የእለት ዜና

የመኪና አስመጪዎች  ኢትዮጲያ ውስጥ መገጣጠሚያ ለማስጀመር ጥያቄ አቀረቡ

የመኪና አስመጪዎች ማኅበር  ራሱን የቻለ  የመኪና   መገጣጠሚያ ተቋም አንድ ላይ በመሆን ሊከፍቱ እንደሆነ እና ይህንንም ሀሳባቸውን   ለትራንስፖርት ሚኒስቴር  ጥያቄ ማቅረባቸውን ለአዲስ ማለዳ ተናገሩ፡፡

ከሶስት ሺህ በላይ  የመኪና አስመጪዎች  አለን  የሚሉት የመኪና አስመጪዎች ማኅበር ዋና ስራ አስኪያጅ መሃመድ አህመዴ  የማኅበሩ አባላት አንድ ላይ  በመሆን መኪና በአገር ውስጥ መገጣጠም እንዲችል  ብለን በተደጋጋሚ ጥያቄ ለሚኒስቴር መስርያ ቤቱ አቅርበናል ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ጨምረው ተናግረዋል፡፡

መሃመድ እንዳሉት ከሆነ የማህበሩ አባላት ከሆኑ አስመጪዎች ይሄ ሃሳብ የመጣውም  መንግስት ባወጣው ህግ መሰረት  አዳዲስ መኪኖች እንጂ ጥቅም ላይ የዋሉ መኪኖች ወደ ኢትዮጲያ መግባት የለበትም የሚለውን ሕግ መሰረት አድርጎ እንደሆነም ጠቁመዋል፡፡

በዚህም  ጥቅም ላይ የዋሉ መኪኖችን ማስገባት ስለማይቻል የታሰበው ነገር ወደ መኪና ስራ ብንገባና መኪና መገጣጠሚያ ኩባንያ ብንከፍት ብለን እንቅስቃሴ ጀምረናል ብለዋል ፡፡  በመስከረም 19 /2013  የትራንስፖርት ሚኒስቴር  ሰብስበውን ነበር የሚሉት መሃመድ የመኪና መገጣጠሚያ ለማቋቋም ፍላጎቱ እንዳለን እና  ነገር ግን የትራንስፖርት ሚኒስቴርም መንግስትም ጣልቃ ቢገባ ቁጥራችን ከ 3 ሺህ በላይ ነው ሲሉም ተናግረዋል፡፡  ከፍተኛም መነሻ ስለሚኖረን ወደ መገጣጠሚያ ፋብሪካ እንድንለወጥ  በአክሲዮን መደራጀት ይቻላል ብለን  በእለቱ በሸራተን በነበረው ስብሰባ ላይ ጥያቄ አቅርበናል ብለዋል፡፡  ይሄን ጥያቄ ስናቀርብ የመጀመርያችን አይደለም የሚሉት የመሃበሩ ሃላፊ ለኢንቨስትምንት ኮሚሽን ከሶስት ወር በፊት  ቅድሚያ አቅርበን ነበር ‹‹ ነገር ግን ገና ሂደት ላይ ያለ ነገር በመሆኑ ጥናት እና ምን ያህል የገንዘብ አቅም እንደሚያስፈልገን ግን አልታወቀም›› ብለዋል፡፡

አሁን ላይ መሰረተ ሃሳብ ላይ ነን ያሉት የመሃበሩ ሃላፊ ፍቃዱ ሲሰጠን ደግሞ ወደ ጥናት እንገባለን ብለዋል፡፡  ነገር ግን ከመንግስት ከፍተኛ እርዳታ ያስፈልገናል የሚሉት ዋና ስራ አስኪያጁ  ቁጥራቸው በዛ ያለ መሆኑን ጠቅሰው   በማህበሩ ያሉት አስመጪዎች ‹‹የገንዘብ ችግር ላይኖርብን ይችላል፡፡ ከ ሶስት ሺህ በላይ የሆነው አስመጪዎች እያንዳንዳችን አንድ ሚሊዮን ብናወጣ እንኳ ከሶስት ቢሊዮን ብር በላይ መሰብሰብ ይችላል››  ይሄ አነድ ትልቅ መገጣጠሚያ መክፈት ያስችላል ሲሉም ጨምረው ተናግረዋል፡፡

ይህ መሆኑ ከፍተኛ ጥቅም እንዳለው እና አብዛኛው አስመጪ የግሉ የሆነ መሸጫ ቦታ አለው የሚሉት ስራ አስኪያጁ አባል የሆኑት እራሳችን ከገጣጠምነው ላይ በመውሰድ መቸርቸር ይችላሉ ይሄም ይበልጥ አዋጭ ይሆናል  ብለዋል፡፡

በተያያዘም ትራንስፖርት ሚኒስቴር በበኩሉ  የቀረበው ጥያቄ ተገቢነት ያለው እና ታይቶ እንደሚወሰን በመድረኩ ተናግረዋል፡፡ በተያያዘም  በመድረኩ ላይ ከተነሱ ዋና ዋና ጥያቄዎች መካከል  የኤሌክትሮኒክስ  መኪና ጉዳይ ዋናው ሲሆን  መኪናው እንደሚያስፈልገው መጠን ‹‹ በነዳጅ ማደያዎች አካባቢ ቻርጅ ማድረጊያ መኖር አለበት ተብሏል፡፡

ከዛም ባለፈ በስፋት ከተነሱት ሃሳቦች  የአገር ውስጥ መገጣጠሚያዎች እንዲበዙ የማድረግ እና  ከዛም ባለፈ ወደ አገር ውስጥ( import)  የሚደረገውን መኪና ለመቀነስ  ታስቦ ስራዎች መሰራት እንዳለባቸው ተነስተዋል፡፡ በውይይቱ ላይ  የፌደራል ትራንስፖርት ባለ ስልጣን  ዋና ዳይሬክትር የሆኑት  አብዲሳ ያደታ እና  የትራስፖርት ሚኒስቴር ሚኒስትሯ ዳግማይት ሞገስ ጥያቄዎች እንደቀረበላቸው ተጠቁሟል ፡፡ ማህበሩ አያይዞም በአገር ውስጥ መኪናዎችን መገጣጠም ተሸከርካሪዎችን ወደ አገር ውስጥ ለማስገባት የሚወጣውን ከፍተኛ  የውጪ ምንዛሪን በማስቀረት ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ተናግረዋል።

 

 

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com