የእለት ዜና

የብረታ ብረትና ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ከወጪ ንግድ ከ6 ሚሊዮን ዶላር በላይ አገኘ፤ ከ44 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ለማግኘት አቀዷል

የብረታ ብረት እና ኢንጅነሪንግ ንዑስ ዘርፍ በ2013 በጀት ዓመት በኹለት ወራት ውስጥ ወደ ውጭ ከላካቸው ምርቶች ከ6 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ማግኘቱ ተገለጸ።

ኢንስቲትዩቱ 44 ነጥብ 96 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ዋጋ ያለው ምርት በማምረት ለውጭ ገበያ በማቅረብ ገቢ ለማግኘት አቅዶ እየሠራ መሆኑን አስታወቀ።

በተያዘው በጀት ዓመት በንዑስ ዘርፉ በሐምሌና ነሐሴ ወራት አራት ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ዋጋ ያላቸው ምርቶች ወደ ውጭ አገር ለመላክ ዕቅድ ይዞ ከ6 ሚሊዮን 485 ሺሕ ዶላር በላይ ዋጋ የሚያወጡ ምርቶችን በመላክ ገቢ መገኘቱን ኢንስቲትዩቱ ጠቅሷል።

ኢንስቲትዩቱ ድጋፍ ከሚያርግላቸው አምራች ኢንዱስትሪዎች ጋር በቅንጅት እየሠራ ሲሆን፣ በበጀት ዓመቱ በመጀመሪያ ኹለት ወራት ማለትም በሐምሌና ነሐሴ በኤሌክትሪካልና ኤሌክትሮኒክስ እንዲሁም በመሠረታዊ ብረታ ብረትና ኢንጅነሪንግ ምርት ዘርፎች የተለያዩ ምርቶችን ወደ ውጭ በመላክ የውጭ ምንዛሬ ማግኘት መቻሉንም ለአዲስ ማለዳ አስታውቋል።

በዚህም በኤሌክትሪካልና ኤሌክትሮኒክስ ምርቶች 3 ሚሊዮን 600 መቶ ሺሕ ዶላር ዋጋ ያለው ምርት በማምረት ለገበያ ለማቅረብ ታቅዶ ከ6 ሚሊዮን 138 ሺሕ ዶላር በላይ ገቢ መገኘቱ ተገልጿል። በዚህም ከእቅዱ በላይ ያሳካ መሆኑን የሚያመላክት ነው። አፈጻጸሙም 170 ነጥብ 5 በመቶ መሆኑን የኢንስቲትዩቱ የኮምዩኒኬሽን ዳይሬክተር ፊጤ በቀለ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

ለገቢው መገኘት አምስት የአገር ውስጥ እና የውጭ አገር አምራች ድርጅቶች ድርሻ እንዳላቸው የተገለጸ ሲሆን፣ አብዛኛው ገቢ የተገኘውም ከተንቀሳቃሽ ስልኮችን ወይም ሞባይል ስልኮችን ወደ ውጭ አገር በመላክ እንደሆነ ፊጤ አክለው አስታውቃል።

ምርቶቹ የተላኩባቸው አገራት 12 ሲሆኑ ከእነዚህም ከአፍሪካ ናይጄሪያ፣ ሶማሊያ፣ ቶጎ የሚጠቀሱ ናቸው። እስራኤልና ኔዘርላንድም ምርቶቹ ከተላኩባቸው አገራት መካከል ተጠቃሽ መሆናቸውን ፊጤ ተናግረዋል።

በመሠረታዊ ብረታ ብረት እና ኢንጅነሪንግ ምርት ዘርፎች ደግሞ 400 ሺሕ ዶላር ዋጋ ያለው ምርት ወደ ውጭ አገር ለመላክ ዕቅድ ተይዞ ከ346 ሺሕ ዶላር በላይ ዋጋ ያለው ምርት ተልኳል። አፈፃፀሙም 86 ነጥብ 68 በመቶ መሆኑን ኢንስቲትዩቱ ጠቅሷል።

በዚህ ምርት ዘርፍ በወጪ ንግድ እንቅስቃሴ የተሳተፉ የአገር ውስጥ አምራች ድርጅቶች ከ20 በላይ ሲሆኑ፣ የገበያ መዳረሻ አገሮች ከ10 በላይ መሆናቸው እና መዳረሻ አገራቱ ከአፍሪካ ሩዋንዳ፣ ናይጄሪያ ሶማሊያ እንዲሁም ከአውሮፓ አገራት ደግሞ ጀርመን እና ኔዘርላንድ ተጠቃሾቹ ናቸው ተብሏል።

በመሠረታዊ ብረታ ብረት እና ኢንጅነሪንግ ምርት ዘርፎች የእቅዱን ያህል እንዳያሳከው ያደረገው የግብዓት እጥረት አንዱ ችግር መሆኑን ፊጤ ገልጸዋል። በአጠቃላይ በንዑስ ዘርፉ በሐምሌና ነሐሴ ወራት አራት ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ዋጋ ያላቸው ምርቶች ወደ ውጭ አገር ለመላክ ዕቅድ ተይዞ ከ6 ሚሊዮን 485 ዶላር በላይ ዋጋ የሚያወጣ ምርት በመላክ ገቢ መገኘቱን ኢንስቲትዩቱ አስታውቋል።

የብረታ ብረት እና ኢንጅነሪንግ ንዑስ ዘርፍ በ2012 በጀት ዓመት ቁጥራቸው ከ20 በላይ የሆኑ ድርጅቶች ወደ ውጭ አገራት ከላኳቸው የኤሌክትሪካልና ኤሌክትሮኒክስ ምርቶች ከ40 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ መገኘቱን የብረታ ብረት ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት የኮርፖሬት ኮምዩኒኬሽን ዳይሬክተር ፊጤ በቀለ ለአዲስ ማለዳ ጋዜጣ መግለጻቸው ይታወሳል።

ገቢው የተገኘው በበጀት ዓመቱ 11 ወራት ጊዜ ውስጥ በኢንስቲትዩቱ የብረታ ብረትና ኢንጅነሪንግ ንዑስ ዘርፍ ድጋፍ ከሚደረግላቸው የግል ድርጅቶች ሲሆን፣ ወደ 30 የሚሆኑ መዳረሻ አገራት የብረታ ብረት እና ኢንጅነሪንግ (ኤሌክትሪካልና ኤሌክትሮኒክስ) ምርቶችን በመላክ 37 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ማግኘት መቻሉንም አስታውቆ ነበር።

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com