90 ዓመታት የአልበገር ባይነት ጉዞ

Views: 198

አገር በዜጎች ይገነባል። ዜጎቿ በየትኛውም አስተሳሰብ ደረጃ እና ንቃተ ሕሊና ቢሆኑ ለአገር ግንባታ እና ለአገር ማቆም ሁሉም እኩል ባለቤትነት እና ደርሻ ይኖራቸዋል። በዜጎች መፈቃቀድ እና መደጋገፍ ላቅ ሲልም መወቃቀስ አገር ከዘመመችበት ትቃናለች፤ ከወደቀችበት ትነሳለች፤ በከፍታም ላይ ከሆነች ከፍ ብላ ልዕልናዋን አስጠብቃ ትበራለች አገርም ትሆናለች።

የኢትዮጵያ ጉዳይም ከዚህ የሚለይ አይደለም የ3 ሽሕ ዘመን ታሪክን ወደ ኋላ ሔደን ባየንበት እና በምንዳስስበት ጊዜም አገረ መንግስት በዜጎች ቆሞ ነገስታት በጠቢባን ተመክረው እና ተነቅፈው የወንበራቸውን ዓይን ከሸወራራነት መልሰዋል። ‹‹አነዋሪ›› እና ‹‹አደጓሪ›› የተለያየ ገቢር ያላቸውን ሰዎች ቀጥረውም ከሚያሞካሿቸው አደግዳጊ በዙሪያቸው ከሚገኙ ግለሰቦች ባለፈ ወደ አሸሟሪዎች እና ህጸጽን ነቅሰው ወደ ሚያወጡ አነዋሪዎች በማዘንበል ምን ተባለ? ምንስ ጎደለ በሚል ከተቺዎች ጠንካራ ምክርን በማውጣት የመንግስታቸውን ካስማ እና የዘመነ መንግስታቸውን ዕድሜ አርዝመው ፤ አገርን አስቀጥለዋል። አገርን ከትውልድ ወደ ትውልድ እያሸጋገሩ በዘመናት መካከልም የሚያጋጥመውንም ችግር ከጠቢባን ጋር እየፈቱ የተሸገሩ መንግስታት ጥቂት አይደሉም አሁንም እንደዛው ይቀጥላሉ። ይሁን እንጂ ከነገስታት እና ከገዢዎች ባሻገር ጠቢባን ሲነሱ፤ ሲወሱ እና ሲወደሱ የሚገኙበት መድረክ እጅግ ጥቂት ነው። ለየት ብለው ወጥተው ታሪክ የመዘገባቸው እና ዘመን ያገነናቸው ካልሆኑ በስተቀር በየቤተ መንግስቱ ጓዳ ተሸሽገው የዕለት ተዕለት የንግስና ጉዞን ያቃኑ እና ነገስታትን የገሰጹ ሲወደሱ እምበዛም አይታይም።

ይሁን እንጂ ኢትዮጵያ በጠቢባን እና በሊቆቿ የጠበብትነት ደረጃ እና ዕውቀት ልክ ከዓለማት ተርታ ለመመደብ እና ተመድባም አስጠብቃ ለመሔድ የቻለች አገር ለመሆኗ በዓለም ቁልፍ ስፍራዎች እና ስማቸው በግንባር ቀደምትነት ከሚጠቀሱ ስፍራዎች ላይ በኃላፊነት እና በከፍተኛ የሙያ ደረጃ ላይ ተሰድረው የሚገኙ ዜጎቿ ምስክር ናቸው። በተጓዳኝም ነገስታትን በሰላ ትችታቸው እየሸነቆጡ የሚቆጠቁጥ ቀን መጥቶ ነገስታት ቁጣቸው ሲጠነክርም ወደ ዘብጥያ እየተወረወሩ ትችታቸውን እና አደባባይ ነቀፌታቸውን የማይተው ጥቂት ጠቢባንም ኢትዮጵያ አፍርታለች።

ዘጠና ዓመታትን በአልበገር ባይነት ያሳለፉት እና የአገር አድባር፣ የአገር ዋርካ፣ መምህር፣ የስነ መልክዓ ምድር ሊቅ፣ ጸሐፊ፣ የሰው ቁስል የሚጠዘጥዛቸው የሰብዓዊ መብት ተሟጋች፣ አምባገነኖችን የሚጋፈጥ ሰፊ ደረት ባለቤት እና ጭቆናን የማይሸከም ስስ ትከሻ ባለቤት መስፍን ወልደማሪያም (ፕ/ር) ወይም ደግሞ በወዳጆቻቸው አንደበት ‹‹የኔታ››።  መስፍን ወልደማሪያም አዲስ አበባ ተወልደው አዲስ አበባ ያደጉ የመሐል አገር ሰው ይሁኑ እንጂ ልባቸው ምጽዋን ተሸግሮ ዳህላክ ደሴት ላይ የሚሰፍፍ በመልክዓ ምድር የማይገደቡ ብርቱ ፍጡር፤ መሐል ፒያሳ ተቀምጠው ደቡብ ኦሞ ኛንጋቶም እና ዳሰነች የጓዳ ጩኸት የሚያደነቁራቸው ሰብኣዊነትን ኖረው ያለፉ የምርጥ ነብስ ባለቤት፤ ሸገር ላይ ከትመው ቶጎ ጫሌን በንስር ኣይናቸው የሚያስሱ ድንቅ ሰው። በዘመናቸው ኢትዮጵያን ያስተዳደሩ ሦስት መንግስታትን በሰላ ብዕራቸው ዕረፍት የነሱ ለምንዱባን ቆመው ለግፉዓን የተዋደቁ የጭቁኖች የቁርጥ ቀን ልጅ የወጣትነት ዘመን ብስጩ፣ የጎልማሳነት ዘመን ተጋፋጭ፣ እርጅና ዘመን መካሪው መስፍን ወልደማሪያም ።

መጽሐፍት

እንጉርጉሮ (ግጥምና ቅኔ)፣ መክሸፍ እንደ ኢትዮጵያ ታሪክ (ታሪክ)፣ ኢትዮጵያ ከየት ወዴት? (ታሪክ)፣ ዛሬም እንጉርጉሮ (ግጥምና ቅኔ)፣ ልማት ኢትዮጵያዊነት በኅብረት (ታሪክ)፣ አዳፍኔ ፍርሃትና መክሸፍ (ታሪክ)፣ እንዘጭ! እምቦጭ! የኢትዮጵያ ጉዞ (ፖለቲካ) Rural Vulnerability to Famine in Ethiopia, 1958-1977 የኔታ በግሩም የቋንቋ ችሎታ ለንባብ ያበቋቸው ዘመን ተሸጋሪ የመጽሐፍ መደርደሪያ አድማቂ እና ሁሉ በሁሉ የሆነ የአዕምሮ ምግብ የሆኑ መጽሐፍት ናቸው። በመጽሐፍት ታትመው መጽሐፍ በሚል ስም ወደ ሕዝብ ደረሱ እንጂ መስፍን ወልደማሪያም በተለያዩ መጽሔቶች እና ጋዜጦች ላይም ሳምንታዊ አምደኛ በመሆን በሰላ ብዕራቸው ያልበረበሩት የዓለም ምስጢር እና አሰናስለው ያላነሱት የኢትዮጵያ ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊ፣ እና ኢኮኖሚያዊ ቋጠሮ የለም የማለት ድፍረቱን የሚሰጡን ደጋፊዎቻችን ናቸው።

መስፍን ወልደማሪያም (ፕ/ር) እጅግ ለበዛው የአጼው ዘመነ መንግስት የዜጎች በደል ግንባር ቀደም ተሟጋች በመሆን እና የመንግስትን ሕጸጽ አይቶ እንዳላየ ሳያልፍ ‹‹ንጉሥ አይከሰስ፤ ሰማይ አይታረስ›› የሚለውን ብሒል ገና በማለዳው አሽንቀጥረው ጥለው ‹‹እንዴት ተብሎ መንግስት ይህን ያደርጋል›› የሚሉ ሞጋች ሀሳቦችን ሰንዝረው ንጉሡን የነካ ከፈጣሪ ተጣላ የሚለውን የአገሬውን ሀሳብ በአደባባይ የሰበረ የጭቆናን ቀንበር ከሕዝብ ላይ ያላላ የያኔው ወጣት በሰውነት ማጎልመሻ የፈረጠመው የዕኩልነት ጠበቃው መስፍን ወልደማሪያም ነበር። ተናዳጅ እና ጠበኛነትን ከሩህሩህ እና አዛኝነት፣ ለተበደለ ከመቆም ጋር አጣጥመው የልጅነት ሕይወታቸውን ያለፉ ግለሰብ ናቸው። ‹‹ሰው›› የሚለውን ክቡር ፍጡር በትክክል በስብዕናቸው የገለጹ ጠበኛነት እና ቁጡነታቸውን በጊዜ ሂደት ጥለው ለተበደለ መቆምን ግን በሕይወት ዘመናቸው መርህ እስኪያደርጉት ድረስ አቅፈው የሔዱ የመርህ ሰው ናቸው። በሚያዚያ 2008 ለንባብ በበቃው ውይይት መጽሔት ላይ ግለ ታሪካቸውን 86ኛ ዓመታቸውን ተመርኩዞ ባዘጋጀው ጽሑፍ ልጅነታቸውን እንዲህ ይገልጸዋል። ‹‹ፕሮፌሰር መስፍን ፈረንጆች (formative age) የሚሉት ወይም አፍላ ዕድሜያቸው ላይ  ጣልያን ኢትዮያን የወረረችበት ጊዜ ነበር። አርበኝነት የሚያደንቀው እና ‹ባንዳነት›ን የሚጠየፈውማንነታቸው የተቀረጸው ምናልባትም የዛን ጊዜ በልጅነት ልቦና ደጋግመው ይሰሟቸው ከነበሩ ትርክቶች በመነሳት እንደሆነ ይገመታል። ከልጅነት ጊዜዎቻቸው በአንዱ አንድ ጣልያናዊ አንድ በረንዳ ላይ ቁጭ ብሎ እግሩን አነባብሮ ሲያነብ ተመልክተው ምን እንዳነሳሳቸው ሳይታወቃቸው ድንጋይ አንስተው በመወርወርቅልጥሙን ብለውት ሲሮጡ ጣልያኑ ተከትሎ አባርሮ ይዞ በእርግጫ የደበደባቸው ከልጅነት ትዝታቸው አንዱ ነው›› ሲል መጽሔቱ ያስነብባል።

በእርግጥ ፕሮፌሰሩ በመጽሐፋቸው እንደገለጹ የነጭን በላይነት ከልጅነታቸው ጀምረው እንደጠሉ በኋላም ወደ ኬንያ ለጉዳይ ሔደው ያጋጠማቸውን ጉዳይም እንዲህ ከትበውታል ‹‹..ኬንያ ናይሮቢ አንዲት መዝናኛ ቤት ተገኝቼ እየተዝናናሁ ነው። ቤቱ እንደ ፓርቲ ቤት ያለ ነው። ባንዱ ጥግ መጠጤን ይዤ፣ የዳንሱ ወለል ላይ ጥንድ ጥንድ ሆነው የሚደንሱ ወጣቶችን አያለሁ። በዚህ መሃል የባሕር ኃይል የደንብ ልብስ የለበሱ እንግሊዛዊያን ነጮች ገቡ። አንዱ እንግሊዛዊ ቀጥታ ወደ ዳንስ ወለሉ ሄደና ከወዳጁ ጋር እየደነሰ ያለውን ኬንያዊ በካልቾ መታው። ኬንያዊው ተርበድብዶ የሴት ወዳጁን ጥሎ ገሸሽ አለ። እንግሊዛዊውም ከዛች ኬንያዊት ጋር መደነስ ጀመረ። በእንግሊዛዊው ድርጊት በጣም ተናደድኩ። ከመቀመጫዬ ተስፈንጥሬ ተነሳሁና ወደ ዳንስ ወለሉ አመራሁ። እኔም እንግሊዛዊውን በካልቾ ጠልዤ ኬንያዊቷን ተቀበልኩ። ጥቂት ካስደነስኳትም በኋላ ለተቀማው ኬንያዊ አስረከብኩ። ይህን ፈፅሜ ወደ መቀመጫዬ ሳመራ እንግሊዛዊው የጠየቀኝ አንድ ጥያቄ ነበር ፦ “ኢትዮጵያዊ ነህ?›› የጀብድ እና እምቢ ባይነት አቋም አብሯቸው ያረጀ መገለጫቸው ነበር።

ከየካቲት 12ቱ የግራዚያኒ ጭፍጨፋ የተረፉ፣ በደርግ የቀይ እና ኢህአፓ የነጭ ሽብርን የተጋፈጡ ፣ ከመንግስቱ ኃይለማሪያም ቁጣ እስከ መለስ ዜናዊ አህአዴግ ዘመን የአንገት ለአንገት ትንቅንቅ ተጋፍጠው መንገህስት ሔዶ መንግስት ተተክቷል። ስልጣንን አባላጊነት አበክረው የሚናገሩት እና ስልጣንን አምርረው ሚጠየፉት የኔታ ገና በለጋነታቸው ጭቆናን መታገል ምለው ነበር ነበርና ወታደራዊው መንግስት በትጥቅ ትግል ተገርስሶ አብዮታዊ ዲሞክራሲ አቀንቃኙ ኢህአዴግ ወደ ስልጣን በመጣበት የመጀመሪያዎቹ ለጋነት ዕድሜ ጨምሮ ሙግታቸውን ጀምረው ነበር። በኤርትራ መገንጠል እና ኤርትራዊያን ናችሁ ተብለው ከኢትዮጵያ አራቱም ማዕዘን ተፈልቅቀው ወደ ማያውቁት ቀየ የተጋዙትን ቀን የከፈላቸውን የአንድ አገር ዜጎችን ጉዳይ በተመለከተ በዓለም አደባባይ ጮኸዋል።

በክህደት ቁልቁለት መጽሐፋቸው ላይ ለንደን ላይ የኤርትራ መገንጠል ዕውን ሆኖ ድርድሩም በአገረ እንግሊዝ በሚካሔድበት ወቅት ከኤርትራ ወገን ፕሬዘዳንት ኢሳያስን በአጋጣሚ አግኝተው ያናገሩትን በእርግጥም ወቀሱትን ቢባል የሚቀል ንግግር እንዲህ ያስቀምጡታል ‹‹ኢሳያስን አንተ የአሉላ አባነጋ ልጅ፣ የዘርዓይ ድረስ ልጅ ሆነህ እንዴት ኢትዮጵያዊ አይደለሁም ትላለህ? ሌሎች ሌሎች ቢሉስ ይሁን አልኩት እርሱም አላሳፈረኝም በትኩረት አዳመጠኝ ›› ይላሉ። የኤርትራ አገርነት አሁንም ለፕሮፌሰር መስፍን የማይዋጥ እና ሳይዋጥላቸውም ይህቺን ዓለም ጥለው የሔዱ ለእምነታቸው የቆሙ አንጋፋ ሙሑር ነበሩ።

በዘመነ  ኢህአዴግ በ1997  በሦስተኛው አገራዊ ምርጫ ላይ ከፍተኛ ፖለቲካ ተሳትፎ ከነበራቸው ግለሰቦች ውስጥ በግንባር ቀደምትነት ይጠቀሱ የነበሩት መስፍን ወልደማሪያም (ፕ/ር) የምርጫ 97 የቅድመ ምርጫ ሽር ጉዶች፣ የምረጡኝ ቅስቀሳዎች፣ ተፎካካሪ ፓርቲዎች እና ገዢው ፓርቲ ያደርጉት ነበረው የገጽለገጽ ክርክር እንዴት ያለ የፍሰሀ ዘመን ላይ ደረስን ተባለበት ድንቅ ጊዜ ነበር። አገር አድባሩ፤ የዕውቀት ጉልላት፤ የሰውነት ጥግ መስፍን ወልደማሪያም (የኔታ) ይህን ወቅት በአስደማሚ የንግግር ችሎታ እና መካች ባጣ ጠንካራ ሙግት ተቀናቃኞችን ድባቅ የሚመቱ ቀልብን የሚገዙ ተከራካሪ እንደነበሩ ሕያዋን ምስክሮች ነን። ይሁን እንጂ ሲያልቅ አያምርምና በሦስተኛው ዓለም የምርጫ ታሪክ አኩሪ አይደለም እና ድህረ ምርጫ ወቅት በቅድመ ምርጫ ታዩት ፈርጦች በሙሉ ወደ ዕስር ተጋዙ። ድሮም የፊት ለፊት ሰው የነበሩት መስፍን ወልደማሪያም (ፕ/ር) በእርጅና ዘመናቸው ወደ ዘብጥያ አምርተው ነበር።

ዓለም ትኩረቱን በያኔዎቹ ታሳሪዎች ዘድርጎ በጊዜው የነበረውን መንግስት እንዲፈታቸው ጫና ለማሳደር ቢሞክርም ወይ ፍንክች የአባ ቢላዋ ልጅ ያለው የመለስ ዜናዊ መንግስት የኔታን ጨምሮ በኋላ ላይ ወደ ትጥቅ ትግል ያመሩትን ዜጎች ዘለግ ላሉ ጊዜያት ማቆት ችሎ በኋላ ላይም በይቅርታ እንዲፈቱ ሆኗል። ‹‹ኢህአዴግ ሕገ አራዊት ነው›› በሚል ትችታቸው ለረዥም ጊዜያት ሲሞግቱ የነበሩት መስፍን ወልደማሪያም ከግንባሩ ጋር ሆድ እና ጀርባ እንደሆኑ የ27 ዓመት ወጣቱ ግንባር ኢህአዴግ በለውጡ ማግስት ፍርስርሱ ወጥቶ ከአራት ድርጅቶች ግንባር አንዱ ሲቀር ቀድሞ አጋር ያላቸው ተጨምረውበት ወደ ብልጽግና ፓርቲ ራሱን ለውጧል፤ በዚህም ውስጥ የኔታ የሚሉት ነበራቸው።

1922 ይህቺን ዓለም የተቀላቀሉት መስፍን ወልደማሪያም (ፕ/ር) በያኔው አንድ ለእናቱ በነበረው አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ማስተማር የጀመሩ እና ረጅሙን የሕይወት ጉዟቸውንም በዛው ያጋመሱ አንጋፋ ሙሑር እንደሆኑም ታሪክ ድርሳናቸው ያወሳል። የጥልቅ ዕውቀት ባለቤት እና የግሩም ስብዕና ጥቅል መኖቸውን የሚናገሩት ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ ናቸው። ከኢትዮጵያ ሳተላይት ቴሌቪዥን ጋር አጭር ቆይታ ያደረጉት በየነ ጴጥሮስ (ፕ/ር) ዕውቀት አባታቸው እንደነበሩ ተናግረው ነብይነታቸውን እና ትንቢታቸውም ጠብ እንዳላለ በ88ኛ ዓመታቸው ላይ ሆነው በአንድ አጋጣሚ በተገናኙበት ወቅት ‹‹ከእንግዲህ አንድ ወይ ኹለት ዓመት ብቆይ ነው›› የሚል የሕይወታቸውንም ኡደት የተነበዩ ሰው እንደነበሩም ይናገራሉ።

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ ፓርቲ ሊቀመንበር እና ቀድሞው የየኔታ የትግል አጋር ብርሀኑ ነጋ (ፕ/ር) ከኢሳት ቴሌቪዥን ጋር ባደረጉት ቆይታም ‹‹በግሌ ትልቅ ነገር ነው ያጣሁት›› ሲሉ ይጀምራሉ መስፍን ወልደማሪያምን (ፕ/ር) ዜና ዕረፍት በሰሙበት ሰዓት የተሰማቸውን ጥልቅ ሀዘን ይገልጻሉ። ‹‹በግሌ ከእርሱ ጋር የማደርጋቸው ውይይቶች እና ክርክሮች ብዙ ትምህርት የሚሰጡ እና ከፍተኛ ዕውቀትን ሚያሲዙ ነበሩ›› ሲሉም በነበር የቀረውን የኹለቱን ግንኙነት አውስተው ይናገራሉ።

ከሁሉም ግን በእኔ እምነት ፕሮፍን (የኔታ ብለው ከሚጠሯቸው ወዳጆቻቸው የተረፉት እንዲህ ነው ሚጠሯቸው) እንደገለጸ ተሰማኝነት የጋዜጠኛ ታምራት ነገራ እንዲህ ሲል ትውውቃቸውን እና መጀመሪያ የነበረውን የርቀት ግምት እና ምልከታ በፕሮፍ ላይ እና  በኋላ ላይ ካገኘው ጋር አሰናስሎ መስክርነቱን በድምቀት እንዲህ ይገልጸል ‹‹በርዕዮተ ዓለም ምክንያት አፍንጫዬን ይዤ የተጠጋኋቸው ፕሮፌሰር መስፍን ግን ፈጽሞ እንደገመትኳቸው ኾነው አላገኘኋቸውም፡፡
አንደኛ፦ በጣም! በጣም! በጣም! ወጣት ይወዳሉ፡፡ የሐሳብ ድግግሞሻቸውን እና ሌክቸራቸውን ታግሶ የሚሰማቸው ከተገኘማ በጣም ደስታቸው ነው፡፡ ዝም ብለው ለሰሟቸው ወይንም ካርታ ከሚያጫውቷቸው እኩዮቻቸው ጋር ከመዋል ይልቅ ከሚጣላቸው ወጣት ጋራ ሲጨቃጨቁ መዋልን ይመርጣሉ እላለሁኝ፡፡ የእኛ ቢጤ እብሪተኛ የኾነን ወጣትን ማልመድን ደግሞ ልክ ፈረስ እንደመግራት ተክነውበታል፡፡ ለምን አይችሉበት!? ስንት ትውልድ በስራቸው አለፈ? እንዲያው ሳናውቅ፣ ዐይናችን ሳያየው፤ ግንኙነታችን ከፕሮፌሰር መስፍንነት ወደ “ፕሮፍነት” ተለወጠ፤ ከእኛ ጋር ተቀላቅለው ቡና መጠጣትና የቆጥ የባጡን ማውራት ተጀመረ፡፡

ሁለተኛ፦ በጤንነት እና በዕድሜ ምክንያት እንደ ዔሊ ለማዝገም ቢገደደዱም ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ እና ሳይታክቱ በእጅጉ ይሠራሉ፡፡ መጽሐፎቻቸውን ሙሉ በሙሉ አሊያም የመጀመሪያውን ድራፍት ራሳቸው ይተይባሉ፡፡

ሦስተኛ፦ በአደባባይ መናገርም ኾነ መጻፍ ከጀመሩበት ጊዜ አንስቶ ፈፅሞ ያልለወጧቸው ዋና ዋና አቋሞች አሏቸው፡፡ ፕሮፌሰር መስፍን ስለ ሰላማዊ ትግል፤ ስለ ስደት፤ ስለ ኢትዮጵያ አንድነት፤ ስለ ሕግ የበላይነት፤ ስለ መሬት ፖሊሲ፤ ስለ ኢትዮጵያ ዳር ድንበር ያሏቸውን አቋሞች ከፈለጋችኹ 50 ዓመት ወደኋላ ተመልሳችኹ ሂዱና አጥኑ፤ አሁንም ያኔም ፕሮፌሰር መስፍን ያው ናቸው››፡፡

በእርግጥም ፒያሳ የስመ ጥር ኬክ መገኛ ኤንሪኮ ያለበትን ዘመን ጠገብ ሕንጻ እንደታጠፉ ቁልቁል ሲንደረደሩ በሚገኘው ሌላ ዘመን ተሸጋሪ የመኖሪያ ሕንጻ ላይ ይኖሩ  የነበረው የኔታ በራቸው ተቆልፎ እንደማያውቅ እግር ጥሎት የገባ ሁሉ ለሕይወት ዘመኑ የሚበቃውን ምክር ተሸክሞ እንደሚወጣ አሳባቂም ነው። ከዓመታት በፊት በመኖሪያ ቤታቸው በተገኘሁበት ወቅት በዛ ባተሌነት በሚገንበት አዲስ አበባ እምብርት ላይ እንዲህ ያለ የጸጥታ ድባብ ይገኛል ብየ ማሰብ የተሳነኝ ጊዜ ነበር። በቅርበት ያውቃቸው ከነበረ እና ቀጠሮ ይዞ ለመጠየቅ ካቀና ወዳጄ ጋር ተደርቤ ነበር እና ያቀናሁት ልብ ድረስ ዘልቆ በሚገባ አባታዊ አስተያየት እየተመለከቱ ‹‹እንግዲህ ሽማግሌ ቤት ረዳት በሌለኝ ሰዓት መጥታችሁ ከእኔ ሻይ እንዳትጠብቁ፤ ነገር ግን ማንቆርቆሪያውም እሳቱም እዚሁ ነው ገብታችሁ መንጎዳጎድ ትችላላችሁ›› ብለው በአብረሐማዊ መንፈስ ተቀብለው አስተናግደውናል። ቤት እንደ አገር ነው በነዋሪው ይሟሻል፣ በባለቤቱም ይቀረጻል። የመስፍን ወልደማሪያም (ፕ/ር) ቤትም እንዲሁ ነው። አብዛኛውን የቤታቸውን ክፍል ከፍተኛ ሆነ የመጽሐፍ ክምር ኹለተኛ ግድግዳ እስኪመስል ድረስ የተቆለለ ነበር። በአንድ አነድናቂያቸው እና አክባሪያቸው እንደተሰጣቸው የነገሩን እና በርካታ በትንሿ አንጎሌ ልመረምረው ያልቻልኳቸውን ጥልቅ ምክሮችን አሸክመው ሰደዱን ። ቆይታው እውነት ለመናገር የሽራፊ ሰክዶች ያህል ያጠረ ቢመስልም ሳይታወቀን አራት ሰዓታትን በመጽሐፍት ታጅበን ተንቀሳቃሽ መጽሐፍ እያናገረን ቆይተን ነበር።

90ኛ ዓመታቸውን ባከበሩ ዕለት ከአዲስ ማለዳ ጋር አችር ቆይታ አድርገው ነበሩት መስፍን ወልደማሪያም (ፕ/ር) በእድሜ ብዛት ለማይዛነፈው የአዕምሯቸው ቅልጥፍና ትልቅ ምስክር መሆን ይቻላል። ቆይታቸው ለካንስ ስንብታቸውም ነበር። የአገር ዋርካ እና አድባር፣ መካሪው ምሑር የሰብዓዊ መብት ታጋዩ ፕሮፌሰር 90ኛ ዓመታቸውን አክብረው እንደተወደዱ ዘልቀው ዓለምን በናጣት ወረርሽኝ ኮሮና ቫይረስ ኮቪድ 19 ወረርሽኝ ማክሰኞ መስከረም 19/2013 ሌሊት አምስት ሰዓት ላይ ይህቺን ዓለም ተሰናብተው ረጅሙን የዘለዓለም ጉዞ ጀምረዋል።

 

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com