2013 ተስፋና ስጋት

Views: 119

የ2013 ዘመን መለወጫ በዓልን ምክንያት በማድረግ በማሕበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ተፅዕኖ ፈጣሪ የሆኑ የተለያዩ ሰዎችን ያነጋገረችው አዲስ ማለዳ ዕይታቸውን እና መልካም ምኞታቸውን እንደሚከተለው ተቀብላለች።

ኡስታዝ አቡበከር መሃመድ
የእስልምና ሃይማኖት መምህር
ኡስታስ አቡበከር ከአዲስ ማለዳ ጋር ባደረጉት ቆይታ እንኳን አደረሳችሁ በማለት ጀምረው፣ ስላለፈው ዓመት ጥቂት አውስተዋል። እንደ እርሳቸው ገለጻ ያለፈው ዓመት እንደ ዓለምም ሆነ እንደ አገር ከባድ ነበር። በተለይ በኢትዮጵያ በኹለት ዓይነት መንገድ ነው ያለፈው ያሉት ኡስታዝ አቡበከር፤ የኮቪድ 19 ወረርሽኝ አንዱ መሆኑን ጠቅሰዋል። ‹‹ከባድና የተፈተንበትም ጊዜ ነው፣ እንደ ማሕበረሰብ ደግሞ ግንኙነታችንን በተወሰነ መንገድ አሳይቶናል፤ እንድናውቀውም አድርጎናል›› ብለዋል።
በፖለቲካው ሁሉንም አንገት ያስደፋ፣ ውጥንቅጡ በዝቶ ያልታሰቡ እና የማይገቡ ነገሮችን ያሳየን ጊዜ ነው ብለዉታል። አክለውም ‹‹ምን አልባት ከለውጡ በኋላ ከባድ ጊዜ ነው ቢባል ማጋነን አይደለም።›› በማለት የተሰማቸውን ገልጸዋል።
እንደ ኡስታዝ አመለካከት ቀን እና ዘመን ተመሳሳይ ነው። በንግግራቸውም ‹‹2012ን ወቅሶ ከማለፍ እኛ ነን ዘመኑን እና ቀኑን መቀየር የምንችለው። መልካም ለሠራበት በመልካም የሚመልስ፣ ጥፋት ለሠራበት ደግሞ የዛኑ ያህል አፀፋ የሚመልስ ስለሆነ ያንን ነው የተመለከትንበት።›› አሉ።
አዲሱ ዓመት ምን ተስፋ ይዞ ይመጣል ብለው ያምናሉ ስትል አዲስ ማለዳ ጠይቃለች። ‹‹እስካሁን ባየነው ጥሩም መጥፎም ላይሆን የሚችልበት ምክንያት የለም። ምክንያቱም እኛው ነን 2012 የነበርነው፣ 2013 የምንሄደውም እኛው ነን። አዲስ ዓመት ሲመጣ አስተሳሰባችንን አድሰን መልካም ለመሆን ካላሰብን በቀር የተለየ ነገር መጠበቅ ለውጥ አይኖረውም። ስለዚህ መልካም እና ሰላም መመኘት እና እሱ እንዲሆን ደግሞ አሻራችንን ማሳረፍ አለብን።›› ብለዋል።
ይህ እንዲሆን ግን አሁንም ተድበስብስው የሚያልፉ ነገሮች መኖር እንደሌለባቸው፣ በግልፅ መነጋገር እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል። እንዲሁ ከላይ ከላይ ያለ ወሬ እና ምኞት ዋጋ አይኖረውም ሲሉም፤ አንድ ሰው ሰላም ማግኘት የሚችለው ወንድሙ ሰላም ሲሆን እንደሆነ ማወቅ፣ ይህንንም መንግሥትም ሕብረተሰቡም ማመን አለባቸው፤ እንደ ኡስታዝ ገለጻ።
ምኞታቸውን ሲያስተላልፉም እንዲህ አሉ፤ ‹‹በአዲስ ተስፋ እና ምኞት ሁላችንም ለመለወጥ ዝግጁ መሆን አለብን። እድሜያችን እየተገፋ እየጨመረ የሚሄድ ነው። አንድ ቀን ባደርን ቁጥር ወደ ፈጣሪ እየቀረብን የምንሄድ ስለሆነ፣ ምን ይዘን ነው ወደ ፈጣሪ የመንቀርበው የሚለውን በማሰብ የተሻለ መቀራረብ፣ የተሻለ ፍቅር፣ ለአገር የተሻለ የምንለፋ የምንሆንበት ጊዜ እንዲሆን እመኛለሁ።››

ኦባንግ ሜቶ
የሰበዓዊ መብት ተሟጋች
‹‹2012 ከሰብዓዊ መብት አጠባበቅ ጋር በተያያዘ፣ የኮሮና ቫይረስን ጨምሮ ከዛም ባለፈ ከበሽታው ውጪ ደግሞ እራሳችንን በራሳችን የገደልንበት ዓመት ነበር።›› በማለት የጀመሩት ኦባንግ ሜቶ ናቸው። ዓመቱ አስጨናቂና አሳዛኝ ቢሆንም ነገር ግን ጥሩ ነገርም አልጠፋም ሲሉ የሕዳሴ ግድቡን ውሃ ሙሌት መፈፀም አውስተዋል።
በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ምክንያት ተማሪዎች ትምህርታቸውን መከታተል እንዳልቻሉም አስታውሰዋል። በ2012 በታሪክ ታይቶ የማይታወቅ ክፋት ታይቷል፤ ጎረቤት በጎረቤቱ እጅ ሞቷል፣ ከሀምሳ ዓመታት በላይ የተለፋባቸው ንብረቶች በደቂቃዎች ወድመዋል፣ ሰው በማንነቱ ሕይወቱ ተቀጥፏል።
ይህን የዘረዘሩት ኦባንግ በድምሩ ለእርሳቸው በዓመቱ መልካም ነገር እንዳልታያቸው በመጥቀስ ነው የዓመቱን ክብደት የገለጹት። ‹‹ነገር ግን አባይ ግድብ ደግሞ ስንሰበሰብ ምን ያህል ጥሩ ሥራ እንደምንሠራ፤ በአንጻሩ ስንከፋፈል ዋጋ ያለው ነገር መሥራት እንደማንችል ነው ያሳየን።›› ሲሉ ተናግረዋል።
እንደ አዲስ በተቀበልነው በ2013ም ከፍተኛ የሆነ ስጋት እንዳላቸው አልደበቁም። ለዚህም ምክንያት ያሉት እንደ አገር እየተፈጠሩ ያሉ ችግሮች እየተወያየንበት እና በግልፅ ጥፋተኛውን ጥፋተኛ፣ ጥፋት ያልሠራውን ደግሞ ንፁሕ ማለት አስፈላጊ ሆኖ ሳለ ያ ባለመደረጉ ነው ባይ ናቸው።
‹‹ይህ ከተስተካከለ ምናልባት ለውጥ ሊኖር ይችላል። በተድበሰበሰ ማንነት ውስጥ ሆነን የተሻለ ነገር መጠበቅ ውጤት የለውም።›› ያሉት ኦባንግ፣ ምን ቢደረግ ይሻላል ለሚለው ሐሳብ ሲያክሉ፤ ‹‹ሕገ-ወጥ ነገሮች መጋለጥ አለባቸው። ከቤታቸው ከመኖርያ ስፍራዎች የተፈናቀሉ አሉ፤ እነርሱ መፍትሄ ሳያገኙ በምን ዓይነት ተስፋ መጪውን ዓመት ያለ ስጋት መጠበቅ እንችላለን? ችግሮች እንደ አገር አሉ፤ እነሱን አምነን እየተነጋገርን ነው ወይ? ለችግሮቻችን መፍትሄ እየፈለግን ነው ወይ? ደኅና እንዳልሆንን እያወቅን ደኅና ነን የማለት በሽታ አለብን። መጪው ዓመት ከሌላው ዓመት ለየት ያለ እንዲሆን እራሳችን ላይ መሥራት አለብን።›› ብለዋል።
ከራስ ነው አዲስ ዓመት የሚጀምረው የሚል እምነት ያላቸው ኦባንግ፣ ሰላምም ከግለሰብ ነውና የሚጀምረው ሁላችን ሰላም ከሌለን ለሌላ ሰው ሰላም መስጠት አንችልም። ብሔር እየመረጥን የምንኖር ከሆነ እንኳን አገር ቤተሰብ አስተካክለን መምራት አንችልም። መኖር ያለብን ሰው መሆናችንን እያሰብን ነው ሲሉ፣ ይህ ሁሉ የሚሆን ከሆነ ጥሩ ተስፋ ሊኖር ይችላል ሲሉ ተስፋቸውን ገልጸዋል።

መስከረም አበራ
በሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ መምህት
ለመስከረም 2012 ድንግርግር ያለ፣ በከፍተኛ ሁኔታ አሳዛኝ እና አሰቃቂ ነገር የተከናወነበት ወቅት ነበር። በንግግራቸውም ሰቆቃ የበዛበት ያሉትን ጊዜ ሲገልፁት፤ ‹‹ሰው የታረደበት ዓመት ነበር።›› ብለዋል። ‹‹አዳዲስ፤ እኛ ዐይተን የማናውቃቸው የመንግሥት ገፆች የታዩበትም ዓመት ነው›› ሲሉም የመሬት ወረራ፣ የባለሥልጣናት ንግግርና መሰል ኹነቶችን በግርድፉ ለማመላከት ሞክረዋል።
በአንጻሩ የተወሰኑ ተስፋዎችም የታዩበት ወቅት ነበር ያሉ ሲሆን፣ አዳዲስ ሐሳቦች የተንሸራሸሩበትን ኹነትም እንደ መልካም አገጣሚ አንስተዋል።
ለአዲሱ ዓመት 2013 የተወሰነ ተስፋ አለኝ ያሉት መስከረም፣ በፖለቲካው በኩል አሰላለፉ ጥርት እንደሚል እንደሚጠብቁ ነው የገለጹት። ምክንያታቸውን እንዲህ ገለጹ፤ ‹‹የተወሳሰበው ነገር 2012 ላይ ተገልጧል። [አስቀድሞ] ድብልቅልቅ ያለ እና ያልጠራ ነገር ነበር። አሁን ግን ማን ምንድነው የሚለውን አውቀናል፤ አያሳስብም።›› ብለዋል።
ያም ቢሆን ለአዲስ ዓመት ቢሆን የሚሉት ምኞት አላቸው፤ ‹‹ሁሉም ሰው የፖለቲካ አስተሳሰብ አለው። በዛው ልክ በዕለት ተዕለት ኑሮው ለፖለቲካው ፍቅር ያለው ሰው አለ። ነገር ግን ‹አገር አገር› የሚሉት አካላት የእውነት ቢሆን መልካም ለውጥ ይኖራል።›› ሲሉ ዕይታቸውንም አጋርተዋል። ከዛም ባለፈ ተቃራኒ ሐሳብ ያላቸው ማራመድ የሚፈልጉትን ሐሳብ ባያፍሩበት ብለዋል። ‹‹የምናፍር ከሆነ ባንይዘው [ሐሳቡን]።አስተሳሰባችንን እና ፍላጎታችንን ለሕዝብ ግልፅ ብናደርግ መልካም ነው።›› በማለት መልዕክታቸውንም አስተላልፈዋል።

መጋቤ እሸቱ ዓለማየሁ
የኦርቶዶክስ እምነት የሃይማኖት መምህር
መጋቢ ሀዲስ 2012ን ፈተና እና ሰቆቃ የበዛበት ዓመት ነው ይላሉ። ‹‹እንደውም ከዚህ ቀደም ከነበረው ለየት ባለ መልኩ ዓለምን ያስተሳሰረ የችግር፣ የፈተና እና የስቃይ ዓመት ሆኖ ያለፈ ነው።›› ብለዋልም።
‹‹የአብዛኛው ችግሮች ጋባዥ ራሳችን ነን።›› ያሉት መጋቢ ሀዲስ፣ በጎሳ እና በብሔር የተደራጁ የፖለቲካ ፓርቲዎች ረጋ ብለው አቋማቸውን ቢያስቡ፣ መወያየት እና መነጋገር ቢጀምሩ፤ በተለይ የኦሮሞን እና የአማራውን ሕዝብ እንወክላለን የሚሉ ቡድኖች ቆም ብለው ቢመለከቱ ሲሉ ምክረ ሐሳባቸውን ሰጥተዋል። አጠቃለውም እንዲህ አሉ፤ ‹‹ብዛታቸው አሳንሷቸዋል፣ ስፋታቸው አጥብቧቸዋል››
በተጓዳኝ መንግሥት ልበ ሰፊ ቢሆን ሲሉ ከገደብ ያለፈ ትዕግስትም ከገደብ በታች የሆነ ትዕግስትም ከባድ ዋጋ እንደሚያስከፍል አሳስበዋል። በዚህ ላይ ትኩረት ቢደረግ ያሉ ሲሆን፣ ማሕበረሰቡ እያንዳንዱ እራሱን በደንብ ፈትሾ ራሱን ከለወጠ፣ ለፖለቲካ ፓርቲዎችም መጨብጨብ ባለብት ብናጨበጭብ፣ ነቀፋ በሚገባው መንቀፍ ቢለምድ ባናደናግራቸው መልካም ነው ሲሉ አክለዋል።
‹‹ካለበለዚያ ግን ከባድ ይሆናል።›› ያሉ ሲሆን፣ በአዲሱ ዓመት 2013 ግን ስጋት እንደሌላቸው ገልጸዋል። ለምን ቢባሉ፣ ‹‹አሸናፊ እና ተሸናፊ ባለመኖሩ ምክንያት ስጋት የለኝም። መልካም የምናደርገውም እኛ ነን፤ የምናበላሸውም እኛው።››

ዶክተር ወዳጄነህ መኻረነ (የሕክምና የሥነልቦና እና ሥነመለኮት ባለሞያ)
በወዳጄነህ ዕይታ 2012 ‹ከዓመታት ሁሉ ምርጥ ዓመት፣ ከዓመታት ሁሉ አሰቃቂ ዓመት› ነበር። ዓመቱ ከተለያየ አንፃር ተጎድተንም ተጠቅመንም ያለፍንበት ነው ሲሉም እንዲህ ላሉበት ምክንያታቸውን አስረድተዋል።
በአንድ ጎን የሕዳሴ ግድቡን ያነሳሉ። 2012 ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን በተመለከተ ከፍተኛ ስጋት ነበር። ‹ተሸጧል› እና ‹አይሞላም› በሚል ብዙዎች ተሳቅቀው በነበሩበት ወቅት፣ ግድቡ በአንጻሩ ሙሌቱ ተጀምሮ፣ ውሃውም ሞልቶ ፈስሷል። በሌላ በኩል ቱሪዝምን አንስተው ከፍተኛ የሆነ ኪሳራ ውስጥ የተገባበት ጊዜ እንደነበረ ያወሳሉ።
ቱሪዝሙን በሚመለከት በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ያስጎበኟቸውን አዲስ አበባን የማስዋብ ሥራ (አንድነት ፓርክን ጨምሮ) በማስታወስ የቱሪዝም ገቢን ከፍ የሚያደርግ ነውና በዛ ተስፋ ማየታቸውን አንስተዋል።
የፍትህን ነገር በማንሳት ደግሞ ‹‹ፍትህ ባለመከበሩ ምክንያት ሰዎች ሲገደሉ በፍርሃት በሰቀቀን ያየንበት፣ ፖሊሶች ሥራቸውን ዘንግተው የታዩበት፣ ሰው ሕግ አለ ብሎ መተማመን ያቃተው ጊዜ ላይ ነበር።›› የሚሉት ወዳጄነህ፤ ነገር ግን በዓመቱ ማብቂያ መዳረሻ ላይ በአንዳንዶች ሲከበር መታየቱን ሳይጠቅሱ አልቀሩም።
ኮቪድ 19 የፈጠረውን መደናገጥ እና ጭንቀት አስታውሰዋል። ቢሆንም በአንጻሩ ሕዝቡ ዘንድ የታየው ማሕበራዊ ኃላፊነትን መወጣትና መተባበር ሲታይ ከፍተኛ የሆነ መተሳሰብ የፈጠረ ነበር ይላሉ። ፖለቲካውን በሚመለከት 2012 ከፍተኛ የሆነ የሐሳብ ፍጭት የነበረበት ነው በማለት ሲገልፁት፣ የተለያዩ ሐሳቦች ወደ መድረክ ወጥተው የተሸጡበት ነው። ቢሆንም በተገኘው ልክ መጠቀም ባለመቻሉ እና ነገሮች አቅጣጫቸውን በመሳታቸው ፍፃሜው እንዳያምር ሆኗል። ብለዋል።
በሃይማኖት በኩል ኮቪድ መግባቱን ተከትሎ በአንድ ላይ ሱባኤ ታውጆ የነበረበት እና በጋራ የጸሎት ስርዓት ሲከናወን የነበረበትን ወቅት አውስተዋል። በዛው ልክ ማምለኪያ ቦታዎች የተቃጠሉበት መሆኑ ደግሞ አስደንጋጭ ክስተት ነው ሲሉ ገልጸውታል።
በአዲሱ ዓመት 2013 ያላቸውን ተስፋ ሲገልጹ እንዲህ አሉ፣ ‹‹ብሔራዊ እርቅ ይደረጋል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ። ከዛም በላፈ ብሔራዊ መግባባት እንዲደረግ ከመንግሥት አካልም ከኅብረተሰቡም ለብሔራዊ መግባባት ትኩረት ቢሰጡ መልካም ይሆናል።››ብለዋል።

ታደለ ፈረደ (ዶ/ር)
የኢትዮጵያ ኢኮኖሚክስ ማኅበር ፕሬዘደንት

በ2012 በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ላይ ፈታኝ ክስተቶች ተስተናግደዋል በማለት ይጀምራሉ። እነዚህንም ሲያብራሩ አንደኛዉ ከኮቪድ-19 ጋር ተያያዞ የተከሰተዉ የጤናዉ ዘርፍ መታወክ፣ የኢኮኖሚ መቀዛቀዝን ያስከተለ የዘመናችን አስከፊ ክስተት መሆኑ ነው ብለዋል። ይህም ከእጅ ወደ አፍ በሆነ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኝ ብዙ ሕዝብ ባላት አገር ምን ያህል ፈታኝ እንደሚሆን አንስተዋል።
‹‹የኢኮኖሚ መቀዛቀዝ በተለይም በአገልግሎት ዘርፍና አምራች ኢንደስትሪዉ ላይ ጎልቶ ይታያል። በተጨማሪም የመንግሥት ገቢና የወጪ ንግድ ሚዛን ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ በማሳደር የማክሮ ኢኮኖሚ መዛባት እንዲባባስ አድርጓል።›› ብለዋል። አክለውም ድንበር ተሻጋሪው ወረርሽኝ ከጤና ወደ ኢኮኖሚ ብሎም ማኅበራዊ ችግሮችን ከመፍጠሩም በላይ ተጽዕኖውን ለማርገብ የሚያስችል አቅምን እየተፈታተነ ይገኛል ብለዋል።
ኹለተኛ ብለው ያስቀመጡት ደግሞ በኢትዮጵያ የተከሰቱ የአደጋ ስጋቶችንና እነዚህም በኢኮኖሚዉ ላይ ያሳደሩትን ጉዳት ነው። እነዚህን የአደጋ ስጋቶች በኹለት መልክ ሲስቀምጧቸው፤ አንደኛው የተፈጥሮ (ለምሳሌ የበረሃ አንበጣና ጎርፍ)፣ ኹለተኛው ደግሞ ሰዉ ሠራሽ (ለምሳሌ የፖለቲካ አለመረጋጋትና የፀጥታ መደፍረስ) ብለው አስቀምጠዋል።
እነዚህ የአደጋ ስጋቶች በምርትና ኢንቨስትመንት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ማስከተላቸውን አውስተው፤ እንደውም ከፖለቲካ አለመረጋጋት ጋር ተያይዞ በኢንቨስትመንት ላይ የደረሰው ውድመት የወደፊት ኢንቨስትመንት ፍሰት ላይም አሉታዊ ተጽዕኖ ይኖረዋል ሲሉ ስጋታቸውን ገልጸዋል።
በአጠቃላይ በ2012 የተከሰቱ አስከፊ ክስተቶች የኢኮኖሚ እደገቱን በከፍተኛ ሁኔታ ጎድተዉታል ያሉ ሲሆን፣ በ2012 የታየ ተስፋ እንደነበር ጠቅሰዋል። ይልቁንም የሕዳሴ ግድብ የመጀመሪያ የዉሃ ሙሌት መጠናቀቅን በዋቢነት አንስተዋል። በአዲሱ ዓመት 2013ም ኢኮኖሚዉ በተወሰነ ደረጃም ቢሆን እንዲያገግም መንግሥትና ሌሎች ባለድርሻ ተዋናዮች አስፈላጊዉን ድጋፍ እንደሚያድርጉ ይጠበቃል ብለዋል።
በመጨረሻም በ2013 ተስፋና ስጋቶችን ደምረው ሲያስቀምጡ እንዲህ ብለዋል፤ ‹‹በ2013 የኮቪድ-19 መድኃኒት አገራች በፍጥነት ማግኘት ከቻለች ለኢኮኖሚዉ መንሰራራት ጉልህ ሚና ይኖረዋል። በአንጻሩ የበሽታዉ ስርጭት ከተስፋፋ በኢኮኖሚዉ ላይ ሊያስከትል የሚችለው አሉታዊ ተፅዕኖ፣ የውስጥ ሰላምና አለመረጋጋት ለኢንቨስትመንትና ለአጠቃላይ ኢኮኖሚዉ እንደስጋት በዋነኝነት የሚጠቀሱት ናቸው።››

ዓለማየሁ ገዳ (ፕ/ር)
የምጣኔ ሀብት ባለሙያ

በ2012 የኢትዮጵያ ምጣኔ ሀብት የገጠመው አስፈሪ ሁኔታ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ እንደ አውሮፓ አገሮችና ሌሎች ክፉኛ ተጎጅ አገሮች ኢትዮጵያ ላይ ቢያልፍ ኖሮ የአገሪቱ ምጣኔ ሀብት ክፉኛ የመንኮታኮት ስጋት ነበረበት ሲሉ አውስተዋል፤ ፕሮፌሰር ዓለማየሁ። በሌላ በኩል በዓመቱ የነበረው ጥሩ ነገር ፈረንጆቹ ከነሐሴ እስከ መስከረም ይሆናል ብለው እንደተነበዩት የኮቪድ-19 ተጠቂዎች ቁጥር ከ6 ሚሊዮን እስከ 8 ሚሊዮን አለመድረሱ፣ ኢኮኖሚውም ማገገም መጀመሩ እንደሆኑ ባለሙያው አስቀምጠዋል።
እንደ ዓለማየሁ ገለጻ የኢትዮጵያ ምጣኔ ሀብት በቀጣይ 2013 ሦስት ክፉ ስጋቶች ሊኖሩበት ይችላል። ከእነዚህም አንደኛው የዋጋ መናር ሲሆን፣ የውጭ ምንዛሬ እጥረት ሳይፈታ መቀጠሉና በኮቪድ-19 ምክንያት ምጣኔ ሀብቱ ክፉኛ ሊጎዳ ይችላል የሚሉት ቀሪዎቹ ናቸው።

በየነ ጴጥሮስ (ፕ/ር)
የኢትዮጵያ ሶሻል ዴሞክራቲክ ፓርቲ ሊቀመንበር

ለበየነ ጴጥሮስ 2012 ኢትዮጵያውያን አንገታቸወን የደፉበት፣ ክፉ ክስተት የተስተናገድበት ቢሆንም መልካም ነገሮችም የታዩበት ዓመት ነበር። በዓመቱ አስከፊ ከሚባሉት ክስተቶች ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭት ተፈጥሮ የሰው ሕይወትና ንብረት ያለ ምክንያት የወደመበት፣ በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ብጥብጥ የተከሰተበት በተለይም ከደንቢ ዶሎ ዩኒቨርስቲ የታገቱ ተማሪዎች ጉዳይ እልባት ሳያገኝ ያለፈበት አስከፊ ወቅት አንደነበር ፕሮፌሰሩ አስታውሰዋል።
በአንፃሩ በዓመቱ መልካም ነገሮች በመጠኑ የታዩበት ዓመት እንደሆነ ያምናሉ። ከእነዚህ መልካም ነገሮች ካሏቸው መካከልም የታላቁ ህዳሴ ግድብ የመጀመሪያ ዙር የውሃ ሙሌት እና ሌሎች የልማት ሥራዎች የተከናወኑበት ዓመት ነው በማለት የዓመቱን በጎ ጎን ጠቃቅሰዋል።
ፕሮፌሰር በየነ ለአዲስ ማለዳ እንደገለጹት በ2013 በኢትዮጵያ ስጋት ሊሆኑ ከሚችሉ ጉዳዮች ውስጥ በትግራይ ክልል ያለስምምነት እየተደረገ ያለው ምርጫ አንዱ ነው ባይ ናቸው። ይህም በቀጣዩ አገራዊ ምርጫ ላይ ስጋት ሊሆን እንደሚችል ጠቁመዋል። እንደውም ወደ ሌሎች አካባቢዎችም እንዳይሰፋ የሚል ስጋት አላቸው።
በአንፃሩ በ2013 የምጣኔ ሀብት እድገት መሻሻል የሚታይበት፣ የፖለቲካ ፓርቲዎችና መንግሥት ብሔራዊ መግባባት ፈጥረው የተሻለ የፖለቲካ ምህዳር የሚፈርበት ዓመት እንደሚሆን ተስፋ አለኝ ብለዋል።

አረጋዊ በርሄ (ዶ/ር)
የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ትብብር ሊቀመንበር

የትዴፓው አረጋዊ በርሄ ከአዲስ ማለዳ ጋር በነበራቸው ቆይታ 2012 ያለፈበትን ሁኔታ ሲመዝኑ ብዙ ተግዳሮቶች፣ የትጥቅ ኃይል ትግል የታየበት አንዲሁም በለውጥ ፈላጊ ኃይሎችና በጥፋት ኃይሎች መካከል ከባድ ፍልሚያ የነበረበት ዓመት ነው ይሉታል።
በአንጻሩ 2012 ከ2011 ጋር የተያያዘ የለውጥ ሂደት የታየበት ዓመት እንደነበርም አረጋዊ መለስ ብለው አስታውሰዋል።
በ2013 ጥሩ ውጤት የሚታይበት ትልቅ የለውጥ ዓመት አንደሚሆን ተስፋ እንዳላቸው ጠቁመዋል። አክለውም በ2013 በሚደረገው ምርጫ ሕወሓት እንቅፋት ሊሆን ይችላል የሚል እምነት እንደሌላቸውና ሕወሓት ምርጫ ቢያደርግም ከዚህ በላይ የሚጓዝበት መንገድ እንደማይኖረው ጠቁመዋል።

ዳንኤል በቀለ (ዶ/ር)
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ኮሚሽነር

በኢትዮጵያ በ2012 የታዮ ፖለቲካዊ ሁነቶቸን በተለይም ከሰብዓዊ መብት አንፃር ክፉ፣ ጥሩና ተስፋ በአንድ ላይ ተደምረው የተስተናገዱበት ዓመት እንደነበር ዳንኤል ለአዲስ ማለዳ ሐሳባቸውን አጋርተዋል። ኮሚሽነሩ እንዳሉት በ2012 ከታዩ ጥሩ ሁነቶች ውስጥ አንደኛው በተለያዩ ተቋማት ሕጎች በስፋት የተፈተሹበትና የተስተካከሉበት ዓመት መሆኑ ነው። እንዲሁም ጥሩ ተስፋዎች የታዩበት ዓመት እንደነበር ኮሚሽነሩ አክለው አስታውሰዋል።
በአንፃሩ በ2012 ፈታኝና ክፉ ኹነቶች ብለው ያስቀመጧቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ የመጣው የብሔር አስተሳሰብ፣ ጽንፈኛ የፖለቲካ እንቅስቃሴዎች፣ ጽንፈኛ ሐይማኖታዊ አካሄዶችን ነው። በመሆኑም በአነዚህ ጽንፈኛ እንቅስቃሴዎች በተለያዩ የአገሪቱ ክፍል የግጭቶች መበራከት የታየበትና በዚህም የበርካቶች ሕይወት ያለፈበት፣ በርካታ ኢንቨስትመንቶችና የሕዝብ ንብረት ያለ አገባብ የወደመበት ዓመት እንደነበር አስታውሰዋል።
‹‹የዓመቱ ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ ከአንድነት ይልቅ ልዩነት ላይ ትኩረት የተደረገበት ዓመት ሆኖ በማለፉ፣ በርካቶች ተጎጂ ሆነው አልፈውበታል።›› ብለዋል።
ኮሚሽነሩ ከ2012 ዓመት ትዝብት በመነሳት በኢትዮጵያ በ2013 ስጋት ሊሆኑ የሚችሉ ነገሮችን ጠቅሰዋል። ከእነዚህም ውስጥ አንደኛው የብሔር ፖለቲካና ጽንፈኛ እንቅስቃሴዎች አሁን ካለው ሁኔታ አንፃር ቀዳሚ ስጋት ሊሆኑ እንደሚችሉ አመላክተዋል። በዚህም የግጭትና ኹከት ስጋቶች ሊኖሩ እንደሚችሉ አስቀምጠዋል።
ኹለተኛው የጠንካራ ተቋማት ተጠናክሮ አለመገንባት ለሚፈጠሩ ችግሮች ቁልፍ መፍትሔ ለመፈለግ ፈተና እንደሚሆን ኮሚሽነሩ ስጋታቸውን አስቀምጠዋል። ለሚፈጠሩ ችግሮች አልባት ማጣት የጠንካራ ተቋም ግንባታ አለመኖር ውጤት ነው ባይ ናቸው።
እንደኮሚሽነሩ ገለጻ ሌላው በ2013 እንቅፋት ይሆናሉ ተብለው ከሚጠበቁ ችግሮች ውስጥ የምጣኔ ሀብት መቀዛቀዝና የወጣቶች የሥራ ዕድል ፈጠራ እጥረት የሚሉት ይገኙበታል።
ሐሳባቸውን ሲያስተላልፉም እንዲህ አሉ፤ ‹‹የኢትዮጵያን ያለፉ ችግሮች ላለመድገም ጽንፈኛ የፖለቲካ አስተሳሰብን መጠየፍና ከልዩነት ይልቅ አንድ ሊያደርጉን በሚችሉ አጀንዳዎች ላይ ማትኮር ይገባል። በተጨማሪም ጠንካራ ተቋማትን በመገንባት ችግሮችን መቋቋም መቻል ይገባል።››

ቅጽ 2 ቁጥር 97 መስከረም 2 2012

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com