‹‹ድሮ ሞት የማትፈራ ከነበርክ አሁን ፈሪ ትሆናለህ››

Views: 256

‹አገር ማለት ሰው ነው፤ ሰው ነው ሰው ነው አገር
ታሪክ የሚሠራ ታሪክ የሚቀይር
ሕዝቤ ነው ኃያሉ ምሰሶና ማገር› የምትል የኢትዮጵያን ገጽ የያዘች ተዋናይት አኳኋን እንዲሁም ድምጽ ከብዙዎች የሕሊና ዐይንም ሆነ ጆሮ የሚጠፋ አይደለም። ያቺ ተዋናይት ከዛ ቴአትር በኋላ ‹የኛ› በተሰኘና ብዙ አድማጭ በነበረው ተከታታይ የራድዮን ድራማ ላይም በትወና አቅሟን አሳይታለች፤ ለምለም ኃይለ ሚካኤል።

የኛ ፕሮጀክት ሥራውን በአዳዲስ ወጣት ተዋንያን በአዲስ ምዕራፍ ሲቀጥል፣ የቀደሙ ‹የኛ› ልጆች በጋራ እንዲሁም በየግላቸው የሙዚቃ ሥራዎችን ማቅረቡን ተያያዙት። ለምለምም ምርጥ የሚባሉ በምስል የታገዙ ነጠላ ዜማዎችን ለአድማጭና ተመልካቹ አድርሳለች። በቴአትር ትምህርት የመጀመሪያ ዲግሪ ያላት፣ በሙያዋም ለወጣቶች እንደ ተምሳሌት የምትቀርበው ተዋናይት እንዲሁም ድምጻዊት ለምለም ኃይለ ሚካኤል የአዲስ ማለዳ እንግዳ ሆና፤ የቀደመ የቴአትር ሥራዋን እንዲሁም ያለችበትን ሁኔታና አዲስ የሙዚቃ ሥራዋን በሚመለከት ከዳዊት አስታጥቄ ጋር ተከታዩን ቆይታ አድርጋለች።

በቴአትር ትምህርት በዲግሪ ደረጃ እንደተማርሽ ይታወቃል፣ ከቴያትር እና ከሙዚቃ ነፍስሽ ወደየትኛው ያደላል?
በቴያትር ብዙ ልምድ የለኝም። ግን ኹለቱም የራሳቸው የእርካታ መጠን አላቸው። እስከአሁን በሕይወቴ የሠራሁት አንድ ትልቅ ቴአትር ነው። ለሕይወቴም ትልቅ መነሻ የሆነኝ ብዬ ልወስደው የምችለው እሱም ‹አገር ማለት ሰው ነው› የሚለው ነው። በጊዜው ትልቅ ተቀባይነት የነበረው የጋሼ አባተ መኩሪያ ድርሰት ነው።
ቴአትር በጣም ደስ የሚል ገጽታ አለው። አድናቆትን ፊት ለፊት እያየኸው፣ ግብረ መልስህንም እዛው እያገኘህ፣ እዛው እያስተካከልክ የምትሠራው ነገርም ስለሆነ ቴአትር እርካታው ደስ የሚል ነው። እውነት ለመናገር ቴአትር እንደባለሙያም ራስህን የምትፈትንበት ዘርፍ ነው። ብዙ የቴአትር ባለሙያዎች አሉ። ከቴአትር ወደ ፊልም የመጡ እና ስኬታማ የሆኑ። ስሜትህ ከዛ ጋር አይርቅም። በቴአትር ደጋግመህ ልትለው፣ ልትሠራው የምትችልበት አጋጣሚ የለም። ያለህ አንድ እድል ነው። እናም እሱ ለባለሞያ ትልቅ ፈተና ነው።

ሙዚቃ ጋር ስትመጣ አብረህ ልትሠራ የምትችላቸው ብዙ ሰዎች አሉ። ደጋግሞ የመሥራትና የመለማመድ አጋጣሚ አለ። በዙሪያህ ብዙ የሚያግዙህ ሰዎች አሉ። ስለዚህ ከኹለቱ ልመርጥ አልችልም፣ ኹለቱንም የምወደው ሙያ ነው። አሁን ትኩረቴ ሙዚቃ መሥራት ላይ ሆነ እንጂ በማበላለጥ ደርጃ አይቼው አላውቅም።

እንደዛ ከሆነ ታዲያ ከቴአትር መድረክ ወይም ከትወናው ለምን ጠፋሽ?
ከቴአተር እኮ ጠፋሁ አይባልም። ወደ ‹የኛ› የሬድዮ ድራማ ነው የተሸጋገርኩት። ያው ‹የኛ› በብቸኝነት (exclusive) ስለነበር ሌላ ሥራ መሥራት አንችልም ነበር። ያኔ ሁሉ ነገር ተዘጋጅቶ ነበር ወደ ስቱድዮ ለቀርፃ እንገባ የነበረው። እድሉ ቢኖር እንኳ መሥራት አልችልም ነበር። ከ‹የኛ› ቆይታ በኋላ ግን ወደ ስርአቱ ለመመለስና ወደ ገበያ ለመግባት፣ ቴአትርም ለመሥራት፣ ፕሮዲዪስ ከሚያደርጉ ባለሙያዎች ጋር ለመገናኘት ትንሽ አስቸጋሪ አድርጎብኛል፤ እድሉንም አላገኘሁም።
ወደፊት ግን እድሉን ካገኘሁ እሠራለሁ። ካልሆነ ግን በራሴም ቢሆን የመሥራት ሐሳብ አለኝ፤ በፊልም እንዲሁም በቴአትርም።።

‹አገር ማለት ሰው ነው› የሚለውን ቴአትር እናንሳ፤ አገር ለአንቺ ምንድን ነው? ‹ሰው ነው› በሚለውስ ትስማሚያለሽ?
አገር ማለት ሰው ነው የሚለውን መልስ ዛሬ ላይ ሆኜ ለመመለስ ትንሽ ይከብደኛል። ስሜቴን ይነካል። እንግዲህ አሁን ላይ ዋጋ የምንሰጣቸው ጉዳዮች ከሰውነት ከአገር ያነሱ ቁሳዊ ነገሮች እየገዘፉ እየተቸገርን ነው ያለነው።

እንደ አጋጣሚ በቅርብ ጊዜ ለአዲሱ የሙዚቃ ሥራዬ ላሊበላ አካባቢ ሄጄ ነበር። ላሊበላ ስንሄድ እዚህ ቁጭ ብለን ስናስብ የጠፋ የሚመስለን እሴቶቻችን ለማገናዝብ እድል አግኝተን ነበር። የሰውን ልጅ ዘቅዝቆ መስቀል፣ ማረድ የመሳሰሉ ዘግናኝ ድርጊቶች መደረጋቸውን ስናስብ፣ መልካም የሚባሉት እሴቶቻችን የት ሄደው ነው ብለን እናዝናለን።

ሥነልቦናችንም የተሸማቀቀ ነው። ጫናውም ቀላል አይደለም። ነገር ግን የሉም ብለን የምናስባቸው እሴቶች እንዳሉ ተረድቼ ተስፋዬ ሞልቶ ነው የመጣሁት። የሰውነት ልክን ተመልክቼበታለሁ። እኔ ባሌ ተብሎ የሚጠራው አካባቢ ነው ተወልጄ ያደግኩት። ተወልጄ ባደኩበት አካባቢ ታዲያ ከገጠር ወይም ራቅ ካለ ቦታ የሚመጡ ሰዎችን በቅርበት የማወቅ እድል ነበረኝ።

ደግነት፣ ሰው ማክበር፣ መተማመን እና ሌሎች ብዙ መልካም ስብእናዎችን ነው ሕዘቡ ዘንድ አስተውል የነበረው። እዚያ የማውቀው ነገር እየጠፋ ነው የሚል የፍርሃት ሐሳብም ነበረኝ። ብዙ ጊዜም አሁን ማን ይታመናል፣ ስለማን ነው ደፍሬ መናገር የምችለው እያልኩ አስብ ነበር።

እንዳልኩህ ከጥቂት ወራት በፊት ለቀረፃ ከላሊበላ 25 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ወጥተን ያገኘነው ማንነት ወይም ማህበራዊ መስተጋብር አሁንም እሴቶቻችን ስለመኖራቸው ይነግርሃል። ለእኔ ያ ትልቅ ማሳያ አድርጌ እወስደዋለሁ። ያልደረሰ ማር ቆርጦ የሚያበላ ሕዝብ፣ ጎረቤት እንግዳ መጣባችሁ ብለው በጆግ ሙሉ ጠላ ይዘው የሚመጡ ሰዎች ያሉበት፣ ከሰውነታቸው ጋር የተጋቡ፣ ቱባ እሴት ያላቸው ማህበረሰቦች መኖራቸውን ይነግርሃል። ማንነታችንን ሳይጠይቁ በሚገባ ነበር ያስተናግዱን።

ላሊበላ እያልን አየዘፈንን መሆኑን ሲያውቁ ደግሞ፣ አካባቢያችንን የሚያነሳይ ዘፈን እየተዘፈን ብለው በጣም ደስ አላቸው። እንግዶች ናችሁ ብለው እኛን ያስተናገዱበት መንገድ እሴቶቻችን ላለመጥፋታቸው ማሳያ ነው። ስለዚህ የሰውነት ማንነት፣ የስብዕና ልክ እንዳለ ገላጭ ነው ማለት ነው።

ሰውነት ውስጥ ያለ፣ ነገር ግን በሆነ ነገር የተሸፈነ አውሬነት ወይም መጥፎ ባህርይ አለው። በአጭሩ እንደ ኤሊ ተፈጥሮ ነው ብለን ማንሳት እንችላለን። ከላዩ ሲታይ ጠንካራ ሆኖ ግን ውስጡ ለስላሳ ገፅታ ያለው ነው። አሁን እያየን ያለነው ትልቁ ክፋት፣ ጭካኔ ከላይ ያለው ነው ብለን ብንወስድ፤ የተሸፈነው ውስጣችን ያለው ብዙዎችን ኢትዮጵያውን የሚገልጽ ባህሪያችን እንደሆነ ይሰማኛል።

አገር ስትል ያ ቁሳዊ ነገሩ፣ ብልጭልጩ፣ ጊዜያዊው ነገር እንዳልሆነ የሰውነት ልክ መጠን እንዳለው ነው በግሌ የምረዳው። እዚያ ድሮ ባሌ እና በቅርቡ ላሊበላ ያሁትን እሴትን የያዘውን ማንነት ነው ሰውነት የምለው ።

ያኔ ግን በጋሽ አባተ መኩሪያ ቴያትር ላይ የተጫወተኩት ‹አገር ማለት ሰው ነው› የሚለው ገጸባህርይ ላይ ሥሜታዊ ነበርኩ። እዚህ ላይ ጨለማን የሚያበራ ታላቅ ወንዝ፣ ንስር ማንነት ወዘተ እያልኩ ስተውን ሌላ ዓለም ውስጥ ነበርኩ። በእውነትም ቴአትሩ በራሱ የሚገልፃቸው ነገሮች ሰውነትን የሚያጎሉ ነበሩ። በዚያን ጊዜ እውነትም አገር ማለት ሰው ነው የሚለው ወደልክነት የሚጠጋ ነበር ማለት እችላለሁ።

አሁን ደግሞ ጎጠኝነት፣ ጎሰኝነት፣ አውሬነት፣ ቂም በቀልን እያየን ስለሆነ አገር ማለት ሰው ነው ለማለት ያስቸግራል። ግን እንደዚህ አይነት ስሜት ሲሰማኝ ትኬቴን ቆርጬ ወደ ላሊበላ አካባቢ መሄድ ይኖርብኛል። በዘር፣ በጎሳ ያልተገደበ እያንዳንዱ ሰው ውስጥ ያለ መልካምነት፣ ሰውነት አለ ማለት ነው። ይህንን እኔም ውስጥ እንዳለ ይሰማኛል።

በ‹የኛ› ቡድን ውስጥ የነበረሽን ቆይታ መለስ ብለሽ ብታስታውሽን?
በቴአትሩ ላይ አገር ማለት ሰው ነውን ቴአትር ከሠራሁ በኋላ ለየኛ ኦዲሽን ተመረጥኩ። የኛ ተከታታይ የሬዲዮ ድራማ ነው ተብሎ ነበር የተነገረን። የኛን ረጅም ጊዜ አብረን ስንሠራ፣ ሳንጋጭ እና በቀላሉ እንድንሠራ ካደረገን አንዱ ተከፍሎን ስለነበር ነው። አብዛኛውን ጊዜ ሰው አብሮ ሲሠራ የሚያጋጨው የጥቅም ጉዳይ እንደመሆኑ፣ እንደዚህ አይነት ነገር እኛ ላይ አልተፈጠረም ነበር።

‹የኛ› ማለት ለኔ ነገሮችን የማይበትን መንገድ ያሰፋልኝ አሪፍ የሬዲዮ ድራማ ነው። በሙያ ደረጃ ብቁ ያደርገኝ፣ በቂ የሆነ ልምድ እንዲኖረኝ ጭምር አስተዋጽኦ ያደረገልኝ ነው። በድምፅም ልምምዶችን እንዳደርግ የረዳኝ ነው። ከተጠቀምኩበት ወደ ብዙ ነገር ልመነዝረው የምችልበት ትልቅ ፕሮጀክት ነበር። ሃላፊነትም ነበር። የሰጡን ሥራ አውቀን በትጋት ሙሉ ጊዜያችን ሰጥተን የሠራነው ሥራ ነበር።

በሚገርም ሁኔታ በደንብ ይዘው፣ ‹ኤጭ!› እያልን እንድንሠራ አላደረጉንም ነበር። በዛም ያንን ፕሮጀክት እወደዋለሁ።
ስክሪፕቱ (ጽሑፉ) በጋራ ነበር የሚጻፈው። እኛም ጋር እንደደረሰን ኹለት ቀን ነበር ልምምዱን የምናከናውነው። እርስ በእርስ ተናብበን ነበር ከነገፀባህሪያቶቹ ጋር ሆነን የሠራነው። ሦስተኛ ቀን ነበር ወደ ቀረፃ ስቱዲዮ የምንገባው።

እንደ አዲስ መሥርታችሁት የነበረው ‹እንደኛ› ቡድንስ የት ደረሰ? አሁን ላይ እንደ ቡድን አዲስ አልበም የማውጣት ሐሳብስ አላችሁ?
አሁን ላይ አልበም አይኖርም። ነገር ግን ከረጅም ዓመት በኋላ ሊኖር ይችላል። ነገር ግን አልፎ አልፎ ነጠላ ዜማ እየለቀቅን ነው።
እኛ እንደ ጓደኝነት እየተገናኘን ስለሥራም፣ ስለሕይወትም እናወራለን። ደግሞ ወደፊት ጠንክሮ አልበም ሊሠራ የሚችል ስብስብ ነው። እንደ ቡድን ግን እንደ አባይ ዘመን ልጆች ያሉ ወዲያው ተቀባይነት ያገኘ ዜማ ነው። ግን በጋራ ለምሥራት እኮ ጉዳይ ይመርጣል፣ ትላልቅ አገራዊ ይዘት ያላቸው፣ ትልልቅ ማህበራዊ ርዕስ ሴቶችን ይፈልጋል።

እሱን ግን እኛም እየሠራን ነው። እንደዚህ ዓይነት ሥራዎች ደግሞ ለገንዘብ ተብለው የሚሠሩ አይደሉም። ለነፍስህ እንዲሁም ማህበራዊ ተፅእኖ ሊፈጥሩ የሚችሉ ርእሶች ሲኖሩ ግን እንሠራለን። አብረን ነን። እየተገኘን፣ እየተነጋግርን እየሠራን ነው። ምንም ክፍተት በመካከላችን የለም። ተበትነዋል፣ በመካከላቸው ክፍተት አለ የሚሉ ወሬዎች ይሰማሉ።

እኛ መካከል ምንም አይነት ክፍተት የለም። ተለያይተዋል፣ ተበታትነዋል የሚሉን እኛ ፈንዲሻ ነን እንዴ? ሐሳብ አይግባችሁ በልልኝ። የሰዎች ግምት ብቻ ነው።
አሁንም ወደኋላ መለስ እንበል፤ ስለ አባተ መኩሪያ አስታውሰሽ የምትይን ነገር ካላ?
ጋሼ አባተ በራሱ አንድ ተቋም ነው። ከእርሱ ጋር ቴአትር መሥራት ለእኔ ‹ሲቪዬ› ማለት ነው። እኔ እዛ ቴአትር (አገር ማለት ሰው ነው) ላይ ለትወና የተመረጥኩት በመጨረሻው ሰዓት ላይ ነው። ሌሎች ልጆች ነበሩ ይሠሩ የነበሩት። እኔ ኮረሱን ወይም ኅብረ ዝማሬውን ነበር እየሠራሁ የነበረው፤ ይሄንንም ለአንድ ወር ነበር የሠራሁት።

ነብዩ ባዬ (ረ/ፕሮፌሰር) ሊገመግም መጥቶ ነበር። ከዚያ በኋላ ‹አንቺ መተወን አትችይም እንዴ?› ብሎ ጠየቀኝ። እኔም ‹ኧረ እችላለሁ፣ ጋሼ አባተ እነሱ እንዲሠሩ ስለፈለገ ነው› አልኩት። ከዚያም ‹ነይ እስኪ ሞክሪ› አለኝና ገባሁ። ነብዩ ስላስተማረኝ ነው። ጋሼ አባተ ግን ተጋባዥ መምህር ሆኖ ይመጣ ነበር። እንደማዜም እንጂ እንደምተውን አያውቅም ነበር።

ጋሼ እያንዳንዱ ቀን ላይ ስትሄድ ሙከራ ነበር የሚሠራው፣ ትላንት የሠራውን ዳይሬክቲንግ ዛሬ አይሠራውም። እየተማርክ ነው የምትሠራው።
በውቅቱም ኢትዮጵያን ወክለው የሚሠሩትን ሦስት ገፀ-ባህሪትን ቆሜ አይ ነበር። አድርጉ የሚላቸውን በደንብ አይ ነበር። ቃለ ተውኔቱንም በደንብ አውቀው ነበር። ሥሪው ስባል አልከበደኝም። ጭራሽ ዳይሬክት እንዲያደርግም እድል አልሰጠሁትም ነበር። ስለዚህ ወጥቼ ሠራሁ።

‹ነፍሴ! ይመችሽ በቃ፤ ችለሽዋል።› አለኝ። ካዛም ገፀ-ባህሪውን ወክዬ ለመሥራት ገባሁ ማለት ነው። እሱንም ቴአትሩ ለመውጣት አንድ ሳምንት ሲቀረው አካባቢ ነበር ተቀይሬ የገባሁት።

እንደዛም ሆኖ የሚቀያይራቸው ነገሮች ነበሩ። መድረክ ላይ ስትወጣ ብቻ ነው ዝም የሚልህ፣ እሱም አማራጭ ስለሌለው ነው እንጂ ዝም አይልህም። ሁሌም ይቀያይራል።

ጋሼ አባተ አንድ ቴአትር ሲያዘጋጅ አጠገቡ ከተገኘ ረዳት አዘጋጅ ሆነህ ሁላ ተቀርፀህ የመውጣት እድል አለህ። ከዚያ ጎበዝ ከሆንክ ደግሞ ዋና አዘጋጅ ሆነህ ትወጣለህ ማለት ነው። ለዚህ ነው ከጋሼ ጋር መሥራት ማለት ትምህርት ቤት እንደመግባት ነው ያልኩት።

በተጨማሪም ጋሼ ሁለገብ ነበር። ሁሉን ነገር በተለየ አቅጣጫ እንድታይ፣ ምን ከምን በኋላ መምጣት እንዳለበት እያንዳንዷን ዝርዝር አካሄድ በጥንቃቄ እንድታይ ያደርግሃል።

እኔ ‹አገር ማለት ሰው ነው›ን በዜማ እቀልፀው ነበር። ‹ነፍሴ…› እያለ እያዜመ ይነግረኝ ነበር። እርግጥ አድርጌ መሥራቴ ታዲያ ሰው ልብ ውስጥ እንዲቀር ያደረገው ይመስለኛል።

የቀን ውሎሽ ምን እንደሚመስል ንገሪን?
የየቀን ውሎዬ እንደማንኛውም ሰው ተነስቼ እታጠባለሁ፣ በመቀጠል ልጄን አጥባለው፣ የተወሰነ ሰዓት ልጄን ካዝናናሁ በኋላ ስልኬን ከፍቼ ኢንትርኔት እመለከታለሁ። ምግብ አበስላለሁ፣ ልጄን ከመገብኩ በኋላ እንዲተኛ አድርጌ ከዛ ወደ ስቱዲዮ አቀናለሁ። አብዛኛውን ጊዜ የማሳልፈው አንዲህ ባለ ሁኔታ ነው።

እናትነትና የጥበብ ባለሞያ መሆን ምን መልክ አለው?
ደስ ይላል፣ እናትነት። እናት ሆኖ ለማያውቅ ሰው መግለፅ ይከብዳል። እናትነት የጥበብ ባለሙያ ስለሆንክ፣ ሐኪም ስለሆንክ ወይም ሌላ የሙያ መስክ ላይ ስለሆንክ የሚለያይ አይደለም። እናትነት እናትነት ነው፤ በቃ!
እኔ በስብዕናዬ ሕይወትን በጣም ቀለል አድርጌ የማይና የምኖር ሰው ነበርኩ። ሁሉንም ነገሮች ላይ ቀለል አድርጌ የምመለከት። እናት ከሆንኩ በኋላ ግን ፈሪ፣ ተጨናቂ፣ ቡቡ እንባዬ ቶሎ የሚመጣ ሌላ የሆነች ሴት ሆኛለሁ ማለት ይቻላል፣ ከእናትነት በኋላ።

እናትነት ማለት እግዚአብሔር አምኖህ በውስጥህ ነፍስን ዘርቶ አንተ ደግሞ ለዛ ሰው ለወለድከው መታመን መቻል እና ከእግዚአብሔር ጋር ያለህን ግንኙነት የሚያጠብቅ ትልቅ ስሜት ያለው ጉዳይ ነው። ፈጣሪ በምን ደርጃ እንደሚወደኝ ያስተዋልኩበት ትልቅ ጉዳይ ነው፤ እናትነት። የምኖርበትንም ትክክለኛ ምክንያት ያወቁበት ነው።

ድሮ ሞት የማትፈራ ከነበርክ አሁን ፈሪ ትሆናለህ። በሕይወት ሳላውቀው ባልፍ የምቆጭበት ትልቅ ጉዳይ ይሆን ነበር ብዬ አስባለሁ። ከሙያ አንፃር ብዙ ሰዎች እንደሚከብድ ያወራሉ። እውነት ነው፤ ጥበብ ላይ ስትሠራ ግን ትንሽ ሊከብድ ይችላል። ምክንያቱም አንተ በአካል ተገኝተህ መሥራት ያለብህ ሥራ ይኖራል።
በዚህ ጊዜ ልጅን ጥሎ መውጣት ያስቸግራል። ግን ኹለቱንም ማስኬድ ይቻላል። ምንም ቢሆን የማትወጣው ማድረግ የማትችለው ጉዳይ የለም። ለሁሉም ደግሞ ጊዜ አለው አይደል የሚባለው? ለልጄም ለጥበቡም ጊዜ አልኝ እያልኩህ ነው ማለት ነው።

ስለ አዱሱ ሙዚቃሽ ጥቂት በይን፣ እንዴት ነበር ሂደቱ፣ ይዘቱስ ምን ይመስላል?
የሙዚቃውን አልበም ማዘጋጀት ከጀመርኩ ቆይቻለሁ። ነፍሱን ይማረውና ገና ኤልያስ መልካ በሕይወት እያለ ነበር የጀመርነው። ከሱ ጋር የተወሰነ ሥራ ሠርተን ነበር። እናም የአልበም ታይፕ ወይም አይነታችንን እስክናገኝ ድረስ የተለያዩ ሙዚቃዎችን እየሞከርን ነበር።

በመጨመረሻም ከአምስት ሐሳቦች መካከል ወሰንን ማለት ነው። አልበም ሊሆን ይችላል ብለን ያሰብነውን ዘውግ አገኘነው። ከኤሊያስ ጋርም ኹለት ሦስት ሙዚቃዎችን ሠርተን ነው ሕይወቱ ያለፈው። ከዚያ በኋላ ቀሪ ሥራዎችን መሰብሰብ ጀመርኩ።

የአልበሙ ይዘት ወጥነት ያለው እንደ ሬጌ ያለ ወይም እንደ ቴክታቶኒክ ያለ አይደለም። አንድ ዓይነት ዘውግ ያለውም አይደለም። ሥራው የእኔን ስሜት ሊገልፅ የሚችል፣ የምፈልጋቸውን ስሜት የያዘ ነው። ባህላዊ ይዘት ያላቸው እንደላሊበላ ያሉ፣ ዘመናዊውንም የያዘ ነው።

ግን እውነት ለመናገር ያላመንኩበትን ሙዚቃ አላወጣም። እግዚዘብሔር ይመስገን አገር ሰላም ከሆነ እና ይሄ አሁን ያለው ኮሽታ ከተረጋጋ፣ መጪው ጊዜም አገራዊ ምርጫ በሰላም ከተጠናቀቀ ገና ብዙ እሠራለሁ። አገር ሰላም ሆኖ ሕዝብ ሙዚቃህን ካላጣጣመልህ፣ ሙዚቃ ማውጣት ኪሳራ ነው። ሰላም ከሆነ ግን ሌሎች ሙዚቃዎችንም አወጣለሁ። እስከዚያ ግን የሙዚቃ ክሊፖችን እየሠራሁ እለቃለሁ።

ቅጽ 2 ቁጥር 99 መስከረም 16 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com