በአዲስ አበባ ወላጆች የትምህርት ቤት ክፍያ በባንክ አንዲከፍሉ እየተገደዱ ነው

Views: 44

በአዲስ አበባ የግል ትምህርት ቤቶች ልጆቻቸውን የሚያስተምሩ ወላጆች የትምህርት ቤት ክፍያ በባንክ እንዲከፍሉ እየተገደዱ መሆኑን ገለጹ።

በአዲስ አበባ ልጆቻቸውን በግል ትምህርት ቤት የሚያስተምሩ ወላጆች ለትምህርት ቤቶች ክፍያ የግድ በባንክ መክፈል አለባችሁ በመባላቸው ሁሉንም ማህበረሰብ ያላገናዘበ እና በአንድ ጊዜ ወደ ባንክ ክፍያ ስርዓት ግቡ ማለቱ ተገቢ አለመሆኑን ይገልጻሉ። አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው ወላጆች ከዚህ በፊት የተማሪዎች ክፍያ በባንክ መክፈል የሚችል ብቻ በፍቃደኝነት ይከፍል እንደነበር ተናግረዋል።

ለአዲስ ማለዳ አስተያየታቸውን የሰጡ ሥማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ ወላጅ እንደሚሉት፣ ዛሬ ላይ ስምንተኛ ክፍል የደረሰውን ልጃቸውን ሲያስተምሩ ከዚህ በፊት ክፍያ የሚከፍሉት በጥሬ ገንዘብ እንደነበር ጠቁመዋል። አዲስ ተግባራዊ እየተደረገ በሚገኘው የባንክ ክፍያ ስርዓት እንዲከፍሉ መገደዳቸውን ጠቁመዋል።

በቅርቡ ከብር ኖት ቅየራው ጋር በተያያዘ አንድ ግለሰብ ወደ አንድ የባንክ ሒሳብ ቁጥር ገንዘብ ለማስተላለፍ ሲሞክር በቅድሚያ በባንኩ ውስጥ የባንክ ሒሳብ ቁጥር በመክፈት እና ከተከፈተው አካውንት ወደ ሌላ አካውንት ማስተላለፍ ብቻ እንደሚችል መመሪያ በመውጣቱ የልጆችን ምዝገባ ክፍያ ሒደትን እንዳንጓተተው እና ወላጆችንም ለድካም እንደዳረገ ለአዲስ ማለዳ አስተያየታቸውን የሰጡ ግለሰቦች ጠቁመዋል።

ከዚህ በፊት የትምህርት ቤት ክፍያ በጥሬ ገንዘብ የሚከፍሉ ወላጆች እንደሚሉት፣ በጥሬ ገንዘብ ሲከፍሉ የክፍያ ሂደቱ በአንድ ጊዜ እንደሚጠናቀቅ ገልጸዋል። ነገር ግን አሁን ላይ በባንክ ክፍያ ስርዓት ሲከፍሉ ወደ ባንክ ሄደው ከከፈሉ በኋላ ለትምህርት ቤቶች ደረሰኝ ማቅረብ እንደሚኖርባቸው ጠቅሰዋል።

የግል ትምህርት ቤቶች በበኩላቸው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቤቶች የተማሪዎችን ክፍያ ወላጆች በባንክ የክፍያ ስርዓት እንድናስከፍል ተገደናል ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል። በመሆኑም ሁሉም የተማሪ ወላጆች ትምህርት ቤት ክፍያ በባንክ መክፈል የማይችሉ በመሆናቸው ወላጆችም ትምህርት ቤቶችም መቸገራቸውን እየገለጹ ነው።

አዲስ ማለዳ በጉዳዩ ላይ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አበበ ቸርነትን አነጋግራ ልጆቻቸውን በግል ትምህርት ቤት የሚያስተምሩ ወላጆች የትምህርት ቤት ክፍያ በባንክ የክፍያ ስርዓት እንዲከፍሉ እና የግል ትምህርት ቤቶችም የተማሪ ወላጆችም ክፍያ በባንክ እንዲከፍሉ ከትምህርት ሚኒስቴር መመሪያ እንደተላለፈላቸው ገልጸዋል።

የግል ትምህርት ቤቶች የተማሪዎች ክፍያ በባንክ የክፍያ ስርዓት ተግባራዊ የተደረገው ቢሮው ከወረዳ እስከ ከፍተኛ አመራር ድረስ በሚመለከታቸው አካላት ውይይት ተደርጎ መግባባት ላይ ተደርሶ መሆኑን የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊው አብራርተዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ በበኩሉ የባንክ ክፍያ ስርዓቱ የተቀላጠፈ ስርዓት ከመዘርጋት አንፃር ከፍተኛ ሚና እንዳለውና የገንዘብ ዝውውሩን በባንክ በኩል ለማስገባት ያግዛል ብሏል።

ቢሮው የትምህርት ቤት የባንክ ክፍያ ስርዓትን ተግባራዊ ለማድረግ በየደረጃው ከተውጣጡ የሚመለከታቸው አካላት ጋር አድርጌዋለሁ ያለው ውይይት የግል ትምህርት ቤቶችን እና ወላጆችን ያላሳተፈ መሆኑን አዲስ ማለዳ ከሕዝብ ግንኙነት ኃላፊው አረጋግጣለች። ኃላፊው ለአዲስ ማለዳ እንዳብራሩት ወላጆች የልጆቻቸውን የትምህርት ቤት ክፍያ በባንክ የክፍያ ስርዓት እንዲከፍሉ የተደረገበት ምክንያት በሂደት ስርዓቱን ለማስለመድና የተቀላጠፈ አገልግሎት እንዲኖር ለማድረግ ነው ብለዋል።

የግል ትምህርት ቤቶች የተማሪዎችን ክፍያ በባንክ የክፍያ ስርዓት ተግባራዊ በማድረግ በቴክኖሎጂ የተደገፈ አሰራርን በመከተል የተሻለ አፈጻጸም ለማስመዝገብ አጋዥ መሆኑ ታምኖበት ነው ተብሏል። በወላጆች እና በግል ትምህርት ቤቶች በኩል የተነሳውን ቅሬታ ‹አዲስ ነገር ለመሸሽ ይመስላል› ሲሉ ሕዝብ ግንኙነት ኃላፊው አጣጥለውታል።

የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ የግል ትምህርት ቤቶች የተማሪ ክፍያ በባንክ በኩል እንዲከፍሉ ትምህርት ሚኒስቴር ባስተላለፈው መመሪያ መሰረት የባንክ ክፍያ ስርዓት ተግባራዊ እንዲደረግ አድርጌለሁ ይበል እንጂ፣ ትምህርት ሚኒስቴር የግል ትምህርት ቤቶች የተማሪ ወላጆችን የትምህርት ቤት ክፍያ በባንክ እንዲከፍሉ አስገዳጅ መመሪያ አለማውጣቱን የትምህርት ሚኒስቴር የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ
ሀረጓ ማሞ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com