የልደቱ አያሌው የፍርድ ቤት ክራሞት

Views: 191

ከታዋቂው የአፋን ኦሮሞ ድምፃዊ ሃጫሉ ሁንዴሳ አሳዛኝ ግድያ በኋላ በተለይ በአንዳንድ የኦሮሚያ ክልል ከተሞችና ዞኖች በተቀሰቀሱ ሁከት እና ግርግር የበርካቶች ሕይወት ተቀጥፏል፤ ሌሎች በርካቶች ለአካል ጉዳተኛ ተዳርገዋል፤ ከፍተኛ የንብረት ውድመትም ደርሷል። ከዚህ ብጥብጥ ጋር በተያያዘ ታዋቂ ፖለቲከኞችም ጨምሮ ብዙ ሺሕዎች ለእስር ተዳርገዋል።

ፖለቲከኛው ልደቱ አያሌው በመጀመሪያ ወጣቶችን ለማሳመጽ የገንዘብ ድጋፍ አድርገዋል በሚል ተጠርጥረው ተይዘዋል። ከብዙ የፍርድ ቤት ምልልስ በኋላም ከሳሽ ዐቃቤ ሕግ ያልተፈቀደ የጦር መሳሪያ በመያዝ ወንጀል የሚል ክስ አቅርቦባቸዋል። ማክሰኞ፣ መስከረም 12 የምስራቅ ሸዋ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመቶ ሺሕ ብር ዋስትና ፈቃድ ጉዳያቸውን ከእስር ቤት ውጪ ሆነው እንዲከታተሉት ይፈቅዳል። ይሁንና የፍርድ ቤቱ ውሳኔ በአስፈጻሚው አካል በኩል ተፈፃሚ ሊሆን አልቻለም። የኦሮሚያ ፖሊስ ሰጠ የተባለው ምክንያት “ልደቱ የአደራ እስረኛ ስለሆኑ መልቀቅ አልችልም” መሆኑ ይበልጥ ያሳዝናል። በርካቶች የፖሊስን ምክንያት ውሃ የማይቋጥር ሲሉም ተችተዋል።

የሆነው ሆኖ ልደቱ የመቶ ሺሕ ብር ዋስትና ቢያሲዙም ሐሙስ፣ መስከረም 14 ከእስር ሳይፈቱ የኦሮሚያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ምስራቅ ሸዋ ዞን ተዘዋዋሪ ምድብ ችሎት የተፈቀደውን የመቶ ሺሕ ብር ዋስትና ማገዱ ተሰማ። የሥር (የዞኑ ከፍተኛ) ፍርድ ቤት ውሳኔው እገዳ ሰበብ ደግሞ በክልሉ ዐቃቤ ሕግ ይግባኝ በመጠየቁ መሆኑም አብሮ ከዜናው ጋር ተጠቅሷል።

ይህ የልደቱ የፍርድ ሒደት ብዙዎችን በሐሳብ አከራክሯል። በተለይ በዋስትና ላይ ዐቃቤ ሕግ ይግባኝ ማለት ይችላል ወይ የሚለው ላይ ብዙ መነጋገሪያ ርዕሰ ጉዳይ ሆኗል።

በአንድ በኩል አሁን አሁን ፍርድ ቤቶች በንጽጽር በነፃነት ፍርድ መስጠታቸው ከነውስንነታቸው አበረታች መሆኑን የሚገልጹትን ያክል ሌሎች የፍርድ ቤት ውሳኔ ተፈጻሚ እስካልሆነ ድረስ ምኑ ነው ፋይዳው ሲሉም ይጠይቃሉ። የአስፈፃሚው አካል ለፍርድ ቤት አለመታዘዝ የአንባገነንነት ማቆጥቆጥ ምልክት አንዱ ማሳያ ነው ሲሉ የጠቀሱም አልጠፉም። ብዙኀኑ ግን ምንም ይሁን ምን የፍርድ ቤት ትዕዛዝ መፈጸም ነበረበት ሲሉ በአጽንዖት አሳስበዋል።

የልደቱ የፍርድ ሒደት ተርታውን ዜጋ ብቻ ሳይሆን የሕግ ባለሙያዎችን ቀልብ ስቦ ብዙ መነጋገሪያ መሆን ችሏል። ሕገ መንግሥቱንም ሆነ ሌሎች ሕጎችን በማጣቀስ የሞቀ ክርክር አንስተዋል። ከግራ ከቀኝ ሕግን መሰረት ያደረጉ ክርክሮችም ተሰምተዋል።

አንድ የሕግ ባለሙያ “ፍርድ ቤት አንድ በወንጀል የታሰረ ሰውን በዋስ እንዲለቅ ያዘዘ እንደ ሆነ ዐቃቤ ሕግ ይግባኝ ማለት ይችላል ወይ?” ሲሉ በፌስቡክ ገጻቸው የጠየቁ ሲሆን ብዙ የሕግ ባለሙያዎች ሕግ እያጣቀሱ ለጥያቄው ምላሻቸውን ሰጥተዋል።

አንድ ባለሙያ የታሰረ ሰው ዋስትና ከተከለከለ ይግባኝ ማለት ይችላል። ከዚህ ውጪ ግን የታሰረ ሰው በዋስ እንዲለቀቅ የተፈቀደለት እንደሆነ ዐቃቤ ሕግ ይግባኝ ማለት አይችልም ሲሉ ሕግ አጣቅሰው ሞግተዋል። የዚህ ሐሳብ ደጋፊዎች ዋስትና ከታሰሩ ሰዎች አንጻር ሕገ መንግሥታዊና ሰብኣዊ ነው ሲሉ ከዐቃቤ ሕግ አንጻር ግን ተቀባይነት የለውም ሲሉ አበክረዋል።

የዚህ ሐሳብ ደጋፊዎች ዐቃቤ ሕግ እስረኛው በዋስትና እንዲለቀቅ በሚሰጥ ብይን ላይ ይግባኝ ለመጠየቅ መብት ከሌለው እስረኛው እንዳይለቀቅ ለጊዜው የማገድ መብት ሊኖረው አይችልም ብለዋል። ከዚህ በተጨማሪም በዋስ የሚለቀቀው እስረኛ ለጊዜው መለቀቁ በመንግሥት ላይ የሚያደርሰውን ጉዳት እና በሌላ በኩል ታስሮ መቆየቱ በታሳሪው ላይ የሚያስከትለው ጉዳት ስናመዛዝነው የእስረኛው መቆየት ይበልጥ ጎጂና ሊመለስ የማይችል ነው የሚል መከራከሪያ አቅርበዋል።

በሌላ በኩል ደግሞ ሌሎች የይግባኝ መብት ላንዱ ተፈቅዶ ለሌላኛው የሚከለከል ከሆነ ፍትሕ ሚዛኑን ያጣል እናም ሥነ ስርዓቱ በግልጽ ባያስቀምጠውም አልከለከለም። ስለዚህ ዐቃቤ ሕግ ይግባኝ መጠየቁ ላይ ፍትሓዊ ከመሆን አንጻር ሕገ ወጥ ነው መፈቀድ የለበትም የሚለው ብዙ ርቀት አያስኬድም ሲሉ በተቃራኒ ወገን ለቆሙት የክርክር ሐሳባቸውን ሰንዝረዋል። ይህንን ሐሳብ በማጠናከር በንጉሡም፣ በደርግም ሆነ አሁን ዐቃቤ ሕግ ይግባኝ ይላል። በዋስትና ላይ በሚሰጥ በዋስ መለቀቅ የሚል ውሳኔ ይግባኝ አይባልበትም የሚል ድንጋጌ የለም ሲሉም ሞግተዋል።

ይሁንና በልደቱ የፍርድ ሒደት ዙሪያ በተርታው ሕዝብም ሆነ በባለሙያዎች መካከል የሚደረጉት ክርክሮች አሁንም ቀጥለዋል። የሆነው ሆኖ ፍትሕ ለልደቱ አያሌው ማለት ግን ያስፈልጋል!

ቅጽ 2 ቁጥር 99 መስከረም 16 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com