የዲዛይን ችግር የሚያንገላታው የአማራ ብልፅግና ፓርቲ

Views: 336

ብልጽግና ፓርቲ ኢሕአዴግን መተካቱ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ወደተሻለ መስመር ይወስዳል የሚል ተስፋ ሰጥቶ እንደነበር በማውሳት የሚጀምሩት መስከረም አበራ፤ የቀደሙ ፓርቲዎች ሥማቸውን ብቻ ሳይሆን በተግባርም እንደሚቀየሩ ይጠበቅ ነበር ብለዋል። በአንጻሩ ይልቁንም የቀድሞው ብአዴን አሁን የአማራ ብልጽግና ፓርቲ የሚጠበቀውንም ሆነ ቃል የገባውን ለውጥ አላመጣም። ይህም ከመሠረቱና ከአመሠራረቱ የወረሰው ችግር ነው ሲሉ ሐሳባቸውን አካፍለዋል።

ኢሕአዴግ የሚባለው ሕወሃትን የሦስት ዋነኛ፣ የአምስት ምክትል ሎሌዎች ጌታ አድርጎ የኖረው ፓርቲ ፈርሶ ብልፅግና በሚባለው ፓርቲ ሲተካ የአገራችን ፖለቲካ የተሻለ መስመር ይይዛል ብለው ተስፋ ካደረጉት ወገን ነበርኩ። የተስፋዬ ምክንያት በርካታ ነው። አንደኛው የአገራችን ፖለቲካ በቀላሉ እርምት ሊያገኝ የሚችለው አስቀድሞ እንዳይሆን አድርጎ ያበላሸው ኢሕአዴግ ራሱ እንዳበላሸው አድርጎ ካስተካከለው ነው በሚል ነበር።

ኹለተኛው ምክንያቴ ሕዝባዊ ለውጡን ከውስጥ ሆነው ያገዙ የኢሕአዴግ ካድሬዎች ለውጥ የፈለጉት በአንድ ጌታ ስር ማደር ሰልችቷቸው፣ በራስ እምነት የመኖር ክብሩ ተገልጦላቸው መስሎኝ ነበር። ሦስተኛው ምክንያቴ ደግሞ ኢትዮጵያን ለማስቀጠል እንሠራለን ሲሉ የኢሕአዴግ ሰዎችንም ቢሆን እስከማመን የሚደርስ ተላላነት ስላለኝ ሳይሆን አይቀርም። የሆነ ሆኖ አገራችንን ከሕወሃት/ኢሕአዴግ መዳፍ መላቀቁ እንዲህ በቀላሉ የሚሆን ስላልሆነ ለውጥ ልናመጣ ነው ያሉ ሰዎችን ጊዜ ሰጥቶ ማየቱ ጥፋት አይደለም።

ብልፅግና የተባለው ፓርቲ ሲመሠረት የአገራችንን ሁለንተናዊ ችግር ይፈታል የሚል የጅል ተስፈኛ እንደማይኖር እሙን ነው። ተስፋው ቢያንስ እንደ ሕወሃት ሰማይ የደረሰ ጌታ እና እንደ አጋር/አባል ፓርቲዎቹ ትቢያ ላይ ተንበርክኮ ‹አቤት ወዴት› የማለትን ያህል የተራራቀ የአዛዥ ታዛዥ ግንኙነት በብልፅግና ፓርቲ ውስጥ አይደገምም የሚል ነበር። ሰማይ ከምድር እንደሚርቅ ተራርቆ የኖረውን የጌታ እና የሎሌ የፖለቲካ መስተጋብር ለማቀራረብ ይረዳል ብዬ በግል አስበው የነበረው ከውጭ ሆነው ሲያዩት በኦሕዴድ እና በብአዴን መኳንንት ዘንድ የመጣ የመሰለው የእሳቤ ለውጥ ነበር።

ይህ ለውጥ ከኦሕዴድ አኳያ የበለጠ ታግያለሁ ብሎ ጌትነት መሻት መጨረሻው እንደ ሕወሃት መሆን እንደሆነ መረዳት አያዳግተውም የሚል ትልቅ ተስፋም ነበር። ከብአዴን አንፃር የድሮው ብአዴን ሆኖ በአማራ ሕዝብ ትከሻ ላይ ለአንድ ተጨማሪ ወር እንኳን መኖር የማይታሰብ እንደሆነ እንደው በጥቂቱም ቢሆን መገንዘብ ተችሏል በሚልም ነው። ሆኖም የኦሮሚያ ብልፅግና ሆኛለሁ ያለው ኦሕዴድም ሆነ የአማራ ብልፅግና ተብዬ የአማራን ሕዝብ እመራለሁ የሚለው ብአዴን ካድሬዎች ያሰብነውን ለውጥ በሚያመጣ መንገድ የተለወጡ አልሆኑም።

አለመለወጡ የሚብሰው ግን በብአዴን ላይ ነው። ኦህዴድ ተቀይሮ የሕወሃትን ቦታ ልያዝ እያለ እንደሆነ ሽመልስ አብዲሳ (አይሰማም መስሏቸው) ካወሩት ብቻ ሳይሆን እነ ታከለ ኡማ ከሚተገብሩት ሁሉ መረዳት ይቻላል። በእርግጥ መለወጥ ሁሉ መልካም አይደለም፤ ወደ ሕወሃትነት መለወጥ ደግሞ ምን ማለት እንደሆነ ግልፅ ነው።

መለወጥ በፊቱ ዝር የሚል የማይመስለው የአማራ ብልፀግና ፓርቲ ነው። ይህ ፓርቲ ከተለወጠም የሚለወጠው ወደ ብአዴንነት ወይም ኢሕዴንነት ነው። የአማራ ብልፅግና ፓርቲ አለመለወጥ፣ ከተለወጠም ወደ በጎ አለመለወጥ በርካታ ምክንያቶች ቢኖሩትም ዋነኛው ምክንያት ግን ሲፈጠር ጀምሮ የተጠናወተው የዲዛይን ችግር ነው። ይህ የብአዴን ዋነኛ ደዌ የሚመነጨው ብአዴንን ዲዛይን ካደረገው ሕወሃት ሆኖ ተሠሪውን ብአዴንን ለማይድን በሽታ አሳልፎ ሰጥቶት ቀርቷል።

ሕወሃት ብአዴንን ሲሠራው የተሠራበትን ዓላማ እያመከነ እንዲኖር ነው። ይህም ማለት ብአዴን የተፈጠረው ለሰፊው የአማራ ሕዝብ መብት መከበር ነው የሚል የይስሙላ ፕሮፖጋንዳ ነገር ነበረ። ሆኖም በእውነታው ዓለም ብአዴን የቆመው ይህን አላማ ለማምከን፣ አማራውን ያለ እውነተኛ መሪ ለማስቀረት ነው። ከዓላማ በተቃራኒ መቆም ማለት ይህ ነው። ይህን ደግሞ ከብአዴን በላይ የቻለበት ፓርቲ የለም።

ሕወሃት ብአዴንን ሲፈጥረው አማራ ሁሉ ጨቁኖኛል፣ አማራ ሁሉ ጠላቴ ነው የሚለውን እሳቤውን ከልቡ ሳይፍቀው ግን ለአፉ ጭቁኑ አማራ ምንም አላደረገኝም ጠላቴ የአማራ ገዥ መደብ ነው ማለት የጀመረ ሰሞን ነው። ሕወሃት የሆዱን በሆዱ አድርጎ ድንገት ጭቁን ነህ ላለው ሰፊው የአማራ ሕዝብ ወኪል ይሆን ዘንድም ኢሕዴንን ‹ብአዴን› ሲል ጠራው። ‹ከዛሬ ጀምሮ ብአዴን ትባላላችሁ› የተባሉት መኳንንትም ከማኒፌስቶ 68 ጀምሮ እስከ ሽግግር ቻርተር ድረስ የኢትዮጵያ ታሪክ መርገም ሁሉ ምክንያቱ አማራ ነው የሚለውን የጌታ ሕወሃትን የፖለቲካ ዘፍጥረት ያነበነቡ ጀመር።

ድርጅቱን እንዲመሩ የተሰየሙት መሪዎችም የሚታየውን የአማራ ሕዝብ ድህነት ይገነዘቡ ዘንድ የሰው ልጅ ልቦና ያልፈጠረባቸው፣ ከአማራ ሕዝብ ጋር የመንፈስ ቁርኝት የሌላቸው፣ ምናልባትም አማራ ወደሚባለው ክልል የሚወስደው መንገድ በየት በኩል ወዴት እንደሆነ ለማወቅ መሪ የሚያስፈልጋቸው የሕወሃት ግዙዎች ናቸው። የእነዚህ ሰዎች ራስ ደግሞ ኤርትራዊው በረከት ስምኦን ነበር። ከፅንሰቱ በዚህ መንገድ የተፈጠረበትን አላማ እያመከነ እንዲኖር ዲዛይን የተደረገው ብአዴን ስም ቢቀይር፣ መዋቅር አስተካከልኩ ቢል ከተሠራበት ግብሩ ፈቅ ነቅነቅ ሊል አልቻለም።

ብአዴን የተሠራበት የራስን ዓላማ አፈር የማልበስ፣ በገዛ ሕዝቡ ላይ ጦር ነቅንቆ ማቁሰል፣ ቢላዋ ስሎ በጀርባ የማረድ ግብር በራሱ ትልቅ ችግር ሆኖ ሳለ ሌላ ችግርን ወዷል። ይህ ችግር የሕወሃት እና የኦሕዴድ የጥንካሬ ምንጭ የሆነው የክርስትና አባት (God father) አልቦ ድርጅት መሆኑ ነው።
እንደ እኛ አገር ተቋማዊነት ባልበረታበት፣ ፖለቲካውም የቤተሰብ መልክ ባለው የዘውግ እሳቤ በሚደወርበት ኋላቀር የፖለቲካ አውድ የክርስትና አባት ፖለቲካ የአንድ ፓርቲ የጥንካሬ ምንጭ ነው። ሕወሃት ከጫካ ጀምሮ ስብሃት ነጋ፣ ስዩም መስፍን፣ አባይ ፀሐዬ የሚባሉ በርከት ያሉ ክርስትና አባቶች ያለው ድርጅት ነው። በመሆኑም የፓርቲው አባላት በጥቃቅን ነገሮች ላይ ልዩነት ቢኖራቸውም የትግራይን ሕዝብ ጥቅም በተመለከተ ግን በጋራ የሚያዩት ርዕይ አላቸው።

ከዚህ ርዕይ ፈቀቅ ሲሉ እነዚህ የክርስትና አባቶች ከመስመር የወጣውን በውግዝም ሆነ በእርግማን ወደ መስመር አንዲገባ ያደርጋሉ። በተመሳሳይ ኦሕዴድም አባዱላ ገመዳ የሚባል ክርስትና አባት አለው። ኦሕዴድ እንደ ሰው አባዱላ፣ እንደ ድርጅት ደግሞ ኦነግ የሚባል የክርስትና አባት ስላለው የተቋቋመበትን የኦሮሞ ብሔርተኝትን ዋነኛ ዓላማዎች ለሰኮንድ ችላ ሳይል ያለ ይሉኝታ ያስፈፅማል። ኦሕዴድን በሕወሃት ወንበር ለመቀመጥ ያበቃውም መንገዱን የሚመራው ክርስትና አባት ያለው ፓርቲ መሆኑ ነው።

የኦሕዴድ የፓርቲ ክርስትና አባት ኦነግ ለኦሮሞ ቆምኩ የሚሉ አካላት ሁሉ ሊያሟሉ የሚገባቸውን ስልታዊ ግቦች ቁልጭ አድርጎ አስቀምጦለታል። ይህን ስልት /ስትራቴጅ/ እንደ ኦሕዴድ ለማስፈፀም ደግሞ አባ ዱላ የተባለው ክርስትና አባት ቅድመ-ሁኔታዎችን ያስተካክላል። ከነዚህ ቅድመ-ሁኔታዎች አንዱ ሕወሃት በመንበሩ ላይ እያለ የኦሮሞ ብሔርተኝነት ፖለቲካ ስጋት እንዳይሆንበት ሲል በፓርቲው ላይ የሚያሳርፈውን ጡጫ በመከላከል ይልቅም ከለላ በመስጠት ወጣት የኦሮሞ ብሔርተኞች ፓርቲውን እንዲቀላቀሉ ያላሰለሰ ሚና ተጫውቷል።

ይህ ሚናውም እንደ ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፣ ለማ መገርሳ፣ አዲሱ አረጋ፣ ሽመልስ አብዲሳ፣ አዳነች አቤቤ የመሳሰሉ የአገርን በትረ ሥልጣን የሚመኙ የኦሮሞ ብሔርተኞች ብቅ እንዲሉ ረድቷል። እነዚህ አዲስ የኦሮሞ ብሔርተኞች ራሳቸው አንደተናገሩት ‹አደናግረው›፣ ‹አሳምነው› እና ‹ቆምረው› የፌዴራል ሥልጣን ላይ ወጥተው በኦነግ ልብ ታስቦ በሥልጣን እጥረት ምክንያት ገቢራዊ ያልሆኑ የኦሮሞ ብሔርተኝት ዋነኛ ሕልሞችን ወደ እውነት ለመቀየር እየሞከሩ ነው።

በአንፃሩ ብአዴን ለራሱ ከእናቱ ሆድ ሲወጣ ይዞት በወጣው የዲዛይን ችግር ወለድ ደዌ በመሰቃየት ላይ ሲገኝ እመራዋለሁ የሚለውን ሕዝብ ደግሞ ለስለት እና ለድንጋይ ሞት አሳልፎ ሰጥቶ ፈዞ ቀርቷል። ብአዴን የተፀነሰው በእንጀራ እናት ማሕፀን ውስጥ በመሆኑ ምንም አይነት የፖለቲካ ዓላማ እየተመገበ ያደገ ፓርቲ አይደለም። ሰው በእናቱ ተወልዶ በእንጀራ እናት ቢያድግ የተለመደ ነገር ነው። ከጅምሩ ለልጇ እድገትን ሳይሆን መቀጨጭን በምትመግብ ‹እንጀራ እናት› ሆድ ውስጥ ተፀንሶ መወለድ ግን በምድር ላይ ታይቶ የማይታወቅ ነገር ነው።

የብአዴን የእንጀራ እናቶቹ በረከት ስምዖን፣ አዲሱ ለገሰ አና ተፈራ ዋልዋ የሚባሉ በየደረሱበት አማራውን የሚያንቋሽሹ እንጅ ለአማራው ሕዝብ ጥቅም የሚሆን አንዳች ስትራቴጅያዊ ዓላማ የማያስቀምጡ ሰዎች ናቸው። እነዚህ ሰዎች ከኢሕዴን ወደ ብአዴን የተቀየረው ጉደኛ ፓርቲ መሥራቾች ቢሆኑም የአማራን ሕዝብ በእውነት የሚመራበትን ስትራቴጅ ለቀጣዩ ትውልድ የሚያቀብሉ፣ መንገድ የሚያቀኑ አባዱላ ለኦሕዴድ የሆነውን አይነት የክርስትና አባቶች ሊሆኑ አይችሉም። የዚህ ጉዳይ መዘዝ የአማራ ሕዝብን ለሠላሳ ዓመት በማይታጠፍ ሰይፍ እንዲታረድ ምክንያት ሆኗል።

እንጀራ አባት እንጂ ክርስትና አባት የሌለው ብአዴን በዚሁ አስገራሚ አፈጣጠሩ ሳቢያ በድርጅቱ ውስጥ ምንም አይነት ወደ በጎ የመለወጥ ክስተት እንዳይኖር እግድ ሆኖበታል። መቀየር ካለም ወደ ባሰ አሽከርነት፣ ወደ ተባባሰ ዓላማ የለሽነትና ወደሚያስገርም ለሕዝብ መከራ ስሜት አልቦነት ነው። ይህ ብአዴን ከተፈጠረበት እስከ ዛሬ ድረስ እንደ ጥላ የሚከተለው እውነተኛ መልኩ ነው። ይህን አስቀያሚ መልኩን ለራሱ ይዞ ቢቀመጥ ብዙም የሚያስጨንቅ ነገር ባልነበረው፤ ችግር የሆነው ብአዴን የሚናቅበትን መናቅ ወደ አማራ ሕዝብ ማስተላለፉ ነው።

ከሕወሃት/ኢሕአዴግ እስከ ኦሕዴድ/ብልፅግና አገሪቱን የሚመሩ ዘውገኛ መሪዎች ብአዴንን በሚያዩበት የንቀት ዐይን የአማራን ሕዝብ ያያሉ። ሕወሃት በብአዴን የተነሳ የአማራን ሕዝብ የመናቁ ነገር ተወርቶ አያልቅም። ከሁሉ የሚብሰው ግን የወልቃይት ጠገዴን መሬት ወስዶ ሕዝቡን በገዛ መሬቱ ላይ ግዞተኛ ማድረጉ ነው።
በጦር ሜዳ ጀብዶ ሥልጣን የያዘው ሕወሃት ቀርቶ ራሱ ብአዴን እሽኮኮ ብሎ ሥልጣን ላይ ያስቀመጠው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ‹ለአንድ ክልል ሕዝብ ብለን ሕገ-መንግሥት አንቀይርም› ሲሉ ንቀታቸውን ጠቆም አድርገዋል። ሲቀጥልም የወልቃይት ጠገዴ ጥያቄ የመልካም አስተዳደር እና የልማት እንጂ የማንነት አይደለም ሲሉ ተሳልቀዋል። ይህ ሁሉ የሆነው የብአዴን ለንጉሥ ማጎንበስ የአማራ ሕዝብ ማጎንበስ ተደርጎ በመቆጠሩ ነው።

ብአዴን ወደ በጎ እንዳይቀየር ዋነኛ ደንቃራ የሆነበት የቆየ ምክንያት በረከት ስምኦን የሚባል የሕወሃት ዋርድያ በቁራኛነት ስለታሰረበት ነው። ይህ ሰው ከጅምር እስከፍፃሜ ፓርቲውን ሲያሾር የኖረ ነው። በረከት ስምኦንን የብአዴን ዋርድያ አድርጎ ያሰረውን የሕወሃትን ገመድ መበጠስ ዘጠኝ ሱሪ መታጠቅን ይፈልግ ይሆናል እንጂ የማይቻል ነገር ግን አልነበረም። ብአዴን ደግሞ እንኳን ዘጠኙ አንዱም ሱሪ እየሰፋ የሚወርድበት ካድሬ የተጠራቀመበት እንደሆነ ማሳያው ዛሬም ድረስ ‹ሕዝቤን ያስገደልክልኝ ሆይ! ካባ ይገባሃል› ባዩ ሰውዬ ከሰው ተመርጦ ክልሉን እየመራ መሆኑ ነው።

የሆነው ሆኖ በኦሕዴድ ውስጥ አባዱላን የመሰለ ክርስትና አባት ያመጣው አጋጣሚ ለብአዴንም ሊሆን የሚችልበት የመጀመሪያው አጋጣሚ አማራ የሆነ ሰው ክልሉን እንዲመራ የሆነበት አያሌው ጎበዜ የተባሉ ሰው ወደ ሥልጣን የመጡበት ዘመን ነበር። ሆኖም ሰውየው ‹ራስ ደኅና› ባይ ነገር ሆነው ኖሮ በኢሕአዴግ ቤት የአማራ ክልልን ለመምራት ቅድመ ሁኔታ ተደርጎ የተቀመጠውን የአማራን ሕዝብ ስቃይ እንደ አስደሳች ዶክመንተሪ ፊልም ቁጭ ብሎ ከማየት ያለፈ አንዳችም የሚታወሱበትን ሥራ ሳይሠሩ ወደሚሄዱበት ሄደዋል።

ቀጥለው የመጡት አመራሮችም ቢሆኑ የዚህን ሰው ፈለግ ከመከተል ያለፈ የሠሩት የለም። በጋራ ተናበው ትርጉም ያለው ሥራ መሥራት ቀርቶ በጋራ የሚያልሙት ሕዝባዊ ዓላማ የለም። ሁሉም የሚያልመው የራሱ ኑሮ የደቀነበትን ፈተና የሚያቀልበትን የራሱን ዓላማ ነው። አንዱ V8 ላይ ለመውጣት ሲያልም ሌላው ከV8 ላለመውረድ ያልማል፣ ሌላው ከሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲም ቢሆን ዶክተር የሚባልበትን ጥበብ ሲያሰላ ሌላው እንዴት በንጉሥ ፊት አጎንብሶ የፌዴራል ባለሥልጣን እንደሚሆን ይተልማል።

ሌላው እንዴት የፌስቡክ አክቲቪስት ቀጥሮ የራሱን ፖለቲካዊ ኪሎ እንደሚጨምር ያልማል። በፓርቲው ውስጥ ያለው የአመራር ፍዘት ከዚህ ዝብርቅርቅ ዓላማ የሚነሳ ነው። አንድ ዓላማ የሌለው ሰው ፈር ያለው አመራር ሊሰጥ አይችልም፤ በራሱ ግላዊ ዓላማ ፍቅር የናወዘ ሰው ለሕዝብ ሊቆም ከቶም አይቻለውም።
እንዲህ ባለ ልሙጥ የታዛዥነት ምግባር ዘመናቸውን ያሳለፉት ብአዴኖች ሕወሃትን በመጣላቸው ከቆየ ማንነታቸው ጋር የማይጣጣም ሥራ ሠሩ በሚል አማራጭ የሌለው ሕዝብ በእነሱው ላይ ተስፋ አደረገ። በዚህ ሰዓት የክልሉ መሪ የነበሩት ገዱ አንዳርጋቸው የአማራ ክልልን የሚመራው ፓርቲያቸው ከሚታወቅበት የአቤት ወዴት ባይነት አባዜ የራሱ ነፍስ ያለው ሰው እንደሚያደርገው ዓይነት ፖለቲካ እንዲያራምድ ያደርጋሉ የሚል ትልቅ ተስፋ ተጥሎ ነበር።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በባህርዳር ከተማ ተገኝነተው ‹እስከ አሁን አንሰማችሁም ነበር። አሁን ግን ፈጥነን እንሰማችኋለን።› ሲሉ በመናገራቸው ተስፋው የበለጠ አድጎም ነበር። ሆኖም ችግሩ ከፅንሰት ውልደት የመጣ የዲዛይን ችግር ስለሆነ ፈቅ ነቅነቅ ማለት አልተቻለም። ጭራሽ የክልሉን ባለሥልጣናት ሽጉጥ ያማዘዘ ልዩነት ተፈጥሮ ቁጭ አለ።

የሽጉጥ መማዘዙ ምክንያት ምን እንደሆነ አጥግቦ የሚነግር አንድስ አንኳን ከእውነት የወገነ ሰው ጠፍቷል። እስከ ዛሬ ከተነገረው ሁሉ በበኩሌ ፍንጭ የሰጠኝ የፖለቲካ አመራሩ እና የፀጥታ ክፍሉ ተስማምቶ መሥራት አለመቻል እንደሆነ ጄነራል ተፈራ ማሞ የፃፉት ጽሑፍ ነው። ይህ ጽሑፍ የሰጠው ፍንጭ የፖለቲካ አመራሩ የተባለው አካል አሁን አሁን የሚሠራው ከበፊቱ አንኳን የባሰ የአጎብዳጅነት ሥራ ጋር ሲነፃፀር ከፀጥታ አካሉ ጋር ያልተስማማበትን ምክንያት ለመገመት አያዳግትም። የሆነው ሆኖ አሁን በፖለቲካ አመራሩ ላይ የሚሰነዘረው ፍላፃ የሚነሳው ከፀጥታ ኃይሉ እንዳይሆን በደንብ ታስቦበት የተሠራ ይመስላል።

ሆኖም ከዚህ በኋላ የሚነሳው ተግዳሮት ዶክመንተሪ ፊልም ሠርተው የማያድበሰብሱት፣ እገሌ ብለው ከሚረግሙት አንድ አካል ሳይሆን ሉዓላዊ ከሆነው ሕዝብ የሚነሳ የፊቱን የጥቂቶች የጠመንጃ ሞት ቅንጦት የሚያደርግ፣ ለወሬ ነጋሪ የማያስተርፍ የዲን እሳትም ሊሆን ይችላል። ሲወለድ የታመመ ሲሞት ብቻ ይፈወሳል!

ቅጽ 2 ቁጥር 99 መስከረም 16 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com