አዲሱ ዘመን ከባለፈው ውጥንቅጥ የምንላቀቅበት ሊሆን ይገባል!

Views: 21

2012 በዓለምም ሆነ በአገር አቀፍ ደረጃ የተለያዩ ሰው ሰራሽ እና ተፈጥሯዊ ችግሮች በርትተው የታዩበት ዓመት ሆኖ አልፏል። ችግሮቹ ከመበርታታቸውም የተነሳ የጥንታዊው የማያዊያን የዘመን አቆጣጠር በ2012 ላይ ማለቁ የዓለም መጨረሻን ያመላክታል የሚለው በፈረንጆቹ አቆጣጠር እውን ሳይሆን ስላለፈ በኢትዮጵያ የዘመን አቆጣጠር ሊሆን ይችላል የሚሉ ድምጾች ጠንከር ብለው ነበር።

በዋነኝነት ይህንን ዓመት በታሪክ በትልቁ ስሙ እንዲነሳ የሚያደርገው ዓለም አቀፉ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ መሆኑ የሚያጠራጥር አይደለም። የፈረንጆቹ አዲስ ዓመት ሊጀምር ሲል በቻይና የተነሳው ይህ ወረርሽኝ በመጀመሪያ የበለፀገውን ዓለም አስጨንቆ የሚመኩበትን ቴክኖሎጂ እና የኢኮኖሚ ጥንካሬ አጣጥሏል። የአጭር ጊዜ ተደርጎ የተወሰደው ወረርሽን ግን ከተከሰተ ዘጠን ወራትን ያስቆጠረ ቢሆንም ምንም ዓይነት በአጭር ጊዜ የመጥፋት ምልክት ሳያሳይ በአስጨናቂነቱ ቀጥሏል።

በአገራችንም ቢሆን ወረርሽኙ ከተከሰተ ስድስት ወራት ያስቆጠረ ሲሆን ስርጭቱ በከፍተኛ ፍጥነት ላይ ይገኛል። ከ50ሺህ በላይ ሰዎች በቫይረሱ እንደተያዙ መረጃዎች የሚጠቁሙ ሲሆን ሕይወታቸው ያለፈ ሰዎች ቁጥር ደግሞ ወደ አንድ ሺህ እየተጠጋ ይገኛል። ባለፉት ዐስር ቀናት ውስጥ የተመዘገበው የየእለቱ የምርመራ ውጤት ቀድሞ ከነበረው ጋር ሲነጻጸር እየቀነሰ የመጣ ቢሆንም በጤና ሚኒስቴር በኩል አገሪቷ ክፉውን ጊዜ አልፉ እየቀነሰ የሚሔድበት ደረጃ ላይ ገብታ መሆኑ ግን አልተገለፀም። ነገር ግን እየቀነሰ መሔዱ ጥሩ ዜና ቢሆንም በአዲሱ ዓመት ወረርሽኙ እንዲያበቃ ጥንቃቄን ማጠናከር ተገቢ ነው።

ከዚያ ውጪ ባለቀው ዓመት አሳሳቢ ሆነው የቆዩት ሰው ሰራሽ ችግሮች የሰላም እጦትን፣ የሕግ የበላይነት ያለመከበርን፣ የመንግሥት ሙሉ በሙሉ የሚታመን አካል ሆኖ ያለመገኘትን፣ የአገር አንድነት ላይ የተደቀኑ አደጋዎችን፣ ጽንፈኛ ብሔርተኝነትን ያካትታሉ። የተፈጥሮ አደጋዎቹ ደግሞ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች በስፋት የተከሰተውን የአንበጣ መንጋ እና የጎርፍ አደጋ ያካትታሉ።

ከላይ የተዘረዘሩት ችግሮች የአገሪቱ የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ ሁኔታ ያልተረጋጋ፣ ብሎም ከፍተኛ ችግሮች የታዩበት እንዲሆን አስገድደዋል። በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የታዩት ብሔር ተኮር እና አልፎ አልፎም ኃይማኖት ተኮር ግጭቶች ከፍተኛ ቁጥር ያላቸውን ኢትዮጵያውያን ሕይወት የቀጠፉ ሲሆን በንብረት ላይ የደረሰውም ውድመት ለመተካት ዘመናት የሚጠይቅ ነው። የብሔር ፖለቲካ እያደር እየከረረ ሕዝቦች ለዘመናት የገነቡትን አብሮ የመኖር እሴት እየሸረሸረ መገንጠል ሲነሳ ብዙ የማያስደንቅበት ደረጃ ላይ አድርሶናል። ኢትዮጵያን መሳደብ፣ ባንዲራዋን ለማየት መጸየፍ፣ አለፍ ሲልም እንደ ቆሻሻ መጣል ወይም ደግሞ የክልልነት ጥያቄ ማንሳት፣ የክልል ወይም የፓርቲ ባንዲራ ከፍ ማድረግ፣ የእኛ እና የእነሱ ፖለቲካ ማራመድ እና ከራስ ብሔር ውጭ ላሉት ብሔሮች ጥላቻ ማሳየት እየተለመደ መጥቷል። በአንጻሩ ደግሞ አገርን መውደድ፣ አንድ ብሔርን ሳይለዩ ለሁሉም ሕዝብ መቆርቆር፣ ለባንዲራ ያለ ፍቅር እና የመሳሰሉት ስሜቶች በጠላትነት የሚያሳዩ እና በመንግሥት አካላትም የሚያሳድኑ ሆነዋል።

የሕዝብን ደህንነት፣ የአገርን አንድነት እና በአገሪቱ ውስጥ ብዘኛ የኃይል ባለቤትነቱን ለማስከበር ሲቸገር የሚታየው መንግሥት በዚሁ በብሔር ፖለቲካ የተተበተበ በመሆኑ አንዳንድ ጊዜ የአንድነት ኃይሎች ያየሉ ሲመስል ብዙም ሳይቆይ ተገላቢጦሹ ይከሰታል። ይህም መንግሥትን አንዴ ወደ ሕዝብ የሚያቀርብ ቀጥሎም እጅጉን የሚያርቅ ሁኔታ እንዲፈጠር በማድረግ ያለውን ተአማኒነት እጅጉን የሚሸረሽር ነው። እርስ በእርሱ የሚጓተት የሚመስለው የመንግሥትን መዋቅር የሞላው የካድሬ ስብስብም እጅጉን ግራ በመጋባት ገዢው ፓርቲ ብሔርተኝነት ይሁን አንድነት ከልቡ የያዘው ግልጥልጥ እስኪል መሃል መሃሉን ለመሔድ እየሞከረ ነው።

አዲሱ ዓመት አገራዊ ምርጫ የሚካሔድበት መሆኑን ግምት ውስጥ በመክተት እና ብሔርተኝነት በከረረባቸው አገሮች ውስጥ ምርጫ ያለውን ነገሮችን የማክረር አዝማሚያ ግምት ውስጥ በመክተት በገዢው ፓርቲ ውስጥ ያለው ጠንካራ የብሔርተኝነት እንቅስቃሴ ከወዲሁ እልባት ሊያገኝ ይገባዋል። አንዳንድ ጊዜ አንድን ብሔር ላለማስቀየም በሚል እየታዩ የሚታለፉ ሕገ ወጥ እና ኢ-ሰብአዊ ድርጊቶች ቆይተው አገራዊ ቀውስ ሊያስከትሉ እንደሚችሉ መገንዘብ ተገቢ ነው።

የቀድሞዋ ዩጎዝላቪያ በ1982 አገራዊ ምርጫ ከማካሔዷ በፊቱ ባሉት ዐስር ዓመታት ውስጥ ብሔርተኝነት ከፍተኛ መንሰራራት እያሳየ እንደነበር የሚታወቅ ነው። ዘንድሮ በአገራችን የምናያቸው የየብሔሩ መገናኛ ብዙኋን በዩጎዝላቪያም ውስጥ በስፋት የነበሩ ሲሆን እኛ እና እነሱ የሚለውን የብሔርተኝነት አስከፊ አስተሳሰብ ያራምዱ ነበር። ነገሮች ከምርጫው በፊት ባሉት ጥቂት ዓመታት ውስጥ እየተካረሩ የሔዱ ሲሆን ምርጫው ሲካሔድ ሁሉም ክልሎች የየራሳቸውን ብሔርተኛ ፖለቲከኞች እንደሚመርጡ ግልጽ ነበር። ምርጫው ተካሒዶ ብሔርተኞቹ ወደ ሥልጣን ሲወጡ በመጀመሪያ ያደረጉት ነገር ነጻ አገር መሆናቸውን ማወጅ ነበር። ያንን ተከትሎ ደም አፋሳሽ ጦርነት በግዛቶቹ መካከል የተካሔደ ሲሆን በመጨረሻም ዩጎዝላቪያ ወደ ሰባት አገርነት ተበትናለች።

ከዩጎዝላቪያ ልምድ የምናየው ምርጫን ማሸነፍ ለብሔርተኞች ጉልበትን የሚጨምር እና ነገሮች ተመልሰው በማይስተካከሉበት መንገድ የአገርን አንድነት እንዲንዱ የሚያግዝ ነው። በአገራችንም በትግራይ ክልል በዚህ ሳምንት በመንግሥት እውቅና ባይሰጠውም የታካሔደው ምርጫ ላይ ተሳታፊ የነበሩ ፓርቲዎች መገንጠልን እንደ ትልቅ አጀንዳ ይዘውት ብቅ ብለዋል። ይህም ምርጫና ብሔርተኞች ሲገናኙ ነገሮች ከሚገባው በላይ እንደሚከሩ አገራዊ ማሳያ ነው።
በመሆኑም ይህንን መካረር ግምት ውስጥ በማስገባት ከምርጫው በፊት የርዕዩት ዓለም ፉክክሮች ቦታ የሚያገኙበትን መንገድ መፈልግ አስፈላጊ ነው። ከዚህ አንጻር አዲሱ ዓመት የአገሪቱ ፖለቲካ ከብሔር የማንነት ጥያቄዎች በዘለለ የርዕዩተ ዓለም ፍጭቶች እና የሃሳብ የበላይነት ለመያዝ የሚደረግ ፉክክርን ያካተተ እንዲሆን መጣር እንደሚያስፈልግ አዲስ ማለዳ ታምናለች።

በመሆኑም አዲሱ ዓመት የሕዝብ ደህንነት የሚጠበቅበት፣ የብሔር እና የኃይማኖት ግጭት በብሔር እና ኃይማኖት ወዳጅነት የሚተካበት፣ የመንግሥት እና የሕዝብ መተማመን የሚጨምርበት፣ የመለያየት ሳይሆን የመዋደድ ዘመን እንዲሆን አዲስ ማለዳ ትመኛለች።

ከዚህ በተጨማሪ የመንግሥት ባለሥልጣናት ለፓርቲ ባላቸው ታማኝነት የሚመረጡበት አሠራር የሚቀርበት፣ በሙያቸው ብቁ የሆኑ ሰዎች ወደ ፊት የሚመጡበት፣ አጎብድዶ አዳሪዎች ትምህርት ቤት የሚገቡበት፣ እየተሸረሸሩ የመጡት አገራዊ እሴቶቻችን የሚያንሰራሩበት እና አንድነታችን የሚጨምርበት ዘመን እንዲሆን አዲስ ማለዳ ትመኛለች።

አዲሱ ዓመት ሰላም የሚሰፍንበት፣ ቀና ሃሳቦች ተቀባይነት የሚያገኙበት፣ ደስታ የሚሰፍንበት፣ ጥጋብ የሚሆንበት እና እኩልነት የሚሰፍንበት እንዲሆን በጋራ ልንረባረብ ይገባል። ባለፈው ዓመት የታዩት አስደንጋጭ እልቂቶች፣ ክፋቶች፣ ወገንተኝነቶች እና ሕገ ወጥነቶች ሁሉ በዚህ ዓመት ቦታ የሌላቸው እንዲሆኑ ሁላችንም የሚጠበቅብንን ልናከናውን ይገባል።

ቅጽ 2 ቁጥር 97 መስከረም 2 2012

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com