የአማራ ልማት ማኅበር 3.5 ቢሊዮን ብር ዓመታዊ በጀት መያዙን አስታወቀ

Views: 58

አልማ የተጀመሩ የትምህርት መሠረተ ልማቶችን ለማጠናቀቅ፣ አዳዲስ ፕሮጀክቶችን ለማስጀመር፣ ለቴክኒክና ሙያ ፕሮጀክቶች እና ለጤናው ዘርፍ ልማት 3 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር ዓመታዊ በጀት መድቧል፡፡ ከዚህ ውስጥ ወደ 2 ቢሊዮን ብር ገደማ የሚሆነውን ለአዳዲስ የመማሪያ ክፍሎች ግንባታ ወጪ እንደሚደረግ ማኅበሩ ገልጿል፡፡

የአማራ ልማት ማኅበር በ2013  5 ሺሕ 20 መማሪያ ክፍሎች የሚኖራቸው 1 ሺህ 255 አዲስ ሕንጻዎችን ለመገንባት አቅዶ እየሠራ መሆኑን  አስታወቀ፡፡ ይህም በ2012  ተገንብተው ከተጠናቀቁት እና በተለያዩ የግንባታ ደረጃዎች ከሚገኙት በተጨማሪ የሚሠራ ነው ተብሏል፡፡ ማኅበሩ በትምህርቱ ዘርፍ በልዩ ትኩረት እየሠራ እንደሚገኝ አስታውቋል፡፡

ማኅበሩ እንዳስታወቀው በ2012 በጀት ዓመት 422 መማሪያ ክፍሎች ያሏቸው 97 የመጀመሪያ ደረጃ እና 114 ክፍሎች ያሏቸው 25 የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የመማሪያ ሕንጻዎች ተገንብተው ተጠናቅቀዋል፡፡ 1 ሺህ 60 የመማሪያ ክፍሎች ያሏቸው 265 የአንደኛ ደረጃ እና 122 የመማሪያ ክፍሎች ያሏቸው 29 የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ሕንጻዎች ደግሞ በተለያዩ የአፈጻጸም ደረጃ ላይ ይገኛሉ፡፡ ከእነዚህ መካከል ወደ 80 በመቶ የሚሆኑት በመጠናቀቅ ሂደት ላይ መሆናቸውንና የመጀመሪያው ወሰነ ትምህርት ከመጠናቀቁ በፊት ለመጨረስ እየተሠራ መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡ ለዚህም ወረዳዎች ተጨማሪ ሀብት ማፈላለግ በሚችሉበት ሁኔታ ጉባኤ እየተካሄደ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ ጥሩ መግባባት ላይ እየተደረሰ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

የአማራ ክልል ትምህርት ቤቶች የጥራት ደረጃቸው ዝቅተኛ ነው፡፡ የተማሪ እና የመማሪያ ክፍል ጥምርታውም ከደረጃ በታች ነው፡፡ አልማ በሦስት ዓመታት ውስጥ የጥራት ደረጃ ያሟሉ ትምህርት ቤቶችን ከ16 በመቶ ወደ 50 በመቶ ማሳደግ የሚያስችል ስትራቴጂያዊ እቅድ አውጥቶ እየሠራ ይገኛል፡፡ ለዚህም የነባር ትምህርት ቤቶችን ደረጃ ማሻሻል እና ምንም በሌለባቸው አካባቢዎች አዳዲስ ትምህርት ቤቶችን ለመገንባት ተግባራዊ እንቅስቃሴ ጀምሯል፡፡ ማኅበረሰቡ የችግሩን መጠን በሚገባ በመረዳት የራሱን ችግር በራሱ አቅም ለመሸፈን በሚደረገው ጥረት ተሳታፊ እንዲሆንም ጥሪ ቀርቧል፡፡

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com