የስራ አጥ ቁጥርን በቀላሉ ማወቅ የሚያስችል ዲጅታል ስርዓት ሊዘረጋ ነው

Views: 86

የሠራተኛ እና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር እና የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ሰራተኛ እ ማህበራዊ ዘርፍን ዘመናዊ በማድረግ አሰሪ እና የሰራተኛን እና የስራ አጥ ቁጥርን በቀላሉ ማወቅ የሚያስችል እንቅስቃሴን ‹‹ዲጂታላይዝ››ለማድረግ ስራ መጀመሩ ተገለፀ፡፡

በሚኒስቴር መስርያ ቤቱ ያለውን መረጃ ግልፅ ለማድረግ እና ስራን የተቀላጠፈ የሚያደርግ፣ ሙሉ መረጃን በቀላሉ ለማግኘት የሚያስችል እና ሙሉ እንቅስቃሴውን በቴክኖሎጂ ለማገዝ የሰራተኛ እና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ከሳይንስ እና ኢኖቬሽን ጋር መፈራረሙን የዲጂታል እና ትራንስፎርሜሽን ፕሮግራም ጀነራል ዳይሬክተር አብዮት ባዩ (ዶ/ር) ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል፡፡

ቴክኖሎጂው በአገር ውስጥ የሚገኘውን የሠራተኛ ኃይል ክፍት የስራ ቦታዎች ብዛት፣ የስራ እና የስራ አጥ መረጃ ፣ እጅግ ተፈላጊ የስራ መደቦች እና ክህሎቶችን ዓይነት የያዘ የስራ ገበያ መረጃ እንዲኖር የሚያስችል ሲሆን የአገሪቱን የሥራ ገበያን ተወዳዳሪነት የሚጨምር ቴክኖሎጂ እንደሆን በስምምነቱ ተገልጻል፡፡

ስርዓቱን በዘመናዊ መንገድ የማስተካከሉ ስራ የተጀመረው ከሁለት ወራት በፊት እንደሆነ የተናገሩት የዲጂታል እና ትራንስፎርሜሽን ፕሮግራም ጀነራል ዳይሬክተር ዶ/ር አብዮት ባዩ ከአጭር ጊዜ ፕሮግራም ውስጥ በመካተቱ ምክንያት በአንድ አመት ከስድስት ወራት ባነሰ ጊዜ ውስጥ ተጠናቆ ወደ ስራ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

እርሳቸው እንዳሉት በ18 ወራት እንዲጠናቀቁ ተብለው የሚያዙ ፕሮጀክቶች የአጭር ጊዜ ምድብ እንደመሆናቸው ይሄም በአጭር ጊዜ ፕሮግራም ውስጥ ነው የተካተተው በማለት ለአዲስ ማለዳ
ተናግረዋል፡፡

ከዚህም ባለፈ የመረጃ አያያዝ ስርዓቱን ወደ ዘመናዊነት ለማሳደግ በሚሰራው ስራ ውስጥ ለቴክኖሎጂ እና ኢኖቬሽን ሚንስትር የሚከፈል ምንም ዓይነት የአገልግሎት ክፍያ እንደሌለ እና
ምን አልባት ከፍተኛ ወጪ ቢያስፈልግ እንኳን በጋራ በመሆን ሀብት በማሰባሰብ የሚሸፍን እንደሆነ የሰራተኛ እና መሃበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር አማካሪ የሆኑት ዳንኤል ሽታዬ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል፡፡

ስርዓቱ ተግባራዊ ሲሆን የግል እና የመንግስት ተቋማት እንደሚካተት የገለፁት አብዮት(ዶ/ር) ከወረዳ ጀምሮ ያለው የስራ አጥ ቁጥር በእድሜ ከፋፍሎ፣ ምን ያህል ሰራተኛ እንዳለ በየእድሜ
ክልል፣የሚያስቀምጥ ሲሆን ከዚም ባለፈ ምን ያህል የግል እና የመንግስት ድርጅቶች እንዳሉ በማካተት በስራ ዘርፋቸው በመለየት የሚቀመጥበትን አሰራር እንደሚይዝ ታውቋል፡፡

ይህም ሰራተኛን እና አሰሪውን በቀላል መንገድ ለማገናኘት ፍቱን ይሆናል ብለዋል፡፡ ከዛም በተጨማሪ በአሁኑ ሰዓት አነስተኛ እና ቀላል ቁጥር ያላቸውን የስራ ዘርፎች ምናልባት ከጊዜ በኋላ የሰራተኛ እና የስራ ዘርፉን የሚፈለጉ ሰዎች ሊበዙ ስለሚችሉ ያንን ለመቆጣጠር የሚያስችል ስርዓት ለመዘርጋት ይጠቅማል ተብሎ መታሰቡንም ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል፡፡

በተያያዘ ስራ ፈላጊዎች እና ቀጣሪዎች የሚሳተፉበት እንደመሆኑ መጠን፤ የሥራ ቅጥር ሲወጣ ወይንም ሥራ ፈላጊዎች በምን ዘርፍ እንደሚፈልጉ አንድ ቋት ማግኘት ስለሚቻል ድካምን እንደሚያቀልም የዲጂታል እና ትራንስፎርሜሽን ፕሮግራም ጀነራል ዳይሬክተር ዶ/ር አብዮት ባዩ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል፡፡

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com