በመረጃ የመጥለቅለቅ አደጋን በኃላፊነትና በተዓማኒነት መጋፈጥ

Views: 62

ከመንግሥትና ከሕዝብ መካከል ሆኖ እንደ ዐይን ደግሞም እንደ ጆሮ የሚያገለግለው የብዙኀን መገናኛ እንዲሁም የጋዜጠኝነት ሙያ ከፍተኛ አጣብቂኝ ውስጥ ተገኝቷል። እንደውም የሚፈተንበት ጊዜ ሳይሆን አይቀርም። ምክንያቱ ደግሞ ሁሉም ያሻውን በአጭር ፍጥነት ለብዙዎች ማድረስ የሚችልበት አውድ በተፈጠረበት ዘመን፣ ሚዛናዊና ትክክለኛ የሆነውን ነገር አጥርቶ ማቅረብ ወሳኙ ሥራ ነውና። ይህንን ነጥብ አጥብቀው ያነሱት አብርሐም ፀሐዬ፣ የጋዜጠኝነት ሙያዊ ግዴታን መወጣት ከመቼውም በላይ የሚያስፈልግበት ጊዜ አሁን ነው ይላሉ።

የሰው ልጆች አግባብ ባለው የአኗኗር ስርዓት የሚኖሩ ሥልጡን እንሰሳት ይባላሉ። በተነጻጻሪነት ነጻና ግብረ ገብ ያላቸው ፍጡራንም ናቸው። የሰዎች ነጻነት ሌላውን ሰው ለጉዳት እስካልዳረገ ድረስ የተዘረጋ ኬላ አልባ ተጓዥ ነው። ሰዎች ለሚሠሩትና ለሚናገሩት ነጻ ናቸው። አስተሳሰባቸውን መሬት የማውረድ ነጻነትን የተጎናጸፉ በመሆናቸው የቱንም የማድረግና የማሰብ ፍላጎታቸው የተጠበቀ ነው።

በዚህም የተነሳ ዓለም በጊዜው ሂደት ውስጥ በመሻሻል ወይም በለውጥ ውስጥ እንድታልፍ ምክንያት ሆኗል። ሰዎች የአፈጣጠር ነጻነታቸውን ተጠቅመው የተሻለ አኗኗር ለማግኘት በሚደረገው ጥረት ውስጥ አድካሚ ሥራዎችን የሚያቀሉ ቴክኖሎጂዎችን በመፈልሰፍና በእነርሱ በመጠቀም ከቀደሙት ዘመናት አንጻር ይኸኛው ጊዜ ተመራጭ እንዲሆን አስችለዋል፤ የወደፊቱም የበለጠ ይሆናል። በዚህ ሂደት ውስጥ ግኝቶችን ለማሰራጨት፣ በተቃራኒው ደግሞ ለሰው ልጆች ስጋት የሆኑትን ለማሳወቅ እንዲቻል መረጃዎችን የማስተላለፍ ሥራ እንደዋና ተግባር በመታየቱ በሰዎች መካከል ተግባቦት ሊያድግ ችሏል።

ይህም አንዱ ጋር ያለው ሌላው ጋር እንዲገኝ ጠቅሟል፤ የአንዱ ሃብት ለሌኛው ግብዓት ሆኗል። ቋንቋ፣ ርዕዮተ ዓለም፣ ባህል፣ ሐይማኖት ተወራርሰዋል። ግንኙነት እጅግ አስፈላጊ በመሆኑ መረጃ እንደ ትልቅ ሀብት በመቆጠሩ የመረጃ ዘመን (Information Era) ተብሎ እስከመሰየም ተደርሷል። በዚህም ምክንያት የብዙኀን መገናኛዎች ተወልደዋል።

እነዚህ ተቋማት የማኅበረሰቡ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ጉዳዮች ዋና የጀርባ አጥንት ሆነው ብቅ ብለዋል። ጋዜጠኝነቱም ዋና ዘዋሪ በመሆን እንደሌሎቹ ሙያዎች ሁሉ መደብ አግኝቶ እያገለገለ ነው። ጋዜጠኝነት በአጭር ጊዜ ውስጥ ተጽእኖ በመፍጠር ሕዝብና መንግሥት መካከል የቆመ ከፍተኛ ባለድርሻ አካል ሆኖ እየታየ ያለ ነው። ኃይል ያላቸው መንግሥታት ከተቻላቸው እንዲጠቅማቸው ሲሉ ይቀርቡታል፤ በቻሉት ሁሉ ሊጠቀሙበት የሚሹት ዘርፍ ነው። በገንዘብ የተጠናከሩት ደግሞ አጥብቀው ይፈልጉታል፤ እስከተቻላቸው ድረስ ግን ይሸሹታል። ጉልበተኞች አስፈራርተው ያስቆሙታል።

ጋዜጠኝነት በመፈራትና በመከበር እንደየ አገሩ የፖለቲካ ባህል ሲሳደድ፣ ሲከበርና ሲፈራ እየኖረ ያለ ግዙፍ ዘርፍ ሲሆን፣ የገዳዮችን ዱካ በማጥፋት ጋዜጠኞችን መግደል በየጊዜው እየታየ ያለ ጥሬ ሐቅ ነው። ዓለም ነገሯ ውስብስብ እየሆነ በመጣ ቁጥር የኃይል ተቀናቃኝና ተወዳዳሪ ኃይላት በየቦታው ይታያሉ። እነዚህ አካላት ያለመገናኛ ብዙኀን ድጋፍ የትም እንደማይደርሱ በማመን በጥቅምና በማስፈራራት የብዙኀን መገናኛውን ለመጠቀም ይፈልጋሉ። ሐሰትና ሐሰተኞች በበዙባት ዓለም ተዓማኒነትን፣ ኃላፊነትንና ሰብዓዊነትን ግድ የሚለው የብዙኀን መገናኛ ለመኖር ይቸገራል። ጋዜጠኝነት እስከዛሬም ፈተና ላይ ነው።

ሰዎች በነጻነት እንዲኖሩ ማድረግ የሚቻለው የተሻለ አስተሳሰብና ተግባቦት (communication) መፍጠር ሲቻል ነው። ጋዜጠኝነቱ ይህንን ጉዳይ በግልና በተቋም ደረጃ ይከውናል። የአስተዳደር ብልሹነትን በመጠቆምና በማጋለጥ የተሻሉ ስፍራዎች ሰፊ ቦታ እንዲያገኙ ማድረግ የጋዜጠኝነት ዓላማ ነው። አንድ ጋዜጠኛ ለሚያቀርበው መረጃ የአቅራቢውን ፍላጎት ተንተርሶ አይደለም። ሚዛኑን እስካልሳተ ድረስ ዜናዎች ይሠራሉ፤ የሕዝቡን ፍላጎት ባማከለ ከሥልጣንና ከገንዘብ ጫና ውጪ ሆኖ ተዓማኒ ዜና መሥራት ግዴታ ነው። ጋዜጠኝነት እውነት የሆኑትን ክስተቶች ትክክለኛነታቸውን በማጣራት ይፋ የማድረግ ሙያዊ ግዴታ አለበት። ለዚህም ነው ፈተናው የሚበዛው!

ጋዜጠኝነት ከኃላፊነትና ከተዓማኒነት አንጻር

ጋዜጠኝነት ኃላፊነት ነው። በአንድ አገር ዴሞክራሲን ለማስፈን ከተፈለገ ገለልተኛ (independent) ሙያውን የጠበቀና (professional) ኃላፊነት የሚሰማው (responsible) ጋዜጠኛና ጋዜጠኝነት ሊኖር ግድ ነው።

ጋዜጠኝነት መረጃ መስጠት፣ ተፈላጊ ጉዳዮችን በመምረጥ መወያያ እንዲሆኑ ማኅበረሰብ ላይ ንቃት የመፍጠርና ክፍተቶች ሲኖሩ ትችቶችን በማቅረብ የሚሠራ ሙያ ነው።

በአንድ አገር ላይ እንደወሲባዊ ጥቃቶች፣ የሕጻናት ጉልበት ብዝበዛ፣ ለሥራ ተብለው በሚቀርቡ ኬሚካሎች የሚጎዱ ሰዎችን የመሳሰሉ ጉዳቶችን መፈተሽና ይፋ ማድረግ ጋዜጠኝነት መሥራት ከሚገባው ሥራዎች መካከል ከቀዳሚዎቹ ተርታ የሚመደቡ ናቸው። ጋዜጠኝነት የተነገረውን ወይም የቀረበለትን ብቻ ለማስተላለፍ የሚሠራ ሙያ አይደለም።

ማርክ ትዌይን እንደሚለው ‹የሕዝብ ትልቁ ችግርና ቅሽምና ጋዜጣ ላይ የወጣን ጉዳይ ሁሉ ማመኑ ላይ ነው።› ይላል። ጋዜጠኝነት ከተሳሳተ ሕዝብ ይሳሳታል። የስህተቱ ውጤት ደግሞ መጨረሻ ላይ የሚያመጣው ጉዳት ይኖራል። የተሸፋፈነ ወይም የተደበቀ ነገር ደግሞ ቀርቶ አይቀርምና ነገሮችን በይፋ በማውጣት የሕዝቡን የማወቅ፣ የመወያየትና መፍትሄው ላይ ተሳታፊ የማድረግ ሥራ እንዲተገበር ማድረግ ጠቀሜታው ላቅ ያለ ነው። ይህ ዓይነት አሰራር እንዲበረታታ በማድረግ በአንድ አገር ላይ ከላይ እስከታች ግልጽ አሰራር እንዲሰፍን ማገዝ ይቻላል። የጋዜጠኝነትም ዋንኛው ኃላፊነት ይህ ነው።

ጋዜጠኝነት ተዓማኒነት በእጅጉ የሚጠበቅበት ዘርፍ ነው። የተከሰተን ማንኛውም ጥሬ ሃቅ እንደወረደ ከማቅረብ ወይም ከማስተላለፍ ይልቅ እውነትነቱንና አግባብነቱን ግራና ቀኝ የመፈተሽ፣ ጠለቅ ብሎ በማየትና ዙሪያ ገባውን በመበርበር መነሻና መድረሻውን የማየትና የመገመት ላቅ ያለ ሥራና ዕይታን የሚሻ ሙያ ነው።

ሕዝብ ነገሮችን ወይም ክስተቶችን ከተለያየ አቅጣጫ ማየት እንዲችል መረጃዎችን የመስጠት ብቃት ይጠበቃል። ዓለም እጅግ ውስብስብ ክዋኔዎች የበዙባት ሆናለች። ለሕዝቡ ደግሞ በዚህ ልክ የሚከታተል ጋዜጠኝነት ወይም ብዙኀን መገናኛዎች በኃላፊነትና በተዓማኒነት ካልተሰማሩ በስተቀር ሕዝብ አስተማማኝ መረጃ የማግኘትና በዚህ ላይ ተመስርቶ ትክክለኛ ድምዳሜ ላይ መድረስ ያዳግተዋል።

ተዓማኒነት ሲባልም ነገሮችን በአሉባልታ ሰምቶ ያለማረጋገጫ ለመረጃነት በማብቃትና ከሚገባው በላይ በማጦዝ የጋዜጣ ማሻሻጫ ማድረግ አይደለም። መገናኛ ብዙኀን ተዓማኒነት መፍጠር ይገባቸዋል ሲባል እውነተኛ መረጃዎች ቢሆኑ እንኳን ከሕግ አንጻር ባለማየት ወይም የሚመጣውን አሉታዊ ውጤት ባለመገንዘብ የተሰማና የታየን ጉዳይ ሁሉ ለሚዲያ ፍጆታ በማዋል ተጨማሪ ስህተት ላለመፍጠር መጠንቀቅም ነው።

መረጃዎች የግለሰቦችን ሰብዓዊ መብት በመጣስ የሚሰበሰቡም አይደሉም። ከዚህ በፊት እንግሊዝ ውስጥ ከ168 ዓመታት ቆይታ በኋላ የተዘጋ ጋዜጣን ካስታወስን የታዋቂ ሰዎችና የባለሥልጣናትን ስልኮች በመጥለፍ መረጃዎችን በሕገ ወጥ መንገድ ጥሶ እየመነተፈ ይፋ ሲያደርግ ሊደረስበት በመቻሉ ነው። በአጠቃላይ ጋዜጠኝነት ኃላፊነትንና ተጠያቂነትን ተሸክሞ የሚጓዝ ጥንቃቄን የሚጠይቅ ዘርፈ ብዙ ሙያ ነው። ለዚህ ዓይነት ጥልቅ ዕይታና የማመዛዘን ብቃት ለሚጠይቅ ሥራ ደግሞ ትልቅ አቅም ያለው ጋዜጠኛና ብቃት ያለው በሙያ የተደራጀ የመገናኛ ብዙኀን ያስፈልጋል።

ለመደምደም ያህል ቀደም ባለ ጊዜ አንድ የእንግሊዝ ፖለቲከኛ ያሉትን ጠቅሰን እንለፍ። ‹ፖለቲከኞች ወይም ባለሥልጣናት በብዙኀን መገናኛ ላይ ፍራቻ ካላቸው፣ አንድ የመርከብ ካፒቴንም የገዛ መጓጓዣ ባህሩን እንደፈራው ይቆጠራል።› (“…for a politician to complain about the press is like a ship’s captain complaining about the sea.”) ይህም ሲባል ካፒቴኑ የሆነ በራሱ ያልተማመነው ነገር አለ ማለት ነው። በትክክል እየሠራሁ ነው የሚል ሰውም የብዙኀን መገናኛን አይፈራም።

 የመረጃ መጥለቅለቅ

የዚህ የጊዜያችን ተግዳሮት ማኅበረሰብ በመረጃ መጥለቅለቅ እየተጎዳ መምጣቱ ነው። የቱ ትክክል የትኛው የተሳሳተ መሆኑን ለመለየት በማይችልበት አደጋ ውስጥ ይገኛል። መረጃዎች የፖለቲካና የምጣኔ ሃብት አሻጥር ተሸክመው ከእውነተኛው መረጃ ጋር ተደባልቀው ወደ ሕዝቡ ይረጫሉ። ጥቅምን ለማስጠበቅና ሥልጣንን ለማረጋገጥ ሲባል የተሸራረፉ መረጃዎች በብዙኀን መገናኛ በኩል ከላይ ወደታች ይፈሳሉ።

ለዚህ ነው ጋዜጠኝነት በጥቅም ፈላጊዎች ምክንያት ለሕዝብ ሐቅን የማስተላለፍ ተግባሩ አጣብቂኝ ውስጥ እየወደቀ ያለው። የግለሰቦችና የአገራት ሀብት የማፍራት ገደብ የለሽ ፍላጎት የተመጣጠነ የሀብት ክፍፍል እንዳይኖር አድርጎታል። ተናጥቀህ ብላ በዓለማችን ሰፍኗል። በዚህ መካከል ሰብዓዊነትና የማኅበረሰብ እሴቶች እየተሸረሸሩ ነው።

ፖለቲካዊና ምጣኔ ሀብታችሁን እናስከብርላችኋለን በሚል የቡድን መሪዎች እየተፈለፈሉ ነው። ዘረኛ፣ አክራሪና ዋሾ መንግሥታት ቦታ እያገኙ መጥተዋል። እውነቱ ግን ሌላ ነውና ይህ ዓይነት አስተሳሰብ አገር አፍርሷል፤ ለእልቂት ዳርጓል። የተለያየ ፍላጎትና መልክን ይዞ አንድ የመሆን ብዝኀነት (Diversity) እየቀጨጨ በመሆኑ በተለይም አፍሪካ የመለያየትና የመነቋቆር እንዲሁም የመገዳደል አደጋ ውስጥ ሆናለች። በዚህም ብዙ ንጹሃንን አጥታለች፤ እያጣችም ነው። ዓለም በቀለም፣ በዘር፣ በአካባቢና በቋንቋ መከፋፈል ውስጥ እየገባች በሄደች ቁጥር የተፈጥሮ ሀብትን የመቀራመት፣ በዚህም ስግብግብነት የሚፈጥረው ግጭት ለአደጋ ይዳርጋል።

ከመረጃና መገናኛ ብዙኀን ሥራ ጋር ተያይዞ በርካታ ምሁራን ጋዜጠኞችንና ሕዝብን ይመክራሉ። በአብዛኛው በመረጃ ደረጃ የሚሰሙ የአናሳ ቡድን መሪዎች፣ የየአገራት መሪዎች፣ እንዲሁም ከነዚህ ጋር የጎንዮሽ ጥቅም ያላቸው ታዋቂና አዋቂ ሰዎች ትርክት ፖለቲካዊ ተዓማኒነትን በመፍጠር ላይ የተመሠረተ ነው። በጊዜያዊነት የሥልጣን መንበራቸውን ለማጠናከር፤ ያቀዱትን የጥቂት ቡድኖችን ተጠቃሚነት ለማስፈን፣ እንደ እቅድ የያዙትን የጥቂት ቡድኖችን የበላይነት ለማስጠበቅ፣ በአብሮ መሆን ውስጥ ያጡትን ጥቅም በመነጠል ለማግኘት ሲሉ የታላቅነት ትርክትን ያነግሳሉ።

ቡድኖቻቸው የተለየና ያልተፈጠረ ዶሴ እንዳለ አድርገው በመግለጥ ያልተጻፈ ያነባሉ። ያልተከሰተ እንደተከሰተ በማድረግ ፍርሃትን ይወልዳሉ ወይም በተቃራኒ የተሻለ ነገ አለ በሚል ቀቢጸ ተስፋ መረጃ በማንሸራሸር ተከታዮቻቸውን ያቅፉበታል። ይህ የመረጃ መጥለቅለቅ አደጋ በወቅታዊ የፖለቲካ ትርክቶች የተሞላ ነው።

የሕዝብን ታሪክ፣ ባህላዊ እሴትና እምነት በመሸርሸር ጥርጣሬን የሚፈጥሩ አደገኛ መረጃዎች እየተፈበረኩ ነው። አሁን ላይ ጋዜጠኝነት ከምንግዜውም በላይ ያስፈልጋል። ያየውን እውነት መሳይ ንግግርና ኹነት ዙሪያ ገባውን ተመልክቶ ካልፈተሸ በስተቀር ራሱም የመረጃ መጥለቅለቁን አደጋ በማባባስ ሕዝብን አቅጣጫ ያስታል። በስተመጨረሻም ማንም የማይጠቀምበት አደጋ ተከስቶ ለፈራጅም ለተፈራጅም አለመብቃት አለና በኃላፊነትና በተዓማኒነት መሥራት ሙያዊ ግዴታ ነው።

አብርሐም ፀሐዬ የተግባቦት ባለሞያና የቢዝነስ አማካሪ ሲሆኑ በኢሜይል አድራሻቸው geraramc@gmail.com ላይ ይገኛሉ

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com