝኀነት እንደሚካካስ እናምናለን።

ሼሕ አሊ መሐመድ ሺፋ
ከምክር ቤቱ ምክትል ፕሬዝዳንት
ወረርሽኙንስ ያመጣው ማን ነው? ወረርሽኙ የመጣውኮ በሰው ልጆች ኃጢአት ነው፤ በእንስሳት አይደለም። በከብት፣ በበግ፣ በፍየል ኃጢአት አይደለም ይህ ወረርሽኝ የተከሰተው። ወረርሽኝኮ ብዙ ጊዜ ተከስቷል፣ ግን እንዲህ ዓለምን ያዳረሰ ወረርሽኝ በታሪክ እንዲህ ያለፈ የለም። ይህንን ያየን ሰዎች መለያየት እንደማይጠቅም፣ መነታረክ እንደማይጠቅም ተረድተናል። የትም እንደማንደርስም ተረድተናል። የሃይማኖት አባቶች አሁን ብቻ ሳይሆን ከአሁንም በፊት ነው። ኢትዮጵያንም ለየት የሚያደርጋት አንዱ ይህ ነው።
የሚያጋጩትና የሚያጣሉት እነማን እንደሆኑ ይታቀዋሉ። ጥቅምና ሥልጣን ፈላጊዎች፣ ይህቺን አገር ብትንትን ለማድረግ የሚፈልጉ ሰዎች ናቸው። እንደነ ሶርያ እና ሊብያ እንድትሆን የሚፈልጉ ሰዎች ናቸው። ይህቺ አገር ደግሞ የጸሎት አገር ናት። ያስቡታል እንጂ ማንም አይነካትም። በነገራችን ላይ አገር ትፈርሳለች ሲባልኮ ምድሩ አይጠፋም፣ የምንጠፋው እኛ የሰው ልጆች ነን።
ስለዚህ ይህን አብሮነታችንን፣ አብሮ መሥራቱን፣ መተባበሩን መቀጠል ያስፈልጋል። እንጂ ከዚህም ሌላ የከፋ ሊገጥመን ይችላል። በትብብር ግን ማሸነፍ እንችላለን። ይህ ነገር ባይመጣኮ ግብጽ ደብድባን ሊሆን ይችል ነበር። አብሮነታችንን ግን ማንም ሊነካ አይችልም። ይህ ሲባል ለፖለቲካ አይደለም፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወይም የከተማችን አስተዳደር እንዲወዱን አይደለም። እውነተኛውን ነገር ነው ያስቀመጥ ነው።

ዶክተር ተግባር ይግዛው(የኢትዮጵያ የሕክምና ማኅበር ፕሬዝዳንት)
የኮቪድ ወረርሽኝ ለጤና ባለሞያዎች ብዙ ፈተና ይደቅናል። የመጀመሪያው አሁን ፊት ለፊት ያለው አስጨናቂ ነገር ጤና ባለሞያዎች ከሌላው ማኅበረሰብ የበለጠ ተጋላጭ ናቸው። ምክንያቱም ሌላው ሰው ቤቱ ቁጭ ካለና ርቀቱን ከጠበቀ ምንም አይሆንም። ጤና ባለሞያዎች ግን ሥራቸው ነው። የኮቪድ ታማሚን ሆነ ሌላ ዓይነት የጤና አገልግሎት የሚፈልግን ሰው እንክብካቤ መስጠት አለባቸው፣ ከታካሚ ጋር ይገናኛሉ።
ከላይ የተንጠለጠለ ስርዓት ብቻ አይደለም በሽታ መቆጣጠርን ውጤታማ የሚያደርገው። እያንዳንዱ ወረዳና ማኅበረሰብ አቅም ሊኖረው ይገባል። ለምሳሌ የታመሙትን ሰዎች መለየት፣ ማፈላለግ፣ ኅብረሰተቡን ማስተማር፣ ማስተባበር፣ የተቸገሩትን መርዳት፣ ይህ አቅም ሁሉም ጋር መኖር አለበት። ይህ ሁሉ የለም። ይህ ግን በኹለትና ሦስት ወር የምታመጪው ሳይሆን፣ መጀመሪያ የሚገነባ ስርዓትም ነው።ሁሌም የምሰጠው ምሳሌ አለ። አንድ ጫካ ውስጥ እሳት ቢነሳ፣ የተወሰነ ቦታ ላይ ብቻ አጥፍቶ የተወሰነ የሚነድ ቢኖር እሳቱን ልትቆጣጠሪ አትችይም። እናም ይህን ወረርሽኝ ለመቆጣጠር ግማሹ ሰው ጥንቃቄ ማድረጉ ሳይሆን አብዛኛው ሰው ብንችል ሁላችንም የሚመከሩትን ምክሮች መተግበር ከተቻለ፣ በሽታውን የመቆጣጠር ደረጃችን ከፍ ያደርጋል ነው።

ዘሚ የኑስ (የኒያ ፋውንዴሽን መሥራች)
ኦቲዝም በጣም እየበዛና እየጨመረ ነው። ባይሆን ደስ ይለናል። ከሆነ ግን ሁሉም ሰው ተዘጋጅቶ መጠበቅ አለበት። ከሆነ ምንም ማድረግ ስለማይቻል ከአሁኑ መዘጋጀትና መቀበል፤ ልጄ ሰይጣን አለበት ሳይሆን መልዐክ ነው ብሎ ማመን ነው። ከሁሉም ሃይማኖት ያሉ የሃይማኖት መሪዎችም ልጆቹን ሰይጣን አለበት የሚለውን ቢተዉ ጥሩ ነው፤ ወላጆች እኔ አጋጥሞኝ እንደነበረው ልጆቻቸውን እንዳይፈሩ።
ኹለት ነገር ባነሳ ደስ ይለኛል። አሁን ባለንበት ሁኔታ ቁስል አለብን። በእኛ ችግር ሀብት መሥራት የሚፈልጉትን አንቀበልም። እናስተምርላቸኋለን እያሉ የማይገባ ገንዘብ የሚጠይቁ ሰዎች ተነስተዋል፤ በተለያየ መልኩ። ይሄ በቁስላቸን ላይ መነገድ ስለሆነ አንቀበለውም። የሚከፍሉ ሰዎችም መጠንቀቅ አለባቸው የሚለው አንዱ መልእክቴ ነው

ጀዋር መሐመድ የኦሮሚያ ሚድያ ኔተወርክ ሥራ አስኪያጅ
የፌዴራል ስርዓት በተለይ እንደ ኢትዮጵያ ዓይነቱ ኹለት ነገሮችን እንዲያሟላ ይጠበቃል። አንዱ እና ቀዳሚው ብሔሮች መዋቅራዊ ክልል እንዲኖራቸው ማድረግ ነው። ኹለተኛው ፍትኀዊ የሥልጣን እና የሀብት ክፍፍል መምጣቱ ነው። የመጀመሪያውን ያለ ዴሞክራሲ ማድረግ ይቻላል፤ የሥልጣንና ሀብት ክፍፍሉን ግን ያለ ዴሞክራሲ ማድረግ አይቻልም።
በኢሕአፓ ቁንጮዎቹ የአማራና ትግራይ ልኂቃን ነበሩ። ዛሬኮ ‹‹ዜግነት›› የሚሉ ግለሰቦች ኢሕአፓ ውስጥ ነበሩ። ዛሬ ‹‹ብሔር›› የሚሉት መኢሶን ነበሩ። ስትጨፈልቀው የትግራይ ብቻ ነው እንጂ መንገድ የቀየረው፤ የአማራና የኦሮሞ ፖለቲካ ነው።
የልኂቃን ስሌትም ነው፤ በየትኛው ብሔድ ነው በአቋራጭ ሥልጣን ሊመጣ የሚችለው ነው። ከዛ አንፃር የብሔር እንቅስቃሴ የምንለው የቡድን ነው። ፈጣኑ ሒደትም በቡድን መሰባሰብ ነው። የበላይ የሆነው ቡድን ግን አንድ ለአንድ የሆነውን ነው የሚፈልገው።
ብልፅግና ላይ የሚነሳው አንድ የጋራ ሥምምነት ሳይደረግ ወደ ውሕደት ከተገባ፣ ጥያቄዎችን በሙሉ ይዞ ስለሚገባ መቋቋም አይችልም ነው። በእርግጠኝነት ብልፅግና ፓርቲ አይዘልቅም። በአማራና በኦሮሞ መካከል ያለውን ሁኔታ በምን መልኩ ይዘውት እንደሚቀጥሉ ያሳስባል።

ሊቀ ትጉሃን ቄስ ታጋይ ታደለ- የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ

ኢትዮጵያ ውስጥ በየትኛውም የፖለቲካ ገዳይ ይነሳ፣ ማወራረጃው ቤተ እምነቶች ናቸው።
ስለዚህ ፖለቲካ ከቤተ እምነት እጅህን አንሳ ነው ያልነው።
ፖለቲከኞች ራሳችሁን ችላችሁ የፖለቲካ መደባደቢያ ቦታ አዘጋጅታችሁ ኳሱን እዛው ሜዳ ላይ ተጫወቱ፣ ወደ እኛ ወደ ቤተ እምነቶች፣ ወደ ሃይማኖቶች ኳሱን አትጠልዙት፣ ይህንን አቋማችንን በተደጋጋሚ ገልጸናል።

 

በለጠ ሞላ (የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ) ሊቀመንበር
በአማራው ብቻ ሳይሆን፣ የአማራ ተወላጅ ያልሆኑ ኢትዮጵያን አንድነት የሚፈልጉ ልኂቃን የሞራል ድጋፍ ይሰጡናል። ምክንያቱም በአማራነት ብንታገልም፣ ርዕያችን ለኢትዮጵያ የሚሆን ነው። ሕዝባችን ከደረሰበት መዋቅራዊ በደል ተላቆ፣ ራሱን ሆኖ፣ ጥያቄዎችን አስመልሶ፣ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ማዕቀፍ ደግሞ እኩል ከሌሎች ጋር ተሳታፊ የሚሆንበትን፣ ለእኩልነት፣ ለፍትህና ለሰላም አስተዋጽኦ የሚያደርግበትን ነገ ነው የምንፈልው። ይህን ርዕያችን በሚዲያዎችና በውይይት መድረኮች ላይ፣ ለሕዝብ እንዲሁም ለመንግሥት ለማስገንዘብ ጥረት አድርገናል።
በእርግጥም የአማራ እሳቤ ከኢትዮጵያ ጋር የታሸ ነው። በኢትዮጵያ አገር ግንባታ ውስጥ፣ የሌሎችን ሚና በማሳነስ ሳይሆን፣ አማራው ሰፊ ተሳትፎ ነበረው። አገር በመገንባትና ነጻነትን ጠብቆ በማቆየት ሚና ተጫውቶ አልፏል። እናም ሕዝቡ የኢትዮጰያዊነት እሳቤ እንዲላበስ ሆኗል።
ይህን ትልቅ ማንነቱን በአገር የሚያስብ ሕዝብ፣ በአንዴ ወደ ብሔር ማንነት ውስጥ ለመሰብሰብ አስቸጋሪ ነው። አማራው ራሱ አይቀበለውም ነበር። ዛሬም ድረስ ፈተናችን ነው። ብዙ ብንሠራም የሚቀር አለ። እናም ከረር ያለ አማራ ንቅናቄ ሲፈጠር ለብዙዎች አስደንጋጭ ነበር። ለስርዓቱ እንዲሁም ለአማራውም ጭምር፣ ከረርና ጠንከር ተብሎ መሠረታዊ ጥያቄዎች መስተናገድና መመለስ አለባቸው፣ አማራው በዚህ አግባብ በደል ደርሶበታል የሚል ንቅናቄ ወደ መድረክ ሲመጣ ብዙዎችን አስደንቋል።

ማጂ ኃይላመሪያም (ረ/ፕ)
በኢትዮጵያ በገጠራማው ክፍል በአዕምሮ ጤና ረገድ ሰፋ ያለ ምርምር ያካሔዱ እና ጠለቅ ብለው ከተሠሩ ጥናቶቻቸው የተነሳ ጠንካራ ግኝቶችንም ይፋ ማድረግ ችለዋል።
ከተለመደው ወጣ ያለና ያልተጠበቀ ነገር ድንገት ሲከሰት ደግሞ አብዛኛውን ጊዜ የተለያየ የሥነልቦና ምላሾች ይኖራሉ። በዚህም ፍርሀትና ጭንቀት፣ ውጥረት እንዲሁም ንዴትና ግራ መጋባት ይኖራል። በጣም የተለያዩ ዓይነት ግብረ መልሶች ይኖራሉ። እነዚህ ስሜቶች እውነት ነው። ለምን እንዲህ ተሰማኝ መባል የለበትም። ትክክለኛ የሆነ ስሜት ነው።
እኛ አገር ከማንኛውም አገር የተለየ የአእምሮ ጤና ችግር የለም። ኢትዮጵያዊ ስለሆንን ለአእመሮ ችግር አንጋለጥም ማለት አይደለም ወይም ከሌላው የባሰ ተጋላጭ ነን ማለት አይቻልም። ልዩነቱ ሕመሙን ማወቅና ሕክምና መፈለግ ላይ ነው። ለምሳሌ ድባቴን ብንወስድ፣ ሌላው አገር ውስጥ አብዛኛው ሰው ለዚህ ብቻ ምርመራ ይካሄዳል።
በመጀመሪያ ሰው ስለሆንን ለየትኛውም የአእምሮ ጤና ችግር ተጋላጭ ነን። ለምሳሌ በኢትዮጵያ አኗኗራችን ማኅበራዊ ቅርበት አለው። ጥናቶች እንደሚያሳዩት የጠበቀ ማኅበረሰባዊ ግንኙነት ያላቸው ከድባቴ የተጠበቁ ናቸው የሚሉ ሰዎች ነበሩ። ያንን የሚጻረር በኢትዮጵያ ውስጥ የተደረገና የታተመ ጥናት አለ።

ቅጽ 2 ቁጥር 97 መስከረም 2 2012

 

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com