ሀብታቸውን ያላስመዘገቡ 184 ባለስልጣናት ምርመራ እንዲቋረጥ ተደረገ

Views: 513

ጠቅላይ አቃቢ ሕግ ከዚህ ቀደም ሀብታቸውን ለማስመዝገብ ፈቃደኛ ሳይሆኑ በመቅረታቸው ምርመራ እንዲደረግባቸው ለምርመራ ተላልፈውለት የነበሩ 184 ባለስልጣናት  ምርመራ እና ክሳቸው እንዲቀር አዘዘ፡፡

የፌደራል ስነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ሀብታቸውን ለማስመዝገብ በተደጋጋሚ ቢጠየቁም ፈቃደኛ ሳይሆኑ በመቅረታቸው ለፌደራል ጠቅላይ አቃቢ ሕግ እና ለፌደራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ስም ዝርዝራቸው ተላልፎ የነበሩ 184 ባለስልጣናትን ምርምራ እና ክስ ሳይመሰረትባቸው ሀብታቸውን በቅጣት እንዲያስመዘግቡ ጠቅላይ አቃቢ ህግ ለኮሚሽኑ ደብዳቤ መላኩን የኮሚሽኑ የሀብት ምዝገባና ማሳወቅ ዳይሬክተር መስፍን በላይነህ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል፡፡

የኮሚሽኑ የሀብት ምዝገባና ማሳወቅ ዳይሬክተሩ መስፍን ለአዲስ ማለዳ አንደገለጹት ጠቅላይ አቃቢ ሕግ ለኮሚሽኑ የባለስልጣናቶቹ ምርመራና ክስ እንዲቋረጥ እና በቅጣት ሀብታቸወን እንዲያስመዘግቡ የጠየቀው ለህዝብሲባል ነው የሚል መልዕክት በደብዳቤው ላይ መካተቱን ጠቁመዋል፡፡

የፌደራል የሥነምግባር እና የፀረሙስና ኮሚሽን ሀብታቸውን ለማስመዝገብ ፈቃደኛ ያልሆኑ 184 ከፍተኛ የመንግስት ባለሥልጣናት ጉዳያቸው በምርመራ እንዲጣራ እና ክስ እንዲመሠረት ነሐሴ 20/2012 ስም ዝርዝራቸውን ለኢ.ፌ.ዴ.ሪ ጠቅላይ ዓቃቤ እና ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን መላኩን አዲስ ማለዳ መዘገቧ ይታወሳል፡፡ ይሁን አንጅ ጠቅላይ አቃቢ ሕግ የ 184 ባለስልጣናትን የሀብትም ምዝገባና የገቢ ምንጭ ማሳወቅ ህግ በመተላለፋቸው ክስ መመስረትና ማሰር በመንግስት ላይ ኪሳራ ያስከትላል በማለት ለኮሚሽኑ ደብዳቤ መላኩን አዲስ ማለዳ አረጋግጣለች፡፡

በዚሁ መሰረት ጠቅላይ አቃቢ ህግ ለኮሚሽኑ በላከው ደብዳቤ ባለስልጣናቱ የሀብት ምዝገባ አዋጁ በሚፈቅደው አሰራር መሰረት 1000 ብር ተቀጥተው በአምስት ቀናት ውስጥ ሀብታቸውን እና የገቢ ምንጫቸወን አንዲያሳውቁ በደብዳቡው ገልጿል፡፡ አቃቢ ህግ ለኮሚሽኑ በላከው ደብዳቤ ባለስልጣናቱ ከጥቅምት 1/2013 አ\ እስከ ጥቅምት 6/2013 ድረስ በራሳቸው ፈቃድ ሀብታቸውን እና የገቢ ምንጫቸወን ለኮሚሽኑ አንዳሳውቁ ቀነ ገደብ ያስቀመጠ ሲሆን ይህ የመጨረሻ እድል መሆኑ ተገልጿል፡፡

ጠቅላይ አቃቢ ህግ ለኮሚሽኑ በላከው ደብዳቤ ላይ በተጠቀሰው የሀብት ማስመዝገብ እና የገቢ ምንጭ ማሳወቅ ቀነ ገደብ የማያስመዘግቡ ከሆነ ጠቅላይ አቃቢ ህግ በባለስልጣቱ ላይ ምርመራ እንደሚደርግ እና ክስ እንደሚመሰርት ገልጿል፡፡ አቃቢ ሕግ በደብዳቡው ላይ እንዳሰፈረው የመንግስት ባለስልጣናት ኮሚሽኑ ሀብታቸወንና የገቢ ምንጫቸወን እንዳስመዘግቡ በተደጋጋሚ በመገናኛ ብዙሀን ማስታቂያ ቢነገሩም በወቅቱ ለማስመዝገብ ፈቃገኛ ባለመሆናቸው እና የተጣለባቸወን ግደታ በአግባቡ ስላልተወጡ አግባብ ባለው ህግ መሰረት ጉዳያቸው ተጣርቶ ህጋዊ እርምጃ እንድወሰድ የተመራለት መሆንኑ ገለጿል፡፡

በአዋጅ ቁጥር 668/2012 መንግስት ባለስልጣነቱ ሀብታቸውን የማስመዝገብና የገቢ ምንጫቸውን የማሳወቅ ግደታ እንደሚጥል የጠቀሰው አቃቢ ህግ አሁን ባለው ሁኔታ በ184ቱ ባለስልጣት ላይ ምርመራ በማካሄድ ለህግ ማቅረብ በመንግስት ስራ ላይ የሚፈጥረው ጫና የመንግስትን ስራ የሚጎዳ መሆኑ ስለታመነበት ለአመራሮቹ አንድ የመጨረሻ እድል ተሰጥቷቸው በቅጣት ሀብታቸውን እንዳስመዘግቡ ትእዛዝ ሰጥቷል፡፡

የኮሚሽኑ የሀብት ምዝገባ ዳይሬክተር ለአዲስ ማለዳ እንደገለጹት በመንግስት ተቋማት በኩል የሚፈጸሙ የሙስና ወንጀሎችን ለመከላከል ከትንሽ እስከ ትልቅ የህግ አስራሮች እኩል መተግበር እንደሚገባቸው አሳስበዋል፡፡ ዳይሬክተሩ አክለውም በየደረጃው የሚፈጸሙ የመንግስት ሀብት ምዝበራን ለመከላከል ሁነኛው የመከላከያ ዘዴ በየደረጃው ያሉ የመንግስት ባለስልጣናትንና አመራሮችን ህግ በሚጥሱበት ጊዜ በእኩል አይን ተጠያቂ ማድረግ ነው ብለዋል፡፡

አዲስ ማለዳ የባለስልጣናቱን ክስ መቋረጥ ተከትሎ ውሳኔውን ለኮሚሽኑ ያሳወቀውን ፌደራል ጠቅላይ አቃቢ ህግ ተጠማሪ ማብራሪያ ለማግኘት በተደጋጋሚ ብትደውልም የሚመለከታቸው አካላት ስብሰባ ላይ ናቸው በማለታቸው ሊሳካ አልቻለም፡፡

 

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com