የደራሲው ዕይታዎች – ከ‹ሰባት ቁጥር› መጽሐፍ ባሻገር

Views: 64

አሜሪካዊው ደራሲና የተውኔት ጸሐፊ ሬይ ብራድበሪ እንዲህ ብሏል፤ ‹‹የአንድ አገር ባህል ለማጥፋት መጻሕፍትን ማቃጠል አይጠበቅም። ሰዎች እንዳያነቡ ማድረግ ብቻ ነው።››

መጻሕፍት የእውቀት፣ የታሪክ፣ የባህል፣ የማንነትና መሰል አገር የሚያክል መረጃ ተሸካሚዎች ናቸው። በአገራችንም ምንም እንኳ የንባብ ባህሉ የሚታማ ቢሆንም፣ የተሰጣቸውን መክሊት ሳያተርፉበት ላለመመለስ የሚተጉ፣ የሚጽፉ ደራስያን ብዙ ናቸው። ከዘመናዊት ዓለም የተገኘውን ክህሎት ከነባር እውቀት ጋር አዋህደው ዘመንን የዋጀ ሥራም የሚያቀርቡ ጥቂት አይደሉም።

እንዲህ ባለ መንገድ ስድስት መጻሕፍትን ለንባብ ያበቃው ይባቤ አዳነ የአዲስ ማለዳ እንግዳ ነበር። ብዙዎች ‹አክሳሳፎስ› በተሰኘ የመጀመሪያ የመጽሐፍ ሥራው የሚያወሱት ሲሆን፣ በቅርቡ ለንባብ ያበቃው ‹ሰባት ቁጥር› መጽሐፍም እንደዛው ለንባብ ቅርብ የሆኑ ሰዎችን ቀልብ ገዝቷል። በኹለቱ መካከልም አምስት መጻሕፍትን አድርሷል።

ይባቤ ከአዲስ ማለዳ ጋር ባደረገው ቆይታም ስለሕይወት ጉዞው፣ ስለመጽሐፍቱ እንዲሁም በአገር በቀል እውቀት ላይ ስላሉ አመለካከቶች ዕይታውን አካፍሏል።

ስለ ‹ሰባት ቁጥር›

ሰባት ቁጥር መጽሐፍ ለንባብ የበቃ ሰሞን በማኅበራዊ ድረ ገጾች የተለያዩ ሐሳቦ ሲነሱ ነበር። ይልቁንም በተመሳሳይ ርዕስ ከወጣውና በመስፍን ሰለሞን ሙሀባ ከተጻፈው መጽሐፍ ጋር በተገናኘ የተነሳ ውዝግብ ነው። ጉዳዩንም የተለያዩ መገናኛ ብዙኀን በትኩረት የቃኙት ሲሆን፣ ኹለቱን ደራስያን በአንድ መድረክ በማገናኘት እንዲነጋገሩም ሆኗል። መጽሐፍቱ በርዕስ ይመሳሰሉ እንጂ በይዘት ግን ልዩነት እንዳላቸው ልብ ይሏል!

ይህ ይቆየንና ወደተነሳንበት ጉዳይ እንመለስ። ይባቤ በዚህ መጽሐፉ ‹ሰው ማለት ሰባት ቁጥር ነው።› ይላል። በኢትዮጵያ ሰባት ቁጥር የተለየ ትኩረት የተሰጠው ይሁን እንጂ በውጪ አገር ሁሉንም ቁጥር ከሰው ጋር ያገናኛሉ። ዓለም ራሱ ቁጥር ነው ብለው ስለሚያምኑም ነው ሲል ያስረዳል።

ሰባት ቁጥርን በሚመለከት ታድያ በባህርማዶም የተጻፉ እንዳሉ የሚያነሳው ይባቤ፣ እነዛም ግን በሰባት ቁጥር ላይ ልዩ ትኩረት አድርገው ሳይሆን ሰባትን እንደሌሎች ቁጥሮች አንድ አካል አድርገው ነው። በኢትዮጵያ ግን ስለ ሰባት ቁጥር፣ ከሰውና ከተፈጥሮ ጋር ያለው ግንኙነትና በዚህም ውስጥ የሚነበበው ምስጢር ዙሪያ የተጻፈ ብዙ እንዳለ ይጠቅሳል። ‹‹የበለጠ ማጥናት ግን ሊጠይቅ ይችላል›› ይባቤ እንዳለው ነው።

ይህ መጽሐፉ ታድያ ስለሰባት ቁጥር ብቻ አይደለም። ይልቁንም ሕይወትን በሰባት ቁጥር ውስጥ የሚያሳይ ነው። ከዛም ተሻግሮ ደግሞ ግብጽና ኢትዮጵያን በሚመለከት ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር በተያያዘ ያሉ ጉዳዮችንም ያነሳል።

እንዴት ወደ መጽሐፍ?

‹‹ለሕይወት መንገዴ ትልቁ አስተዋጽኦ ቤተክርስትያን ናት።›› ይላል መለስ ብሎ ጉዞውን ሲያስታውስ። በቤተክርስትያን ትምህርት ዘልቆ እስከ ቅኔ ቤት መማሩም ዕይታውን እንዲያሰፋ እንደረዳው፣ ቅኔ ፈጠራን ለማዳበር ምን ያህል እንደሚያግዝም አያይዞ ያወሳል።

ሌላው ወደ መጽሐፍ ሥራ እንዲዘልቅ ያደረገው ምክንያት ደግሞ በመደበኛ ትምህርት ላይ ሳለ ተጓዳኝ መጻሕፍትን ማንበቡ ነው። ‹‹የመጀመሪያና ኹለተኛ ደረጃ ትምህርት ጅማ ነው የተማርኩት። በዛም ተጓዳኝ መጽሐፍ ማንበብ ጀመርኩኝ።›› ይላል። ታድያ አንድ ቀን በሥም ብቻ ያውቀው የነበረውን የአቤ ጉበኛን መጽሐፍ አነበበ። የአቤ ጉበኛን የትውልድ ስፍራ ያውቅ ነበርና፤ ‹ከዚህ አካባቢ ይህን የሚያህል ታላቅ ደራሲ ወጥቷል!› የሚል በርትቶ ተሰማው። ምንአልባት ያ ቅጽበት ዛሬ የደረሰበት ጉዞ ውጥን ሳይሆን አልቀረም።

‹‹ለሥነ ጽሑፍ ያገዘኝና ብርታት የተሰጠኝ ቤተክርስትያን ትምህርት ነው። ጅማ ተጓዳኝ መጻሕፍትን እያነበብኩኝ ስሄድ ራሴን መፈለግ ጀመርኩ። እንዴት ከተደራሲ ጋር መግባባት እንዳልብኝ የገባኝና መንገዱን ያገኘሁት ደግሞ ከዘመናዊው ትምህርት ነው።›› ይላል ይባቤ፤ የመጽሐፍ ሥራዎቹ ቅኝት ከየት የተወረሰ እንደሆነ ሲያስረዳ።

መደበኛ ትምህርቱን አጠናቆ ወደ ዩኒቨርሲቲ ሲገባ ነበር፣ የኹለተኛ ዓመት ትምህርቱን ሲጀምር አክሳሳፎስ የተሰኘ የመጀመሪያ መጽሐፉን የጀመረው። መጽሐፉን እያዳበረው ሄዶ፣ ሐሳብ በሐሳብ ላይ ላይ እየታከለ፣ በንባብ የጎደለውን እየሞላ፤ ከጎንደር ዩኒቨርሲቲ ትምህርቱን ጨርሶ አዲስ አበባ ገባ። ያኔ ነው አክሳሳፎስ የሕትመት ብርሃን ያየው።

ይባቤና የብዕር ሥም

ይባቤ የመጽሐፍ ሥራዎቹን ‹ሰባት ቁጥር›ን ጨምሮ በብዕር ሥም ነው ያወጣቸው። ይህንንም የሚያደርገው ዋናው ጉዳይ ሊያስተላልፍ የፈለገው ሐሳብ መሆኑን በማመን ትኩረቱን በዛ ላይ አድርጎ ነው። በትህትናም ከራሱ ሥም ይልቅ የመጽሐፉን ሐሳብ ገንኖ እንዲወጣ በመሻቱ ነው፤ ለአዲስ ማለዳ እንደነገራ።

ነገር ግን ያንን ማድረገጉ ትክክል እንዳልነበር ከመረዳት ላይ መድረሱን አንስቷል። ለዛም ነው ‹ሰባት ቁጥር› መጽሐፉን በሦስተኛ እትሙ በራሱ ሥም ያደረገው።

የይባቤ ዕይታ

አገራት ዘመናዊ ቀለምን በመላበስ ሲጀምሩ እንደ ብልሃት መጠናቸው ራሳቸውን የኖረ እውቀትና ባህል ሳይዘነጉ ነው። አንዳንዶች ደግሞ የቀደመውን ቀለም ይተዋሉ፤ ይረሳሉ። በኢትዮጵያም በብዙ መልክ የተተወ፣ የተዘነጋ አገር በቀል እውቀት አለ። ይህም ክፍተቱ ምኑ ጋር ይሆን የተፈጠረው የሚል ጥያቄ ያስነሳል።

ይባቤ በበኩሉ የሆነ ቦታ ላይ የተሰበረም ባይሆን የተጣመመ ድልድይ አለ ይላል። ‹‹ችግሩ የአንድ የሆነ አካል ጥፋት አይደለም። ሁላችን በቀጥታም በተዘዋወሪም አጥፍተናል። ፖሊሲና ዐለማቀፍ ተጽእኖም አለ።›› ሲል ዘመናዊነት ከአገር በቀል እውቀት ጋር ተሰናስሎ ያልቀጠለበትን ምክንያት ያስረዳል።

ያም ብቻ አይደለም፤ የኢትዮጵያ ሊቃውንት ዝምታም ለዚህ አስተዋጽኦ አድርጓል ባይ ነው። ሊቃውንቱ ዘመኑን የሚጥን ሥራ እየሠሩ አይደለም። መናገር ባለባቸው ደረጃ አለመናገራቸው፣ እንደ ጥንቱ አራቱ ኃያላን እስከሞትና መሰየፍ ድረስ መንግሥታትን የሚታገሉ በብዛት አለመታየታቸው ለዚህ ሰበብ ሆኗል። የእምነት አባቶችና አዋቂ የተባሉት ሳይቀር ከፖለቲካው መገናኘታቸው ደግሞ ዝምታቸውን አጠንክሮታል።

‹‹የመጥፎዎች ሩጫ ነፍስ እንዲኖረው ያገዘው የእነርሱም ዝምታ ነው።›› ሲል በአንድ መንገድ ይጠቀልለዋል። ከእነዚህም በተጓዳኝ በስርዓተ ትምህርት ሆነ ተብሎ የጎደፈም አለ የሚለው ይባቤ፣ በእነዚህ ሁሉ ምክንያቶች ለዚህ ትውልድ ሊታዘን እንደሚገባ ይላል።

ታድያ ትውልድም ጋር እንከን ሳይኖር ቀርቶ አይደለም። የሥልጣኔን ምንነት በሚገባ አለመረዳት፣ ቆም ብሎ አለማየትና ከውጪ የቀረበውን ሁሉ ጥሩ ነው ብሎ መቀበል በትውልዱ ላይ የሚታይ ግድፈት ነው ሲል ይገልጸዋል። ‹‹ለዓለማቀፍ ተጽእኖ ሰለባ መሆንም ድክመት ነው። በዚህ ወጣት ላይ ብዙ ተጽእኖና ፈተና አለ። በገዛ ሞባይልና ቲቪው የሚቀርብለት ብዙ ነገር አለ። የሚመራው መንግሥትም ሲዋሽ ያያል። ከላይ ደፍርሶ ከታች ሊጠራ አይችልም።›› ሲል በሁሉም መልኩ ለውጥ እንደሚያሻ ያሳስባል።

 ኢትዮጵያዊ ሰው – ከ‹ሰባት ቁጥር› ባሻገር

ሰባት ቁጥር ከሰው ጋር ያለው ትስስርና ተጓዳኝ ምስጢር አንባብያን ከመጽሐፉ ያገኙት ዘንድ እናቆየው። ወዲህ ግን ስለ ሰውነት ብሎም ኢትዮጵያዊነት ሲነሳ ይባቤ አንድ ክስተትን ያወሳል። ደርግ ከሥልጣን ወርዶ ኢሕአዴግ ወደ አገር መምራት ሊመጣ በነበረው ወቅት አገር ለሰባት ቀናት ያለመንግሥት ቆየታለች። ግን ሰላም ነው። ያ ክስተት ዛሬ ቢሆንስ ኖሮ?

አጭር በሚመስል የዓመታት ልዩነት ውስጥ ያለው በግብረገብነት እንዲሁም ሰብአዊነት ላይ ያለው ልዩነት የደረስንበትን ደረጃ ያሳያል ብሎ ያምናል፤ ይባቤ። ‹‹አሁን መንግሥት ባይኖርስ?› ሲል ይጠይቃል። ‹‹መከላከያ/ወታደር እንኳ እያለ ሰው ይሞታለ። ደረጃችን እንዴት እንደወደቀ ዐይተናል።›› ሲል ይገልጸዋል።

አያይዞ ያነሳውና እንደ ኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን እንደ አፍሪካም ያለው ችግር፣ ፈታኝ ነገር ካልገጠመ በቀር ለመፍትሄ አለመዘጋጀትን ነው። ‹‹ትምህርት ቤት ስንማር እንኳ ፈተና ሲደርስ ነው የምናጠናው። ብዙ ነገር ተገደን ነው የምናደርገው። ይህ የሆነው ግብረገብነት ስለጎደለን ነው።›› ሲል ያለውን ስህተት ያነሳል።

የውጪውን ተጽእኖ አውስቶ፣ ሰው ሊገደብ አልያም ተጽዕኖ ሊያርፍበት የሚችለው በሚፈቅደውና በሚቀበለው መጠን ነው ይላል። በአንጻሩ ግን በተለይም በከፍተኛ የትምህርት ተቋመት ከውጪ እንደወረደ የሚመጣውን በመቀበል ባህር ማዶ ያሉ ባለጸጋ አገራት ያሻቸውን ተጽእኖ እንዲያሳርፉ አስችሏቸዋል።

‹‹ዩኒቨርስቲ የሰው በረት ሆኗል/ነው። እንደውም አሁን ይመጥነዋል። በረት የእንስሳ ነው፣ እኛ ከዛም አንሰናል። እንስሳ ዱላ ይዞ አይዞርም።›› ስል በትምህርት ተቋማት ይታይ የነበረውን ጥፋት አብዝቶ ይኮንናል። በዩኒቨርሲቲ የሚሰጠውን ዝም ብሎ እንዲውጥ የተደረገ ወጣት፣ የተሰጠውን ሳያመነዥግ ይውጣል። ይህም ለአገሩም ለራሱም አጥፊ እንዲሆን ያደርገዋል።

‹‹መጀመሪያ ሰው በራሱ ማንነት ራሱን ችሎ መቆም አለበት። ክፉና ደጉን የሚለይ አእምሮ ተሰጥቶናል። ሁሉም ሰው እያንዳንዱ የጎደለውን የሚሞላበት የተለያየ የተሰጠው ጸጋ አለ። ሁሉንም አንድ የሚያደርገው ደግሞ አእምሮው ነው። መጀመሪያ ለትልቅ ነገር ዓላማ የተፈጠረ ሰው መሆኑን መቀበል አለበት። ቀጥሎም በአገሩ እውቀት መመካት፣ ለማስተካከል እንዲቻልም የተበላሸውን ማወቅ ያስፈልጋል።›› ይለል ይባቤ።

ያም ሆነ ይህ አሁንም ተስፋ አለ ባይ ነው። ይልቁንም ትውልድ ወደ ቀደመው የአገሩ እውቀት መጥቶ ለማወቅና ለመመራመር የሚተጋት ጊዜ መምጣቱ እንደማይቀር ያምናል። እንዴት የተባለ እንደሆነ መልሱ እንዲህ ነው፤ ‹‹ምክንያቱም የውጪውን ቃርመን የሚጨበጥ እናጣለን። ፈረንጅ የሚሰጠን ገለባውን ነውና።›› ነው መልሱ።

የሕይወት ጉዞ

ይባቤ በሕይወቱ በብዙ ፈተና አልፏል። ወላጅ እናቱን በልጅነት እድሜ ያጣ ሲሆን፣ ያደገው ከአያቱ ጋር ነው። እህት ስለሌለው ቅር ቢሰኝም ኹለት ወንድሞች ግን አሉት። አያቶች አንደላቀው እንደሚያሳድጉ ይታወቃልና፣ እርሱም በተመሳሳይ ደስተኛ ሆኖ ልጅነቱን እንዳሳለፈ ያወሳል። ያም ቢሆን እንደ ልጅ መጫወትና መቦረቅን የመረጠ አልነበረም። እንደውም ለትምህርት ልዩ ፍቅር ነበረውና ትኩረቱ ለዛው ነበር።

በቤተክርስትያን ትምህርት ነው ትምህርቱንም የጀመረው። አንድ ብሎ ከንባብ ቤት ጀምሮ እስ ቅኔ ቤትም ዘልቋል። ይህንን ትምህርት እንዲማርም አያቱ ምክንያት እንደነበሩ ያስታውሳል። ‹‹የመጀመሪውን መስር የዘረጋችልኝ አያቴ ናት። የእህል ጉዳይ ችግር የለም፤ ትምህርት ነበር ችግሩ። እንደ አሁን አይደለም።›› ሲልም ከቤተክህነት ትምህርት ውጪ ዘመናዊ የቀለም ትምህርት በቶሎ እንዳልጀመረ ያወሳል።

እድሜው ከፍ እያለ ሲሄድ ታድያ የራሱን መንገድ የሚያወጣ፣ የሌሎች ፍላጎት እንዲጫንበት የማይሻ ሆነ። ‹ነገስ?› ብሎ የወደፊቱንም ማሰብ የጀመረው በለጋ እድሜው ነው። የቤተክህነቱን ትምህርት ከገፋበት ወደ መሪጌታ ማዕረግ እንደሚያደርሰው ተረዳ። ያ ግን ጥጉ እንዲሆን አልፈለገም። እናም ዘመናዊ የቀለም ትምህርትን አብዝቶ ፈለገ። አደረገውም።

‹‹ቤተሰቤ በዚህ ደስተኛ አልነበረም። ብዙም ተቀጥቻለሁ። ጅማ ድረስ የሄድኩትም ለዛ ነው። ካሰብኩት ዓላማ ዝንፍ ላለማለት ብዬ።›› ሲል የትምህርት አሃዱውን ለአዲስ ማለዳ አጫውቷታል። ትምህርትን ፍለጋ ወደ ጅማ አቀና። ወንድሙ በዛ ቢኖርም ከእርሱ ጋር ለመኖር አልሆነለትም። የዚህም ምክንያቱ ቤተሰቦቹ ወደ ዘመናዊ ትምህርት መግባቱን ስላልወደዱን ወንድሙም ከቤተሰብ መቀያየምን ባለመፈለጉ ነው።

ይባቤ በዚህም ጉዞው አልተገታም። ‹‹ዓላማዬ መማር ብቻ ስለሆነ ብዙ ውጣ ውረድ አሳለፍኩኝ።›› ይለል፤ ከብዙ በጥቂቱ እያነሳ። ያኔ ነው ፓታክ ከሚባል በጅማ ዩኒቨርሲቲ የኤሌክትሪካል ምህንድስና መምህር ከሆነ አንድ ሕንዳዊ ጋር የተገናኙት። ይህ ሰውም ሊያስተምረው ፈቀደ። በቤቱም እንደ ጥበቃ እያገለገለው፣ በር በመክፈትና በመዝጋት እንዲሁም የተባለውን በመታዘዝ፣ ትምህርቱን እየተማረ ኑሮውን ከፓታክ ጋር አደረገ።

በዘመናዊ የቀለም ትምህርት ጎበዝ የነበረው ይባቤ፣ ይማርበት በነበረው ‹ጅሬን› በሚባል ትምህርት ቤት፣ መምህራኑ ሳይቀር ተሟግተው ክፍል እንዲዘል መደረጉንም በፈገግታ ያነሳል። እርሱ ዝም ብሎ ሳለ መምህራኑ ስለእርሱ ያደረጉትን መግትም እንደማይረሳውም ጭምር።

ሕንዳዊው ፓታክም ያንን ሲሰማና የተማሪው ይባቤን ውጤት ሲያይ በእጅጉ ደስተኛ ይሆን ነበር። ‹‹ቀናነትን፣ ለሰዎች መኖርን የተማርኩት ከእርሱ (ከፓታክ) ነው። ማህበራዊ ሕይወት የሚባለው ለሰዎች መኖርና መስጠት መሆኑን ያወቅኩት ከውጪ ከመጣ ፈረንጅ ነው።›› ይላል።

ታድያ ፓታክ ይባቤን ምን ላድርግልህ ሲል ይጠይቀዋል፤ ለጎበዝ ተማሪ እንዲህ ማለት የተገባ ነውና። ይባቤም በጊዜው ትምህርቱ ብቻ ነበርና ቁምነገሩ ‹‹ነገ ድንገት ባትኖር ትምህርቴ ሊታጎል ይችላል። እናም ሥራ ፈልግልኝ›› ሲል ሥራ ማግኘትና እየሠራ መማር እንደሚፈልግ ይገልጻል። ፓታክም ለጅማ ዩኒቨርሲቲ ደብዳቤ ጻፈ። ያኔ ይባቤ ጅማ ዩኒቨርሲቲ አትክልተኛ ሆኖ እየሠራ ከሚወደው ትምህርት ጋር ቆይታውን ቀጠለ።

‹‹በዛ እየሠራሁ አንደኛና ኹለተኛ ደረጃ ትምህርቴን ጨረስኩኝ። አሥራ ኹለተኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ሲቀረኝ ግን ወደ ጎጃም ሄድኩኝ።›› ይላል። ይህ የሆነው ደግሞ በጅማ ኦሮምኛ እንደ አንድ የትምህርት ዓይነት ፈተና ይሰጥ ስለነበር፣ እርሱ ደግሞ ለፈተና በሚያደርስ መጠን ቋንቋውን አውቀዋለሁ ብሎ ስላላመነ ነው።

‹‹ጊዜአዊ ምቾት ለዘላቂው ሕይወት ጉዳት ሊሆን አይገባም ብዬ አምናለሁ። መሠረት ላይ መሥራት ያስፈልጋል። አሁን ተመችቶ በኋላ ከመቸገር አሁን ተቸግሮ በኋላ መደሰት ይሻላል። ቀጣዩን ነበር የማስበውም።›› ሲል በጅማ ዩኒቨርስቲ ከነበረው ምቾት ይልቅ ትምህርቱን አስቀደመ። 12ኛ ክፍል ብሐየራዊ ፈተና ከተፈተነ በኋላ ጎንደር ዩኒቨርስቲ ደረሰው። የቋንቋና ሥነ ጽሑፍ ትምህርቱንም በጎንደር ዩኒቨርስቲ አጠናቀቀ።

በቅርቡና ወደፊት

ይባቤ ሰባት ቁጥር የተሰኘው መጽሐፍ ኹለተኛ ቅጽ እንደሚኖረው ተናግሯል። ይህ መጽሐፍ የሚወጣበትን ጊዜ በእርግጥ መናገር ባይቻልም፣ ይህን ዓመት ማለትም 2013ን እንደማይዘል ግን ያረጋግጣል። ‹‹ሐሳብ ስለሚጨምር፣ የሚያጠናክሩ መጻሕፍትም የማገኝ ስለመሰለኝ ትንሽ ማቆየቴ አይቀርም።›› ሲል ተናግሯል።

‹‹አገር ሰላም ሲሆን ነውና ሁ ቀጣዩም በዚህ መልክ ነው የሚጻፈው። ሰባት ቁጥር ጎልቶ የሚወጣት ነው የሚሆነው።

በሌላ በኩል አቤ ጉበኛን ደጋግሞ የሚያነሳው ይባቤ፣ ብዙ አልተነገረለትምና አቤ ጉበኛ በቋሚነት የሚወሳበትን አንዳች ሥራ የመሥራት ሐሳብ አለው። በጊዜው በእድሜው ከሚጠበቀው በላይ ሠርቷል ሲል የሚያወሳውን አቤ ጉበኛን፣ ለሞተለት ዓላማ እስከሞት የሄደ መሆኑ ደግሞ ምን ያህል ትልቅ ዋጋ እንዳለው ለመጥቀስ ይሞክራል። እና ‹‹አቤ ጉበኛ ለእኔ ጉልበቴ ነው።›› ይላል።

‹‹ለወደፊት ብዙ ሐሳብ አለኝ። በተለይ ከንባብ ጋር በተገናኘ ልሠራ የማስበው አለ። እንደ አቤ ጉበኛ ያሉ ሰዎችም የሚዘከሩበት ቋሚ መድረክ፣ ትምህርት ቤት ከመክፈት ጀምሮ ወይም ሲምፖዝየም ማዘጋጀት እፈልጋለሁ። በሕይወት ያሉ ጉልበት የሚሆኑ ሰዎችንም ወደፊት የማምጣት ሐሳብ አለኝ። እነዚህ ሊቃውንት ዝምታቸው አንድም መድረኩ ባለመፈጠሩ ሊሆን ይችላልና።›› ብሏል።

በዚህ እናጠቃል፤ ይባቤ ከአዲስ ማለዳ ጋር በነበረው ቆይታ ከንግግሩ መካከል ይህን አለ፤ ‹‹እውቀትና ችሎታ ብሔር የለውም። ከትጋት የሚመጣ ነው እንጂ።››

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com