በመቶው ሳምንታት…

Views: 118

አዲስ ማለዳ እነሆ አንድ መቶኛ እትሟን አድርሳለች። ሊደርሱ ካሰቡበት ስፍራ በሚወስደው ረጅም ጉዞ መካከል ላይ አረፍ ማለት ደንብ ነውና፣ መቶኛዋ ላይ ሆናም መለስ ብላ በዘገባ፣ መረጃና ሐሳብ በማካፈል ያለፈቻቸውን ጊዜያት ልትቃኝ ወደደች።

‹ሲቄ› የኦሮሞ ሴት የምትይዛት በትር ወይም ቀጭን ዱላ ናት። ግን በላይዋ ላይ ብዙ ኃይል አለ። ይህም በሚቀበለውና በሚያምነው ማኅበረሰብ ዘንድ ዋጋው ከምንም በላይ የላቀ ነው። አንድ ከአወሮፓ የመጣ ሰው የሲቄን ምንነት ካልተነገረው በቀር ሊያውቅ አይችልም። ሲቄን ከልጅነት እስከ እውቀቱ በሚያውቅ ማኅበረሰብ ግን በአንጻሩ ሰላም፣ መታዘዝና መከባበር በሲቄዋ ላይ ይታየዋል።

በአዲስ ማለዳ የሲቄ አምድም እንዲህ ባለ መንገድ፣ ለሚቀበል፣ ተረድቶ ሊተረጉም ለሚችለው ሁሉ ሐሳቦች ሲተላለፉ ነበር። ምን ያህል ተጽእኖ መፍጠር እንደተቻለ፣ ምን ያህል ጥያቄን በልቦና ፈጥሮ ወደ መመራመር የሚያቀርብ ሐሳብ ተገኝቶ እንደሆነ ለማወቅ ጥናት ሳያስፈልግ አይቀርም። ከዛ ባለፈ ግን በወፍ በረር ልንቃኘው የምንችል ገሀድ መልክ አለው።

በእርግጥ የተለያዩና በርካታ፣ ወቅታዊና የኖሩ ሐሳቦች ተነስተዋል፤ በሲቄ አምድ። ግን ሐሳብ አቅራቢዎች በብዝኀነት አልታዩም። ስለሴቶች ጉዳይ መገናኛ ብዙኀን በቂ ሽፋን አይሰጡም ወይስ ይሰጣሉ የሚለው በሙግት ላይ ሆኖ እያለ፣ ያለውን አውድ መጠቀም ግን በብዛት አይታይም።

ነገሩን ከዚህ አምድ አንጻረ ብቻ በማየት አይደለም ይህ ነጥብ የተነሳው። በበርካታ መገናኛ ብዙኀን ያሉ በጉዳዩ የሚሠሩ ባለሞያዎችም ‹አስተያየት ስጡን› ብለው ሲጠይቁ የሚሰጣቸው ደጅ እንደሚያስጠናቸው፣ ‹ሐሳባችሁን በጽሑፍ አካፍሉን› ብለው ሲጠይቁም እንካችሁ የሚል እንደሌለ ይናገራሉ። በአንጻሩ ግን ለውጥ እንዲመጣ ይፈልጋሉ፣ ድምጽ የሚሆነን አጣን የሚሉ ይሰማሉ።

እንዲህ በማለት ሁሉንም መውቀስ እንደማይቻል ግልጽ ነው። ብዙ ሥራ አጥ ባለበት አገር ሠራተኛ አጣሁ የሚል አሠሪ እንደሚገኝ ሁሉ፣ ምንአልባት ሐሳቡን ሊያስተላልፍ፣ ሊናገር ወይም ሊጽፍ የሚፈልግ ሰው እና አውዱን የፈጠረው አካል አልገናኝ ብለው ይሆናል።

የውሃ ጠብታ በዘመናት ሂደት ድንጋይን ትሰብራለች። ዓለም ዛሬ ያላትን መልክ የያዘችው በአንድ ጀንበር አይደለም፣ በብዙ እልፍ ዓመታት ነው። ዛሬ ያለንበት ጥሩም ሆነ አስከፊ ኹነት በጊዜ ውስጥ፣ በአዝጋሚ ሂደት አልፎ የደረሰ ነው። እናም በሴቶች ጉዳይ እውነት ለውጥ ለማምጣት የሚፈልጉ ሰዎችም የትኛውንም አምድ ሊንቁ፣ ቸል ሊሉ አይገባም።

በብዙ ቁምነገር የሚጠበቁ ሰዎች በማኅበራዊ ድረ ገጽ ላይ የሆነ ያልሆነውን በመጻፍ፣ በመነቋቆር፣ የእልህ መልስ በመሰጣጠት፣ በመሰዳደብ ሲባክኑ እያየን ነው። በዛ መልክ በየሳምንቱ በሚፈጠርለት አዲስ አጀንዳ ያለፈውን አጀንዳ እርግፍ አድርጎ በሚረሳ ትውልድ መካከል ላለመረሳት ጥረት ማድረግ ይቻል ይሆናል። በትክክል ለውጥ ማምጣት ግን የሚቻል አይመስለኝም።

ደግሞም ያንንም አውድ በአግባቡ የሚጠቀሙ እንዳሉ ግልጽ ነው። በተለይ በሴቶች ሥም የሚሠሩ፣ ስለሴቶች ቆመናል የሚሉና ስለሴቶች እንደሚሟገቱ የሚናገሩ ሰዎች፣ ጥቂት ጊዜ ወስደውና ሰጥተው ሐሳባቸውን ለማካፈል ፈቃደኛ ካልሆኑ መልካም አይደለም። በፖለቲካው ካሉ ሰዎች ወኔ ቅንጣቱን የሚያህል የጽናት ምልክት ካልታየባቸውም እንደዛው።

አዲስ ማለዳ ሌላ ብዙ መቶ እትሞችን ወደፊት ልትገሰግስ አልማለች፤ ጥሪዋም አብረን እንጓዝ የሚል ነው። እናም አብረን እንጓዝ!

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com