በአፍሪካ 50 ሚሊዮን የሚሆኑ ዜጎች በከፋ የድህነት ደረጃ ላይ ሊደርሱ ይችላሉ ተባለ
አፍሪካ በአሁን ወቅት የዓለም ስጋት በሆነው የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ምክንያት በዘንደውሮው በፈረንጆቹ በ2020 መጨረሻ ላይ 13 ሚሊዮን የሚሆኑ ዜጎቿ ከድህነት ወለል በታች ይወድቃሉ ተብሎ ሲጠበቅ ወደ 50 ሚሊየን የሚሆኑት ደግሞ በከፋ የድህነት ደረጃ ላይ ሊደርሱባት ይችላል ተብሎ እንደሚገመት የቢል እና ሚኒንዳ ጌትስ ፋውንዴሽን አስታወቀ ፡፡
በዚህ ዓመት በወባ በሽታ የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር ደግሞ በእጥፍ እንደሚጨምር የተተነበየ ሲሆን በዓለም ዙሪያ ከአንድ ዓመት በታች የሆኑ 80 ሚሊዮን ሕፃናትም በቀላሉ መከላከል በሚቻሉ በሽታዎች ተጋላጭ ሊሆኑ ይችላሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ፋውንዴሽኑ ለአዲስ ማለዳ በላከው ሪፖርቱ ላይ አመላክቷል።
ከዚህ በተጨማሪም በ25 ዓመታት ውስጥ በአህጉሪቱ እየተከሰተ ባለው የኢኮኖሚ ውድቀት ምክንያት የተፈጠረው ኢኮኖሚያዊ ጉዳት ልዩነቶችን እና ኢ-ፍትሐዊነትን እያጠናከረ ነው ሲል ፋውንዴሽኑ ጠቁሟል፡፡
ሴቶች እና ሌሎች ተጋላጭ አካላት በእኩልነት እጦት እየተሰቃዩ ሲሆን ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ሀገራትም በምግብ እጥረት ችግር ላይ ናቸው፤ የትምህርት ቤቶች መዘጋትም በይበልጥ የገጠር ልጆች ላይ ከፍተኛ ተጽእኖ አሳድሯል ሲል በሪፖርቱ ላይ አመላክቷል፡፡
በመሆኑም ቢል እና ሚሊንዳ ጌትስ ፈውንዴሽን የኮቪድ-19 ወረርሽኝ የ20 ዓመታት ዕድገትን ያደናቀፈ መሆኑን ጠቅሶ ወረርሽኙን ለማስቆም ዓለም አቀፍ ርብርብ እንዲደረግ ጥሪው አቅርቧል።