የእለት ዜና

በየነ ጴጥሮስ (ፕ/ር) አዲስ ባንክ እያቋቋሙ ነው

በበየነ ጴጥሮስ (ፕ/ር) ቦርድ ሰብሳቢነት የሚቋቋመው ሆሳዕና ባንክ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ ያወጣውን ደንብ እና መርሆዎች በመከተል በኹለት ቢሊየን ብር የተፈረመ ካፒታል በምስረታ ሂደት ላይ እንደሚገኝ ተገለፀ። በዋነኝነት በደቡብ አፍሪካ በሚኖሩ የደቡብ ክልል ተወላጅ ኢትዮጵያዊያን አነሳሽነት በምስረታ ላይ የሚገኘው ይህ ባንክ በአገራችን ያለውን ውስን የፋይናንስ ዘርፍ በማጠንከር ስራ ላይ የራሱን የሆነ አስተዋፅዎ እንደሚያበርክት ተገልጿል።

በተጨማሪም በተለያዩ የደቡብ ከተሞች፣ በአዲስ አበባ፣ በናዝሬት፣ በድሬዳዋ እንዲሁም በሌሎች ትልልቅ ከተሞች ያለውን የፋይናንስ አቅም እና የማህበረሰቡን የመቆጠብ ባህል ታሳቢ በማድረግ የባንክ አገልግሎትን በሁሉም ቦታ በይበልጥ ተደራሽ የማድረግ እቅድን ይዞ በመመስረት ላይ እንደሚገኝ የባንኩ የፕሮጀክት ማናጀር የሆኑት ኤርሲዶ ሌንዴቦ (ዶ/ር) ለአዲስ ማለዳ አስታውቀዋል።

ባንኩም በኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ በተቀመጠው ዝቅተኛ የመመስረቻ ካፒታል መሰረት በ2 ቢሊየን ብር የተፈረመ ካፒታል በምስረታ ላይ የሚገኝ ሲሆን በአሁኑ ሰአት 2 ሚሊየን አክሲዎኖች ለሽያጭ በማዘጋጀትና የአንድ አክሲዮን ዋጋ አንድ ሺህ ብር ሆኖ አንድ ሰው መግዛት የሚችለው ዝቅተኛ የአክሲዮን መጠንን ሃያ በማድረግ በምስረታ ላይ እንደሚገኝም ተገልጿል።

በተጨማሪም አክሲዮን ገዢዎች የአክሲዮን ግዢውን በሚያከናውኑበት ወቅት የፈረሙበትን የአገልግሎት ክፍያ 6 በመቶ መክፈል ይጠበቅባቸዋል ያሉት ኤርሲዶ የአክሲዮን ሽያጭ አከፋፈል ስርአቱም አቅሙ ያላቸውና የሚችሉ አጠቃላይ አክሲዮኑን በአንዴ ከፍለው መውሰድ የሚችሉ ሲሆን ለሌሎች ግን አከፋፈሉን በማቅለልና በመጀመሪያው ስድስት ወር ውስጥ የፈረሙትን ሀምሳ በመቶ እንዲከፍሉ በማድረግ ቀሪው ሀምሳ በመቶ ደግሞ በአንድ አመት ተኩል ውስጥ መክፈል እንደሚችሉም አስረድተዋል።

ባለፈው ስድስት ወራት ውስጥ ከኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ የቅድመ ምዝገባ ፍቃድን ለማግኘት አደራጆችን የማሰባሰብ፣ የባንኩን መነሻ እቅድ ላይ ጥናቶች የማድረግ፣ በዘርፉ ላይ የተጠኑ ሌሎች ጥናቶችን የማየትንና ባንኩ ትኩረት ሰጥቶ ሊሰራባቸው የሚችልባቸውን አካባቢዎችን የመለየት ስራዎች ሲሰሩ መቆየታቸውን የገለፁት ኤርሲዶ ብሔራዊ ባንክ ካመለከትን በኋላ ግን በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ የአክሲዮን ሽያጭ ፍቃድ አግኝተን ወደ ተግባር ለመግባት ችለናል ሲሉም ለአዲስ ማለዳ ገልፀዋል።

ባንኩን በማደራጀት፣ ካፒታል በመሰብሰብ እና በማማከር ስራ ውስጥ የሚሳተፉት ግለሰቦች በዘርፉ ላይ ከፍተኛ የሆነ ልምድ ያላቸው ናቸው ያሉት የባንኩ ፕሮጀክት ማናጀር የማደራጀት ስራውን በዋና ሰብሳቢነት በየነ ጴጥሮስ (ፕሮፌሰር)፣ በምክትል ሰብሳቢ አንባሳደር ተስፋዬ አቢሶ እንዲሁም ሌሎች በዘርፉ ከብዙ አመታት በላይ ልምድን ያካበቱ ባለሙያዎች የተካተቱበት ሲሆን በተጨማሪም የስራ እቅዱን ከፍ አድርገው የሚሰሩና የቴክኖሎውን ዘርፍ በማጠናከር ስራ ላይ የተሰማሩ ትልልቅ አማካሪ ድርጅቶች የተካተቱበት መሆኑንም ገልፀዋል።

ለምስረታ የሚያስፈልገው ካፒታል ተሰብስቦ ሲሞላ ጠቅላላ ጉባኤው ተጠርቶ የአክሲዮን ባለድርሻዎች ድርጅቱን የሚመሩ ከፍተኛ አመራሮችን በቦርድ ደረጃ ይመርጣሉ። ቦርዱ ደግሞ ፕሬዝዳንትና ምክትል ፕሬዝዳንት መርጦ ወደመደበኛው የባንክ ዘርፍ እንደሚቀላቀልም ኤርሲዶ አስታውቀዋል።

በከተማ ስሞች የባንኮች ስምን መሰየም በኢትዮጵያም ይሁን በአለም ላይ እየተለመደ ያለ ነገር መሆኑን የጠቆሙት ዳይሬክተሩ አብዛኛው መስራች አባላት የተለያዩ እንደ ጊቤ ባንክ፣ ፀሀይ ባንክ እና ሌሎች ለባንኩ መጠሪያነት እንዲውሉ አቅርበው የነበረ ቢሆንም በመጨረሻም ሆሳዕና የሚለው ስያሜ እንዲፀድቅ መደረጉን ገልፀዋል። የመጠሪያ ስሙ ከሆሳዕና ከተማ ጋር ስለተያያዘ የዛ አካባቢ ይሁን እንጂ ባንኩ ብሄራዊ እራዕይን ሰንቆ የተመሰረተና ወደ ፊትም የአፍሪካም ሆነ የአለም ገበያ ሲከፈት መነሻውን እዚህ በማድረግ በአፍሪካ ደቡብ አፍሪካ፣ ኬንያ፣ ደቡብ ሱዳን እንዲሁምወደ ሌሎች ኢትዮጵያዊያን ወደሚገኙባቸው አገራት የመሄድ እራዕይ ይዞ የተቋቋመ መሆኑንም ለአዲስ ማለዳ አስታውቀዋል።

የባንኩ መመስረት ዋንኛው አላማ አጋር በመሆን አክሲዮን የሚገዙ አካላት ትርፋማ የሚሆኑበትና አገራዊ የኢኮኖሚ እድገትን በማምጣት ድህነትን በመቀነስ እንደ አገር እየተደረገ ያለውን ጥረት በማበረታታ እና በመደገፍ ሁነኛ የሚባል አስተዋፅዎ ማበርከት ነው የሚሉት ኤርሲዶ በተጨማሪም በየአመቱ በሚሊየን የሚቆጠሩ ወጣቶች ስራ ፈላጊ በሆኑባትት አገር የፋይናንስና የባንክ ተቋማት መምጣታቸው ብዙ የስራ እድል እንዲፈጠር ያደርጋል ብለዋል።

በዚህም መሰረት ይሄን በውጪ በተለይም በደቡብ አፍሪካ ያለውን የዲያስፖራ አቅም እንዲሁም በደቡብ ህዝቦች ያለውን የስራ ባህል እና የመቆጠብ ልምድ እንደመነሻ ብንጠቀም ወደ ብሄራዊ የባንክ ዘርፉ በፍጥነት መግባት እንችላለን በማለት ባንኩን ለመመስረት መቻሉን ገልፀዋል። በአሁኑ ወቅት በአገራችን 16 የግልና ኹለት የመንግስት በአጠቃላይ 18 ባንኮች በስራ ላይ የሚገኙ ሲሆን 17 ተጨማሪ ባንኮችም ለመመስረት ከኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ የቅድመ ምዝገባ ፍቃድን የጠየቁ ሲሆን ከእነሱም ውስጥ አራቱ ፍቃዱን አግኝተው በምስረታ ሂደት ላይ ይገኛሉ።

ቅጽ 2 ቁጥር 97 መስከረም 2 2012

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com