በአፋር ክልል በሁሉም ዞኖች ከፍተኛ የበርሃ አንበጣ እንደሚከሰት ኢጋድ አስታወቀ

Views: 51

በምስራቅ አፍሪካ ከፍተኛ ጉዳት በማድረስ ላይ የሚገኘው የበርሃ አንበጣ በጥቅምት ወር በኢትዮጵያ አፋር ክልል በሁሉም ዞኖች በከፍተኛ መጠን ሊከሰት አንደሚችል የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ድርጅት(ኢጋድ) የአየር ንብረት ለውጥ አስታወቀ።

እንደ ድርጅቱ ትንበያ የበርሃ አንበጣ በአሁኑ ጊዜ በምስራቅ አፍሪካ ባለፉት ስድስት ሳምንታት በኬንያ ስሜን-ምዕራብ አካባቢዎች፣ በኢትዮጵያ በሰሜን እና ሰሜን ምስራቅ እንዲሁም በሰሜንምዕራብ እና ሰሜን ምስራቅ ሶማሊያ መከሰቱን ድርጅቱ አስታውቋል።

በኢትዮጵያ የበርሃ አንበጣ በአሁኑ ጊዜ በአማራ፣ በትግራይ፣ በአፋር፣ በሶማሊ እና በኦሮሚያ ክልል የተከሰተ ሲሆን በተለይም በአማራ ክልል ባለፉት ሳምንታት ከፍተኛ ወድመት ያደረሰ ሲሆን እስከ አሁንም ስርጭቱ እየሰፋ ይገኛል።

በሰሜን ኢትዮጵያ እና በሰሜን ሶማሊያ እያደረሰ ያለውን ከፍተኛ መጠን ያለው የበርሃ አንበጣ መንጋ አሁንም ድረስ ጥፋት በማድረስ ላይ መሆኑን ኢጋድ አስታውቋል።የበርሃ አንበጣው ከፍተኛ የዝናብ መጠን ባገኙ እና ጥሩ ሰብልና እጽዋት በሚገኝባቸው አካባቢዎች በእድገት ላይ ያሉ(ጎልማሳ) መንጋ በብዛት እየተገኙ መሆኑንም ድርጅቱ ጠቅሷል።

የበርሃ አንበጣውን ለመከላከል ኢትዮጵያም ከፍተኛ ጥረት እያደረገች መሆኑን እና ለኬሚካል እርጭት የሚገለግሉ አውሮፕላኖችን ከተለያዩ አገራት በልገሳ ለማግኘት በጠቅላይ ሚኒስቴር ጽህፈት ቤት በኩል ጥረት እየተደረገ መሆኑ ታውቋል።

የግብርና ሚኒስቴር ዲኤታው ማንደፍሮ ጌታሁን(ዶ/ር) በሳምንቱ አጋማሽ በጋዜጣዊ መግለጫ በሰጡበት ወቅት እንዳስታወቁት ከሆን በኢትዮጵያ የተከሰተውን የበርሃ አንበጣ ለመከላከል 10 አውሮፕላኖች እንደሚሰፈልጉ ገልጿል።

የግብርና ሚኒስቴር የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አበር ለማ ለአዲስ ማለዳ እንዳስታወቁት የበርሃ አንበጣውን ለመከላከል በቂ የኬሚካል አቅርቦት እንዳለ ገልጸው ትልቁ ችግር ግን የአውሮፕላን እጥረትና መንጋው የሚከሰትባቸውን ሁሉንም ቦታዎች ለአውሮፕላን እርጨት አመቺ አለመሆናቸው ነው ብለዋል።

እስካሁን የበርሃ አንበጣን ለመከላከል የኬሚካል ርጭት በማካሄድ ላይ እያሉ ኹለት አውሮፕላኖች ተከስክሰዋል። አንደኛው መስከረም 22/2013 በአማራ ከልል ወረባቦ ወረዳ ሲሆን ኹለተኛው ደግሞ በኦሮሚያ ክልል በምስራቅ ሐረርጌ ጃርሶ ወረዳ ነው የተከሰከሱት።

በሌላ በኩል በአማራ ክልል ከፍተኛ ቦታዎች እና ወደ ሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍሎች የአንበጣ መንጋው ስርጭት ሊስፋፋ እንደሚችል የምሥራቅ አፍሪካ የበርሃ አንበጣ መቆጣጠሪያና መከላከያ ድርጅት አሳስቧል። የአውሮፕላን የኬሚካል ርጭት ማካሄድ ወሳኝ መፍትሔ በመሆኑ የመከላከል ሥራውን ለማገዝ የሚረዳ በድርጅቱ አንድ አውሮፕላን መስከረም 30/2012 ኢትዮጵያ እንደሚገባም ድርጅቱ አስታውቋል።

የበርሃ አንበጣውን ከፀረ ተባይ ኬሚካል ለየት ባለ መልኩ መከላከል በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ጥናትና ምርምር እየተካሄደ እንደሆነ ከምሥራቅ አፍሪካ የበርሃ አንበጣ መቆጣጠሪያና መከላከያ ድርጅት አስታውቋል።

የበርሃ አንበጣ መንጋ ከተከሰተባቸው ቦታዎች በአማራ ክልል በደቡብ ወሎ ዞን ለአውሮፕላን ርጭት የቦታው አቀማመጥ ምቹ ባለመሆኑ ስርጭቱን በአውሮፕላን እርጭት ለመከላከል አስቸጋሪ አድርጎታል ተብሏል።

ግብርና ሚኒስቴር መስከረም 27/2013 በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ የአንበጣ መንጋውን ለመከላከል እየተደረገ ያለው ርብርብ እንድጠናከር አሳስቧል።

የበርሃ አንበጣ በአማራ ክልል ሰሜን ወሎ ዞን አካባቢዎች ከቁጥጥር ውጪ እየሆነ ነው ተብሏል። ከፍተኛ ቁጥር ያለው መንጋ በተከሰተባቸው ቦታዎች በሰብል ላይ ሙሉ በሙሉ ጉዳት ማድረሱ ተመላክቷል። አዲስ ማለዳ ባለፈው ሳምንት እትሟ በራያ ቆቦ ወረዳ በዘጠኝ ቀበሌዎች የተከሰተው መንጋ በጤፍ ሰብል ላይ መቶ በመቶ ማውደሙን መዘገቧ የሚታወስ ነው።

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com