የአዳዲስ ብር ኖቶች አንድምታ

Views: 217

በሳምንቱ የሥራ መጀመሪያ ሰኞ፣ መስከረም 4 ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በጽ/ቤታቸው ከብሔራዊ ባንክ ገዢ ይናገር ደሴ (ዶ/ር) ጋር በመሆን ከፍተኛ የመንግሥት ሹማምንት እና ጋዜጠኞች ባሉበት ኢትዮጵያ አዳዲስ የብር ኖቶች መቀየሯን ማስታወቃቸው በብዙዎች ዘንድ ድንገቴ ስሜትን ፈጥሯል። ‘ፕሮጀክት ኤክስ’ በሚል በከፍተኛ ሚስጢር ተይዞ መሠራቱን ያስታወቁት ዐቢይ፥ ከኹለት ዐሥርታት በላይ ያገለገሉት የ10፣ የ50 እና የ100 ብር ኖቶች በአዲስ እንዲተኩ ሲደረግ ለመጀመሪያ ጊዜ የ200 ብር ኖት ደግሞ ገበያውን እንዲቀላቀል መደረጉን አስታውቀዋል።

የታተሙት የብር ኖቶች ብዛት 2.9 ቢሊዮን ሲሆኑ 262 ቢሊዮን የገንዘብ ዋጋ አላቸው። ሌሎች ወጪዎችን ሳይጨምር፥ መንግሥት ለእነዚህ አዳዲስ የብር ኖቶች ኅትመት 3.7 ቢሊዮን ብር ወጪ ማድረጉም ታውቋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩም ሆኑ የብሔራዊ ባንክ ገዢው ለአዳዲስ ብር ኖቶች ወደ ገበያ መግባት ገፊ ምክንያቶች ብለው ከጠቀሷቸው ዋናዎቹ ከገንዘብ ጋር የተገናኙ ሕገ ወጥ ዝውውሮችን ለመግታት እንደሆነ፤ ከባንክ ውጪ የሚገኝ ገንዘብ እስከ 113 ቢሊዮን ብር ይደርሳል መባሉን ተከትሎ ለሕገ ወጥ ንግድ በተለይም በኮንትሮባንድ ላይ የተሰማሩ ግለሰቦች ለማስቆም በሚል እሳቤ መሆኑም በመድረኩ ላይ ተገልጿል።

መግለጫው የብዙኀንን ቀልብ ለመሳብ ጊዜ አልወሰደበትም። አንዳንዶች እርምጃውን ፖለቲካዊ ሲሉት ሌሎች ደግሞ የምጣኔ ሀብቱን እንቅስቃሴ ለመቆጣጠር ይበጃል ሲሉ ድጋፋቸውን ቸረውታል። እርምጃው ፖለቲካዊ ነው የሚሉት በሙስና እንዲሁም ከሕግ አግባብ ውጪ ገንዘብ ያከማቹትን ለመምታት ያለመ ነው ሲሉ በተለይ እጃቸውን ሕወሓት ላይ ቀስረዋል። አንዳንዶች የሐዘኔታ ይሁን የለበጣ በግልጽ ባይታወቅም ሕወሓት ጦርነት ለመቀስቀስ ስትባትል የማትችለው ፈተና ፊቷ ተደቀነ ሲሉ ሐሳባቸውን በማኅበራዊ ትስስር መድረኮች ላይ አንጸባርቀዋል።

ብዙ ጊዜ በፌስቡክ ገጻቸውም ሆነ በመደበኛ መገናኛ ብዙኀን በፋይናንስ ዙሪያ ትንታኔ በመስጠት የሚታወቁ አንድ ባለሙያ የብር ኖቶችን ለመቀየር ሲታስብ ዓላማዎቹ የሚሳኩ መሆኑን እርግጠኛ መሆን ያስፈልጋል ሲሉ የህንድን ተመክሮ አጋርተዋል። የህንድ መንግሥት ከአራት ዓመታት በፊት ከገንዘብ ኖቶች ቅያሬ ጋር በተያያዘ ያጋጠመውን ተግዳሮት በመዘርዘር “መንግሥት ሆይ! ዓላማህ ግልጽ፣ ዝግጅትህም በቂ ይሁን” ሲሉ ምክራቸውን ለግሰዋል።

መግለጫ በተሰጠበት ዕለቱን በተለምዶ ጋንዲ ሆስታፒታል አካባቢ የዶላር ምንዛሬ የሚያካሂዱ ሱቆች እንዲታሸጉ መደረጉ፤ ድንበር ከሚጋሩ አገሮች በተለይ ከጅቡቲ የሚመጡትን እንዲሁም በኢትዮጵያ አየር መንገድ በኩል ሊገቡ ይችላሉ የተባሉ ሕገ ወጥ ገንዘቦች ጥብቅ ቁጥጥር እየተደረገባቸው ለመሆኑ መረጃዎች ያመለክታሉ።
አነጋጋሪ የሆነው ሌላው ጉዳይ ልክ እንደተጠበቀው ከተለያዩ ቦታዎች በመቶ ሺሕዎች እና ሚሊዮኖች የሚገመቱ ብሮች በሕገ ወጥ እንቅስቃሴ ምክንያት የመያዛቸው ዜናዎች እየተበራከቱ መጥተዋል። ለአብነትም ከ2.3 ሚለዮን ብር በላይ በቤኔሻንጉል ጉሙዝ ክልል መያዙ ተተቃሽ ነው።

በሌላ በኩል በሕገ ወጥ መንገድ ገንዘብ አከማችተዋል የተባሉ ግለሰቦች ቀዳዳ ፍለጋ ምናልባትም ገንዘባቸውን በተንቀሳቃሽ እና ቋሚ ንብረቶች ግዢ ላይ በማዋል ተገቢያ ያልሆነ የንግድ መዛባት ሊያደርሱ ይችላሉ የተባለውን ጉዳት ለመቀነስ በማሰብ መንግሥት አዲስ አሠራር ዘርግቷል። በየፌደራል የሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ ኤጀንሲ ከመስከረም 7 ጀምሮ ማንኛውም ሽያጭ እና ብድር በባንክ በኩል በማድረግ ንብረት በጥሬ ገንዘብ መግዛት እንደማይቻል፤ ይህ ማለት እንደበፊቱ ከገዢው ወይም ከአበዳሪው የባንክ ሒሳብ ወደ ሻጭ ወይም ተበዳሪው ሒሳብ እንዲዘዋወር የሚያስገድድ አሠራር ተግባራዊ ተደርጓል። በአጭሩ ከገዢ ኪስ ወደ ሻጭ ኪስ የሚደረግ ግብይት አይኖርም ማለት ነው።

በርግጥ ዘለቄታዊው የብር ኖቶች መለወጥ አንድምታ በጊዜ ሒደት ውስጥ እየጠራ የሚመጣ እንደሚሆን የብዙዎች እምነት ነው።

ቅጽ 2 ቁጥር 98 መስከረም 9 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com