የእለት ዜና

በ2.2 ቢሊዮን ዶላር ሦስት ፋብሪካዎች ሊገነቡ ነው

በአማራ ክልል በሰሜን ሽዋ ዞን በመርሐቤቴ ወረዳ ዌስት ቻይና ሴመንት(west chaina cement) የተባለ የቻይና ኩባንያ በ2.2 ቢሊዮን ዶላር ወጪ ከአንድ አመት ባነሰ ጊዜ ውስጥ የሲሚንቶ ፋብሪካ፣ የጤፍ ምርት የፓስታና መኮረኒ ፋብሪካ እንዲሁም የብርጭቆ ፋብሪካ ለመገንባት ከአማራ ክልል መንግስት ፈቃድ ማግኘቱ ተጠቆመ።

ዌስት ቻይና የተባለው በሲሚንቶ ምርት ላይ የተሰማራው ድርጅት በአማራ ክልል በሰሜን ሽዋ ዞን መርሐቤቴ ወረዳ ላይ ፋብሪካ ለመገንባትና ወደ ስራ ለመግባት የመሰረተ ልማት ምቹነትና ምርቱን ለማምረት የሚያገለግሉ ጥሬ እቃዎች መኖራቸው ቀድሞ በወረዳው ላይ በመገኘት ጥናት እንዳደረገ የመርሐቤቴ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ ተሾመ አስፋው ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል። ፕሮጀክቱ የመጣው አዲስ አበባ በሚገኘው የአማራ ክልል ኢንቨስትመንት ቢሮ በኩል መሆኑን የወረዳው ዋና አስተዳዳሪ ተሾመ አክለው ጠቁመዋል። ድርጅቱ በቦታው ላይ ወደ ስራ ለመግባት ምቹ ሁኔታዎች መኖራቸውን ቀድሞ በማረጋገጥ ለክልሉ መንግስት የፈቃድ ጥያቄ ማቅረቡንም ዋና አስተዳዳሪው ገልጸዋል።

ዌስት ቻይና ሴመንት ድርጅት በወረዳው ፋብሪካ ሊገነባበት ቦታ ላይ በመገኘት የመሰረተ ልማት ምቹነትና ለምርቱ ግብዓት የሚሆኑ ጥሬ እቃዎች ክምችት መኖሩኑ በማረጋገጥ ፋብሪካውን ለመገንባት ለክልሉ መንግስት የፍቃድ ጥያቄ አቅርቧል ተብሏል። ድርጅቱ አስቀድሞ በቦታው ላይ ያለውን ጥሬ እቃ በማጥናት ማምረት የሚፈልገውንና እንድሰጠው የሚፈልገውን የግንባታ ፍቃድ እንዲሰጠው በጠየቀው መሰረት የክልሉ መንግስት በጉዳዩ ምክክር አድርጓል ተብሏል። በዚሁ ውይይት ላይ ድርጅቱ ከአንድ ዓመት ባነሰ ጊዜ ውስጥ ፋብሪካውን ወደ መገንባት እንዲገባ ስምምነት ላይ መደረሱን ተሾመ አመላክተዋል።

በክልሉ መንግስትና በቻይናው ዌስት ሴመንት ድርጅት ጋር የተደረገው ስምምነት ድርጅቱ በቦታው ላይ ያለውን ማዕድን በዝርዝር በማጥናት በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ ግንባታ እንዲገባ ስምምነት ላይ መደረሱ የተጠቆመ ሲሆን ከሚደረጉት ጥናቶች ውስጥ የአካባቢ ተጽዕኖና ለምርት ግብዓት የሚሆኑ ማዕድናት ቦታ ዝርዝር ጥናት የሚሉት እንደሚገኙበት ዋና አስተዳዳሪው ተናግረዋል።

በድርጅቱ ጥያቄ መሰረት የክልሉ መንግስት ነሐሴ 26/2012 በባህርዳር ከተማ በብሉ ናይል ሆቴል የክልሉ ፕሬዘዳንትና ሌሎች የክልልና የዞን ከፍተኛ አመራሮች በተገኙበት በቻይና እና በሌሎች አገራት ስምንት የሲሚንቶ ፋብሪካ ካለውና በዘርፉ የካበተ ልምድ ካለው ግዙፍ ኩባንያ ጋር ስምምነት ላይ ተደርሷል።
በቅርቡ ከክልሉ ማዕድንና ኢንቨስት መንት ቢሮ የተውጣጣ አጥኚ ቡድን እና የአካባቢ ተጽዕኖ ምዘና ቡድን በጋራ በመሆን የቦታ ልየታ ጥናት አንደሚደረግ ዋና አስተዳዳሪው አመላክተዋል። እንደ ዋና አስተዳዳሪው ገለጻ በወረዳው ላይ በቂ የሚባል የመሰረት ልማት አንዳለ ጠቁመው በወረዳው ላይ ከዚህ ቀደም የነበረው የመንገድ መሰረት ልማት እየተቀረፈ መሆኑን ተናግረዋል።

በተጨማሪም ወረዳው በቂ የኃይል አቅርቦት አለውም ተብሏል። በወረዳው ካለው 12.5 ሜጋ ዋት ኃይል በጥቅም ላይ የዋለው 4 ሜጋ ዋት የሚሆነው ብቻ መሆኑ የታወቀ ሲሆን፤ አሁን ያለው 8 ሜጋ ዋት ኃይል ለሚገነባው ፋብሪካ በቂ እንደሆነም ተመላክቷል ወረዳው ከዚህ በፊት በተለይም የመንገድ መሰረተ ልማት ችግር አንደነበረበት ያስታወሱት ዋና አስተዳዳሪው አሁን ላይ በወረዳው ከአስፓልት መንገድ ስራ ጋር ተያይዞ ትልልቅ የኢንቨስትመንት ፍላጎቶች እየጨመረ መምጣቱ ተመላክቷል።

የወረዳው ዋና አስተዳዳሪ ለአዲስ ማለዳ አንደጠቆሙት በወረዳው ሌሎችም የኢንቨስትመንት ስራዎች በሂደት ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል። ወደ አካባቢው ገብተው ለመስራት ፍላጎት ያሳዩ በቀለምና መአሳ ምርት ዘርፍ ለመሰማራት ፍላጎት ያሳዩ ድርጅቶች በሂደት ላይ መሆናችን አመላክተዋል።
ከዚህም የአካባቢውን ፀጋ ለመጠቀም በተጨማሪ በሆቴልና ቱሪዝም ዘርፍ ለመሰማራት ፍላጎት ያሳዩ ድርጅቶች አሉ ተብሏል።

ቅጽ 2 ቁጥር 97 መስከረም 2 2012

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

error: Content is protected !!