የነጻነት መገለጫ ምንድን ነው?

Views: 148

አዲስ ዓመት ሲቃረብ የተለያዩ ይልቁንም ሴቶች በጋራ የሚሳተፉባቸው በዓላት በብዛት ይመጣሉ። አሸንዳ፣ ሻደይ፣ ሶለል፣ አሸንድዬ እና ሌሎችም ካለማወቅ የተነሳ ያልጠቀስኳቸው በዓላት በመስከረም ዋዜማ ብቅ የሚሉ ናቸው። በእነዚህ በዓላት ሴቶች በነጻነትና እንደልባቸው ከቤተሰብ ቁጣን ሳይደርስባቸው፣ በማንም ነቀፋን ሳያስተናግዱ በአደባባይ ደምቀው የሚታዩበት ነው።

እንደ ምሳሌ ብናነሳ አንዳንድ አካባቢዎች ላይ ከመስከረም መግባት ዋዜማ የሚገኙ ቀናትን የስጦታ ቄጠማ በመልቀም፣ አበባ በመሰብሰብ ለስጦታ ከማዘጋጀት ጀምሮ በየቤቱ እየዞሩ ‹አበባየሆሽ› እየዘፈኑ ሽልማትን ይቀበላሉ። ይህም የሴቶች ኅብረት በደንብና በሚገባ የሚታይበት አንዱ አጋጣሚ ነው።
ብዙውን ሥልጣኔ ከባህር ማዶ ለማምጣት የምንባትል መሆናችን እንጂ፣ እንዲህ ያሉ ኅብረቶች ብዙ ለውጦችን ለማምጣት መሠረት በሆኑን ነበር።

ነገራችን ወዲህ ነው፤ እነዚህን በዓላት የነጻነት መገለጫ አድርገው የሚገልጹት አሉ። እርግጥ ነው፤ ለትምህርት እንኳ ከቤታቸው እንዲወጡ ፈቃድ የማያገኙ ሴቶች በእነዚህ በዓላት ነጻነትን ያገኛሉ። ከጓደኞቻቸውና አካባቢያቸው ልጆችም ጋር የሚያሳልፉትን ጊዜ ይሰጣቸዋል። ግን ነጻነት ይህ ነው?

አንዲት በእነዚህ በዓላትን ጠብቀው በሚመጡ ክዋኔዎች ላይ በልጅነት ትሳተፍ እንደነበር የምታወሳ ሴት፣ በእነኚህ በዓላት ዙሪያ አስተያየቷን ስትሰጥ ሰማሁ። ምን አለች? እነዚህን ቀናት የተለየ የነጻነት ቀን አድርገን የምናስብበት እድሜ ነበር። ይህም ሕይወታቸውን ወደ አጉልና ወደማይፈልጉት መስመር የወሰደባቸው ሴቶች እውቃለሁ። ነጻነትን በአግባቡ መጠቀም ያስፈልጋል።

በዚህ ሐሳብ ሁሉም ሰው ይስማማል ማለት አይደለም። ግን በአንድ ወገን ነጻነት ለሳምንትና ለጥቂት ቀናት አንዳች ክዋኔን መሠረት አድርጎ የሚገኝ ስጦታ አይደለም። ሰው ሆኖ በመፈጠር የሚገኝ የሰውን አካል ነው። መሆን ያለበትም እንደዛ ነው።

በሌላ በኩል ነጻነትን በምን ገልጠን እንዴት እንጠቀምበታለን ነው። ነጻነት በተጠቃሚው ሚዛን ይቃኛል። ልክ አንድ ሰው ራሱን ‹አልችልም› ሲል አእምሮው ያንን ተቀብሎ ‹አትችልም› እንደሚለው ሁሉ፣ ነጻነትን በተረጎምነው ልክ ነው ማሰሪያውም የሚሆነው። ነጻነት በአለባበስ ነው የሚገለጠው? ነው ወይስ በአነጋገር? በአካሄድ ወይስ አፈንጋጭ ሆኖ መለየት? ነጻነት ማንን ይመስላል? አሜሪካን ወይስ አውሮፓን፣ ነው እስያን?

ይህ ሚዛናችን እንደ ግለሰብ ብቻ አይደለም፤ እንደ አገር ሕዝብ ሆነን ተደምረን ስንታይም ወሳኝ ሚናን የሚጫወት ነው። ሕዝብ ሁሌም ነጻነትን የሚናፍቀውና ‹ባጎረስኩ እጄን ተነከስኩ!› እንዲሰኝ ያደረገው የነጻነቱን ትርጉም በጥቃቅኑ ነገር ስለሚያኖር ነው። ‹እንደልቤ ልናገር!› ይላል። ነጻነቱን ከንግግር እንዳያልፍ ያስባል። ያንን ሲያገኝ ግን ውሃ የሚያነሳ ነገር ከአንደበቱ አይገኝም። እና ሌላ የነጻነት ጥያቄ ውስጥ ይገባል።

በእርግጥ አንጻራዊ ካልሆነ በቀር ከምንም ተጽእኖ በቀላል ነጻ መውጣት የሚቻል አይደለም። የሰው ልጅ ሚዛኑን ባሳለፈው ልምድ፣ በሚያውቀውና በተረዳው መጠን ነውና የሚሆነው የነጻነቱ መለኪያም እንደዛው ያንን መሠረት ያደርጋል።

ወዲህ ግን መነሻ የሆነን በዓላትን ተከትሎ ‹የሴቶች የነጻነት ቀን› የሚለው ጉዳይ ነው። በዚህ መሠረት ነጻነት በአደባባይ እንደልብ መዝፈንና መጨፈር፣ ውበትን መግለጥና ማሳየት፣ ድምጽ አውጥቶ መናገርና ሰብሰብ ብሎ በጋራ መሄድ በሚል መንገድ እየተተረጎመ ይመስላል። ያ ሊሆን አይገባም። ነጻነትን በዘላቂነት በዚህ መንገድ መመዘንም አግባብ አይደለም።

ነገር ግን የእነዚህን ኹነቶች ባህላዊና አገራዊ እሴት ችላ እያልንም ሊሆን አይገባም። እንዳልኩት እንደውም እነዚህን የሴቶች መሰባሰቦች ለተሻለ ለውጥ መጠቀምና መንገዱንም ተከትሎ ጠንካራ ሥራ ለመሥራት ዕድሉ አለ። በአዲሱ ዓመት ትክክለኛ ነጻነታችንን እንፈልግ!
ሊድያ ተስፋዬ

ቅጽ 2 ቁጥር 97 መስከረም 2 2012

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com