1.4 በመቶ ተሸከርካሪዎች ብቻ የፍጥነት መገደቢያ አስገጥመዋል

Views: 132

በተገባደደው አመትበኢትዮጵያ ውስጥ ካሉት ከ 1.2 ሚሊዮን ተሸከርካሪዎች ውስጥ የፍጥነት መገደቢያ መሳሪያ ያስገጠሙ 1.4 በመቶ ብቻ መሆናቸውን የፌደራል ትራንስፖርት ባለስልጣን ገለፀ። ለአዲስ ማለዳ መረጃውን የሰጠው ባለስልጣኑ እንዳስታወቀው የፍጥነት መቆጣጠሪያውን ያስገጠሙ ተሸከርካሪዎች ቁጥራቸው ጥቂት መሆኑን ገልጾ፤ በዚህም ምክንያት የፍጥነት መቆጣጠሪያ በማያስገጥሙ የአገር አቋራጭ ተሸከርካሪዎች ላይ ከመስከረም 1/2013 ጀምሮ የሚሰጡትን አገልግሎት የመከልከል እርምጃ እንደሚወሰድባቸው አስታውቋል።

ባለ ስልጣን መስርያ ቤቱ ለአዲስ ማለዳ እንደገለፀው ከሆነ ከፍጥነት መገደብያ ጋር ተያይዞ የወጣውን አዋጅ ተግባራዊ የማያደርጉት ላይ የመጀመርያ የስምሪት አገልግሎት እንዳያገኙ የሚደረግ ሲሆን ኹለተኛው ቅጣት ደግሞ ያንን ተላልፈው በህገ – ወጥ መንገድ ሲያሽከረክሩ ለመቆጣጠር በአራቱም መዓዘን ኬላ ላይ የቁጥጥር ስራ ይሰራል ተብሏል።

በተጨማሪም ከእነዚህ ውጪ በጊዜያዊነት በገንዘብ ደረጃ ምን ያክል ይቀጡ ለሚለው መመርያ እየተዘጋጀ እንደሆነ የባለስልጣኑ ህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ይግዛው ዳኘው ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።  ባለስልጣን መስርያ ቤቱ የመንገድ ትራፊክ አደጋን ለመቀነስ የተሽከርካሪ የፍጥነት መገደቢያ መሳሪያ ስለ መግጠምና ስለማስተዳደር የወጣውን መመሪያ ተግባራዊ ለማድረግ ሰፊ ስራዎችን ሲያከናዉን የቆየ ሲሆን ፤ እስከ አሁን ድረስ ባለው ሁኔታ ሁሉንም ተሽከርካሪዎችን ጨምሮ በኢትዮጲያ ከ1.2 ሚሊዮን በላይ ተሸከርካሪዎች ያሉ ቢሆንም 17,500 በላይ ብቻ የሚሆኑ ተሽከርካሪዎች ማስገጠማቸውን ተናግረዋል።

ስለሆነም ከመስከረም 1 ቀን 2013 ጀምሮ የፍጥነት መገደቢያ መሳሪያ በተሽከርካሪዎቻቸዉ ላይ ያላስገጠሙ የሀገር አቋራጭ የህዝብ ትራንስፖርት ባለንብረቶች፡ ማህበራትና ድርጅቶች ስምሪት እንደማያገኙ ተገልፁአል። በተጨማሪም ከመናሃሪያዉ ዉጪ በህገ-ወጥ መንገድ የሚሰሩ ካሉ በሁሉም መዉጫ በሮች ላይ ጥብቅ ቁጥጥር የሚደረግ ይሆናል።

የትራፊክ አደጋን ለመቀነስ የተሽከርካሪ ፍጥነት መገደቢያ መሣርያ ስለመግጠም እና ስለ ማስተዳደር በሚል በታኅሳስ ወር 2011 የፀደቀው መመርያ ቁጥር 27/2011 ተግባራዊ ከሆነበት ጊዜ ጀምሮ፣ እስከ 2012 በጀት ዓመት ማጠናቀቂያ ድረስ 17 ሺህ በላይ በሆኑ የጭነት እና የሕዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪዎች ላይ እንደተገጠመ የፌዴራል ትራንስፖርት ባለሥልጣን ለአዲስ ማለዳ አስታውቋል።

የባለሥልጣኑ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊው ይግዛው እንዳስታወቁት፣ በዚሁ በመመሪያው መሰረት መተግበር የጀመረው በ2011 ሲሆን ነገር ግን አሁን በፌዴራል ደረጃ እየተሠራ ያለው አዳዲስ የሚገቡ ተሽከርካሪዎች ላይ አስገዳጅ ሆኖ፣ ገና ወደ አገር ውስጥ ሲገቡ መሣሪያውን ገጥመው እንዲገቡ እየተደረጉ እንደሆነ እና በፈረንጆቹ አቆጣጠር ከ2000 የምርት ዓመት እና ከዛ በኋላ ባሉት ሥሪቶች የፍጥነት መገደቢያ መሣሪያ እንዲገጠም በሚል መመሪያ ወጥቶ እሱን ለማስተግበር እየተሠራም ነው ብለዋል።

የፍጥነት መገደቢያውን እንዳይጠቀሙ ከፍተኛ የግንዛቤ እጥረት አለ የሚሉት ይግዛው ‹‹የፍጥነት መቆጣጠሪያ መግጠም ማለት በቀላሉ መግባት ስንችል መንገድ ላይ ያስረናል›› በሚል እንደማይፈልጉት ተናግረዋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 97 መስከረም 2 2012

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com