‹የመጀመሪያዋ›ን ማስቀጠል

Views: 142

በአገራችን እንዲሁም በዓለም ዐቀፍ ደረጃ ‹ለመጀመሪያ ጊዜ› ተብለው የሚበሰሩ ዜናዎች ከዓመት ዓመት፣ ከዘመን ዘመን እየቀነሱ ሄደዋል። በተለይም ሴቶችን በሚመለከት አሁንም የሚቀሩና ለዓለም ‹ለመጀመሪያ ጊዜ› በሚል መግቢያ ዜና ሆነው የሚቀርቡ ኹነቶች እንደተጠበቁ ነው። ለምሳሌ ዴሞክራሲያዊቷ አሜሪካ እስከ አሁን ድረስ ሴት ፕሬዝደንት ሰይማ አታውቅም።

ከአሜሪካ ጋር መፎካከር ሳይሆን ነገሩን እንደማሳያ ማንሳታችን ነው። በአገራችንም በተመሳሳይ ገና ያልተነኩ፣ ‹የመጀመሪያዋ› የሚባልላቸው ዘርፎች ይቀራሉ። በቅርቡ የመቀሌ ዩኒቨርስቲ በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ ሴት ፕሬዝዳንት ሰይሟል። በተመሳሳይ ሊጠቀሱ የሚችሉ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በጣት ቁጥር እንኳ የሚሞሉ እንዳይደሉ ግን ይታወቃል።

ጉዳዩ እሱም ብቻ አይደለም። ግን ይህ ‹የመጀመሪያዋ› ለምን ቀጥሎ አይታይም ነው ጥያቄው። በአገራችን ጥቂት የማይባሉ ሴቶች በተለያዩ በሴቶች አይደፈሩም በተባሉ መስኮች ተሳትፈው የግል ሕልማቸውን አሳክተዋል፤ ለብዙ ሴቶች ግብ እና ሕልምም ተጨማሪ አውድን ፈጥረዋል። ግን እነማን ተከተሏቸው?
ፕሬዝደንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ለአገራችን የመጀመሪያዋ ፕሬዝደንት ናቸው። የእርሳቸው ኃላፊነትና የሥልጣን ዘመን ከተገባደደ በኋላ ሴት ፕሬዝዳንት ለማግኘት ስንት ዓመት እንጠብቃለን? ነው መቻልን አሳይቶና ‹እንችላለን› ብሎ ዞር ነው?

ለማሳያነት በቅርብ የተገኘውን አነሳን እንጂ በተመሳሳይ በሌላውም ዘርፍ እንደዛው ነው። በእርግጥ አንድ እውነት አለ፤ ‹የመጀመሪያዋ› በሚል ብርቱ ሴቶች በየዘርፉ ምዕራፍ በመክፈቻቸው ለብዙ ሴቶች አረአያ እና ምሳሌ ይሆናሉ፤ ናቸውም። በአንድ ጀንበር ባይሆንም ተከታይ ሴቶች እንደሚገኙ ጥርጥር አይኖርም። ለዛ ግን ከወዲሁ መሠራት የሚገባቸው ሥራዎች አሉ።

አንደኛው ምብቃት የሚባለው ነው። ቅድሚያ ለሴቶች በሚል መስፈርት ሳይሆን እኩል የተወዳደሩ ሴቶች ወደፊት እንዲመጡ ማድረግ ላይ እነዛው ምዕራፍ ከፋች ሴቶች ትልቅ ሥራ ይጠበቅባቸዋል። ጉዟቸውን ማሳየት፣ መምራት፣ ከሕይወት ገጠመኞቻቸውና ልምዳቸው ማካፈል ይገባቸዋል። የመጀመሪያም የመጨረሻም ሆኖ መቅረት ስለማይቻል፣ ቢያንስ የመጀመሪያ ሆነው እንዲሁም በእግራቸው የሚተካውን አሰናድተውም ቢሆን ይመረጣል።

እንዳይጠፋብና! ለምሳሌ በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ አሁን ላይ ፕሬዝዳንት ሆነው ከተሰየሙት ፕሮፌሰር ፈትየን አባይ በፊትም በግል ያሉትን ጨምሮ በመንግሥት ከፍተኛ የትምህርት ተቋም ፕሬዝዳንትና ምክትል ሆነው ያገለገሉ ሴቶች አሉ። ግን እስክንረሳቸው ድረስ ወይም እንደነበሩ እስከማናውቅ ድረስ የጊዜ ርቀት አለው ማለት ነው።
እዚህ ላይ አካሄዱ ተፈጥሮአዊና መደበኛ ከሆነ፣ ግድ የለም እታረማለሁ። ግን እንደሚቻል የሚያውቁና መስመር ላይ የሚገኙ ሴቶች ጥቂት አይመስሉኝም። ጉዳዩ ሥልጣንን ማግኘትና የበላይ አድራጊ ፈጣሪ መሆን አይደለም። ጉዳዩ የሰው ልጅ እንደሚችል ማሳየት ነው፤ ሴትም ሆነ ወንድ። ጉዳዩ ዕይታን መቀየርና ለዓለም አዲስ መልክ መስጠት ነው። ደግሞም አንዳንዴ ወረድ ለሚለውም መልስ ነው፤ ሴቶች አይችሉም ብሎ ለሚያምን።

እናም እንዲህ ነው፤ የመጀመሪያይቱ ሆይ! ተከታዮችሽን በተግባር መርተሽ አሳይተሻል። አሁን ደግሞ ሐሳብን በማካፈልና በቃል አረአያነትሽን አሳይ። የሚከተሉሽን ተመልከቻቸው። ይህ ጉዳይ አጀንዳ የማይሆንበት ጊዜ ይመጣል። ያኔ ‹የመጀመሪያዋ› በሚል ርዕስ በስምሽ የተከፈተው ምዕራፍ፤ ‹ተጀመረ፤ አለቀ› የሚባል ሳይሆን፣ ባለ ብዙ ዘርፍ፣ ባለብዙ መልክ ይሆናል።
ሊድያ ተስፋዬ

ቅጽ 2 ቁጥር 99 መስከረም 16 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com