‹‹በአዲስ አበባ የሚገነቡ ሜጋ ፕሮጀክቶች የበጀት መጋነንና የግልጽነት ችግር አለባቸው›› አብን

Views: 191

በአዲስ አበባ የሚገነቡ 15 ታላላቅ ፕሮጀክቶች ግልጽነት እንደሚጎድላቸው እና የበጀት መጋነን ችግር እንዳለባቸው የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) አስታወቀ።
ንቅናቄው አክሎም የፕሮጀክቶቹን ጉድለት በቅርበት በመከታተል እና ጥናት በማድረግ ተመልክቻለሁ ሲልም አስታውቋል። የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ በጠቅላይ ሚኒስቴር ጽሕፈት ቤትና በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በኩል የሚሰሩ ዋና ዋና 15 ሜጋ ፕሮጀክቶችን ሁኔታ በንቃት በመከታተል ስለፕሮጀክቶቹ ዝርዝር መረጃዎችን ሲሰባስብ መቆየቱን የአብን የፖለቲካ ጉዳዮች ኃላፊ ክርስቲያን ታደል ተናግረዋል።

በዚህም መሰረት በጀታቸው (ወጪያቸው) የታወቁ ፕሮጀክቶች የገንዘብ መጠን በአጠቃላይ 5.737 ቢሊዮን ዶላር (ወቅታዊ ምንዛሬው ከ212 ቢሊዮን ብር በላይ) እና ተጨማሪ 59.2 ቢሊዮን ብር በአንድ ላይ ወደ 271 ቢሊዮን ብር የሚጠጋ እንደሆነ አብን መረዳቱን ክርስቲያን ገልጸዋል። ፓርቲው እንዳስታወቀው በጀታቸው የማይታወቁ ፕሮጀክቶች አንዳሉ አደረኩት ባለው የቅርብ ክትትል ማረጋገጡን አመላክቷል። በዚህም በጀታቸው በግልጽ ያልታወቁ ፕሮጀክቶች ወጭ ሲደመር አጠቃላይ የፕሮጀክቶቹ በጀት ከዚህ በላይ ሊሆን እንደሚችል አመላክቷል።

አዲስ አበባን ተመራጭ የቱሪዝም መዳረሻ ከተማ እንድትሆን የሚደረገውን መንግስታዊ እንቅስቃሴ በመርህ ደረጃ አብን እንደሚደግፍ አስታውቋል። ነገር ግን የሜጋ ፕሮጀክቶቹ እጅግ የተጋነነ ወጭ የሚወጣባቸው በመሆናቸው ንቅናቄው አንዳሳሰበው አስታውቋል። አብን እንዳስታወቀው አንዳንዶቹ ፕሮጀክቶች አገራችን አሁን ካለችበት ሁኔታ አንፃር የቅደም ተከተል ችግር ያለባቸው መሆናቸው፣ከአዋጭነት፣ ባለድርሻዎችን ከማሳተፍ፣ ከዲዛይንና ግንባታ አካሄድ፣ ከብክነትና ሙስናን ከማስቀረት፣ በግልጽ ጨረታ የግንባታ ተቋራጮችን ከመለየት እንዲሁም በየጊዜው ስለፕሮጀክቶቹ ለሕዝብ ግልጽ መረጃ ከመስጠት አንፃር ክፍተቶች ያሉባቸው መሆናቸውን አንደሚያምን አስረድቷል፡፤

መንግስት ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ ግልጽነት ባልተሞላበትና ቅድሚያ የሚሰጣቸውን አንገብጋቢ ጉዳዮች ባላስቀመጠ መልኩ ማዋሉ አብን ያሳስበዋል ተብሏል። በመሆኑም ፓርቲውን መንግስት ስለፕሮጀክቶቹ ለህዝብ ግልፅ ማብራሪያ እንዲሰጥ ጠይቋል። በተጨማሪም በአገሪቱ ያለው የሥራ አጥነት በአስከፊ ሁኔታ ላይ መገኘቱን በማጤን መንግስት ጊዜውንና አቅሙን ለወጣቶች ሥራ እድል ፈጠራና ለኢኮኖሚ ሽግግር እንዲያውል አብን ጥሪውን አቅርቧል።

አብን በቅርበት ተከታትየ አገኘሁት ባለው መረጃ መሰረት ሸገርን የማስዋብ ፕሮጀክት በጀት 31 ቢሊዮን ብር፣ የአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት እድሳት 2 ቢሊዮን ብር እንዲሁም የአዲስ አበባ ቤተመጽሐፍት 2 ቢሊዮን ብር፣ አዲስ ነገ (Addis Tomorrow) በጀት 3 ቢሊዮን ዶላር፣ መሶብ ታዎር 681 ሚሊዮን ዶላር፣ አንድነት ፓርክ የመኪና ማቆሚያ 2.5 ቢሊዮን ብር፣ ከአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት-ለገሐር መስቀል አደባባይ መልሶ ማልማት 2.5 ቢሊዮን ብር መሆኑን አስታውቋል።
ከፕሮጄክቶቹ ውስጥ በጀታቸው ታውቆ ተቋራጫቸው የማይታወቅ ብሎ አብን ካስቀመጣቸው ፕሮጀክቶች እንጦጦ ፓርክ ወጪው 1.5 ቢሊዮን ብር፣ የስብሰባ ማዕከል በጀት 10 ቢሊዮን ብር፣ መሶብ ታዎር ወጪው 681 ሚሊዮን ዶላር በጀት የተመደበላቸው ፕጄክቶች የሚገኙበት ሲሆን፤ መገናኛ የትራንስፖርት ተርሚናል ወጪውና ተቋራጩ አይታወቁም ሲል አብን አብራርቷል።

አዲስ ማለዳ በጉዳዩ ላይ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምላሽ ለማግኘት ለከተማ አስተዳደሩ ፕሬስ ሴክረታሪ ብትደውልም በጉዳዩ ላይ ምላሽ የሚሰጡ ስራ ኃላፊዎች በስራ ምክንያት ከቢሮ ውጭ መሆናቸውን የሚገልጽ ምላሽ በማግኘቷ የከተማ አስተዳደሩን ምላሽ ማካተት ሳይቻል ቀርቷል።

ቅጽ 2 ቁጥር 97 መስከረም 2 2012

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com