የጊዜው ወርቆች

Views: 20

ጊዜና ወርቅ እስከ ፍጻሜው የሚጸና ባይሆንም መመሳሰል አላቸው፤ ኹለቱም ውድ ናቸው። ከግል ገጠመኛቸው በመነሳት ይህን የወርቅና የጊዜን ነገር ያነሱት በርናባስ በቀለ፣ ለሁሉም ነገር ጊዜ እንዳለው ሁሉ አሁን ላይ ወርቅ ሆነው ትኩረት አግኝተው ያሉት ራስን ከኮቪድ 19 መጠበቂያ መሣሪያዎች መሆናቸውን ያነሳሉ። በተጓዳኝ የወርቅ ቤቶች ጭር ብለው ለጤና ጉዳይ ሰዉ የመረባረቡን ነገር አንስተው፣ ሕይወትንም ከዛ በማመሳከር በጊዜ ሁሉን መጠቀም ተገቢ ነው ሲሉ እንዲህ ያወጋሉ።

ነገሩ ከጥቂት ሳምንታት በፊት ነው። የሥራ ዘርፏ ንግድ ሆኖ መሥሪያ ቤቷ ደግሞ ወርቅ ቤት (በወርቅ የተሠራ ሳይሆን ወርቅ መሸጫ መደብር) የሆነ አንዷ ወዳጄ ጋር በሥራ ጉዳይ ደውዬ ነበር። ሰላምታ ከተለዋወጥን በኋላ ‹‹ሥራ እንዴት ነው?›› የሚል ጥያቄ አቀረብኩላት (በቀረብኝ!)። ‹‹ባርኒ ለሥራ ዘርፉ ታማኝ ለመሆን ብለን ክፍት አድርገን እንውላለን እንጂ በዚህ ጊዜ ምን ሥራ አለ!? (አየር የለም እኮ)›› አለች። አስከትላም፤ ‹‹ጊዜው ሰው በሕይወት ለመቆየት የሚረባረብበት እንጂ የጌጥና የቄንጥ አይደለምና›› አላለችኝም መሰላችሁ!?

‹‹ሥራ እና ጊዜ›› በሚል ሐሳብ ጥናታዊ ጽሑፍ ልናዘጋጅ የደወልኩላት አስመሰለችው። ሆሆሆ! እኔ ስለ ሥራዋ የጠየኳት ወደ ዋናው መልእክቴ ከመግባቴ በፊት ጥሩ መንደርደሪያ ይሆነኛል በሚል ነበር። እርሷ ግን መግቢያዬን ዋና ጉዳዬ አድርጋው ቁጭ! በቃ ምን አለፋችሁ…! ያነሳችው ሐሳብ የስልክ ጥሪው ጭብጥ (አንኳር ወሬ) እስኪመስል ተወያየንበት።

ቆይ ግን ‹‹ሥራ እንዴት ነው?›› የሚል በሦስት ቃላት የተዋቀረና ‹‹ደኅና ዋልሽ?›› የማለት ያህል የተለመደ ጥያቄዬ ይህን ሁሉ ያስወራል? ለነገሩ ሰው ልናገር ካለ ከመሬት ተነስቶም ይናገር የለ? ካልሆነም ይህች ወዳጄ የሥራ ዘርፏን ቀይራ መሆን አለበት! ‹‹ወዴት?›› አላችሁኝ? ወደ አውርቶ አደርነት ነዋ! ድሮም አንዳች ትንታኔ የታከለበት ነገር እንደሚመስጣት መች አጣሁት!? እያልኩኝ ማሰብ ጀመርኩኝ።

የተግባቦት (Communication) ተማሪ እንደመሆኔ መጠን ከየትኛውም ንግግር በኋላ ራሴን ‹ኦዲት› የማድረግ ልማድ አለኝ። ከራሴው ጋር በመሆን ራሴ ላይ ባደረኩት ጥብቅ ክትትል ራሴን ከቁጥጥር ስር ማዋል ችያለሁ፤ ስህተቱም እኔው ጋር እንደነበር አስተውያለሁ። እኔ ስለ ሥራዋ የጠየኳት እንዲያው ስለ መጠየቅ (just for the sake of asking) እንጂ ከልቤ አልነበረም። እርሷ የምሯን ስትመልስልኝ ልቤ ግን ለመቀበል ዝግጁ አልነበረም (ልቤ የሥራዋን ደኅንነት የጠየቀው ከልቡ አልነበረምና)።

አንዳንድ ነገሮቻችን እኮ ስለተለመዱ ብቻ እንጂ በማስተዋል የሚደረጉ አይደሉም። ሰላምታዬ ራሱ ሰላም (ከልብ የሆነ መረጋጋት) የሚያስፈልገው ሆኖ አግኝቼዋለሁ። ከእንግዲህ እንኳን ወዳጆቼን ስለ ጤናቸው ስጠይቅ የደውል ጥሪ የምታስተጋባው የቴሌዋ ሴትዮ ራሱ ‹‹ጤና ይስጥልን!›› ስትለኝ ‹‹አብሮ ይስጥልን›› ለማለት ከልብ በሆነ አንዳች ምላሽ የሚኖረኝ ይመስለኛል (እርሷ ባትሰማኝም)።

ወደ ወርቅ መንደር ስመልሳችሁ፤ በዚህ ወቅት የገበያ ሁኔታ በእርግጥም ለእነርሱ ከባድ ነው። የሬሳ ሳጥን ነጋዴ ገበያው የሚደራው ሟች የሚበዛበት ወቅት እንደሆነ ሁሉ የወርቅ መደብሮችም ገበያቸው የሚሞቀው ተጋቢዎች የሚበዙበት ወቅት መሆኑን አንባቢዬም አያጣውም። ለነገሩ እንደው ልማድ ሆኖብን እንጂ ለማግባት ደግሞ ምን ወቅት ያስፈልገዋል!? ትዳር በረከት አይደል? ‹የሠርግ ወቅት› እያልን ነገር ማወሳሰቡን ትተን ከዓመት እስከ ዓመት ብንድር ምኑ ጋር ነው ክፋቱ?

ይህን ሳስብ እኔ ያገባሁ ጊዜ (ከአንድ ዓመት በፊት) ‹‹በግንቦት ወርማ አታገባም!›› ብለው ሰማዩን ዝቅ ያደረጉ ቤተሰቦቼ ጉዳይ መቼም አይረሳኝም። ‹እንዴ! ለምን!?› ስላቸው፤ ‹በቃ በግንቦት ወር ሠርግ አይደረግማ!›› ብለው ክችች። እኔም ግራ ስለገባኝ ይህ ነገር ከቃሉ ይሆን እንዴ? በሚል እሳቤ ‹ግንቦት› የሚለው ቃል ጥናት (Terminology) ላይ ተጠመድኩኝ። ‹ግንቦት› የሚለው ቃል ‹ግንብ› እና ‹ሞት› የሚሉ ኹለት ቃላት/ድምጾች ጥምረት ይሆን እንዴ? ብዬ አሰብኩኝና ለዚህም አቻ ትርጉም ፈለኩለት። ‹በግንቦት የተጋቡ ሰዎች በግንብ ይሞታሉ (ግንብ-ሞት)› የሚል አንድምታ ይኖረዋል አልኩኝና ደግሞ ምንም አልገጥምልህ ሲለኝ ተውኩት።

አዕምሮዬ ሊያርፍ አልቻለምና በመቀጠልም ወሩ የሚጠራበት ቃል ‹ግን› ብሎ ስለሚጀምር መሆን አለበ! ብዬም አሰብኩኝ። በዚህም መሠረት ‹አግብቼ ግን-ብሞት?› የሚል ሐሳብ ሊይዝ እንደሚችል ድምዳሜ ላይ ደረስኩኝ። ደግሞ ለራሴው መልሼ ይህ በፍጹም አይሆንም! አልኩኝ። ‹በመጨረሻም፣ ኤጭ! ጦሴን!› ብዬ ጉዳዩን በጥቅሉ ማሰላሰሉን ተያያዝኩኝ።

‹ግንቦት የጋብቻ ወር አይደለም› ይሉኛል፤ እና የፍቺ ወር ነው? ‹በግንቦት ወር መጋባት ደስ አይልም› ይሉኛል፤ እና መፋታት ነው ደስ የሚለው? እሺ! ግንቦት ወር ደርግ የወደቀበት ስለሆነ ነው? እና እርሱስ ቢሆን ከእኔ ትዳር ጋር ምን አገናኘው? የወደቀው ደርግ… የማገባው እኔ በርናባስ…! እኔ ‹ደርጉ› ወይም ‹ደርጋቸው› አይደለሁ!። ሲቀጥል በግንቦት ወር ደርግ ወደቀና እኔ በወሩ መነሳት (በትዳር) አልችልም!? ብዬ ግራ አጋቢዎቼ ግራ እንደተጋቡብኝ እንዳገባሁ አስታውሳለሁ።
ብዙ ሳላደክማችሁ፤ በቃ ለምን እንደምናደርጋቸው የማናውቃቸው ግን ሽንጣችንን ገትረን የምንከራከርላቸው ነገሮች ቁጥራቸው ብዙ ነው። ‹‹ይህ ሰውዬ እያወራ መኻል ፌርማታ ላይ የሚመጡ ሐሳቦች ሁሉ ይወስዱታል እንዴ!?›› ብለኸኝ ይሆናል፤ ግን የግንቦት ወር ከጋብቻና ከሠርግ የጸዳ እንዲሆን በወሩ እየተቃጣ ያለው አሠራር የወርቅ ቤቷ ወዳጄን በቀጥታ ይመለከታታል።

‹‹ግንቦት ወር ለትዳር አይሆንም›› ሲሉ በተዘዋዋሪ ‹በግንቦት ወደ ወርቅ ቤት መሄድ ለጤናም ጥሩ አይደለም›› እያሉ ነውና። አይይ…. ግንቦት! በዚህ ጉዳይ ከአንባቢዎቼ ግልጽ መረጃ በአድራሻዬ የሚያደርሰኝ ሰው ከተገኘ ሥሙ የባለውለታዎች ማስታዎሻዬ በደማቅ ብዕር ተጽፎ ይቀመጣል።
በሌላ በኩል ደግሞ ከወረርሽኙ የተነሳ የሠርግ ቤት ታዳሚዎች ቁጥር ውስን እንዲሆን መደረጉ ሰዎች ወደ ወርቅ ቤት እንዳይሄዱ ተጨማሪ ምክንያት ሳይሆን አይቀርም። ‹እንዴት?› አላችሁኝ? የእኔ ትውልድ ‹ግርግር ውስጤ ነው!› ይል አይደል? ዝምና ጭር ያለ ነገር አይመቸውም። የሕይወቱ ፍልስፍና የተቃኘበት የኑሮው ዘዬ ለውስጠቱ ብዙም ግድ የማይለው ለውጫዊው ነገር (ለገጽታ ግንባታ) ግን ጠብ እርግፍ የሚል ነው።

‹‹በኻያ ሰው ፊት ከማገባ ይህ ጊዜ እስኪያልፍ ኻያ ዓመትም ቢሆን መጠበቁ ይቀለኛል›› ያለ ሰው አለ ብላችሁ ታምናላችሁ? ከትዳሩ ይልቅ ሠርጉ፣ ከኑሮውም ይልቅ ግርግሩ የሚያስጨንቀው ተላላ ትውልድ እኮ ነው። ትዳር ማለት የሠርግ ቀን ቪዲዮ ክሊፕና ጭፈራ የሚመስለው ስንት ያልተፈወሰ አግቢ የሞላበት አገር መሰላችሁ? ለነገሩ የተጋቢዎቹ ችግር ብቻ ላይሆን ይችላል፤ የልጆቻቸው የነገ ሕይወት ግድ የማይሰጣቸው ግን ለራሳቸው ሥምና ክብር ሲሉ ሰንጋ ጥለው ሕዝብ ካላበሉ (ተበድረውም ቢሆን) ልጅ የዳሩ የማይመስላቸው ወላጆችም እጅግ ብዙ ናቸው። ብቻ ግን ይህ ሁሉ ተደማምሮ የወዳጄን የሥራ ቦታ (ወርቅ ቤት ሠፈር) ጭር አድርጎታል።

በእርግጥ ወርቅ በጣም ተወዳጅና ደስ የሚል ጌጥ ነው፤ ግን ለማጌጥም ጊዜ አለውና በዚህ ወቅት ሰፈሩ ጭር ብሏል። በተለይ ኮቪድ 19 ወደ አገራችን ገና እንደገባ (አሁን እንኳን ተላምዷል /ቤተኛ ሆኗል/ ሕዝቤም ዘንግቷል) ጊዜው የማስክ፣ የአልኮል፣ የሳኒታይዘርና የመሠረታዊ የእህል ፍጆታዎች ነበር። የጊዜው ወርቆችም እነርሱ ነበሩና። አንድ ነገር በራሱ ጥሩ ቢሆንም ውበቱ የበለጠ የሚጎላውና ዋጋ የሚኖረው በጊዜው ውስጥ ነው።

ጊዜውን ካልጠበቀ የፍቅር ቃል፣ በጊዜው የሆነ ቁጣ አንዳች ልብን ደስ የሚያሰኝ ነገር አለው። ወርቅ በዚህ ወቅት ወርቅነቱን አልቀየረም። ግን ፈላጊዎቹ ሰፈር ቀይረዋል። በዚህ ወቅት በጣም የሚያስፈልጋቸው ወርቅ ሳይሆን ሌላ ነገር እንደሆነ ስለተገነዘቡ ወርቅን ፊት ነስተውታል (በወጣቱ ቋንቋ “ላሽ” ብለውታል)። “ወርቃማው ጊዜ (golden time)” የሚባል የተለመደ ሐሳብ አለን አይደል? ምን ለማለት ተፈልጎ ነው? መቼስ ‹በወርቅ የተሠራ ጊዜ› የሚል ምላሽ አልጠብቅም። ‹ወርቃማነት› የሚል ጽንሰ ሐሳብ ሥሙን ያገኘበት ሥረወ-ቃል ባለቤት የሆነው ወርቅ የሚሉት ሥመ-ገናና ማዕድን ራሱ ወርቃማ ጊዜ አለው።

ውድ አንባቢ፤ የአውርቶ አደሯ ወዳጄን አሳብ መነሻዬ አድርጌ የባጡንና የቆጡን ስል በትዕግሥት አብረኸኝ በመዝለቅህ ምን እላለሁ? ከልብ የሆነው አክብሮቴ የገባህበት ገብቶ ያግኝህ። ግና ከወርቅ ሰፈሩ ሁኔታ ተነስቼ ለአንተ ለወዳጄ ሙግት ቢጤ አለኝና እንግዲያውስ ተሞገትልኝ።

የሁሉም ነገር ውበቱ በጊዜው ውስጥ ከሆነ ታዲያ አንባቢዬ ወርቃማ ጊዜውን እንዴት እያስተዳደረው ይሆን? ብዬ ስለ አንተ ለማሰብ ጥቂት ጊዜ ወስጃለሁ። ‹ጊዜ የሰጠው ቅል ድንጋይ ይሰብራል› የሚል የአበው አባባል አለን አይደል? ቅሉ ድንጋዩን የሚሰብረው በጥንካሬ ከድንጋይ በርትቶ እኮ አይደለም፤ ያንን የሚያደርግበትን ጉልበት ጊዜ ሰጥቶት እንጂ።

ምስኪኑን ሥጋ ለባሽ አንተን ሰማይ ሰቅለው ከአማልክት ጎራ የመደቡህ አንተ ከሌለህ መሬት በፀሐይ ዙሪያ መሽከርከሯን እንደምታቆም የነገሩህ እያሞካሹህ አብረውህ አይዘልቁም። ይህም የሆነው በጊዜው ነውና። ምን እርሱ ብቻ!? የሚገርምህ አሁን ይህንን ጽሑፍ የምታነብበት ዐይንህ ብርሃን የሚደክምበት ጊዜ ይመጣል፤ ጉልበትህም ይከዳሃል። በዙሪያህ ያሉ አድናቂዎችህም እንደ ወርቅ ሰፈሩ ደንበኞች ሄደው ግዛትህ (ዙሪያህ) ጭር የሚልበት ቀን ይመጣል። እባክህን ጊዜ ሳለህ የሕይወት ትርጉም ነገር ግድ ይበልህ።

በርናባስ በቀለ፤ የተግባቦት ባለሞያ ሲሆኑ በኢሜይል አድራሻቸው barnlhemic@gmail.com ላይ ይገኛሉ።

ቅጽ 2 ቁጥር 97 መስከረም 2 2012

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com