ድስቱ እና ጉልቻዎቹ

Views: 48

የጉልቻና የድስትን ግንኙነት ከአገርና ከመሪዎች ጋር የሚያነጻጽሩት በኃይሉ፣ በሥልጣን ግብር፣ ጉልቻነት ማለት ገጽን በእሳት እያስመቱ አገርን ያክል ታላቅ ድስት የመሸከምና የማረጋጋት ትልቅ ኃላፊነት ነው ይላሉ። ለጉልቻ የሚመረጠው ድንጋይም ለድስቱ መረጋጋት ወሳኝ እንደሆነ አገር በቀሉን ሙያ በማንጸሪያነት አብራርተዋል። ባለፉት ኹለት ዓመታትም ጉልቻው ባለመርጋቱ የተነሳ በኢትዮጵያ የደረሰውን ጥፋትና ወደፊት ምን ሊደረግ ይገባል በሚሉት ሐሳቦች ላይ ነጥቦችን አንስተዋል።

እንደ አገርኛው አባባል ከሆነ ‹ጉልቻ ቢለዋወጥ ወጥ አያጣፍጥም!› አዎ የመልካም የማጀት ባለሞያ (የኩሽና) ሙያዋ የሚለካው ቡዙውን ጊዜ በውጤቷ ነው – ክሽን አድርጋ በምትሠራው ወጥ። ታዲያ ለዚህ ጣፋጭ ሙያዋ ውጤት ይህች እንደ እንዝርት የምትሾር ባለሞያ ብዙውን ጊዜ የምትሻው ግብአቶችን ነው እንጂ ሙያዋን ለማሳየት ኩሽናን እንኳ የግድ አትልም። ሜዳ ላይ ቢሆን እንኳ ተአምሯን ትተገብረዋለች። ሙያው በእጇ ነውና። ግና ሜዳ ላይም ሆነ ጓዳ፣ እንደባሕሉ ወጥ ሠሪዋ አስቀድሞ ጉልቻዎቿን ትመርጣለች። ምክንያቱም ለድስቷ የሚቀመጥበት የመርጋቱ ሕልውናዎች በመሆናቸው ነው። አገርም እንደ ድስቱ…።

ባለፉት ኹለት ዓመታት በኢትዮጵያ እፁብ ሊሰኝ ይቀርብ የነበረ ለውጥ እንዲሁም ከዚህም ፍጹም ተፃራሪ የሆነ ኢ-ሰብአዊ ድርጊት የሞላበትን አውሬያዊ ነውጥም ዐይተናል። ለዚህ ደግሞ ምክንያቱ አገር የቆመችባቸው ጉልቻዎቿ የማርጋት ግብራቸውን ስተው ድስቱን ለመገልበጥ መነዋወጣቸው ነው።

ጉልቻ ሲመረጥ አይነተኛው መስፈርት ድስቱን ማስመቸቱ ብቻ አይደለም፤ እሳትን መቋቋሙም ጭምር እንጂ። የእሳቱን ሙቀት የማይቋቋም ከሆነ ይፈነዳል፤ በፍንዳታውም ድስቱ አደጋ ያጋጥመዋል፤ አጋድሎ ወጡን ይደፋል አልያም ዘጭ ብሎ (ውስጡ የያዘውን በመጠኑ ወደላይ በትኖ) በስሩ እሳቱ ላይ ያርፋል። የተፈነገለው ጉልቻ ግብሩን ስቷልና ለዝናብ ወጥቶ የሚጣል ደንጊያ ብቻ ይሆናል።

የድስቱ ተፍፃሜት ይህ መሆኑ ብቻ ሳይሆን ምናልባትም እሳት የሆነው ድንጋይ ፍንጥርጣሪም የባለሙያዋን (የወጥዋጯን) ሕላዌ ሊያከትመው ይችላል። በመሆኑም ይህች ባለሙያ ወጧን ልትሠራ ስትሰናዳ ድስቱን የሚያረጉላትን ድንጋዮች መልክ (ቅርፅ) ብቻ ሳይሆን የድንጋዮችን አስተማማኝ አለትነት ለራሷ ሕላዌ ስትል በጥንቃቄ መምረጥ ይኖርባታል። ባለሙያዋ በየጊዜው እሳቱን ትቆሰቁሳለች፥ ትመጥናለች፣ ያለመታከት ድስቷን ታማስላለች። ውስጡ ያለው እኩል ሆኖ እንዲበስል፥ እንዲስማማ በቅደም ተከተል መጨመር ያለባትን ማጣፈጫ ቅመማት እያከለች (በዚህ ሁሉ ጊዜ ታዲያ የድስቷን ነውር ትርክርክ ዙሪያውን እያጠራች) በትዕግስት ታበስላለች። በዚህ ጊዜ ግን ጉልቻ ፈጽሞ ስጋቷ እንዲሆን አታደርግም።

በሥልጣን ግብር፣ ጉልቻነት ጀርባን ወይ ገጽን በእሳት እያስመቱ አገርን ያክል ታላቅ ድስት የመሸከምና የማረጋጋት ትልቅ ኃላፊነት ነው። እነዚህን ብርቱ ጉልቻዎች በመልክ ብቻ ሳይሆን በጽናታቸውና በግልጋሎት አስተማማኝነታቸው መምረጡ ደግሞ በድስት የተመሰለች አገርን እነዚህ ጉልቻዎች ላይ የሚያሸክመው መሪ (ባለሙያ) ኃላፊነት ነው። ምንግዜም ቢሆን ግብዓቱ ቢኖርም እዚህና እዛ ተበታትኖ መሸከፋና ማምጣቱ አንድ ሥራ በሆነበት ጊዜ አይደለም፣ በተትረፈረፈ ግብዓትም ቢሆን እንኳ የተፈለገውን ውጤት ለማምጣት ተፈላጊውን ነገር መለየት ግድ ይላልና።

ይኼ ግዜ ደግሞ የዘመን ንጋት የሚበሰርበት፣ የመልካም አዲስ ዓመት አውዱ የሚታይበት፥ የሚሸ’ትበት ብሎም የሚቀመስበት በዓል ነው። እናም ብዙ ኢትዮጵያውያን ባለሙያ የከሸነችውን መቋደስ ልማዳችን ነው። ግን  ባለሙያዋ እዚህ ደረጃ አድርሳ ለውጤት ከማብቃቷ በፊት በመሠራት ላይ እያለ ጉልቻው ቢወላውል እና ቢደፋ፥ አልያም ድስቱን መልሳ መላልሳ በማንሳት ጉልቻዎችን በመቀያየር ብትጠመድ ሙያዋ ጥራቱም ጣዕሙም ይጓደላል። አበሳሰሉም ያረረና ያልበሰለ ድብልቅ ሆኖ ተመጋቢውን ያውካል። ስለዚህ የድስቱ መቀመጫዎችን መምረጥ ሙያን ከማስመስከር ይቀድማል፤ እንዲያውም የማስመስከሪያ አንዱ ጅማሮ ይሆናል።

አገራችን የተቆመችባቸው ጉልቻዎች በተለይ በእነዚህ ኹለት ዓመታት ግዜ ውስጥ ከማርጋት ግብራቸው ወጥተው ሲነዋወጡና ድስቱን ከወዲያ ወዲህ ሲንጡት አላየን ይሆን?! ነዲድ እሳትን ተቋቁመው የተሰየሙበት ኃላፊነት ላይ ከመርጋት ይልቅ ራሳቸው ፍም እሳት ሆነው ለግብዓትነት የታሰበውን ሁሉ ነድደው እንደ ማገዶ አመድ ሲያደርጉት አላስተዋልን ይሆን? ባለሙያውስ የእነዚህን ጉልቻዎች ‹አውቆ አጥፊነት› ለይቶ ከቀየራቸው በኋላ ሌላ ቦታ ላይ መጎለቱ አለበለዚያም የፈረደበትን መከረኛ ድስት እያመላለሰ በማንሳት አመዱ ላይ ሲያስተካክልና ድስቱን መልሶ እየሰየመባቸው ሲርመጠመጥ አልታዘብንና አላዘንንምን?! አንዳንድ ቦታ ላይ ሙሉ ለሙሉ ጉልቻዎቹ በግብራቸው እንዲቆዩ እንደማይጠበቅና መቀየራቸው ግድ እንደሆነ በባለሙያ ቋንቋ ሲነገር አልሰማንምን?!

‹ጨው ለራስህ ስትል ጣፍጥ፤ ካልሆነ ደንጊያ ነው ብለው ወደውጭ አውጥተው ይጥሉሀል።› የሚለው ከቅዱስ ቃሉ መዝዘን በቀን ተቀን ውሏችን የምናወሳው ‹ብሂል› ለእነዚህ ግብራቸውን ስተው ከደንጊያዎች ግልጋሎትም ተርታ እንኳ ዘቅጠው ለተገኙቱ ጉልቻነትን የመሰለ ኃላፊነት አውቀው በማፍረስ ለተለዩቱ ወደ ዉጭ መ’ጣል ብቻ ቅጣት እንዴት ሊሆን ይችላል?!

ተገቢ ፍርድስ እንዲሆን ዳግምም ሌላ ባለሙያ በስሕተት ሆነ በዳተኝነት መልሶ እንዳይሰይማቸውና መሰል ስሕተትን እንዳይፈጽሙ፥ ከደንጊያ ተራ ተመርጠው የጉልቻነት ኃላፊነትን ለሚሸከሙና ለተሸከሙቱ ቀሪዎቹም ሆነ አዲስ ተጎላች ደንጊያዎች ትምሕርት ይሆናቸው ዘንድ እነዚህ የማርጋት ዕምነትን ዕሳት ሆነው የበሉቱን፥ ድስቱን አነዋውጸው ለደፉቱ በፍትሕ መዶሻ ትዕቢት ጥፋታቸው ከላያቸው ላይ መቀረፅ፥ መወቀር አልያም መድቀቅስ አይገባውምን?!

ፍትሕ ቀሪውን ከማስተማር፥ ሁሉን በእኩልነት ከመዳኘት ባለፈና ሰላምን ከማስፈን ሌላ ስንት ገጽታ አለው?! ባለሙያስ በሚያስቀመጠው መልካም ጉልቻዎች ላይ የሚሰየመው ድስት ውስጥ ሰላምን ለመከሸን አስቦ ሲነሳ አመራረጡ ደንጊያነት ብቻ እንዴት ሊሆን ይቻላል?! እርግጥ ነው ደንጊያን እንደ ደንጊያ አይነቱ ሊመርጡት ግድ ይላል፤ አንዳንዱ ማዕዘን ነው፤  የሰው ልጅ መሰረታዊ ፍላጎቶች ከተሰኙቱ አንዱን – ፅኑዕ ቤትን ያህል ለማነጽ የሚውል ግብአት ነው።

ሌላው ግብሩ ደግሞ የጥፋት ነው። ሞትን ያስጀመረ መግደያ። ቃየል በንጹህ ወንድሙ አቤል ላይ እጁን ቢያነሳ በመዳፉ መሐል ነግሶ የወንድሙን ነፍስ እንዲያጠፋበት የዋለ የደም ማፍሰሻ መሣሪያ የሆነ ነው – ደንጊያነት። ስለዚህ ለጉልቻነት ሲመረጥ ከመካከላቸው ስለተገኘና እጅ ስላነሳው ሳይሆን የተፈለገዉን የማርጋት ዓላማ የሚያሳካ መሆኑን በቅርጹን ዐይቶ፥ የመቋቋምና በእሳት ዋዕይ ውሎው ፈንድቶ በመፈረካከስ፡ ድስቱን ፈንግሎ ራሱም ከነዲድነቱ ለመብረድ ጊዜን የማይፈጅ፥ ሌሎችንም አደጋ ላይ የማይጥል መሆኑን መለየት ያሻል።

እነሆ ጉልቻዎቻችን አንዳንዶቹ በተነዋወጡበትና ድስቱን ባንቀጠቀጡበት ስፍራ ዛሬም እዛው ተጎልተው በነበሩበቱ ተትተዋል። ባለሙያው ላያቸው ላይ የሰየመውን ድስት ብድግ አድርጎ ቅርፃቸውን ‹በፍትሕ መዶሻ› ጠረብ ጠረብ በማድረግ መልሶ ሲሰይመው አላየንምና ደግመው አለማነዋወጣቸውን መናገር አይቻልም። ምናልባትም ዝዋዥዌ እያጫወቱት መስሏቸው ይሆናል። ቀሪዎቹ ደግሞ ሲያነዋውጡ ከነበሩበቱ ታላቅ የጉልቻነት ስርፋ ተነስተው፥ ሌላ ቦታ ተወስደው፥ ሌላ ድስት ተጥዶባቸዋል።

ወዳጄ የፍትሕ መዶሻ ያላረፈበትና ለማስተካከል ያልቀረጸውን፥ ጉርብጥብጥነቱንም ወቅሮ ያላመቻቸው ደንጊያ ላይ አሁንም ሌላ ድስት እንዲሰየምበት መፍቀድ፤ በተቀየረውም ስፍራ የተተካው ጉልቻ ቀድሞ ተጎልቶበት ከነበረበት (መጎለቻ) ቦታው የነበረው ግብሩ ተመዝኖ ካልመጣ ‹ሰላም ለምከሽንበት ድስት ማረፊያ ጉልቻ አለኝ› ለማለት ብቻ ያስመስልበታል። ይሕ ደግሞ ባለሙያውን ያቃልለዋል፤ ሙያውን መተግበር ሳይጀምር ከአጀማመሩ ከአሰነዳዱ ይፈርዱታል። ከአያያዝ ይቀደዳል ከአነጋገር ይፈረዳል አይደል ኗሪው ብሂል?!

መሪ ባለሙያ ስትሆን፣ ለዛውም በእሳት ላይ የተጣደችን እንደ ድስት ሁሉን ዐቅፋ በእኩል መጠን አብስላ ለመመገብ የምትተጋ አገርን አስተዳዳሪነትን ስትወስድ፣ ቅድሚያ የዐይን ሽፋሽፍት ርግብግቢት ቅጽበትን ያሕል ጊዜን እንኳ ወስደህ ደግመህ እንዳታስበው የሚያደርግህ ‹የሰዎችን ሕይወት አደጋ ላይ ሊጥል ይችል ይሆን አይሆን?› ስትል የምትጠራጠርበትን ደንጊያ ለጉልቻነት አለመሰየም ነው። እነዚህ አገር የተጣደባቸው ጉልቻዎች (ከታች እቶኑ እየለበለበው የተሰየመበትን ሰላምን በውስጡ ከትቶ የመከ’ሸን ግብሩን) በእሳት ላይ ለመጽናት በሐላፊነት በመርጋት የሚቆሙና የተሰየመባቸውንም አገር በሰላም እርጋታ የሚያቆሙ ሊሆኑ ግድ ነው።

ባለሙያ ተሰኝተህ ያስመዘገብከው ውጤት ሊኖር ግድ ይላል። የአንድ ስፍራ ግሩም ውጤትህ ከሌላው ቦታ ካስመዘገብከው ዝቅተኛ ውጤት አልያም ምንም ሲከፋም አሉታዊ (negative) ውጤት ጋር ተደማምሮና ተካፍሎ እጅግ ቢያንስ ባዶ (zero) ሊሆን ቢችል እንጂ አሉታዊ (negative) ሊሆን ፈጽሞ አይ’ገባውም። ምንም ደግ ነገር ሥራ፣ የማደግ አብነት የተሰኙትን ግንባታንና የመሰረተ ልማት አውታሮች ማስጀመር ብቻ ሳይሆን ማስጨረስም ላይ ድረስ እንኳን በመቶዎች የሚቆጠር የሰው ሕይወት ቀርቶ አንዲት ነፍስ እንኳ ለዛውም በሰየምከው ጉልቻ የነውጥ አጋፋሪነት ከጠፋ ልትወቀስ ልትገሰጽስ አይገባህምን?

በሙያህ ታምኖብህ ሰው ሁሉ ታበስለውን ደግ ሰላም ሲጠብቅ ጉልቻህ ተንሸራቶ ሲቀሽብብህና ይህ ነገር ሲደጋገም፣ ጉልቻህንም ለሌላ ጉልቻነት እንዳይመረጥና እንዳያሳስት ፍትሐዊነት በሞላው መዶሻ ፈረካክሰህ ለሌላ የጠጠርነት ሕላዌ ካላዋልከው እውነት ሙያህ በምክንያት ይታይልህ ሳይሆን በሰበብ ይታይብህ እንዳይሆን ሰግተህ ነው ተብሎ ቢታሰብስ ‹እኮ እንዴት?!› ስትል ትጠይቅ ይሆን? እንጃ!።

ዛሬም ቢሆን በአንዳንድ ከፍታ ስፍራ የሚገኙቱ ለማርጋት የተመረጡቱ ራሳቸው ተነዋዋጭ በመሆናቸው የተሰየመባቸው ድስት መርጋት አቅቶት ስንቱ ሙያህን አማኝ ተስፈኛ ተሠርቶ የሚበስለውን ሰላም መብላት ሳይችል ኃላፊነታቸውን ያጎደሉቱ እነዚህ ደንጊያዎች በሚወነጭፉትና በሚያስወነጭፉት እሳት ሕይወቱ እየተበላ በሰቆቃ እንዲኖር ሆኗል። ይህንንም የሚያደርጉ ገዳይ ጉልቻዎችህን አስወግድ። ይብቃን!

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com