‹‹ሕብረተሰቡ ስለካንሰር ያለው ግንዛቤ በጣም ዝቅተኛ ነው››

Views: 28

እንደ ዓለም ጤና ድርጀት ሪፖርት በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ በየዓመቱ ሕይወታቸውን ከሚያጡ ሰዎች መካከል 52 በመቶ የሚሆኑት የሚሞቱት ተላላፊ ባልሆኑ ሕመሞችና በድንገተኛ አደጋ ምክንያት ነው። ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችና ሕመሞች በአገራችን በኢትዮጵያ ተገቢውን ትኩረት ባለማግኘታቸው፣ አገሪቷ በየዓመቱ በእነዚህ በሽታዎች 31 ቢሊዮን ብር ወይም 1.8 በመቶ የሚሆነውን አጠቃላይ የአገር ውስጥ ምርት /GDP/ በየዓመቱ ታጣለች።

ልጃቸውን በካንሰር ሕመም ያጡት ወንዱ በቀለ፣ በዛ ምክንያት የደረሰባቸውን መሪር ሐዘን ለመቋቋም፣ የተፈጠረውንም አሰቃቂ ሁኔታ ወደ መልካም አጋጣሚ ለመቀየር የማቲዎስ ወንዱ-የኢትዮጵያ ካንሰር ሶሳይቲ እንዲመሠረት አድርገዋል። ሶሳይቲው በአገር ዐቀፍ ደረጃ ተላላፊ ያልሆኑ ሕመሞችን በአጠቃላይና ካንሰርን በተለይ ለመቋቋም በሚደረገው ጥረት ከፍተኛ አስተዋፅኦ በማድረግ ላይ እንደሚገኝ የሚያወሱት ወንዱ፣ ያለውን ውሱን አቅም በመጠቀም የጤና ሚኒስቴርና የኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት ባለሥልጣን ብሔራዊ የካንሰር መቆጣጠሪያ ዕቅድ፣ ብሔራዊ የሕፃናትና ታዳጊ ካንሰር መቆጣጠሪያ ዕቅድና ተያያዝ ሕግና አማራጭ መንገዶችን በምክረ ሐሳብ በማቅረብ ከፍተኛ አስተዋፅኦ አድርጓል።

እንደ ወንዱ በቀለ፣ የማቲዎስ ወንዱ-የኢትዮጵያ ካንሰር ሶሳይቲ ስራ አስፈጻሚ ከሆነ፣ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ወይም ሕመሞች የጤና ችግር ብቻ ሳይሆኑ የልማት ችግር በመሆናቸው መንግሥትም ሆነ ህብረተሰቡ ትኩረት ሰጥቶ ሊከላከላቸውና ሊቆጣጠራቸው ይገባል።

የማቲዎስ ወንዱ-የኢትዮጵያ ካንሰር ሶሳይቲን በተመለከተ፣ የሚሠራቸውን ሥራዎች እንዲሁም በጠቅላላው ካንሰርን ጨምሮ ተላላፊ ባልሆኑ ሕመሞች ዙሪያ ስላለው ግንዛቤ በማንሳት የተቋሙ ዋና ሥራ አስፈጻሚው ወንዱ በቀለ ከአዲስ ማለዳው ዳዊት አስታጥቄ ጋር ተከታዩን ቆይታ አድርገዋል።

የማቲዎስ ወንዱ-የኢትዮጵያ ካንሰር ሶሳይቲ እንዴት እና መቼ ተመሠረተ?

የማቲዎስ ወንዱ-የኢትዮጵያ ካንሰር ሶሳይቲ የተቋቋመው ሚያዚያ 9 ቀን 1996 ነው። ከዚያ ጊዜ ጀምሮ የተቋቋመባቸውን ዓላማዎች ተግባራዊ ለማድረግ ከፍተኛ ጥረት ሲያደርግ ቆይቷል።

የኢትዮጵያ የካንሰር ሶሳይቲ /ማወኢካስ/ ባለው ተጨባጭ ሁኔታ የተመሠረተው በማቲዎስ ወንዱ ቤተሰብ መኖሪያ ቤት ውስጥ ሲሆን ለስድስት ዓመት ያለአንዳች አስተዳደራዊ ወጪ ማለትም የቤት ኪራይ፣ ደመወዝ፣ ስልክ ወዘተ.. በመሥራት ነው የዘለቀው። እኔም ኹለት ከፍተኛ ኃላፊነቶችን በአንድ ወቅት ለመያዝ ተገደዱኩ።

በብሔራዊ የትምባሆ ድርጅት በጥሩ ደመወዝ፣ በማቲዎስ ወንዱ ያለደመወዝ ለስድስት ዓመት ለመሥራት ተገደድኩ። ሆኖም ለካንሰር መከሰት ከፍተኛ መንስኤ ከሆኑት አንዱ ትምባሆ በመሆኑ ሶሳይቲው ፀረ ትምባሆ ዘመቻ በተመረጡ ዐስር ትምህርት ቤቶች ውስጥ ማካሄድ ሲጀምር፣ በያዝኳቸው ኹለት ኃላፊነቶች መካከል ተቃርኖ በመፈጠሩ ከኹለቱ አንዱን ለመልቀቅ ተገደድኩ።

በዚህም እ.ኤ.አ. ከዲሴምበር 1 ቀን 2ዐዐ9 ጀምሮ ከብሔራዊ ትምባሆ ድርጅት በራሴ ፈቃድ ለቅቄ ማወኢካሶ በሙሉ ጊዜ ተቀላቀልኩ። እስከዚህ ያለው ጊዜና በኋላም ሶሳይቲው ከላይ በተጠቀሰው ምክንያት በአንድ በኩል ህልውናውን ለማቆየትና በሌላ በኩል ደግሞ ማህበሩ የተቋቋመባቸውን ኃላፊነት ለመወጣት ሲያደርግ የቆየው መንገድ በጣሙን ፈታኝ ነበር።

 ዛሬ ላይ ማህበሩ ምን ሁኔታ ላይ ነው፤ ምን ዓይነት ተግባራትንስ እየሠራ ይገኛል?

ማህበሩ ዛሬ ከአንድ ሺሕ 4ዐዐ አባላት እና ከ5ዐዐ በላይ የበጐ ፈቃድ ሠራተኞች አሉት። በተጨማሪም 25 ቋሚ ሠራተኞች በመያዝ ከ364 በላይ የካንሰር ሕሙማንና ቤተሰባቸውን ከክልል ወጪ ወደ አዲስ አበባ የሚመጡበትና የሚመለሱበትን ሙሉ የትራንስፖርት ወጪ በመሸፈን ድጋፍ ያደርጋል።

በተጨማሪ ለሕክምና ሆስፒታል በሚቆዩበት ወቅት (ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል) የማይሰጣቸውን መድኃኒትና የላብራቶሪ አገልግሎት ወጪ በመሸፈን፣ ለጥቃቅን ወጪ መሸፈኛ የሚሆን በወር ብር አምስት መቶ እንዲሁም ለተወሰኑ ሕፃናት በሕክምና መካከል ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ በወር ብር አምስት መቶ በመስጠት ለሕክምና አዲስ አበባ ከሆስፒታል ውጭ በሚቆዩበት ወቅት ባለው 24 አልጋ ባሉት የካንሰር ሕሙማን ማቆያ ማዕከል የትራንስፖርት፣ የመኝታ፣ የምግብና የምክር አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል።

በአጠቃላይ ሰባት ኘሮጀክቶችን፣ ማለትም አንድ በሕፃናት ካንሰር፣ ሦስት በትምባሆ ቁጥጥር፣ አንድ በጡት ካንሰር፣ አንድ በሳንባ ካንሰርና አንድ በተላላፊ ያልሆኑ ሕመሞች ላይ እየሠራ ይገኛል።

በዚህ ጉዞ ትልቅ ድጋፍ የነበራቸውን የመንግሥት ኃላፊዎች ወይም ባለሥልጣናት የነበራቸው አስተዋጽኦ ምን ያህል ነበር?

ሶሳይቲያችን ኃላፊነቱን ለመወጣት ሲያደርግ በቆየው ጥረት የብዙ ድርጅቶችና ግለሰቦች ድጋፍና ትብብር አግኝቷል። የጤና ሚኒስቴር ሆነው ከሠሩት ከዶክተር ቴዎድሮስ አድኃኖም፣ ዶክተር ከሳተብርሃን አድማሱ፣ ኘሮፌሰር ይፍሩ የማነብርሃን፣ ዶክተር አሚር አማንና አሁን ያሉት ዶክተር ሊያ ታደሰ ሶሳይቲው ለሚያቀርባቸው አብረን እንሥራና የተለያዩ ጥያቄዎች ወቅታዊ ምላሽ በመስጠት ከፍተኛ አስተዋፅኦ አድርገዋል።

የቀድሞዋ ቀዳማዊት እመቤት ሮማን ተስፋዬ ለሶሳይቲያችንም ሆነ የካንሰር ሕመም ተገቢውን ትኩረትና ትርጉም ያለው ድጋፍ እንዲያገኝ በማድረግ ከፍተኛ  አስተዋፅኦ አድርገዋል። በትምባሆ ቁጥጥር የኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት ቁጥጥር ባለሥልጣን ዳይሬክተር የነበሩት የሁሉ ደነቀው፣ አሁን ዳይሬክተር ሆነው በመሥራት ላይ የሚገኙት ሄራን ገርባና የሥራ ባልደረቦቻቸው ከፍተኛ አስተዋፅኦ በማድረግ ላይ ናቸው።

የዓለም ጤና ድርጅት የኢትዮጵያ ተጠሪ ጽህፈት ቤት አጋር ድርጅቶችና የእርዳታ ሰጪ ድርጅቶች፣ በአገር ውስጥና ውጭ ያሉ ድርጅቶችና ግለሰቦች ለሶሳይቲያችን መጠናከር ከፍተኛ አስተዋፅኦ አድርገዋል። በአሁኑ ወቅት ሶሳይቲያችን በአገርና በዓለም ዐቀፍ ደረጃ እጅግ የተከበረና የታመነ ድርጅት ለመሆን እንዲችል የብዙ ድርጅቶችና ግለሰቦች የሶሳይቲያችን አባሎች፣ የበጐ ፈቃድ ሠራተኞች፣ የካንሰር ሕሙማንና ቤተሰቦች፣ የሶሳይቲው ሠራተኞች ወዘተ.. ከፍተኛ አስተዋፅኦ በማድረግ ላይ ይገኛሉ።

የዓለም ጤና ድርጅት በዚህ ዓመት ከተጨማሪ ታክስ አዋጅ ጋር በተገናኘ ስለነበራችሁ አበርክቶ በተለይ ትምባሆና አልኮል ምርቶች ጋር በተያያዘ እውቅና ሰጥቷችኋል። የሠራችሁት ሥራ ምንድን ነው፣ እውቅናውስ?

ሶሳይቲያችን ተላላፊ ያልሆኑ ሕመምች በአጠቃላይ እንዲሁም በካንሰርና ትምባሆ ላይ በተለይ በአገራችን ብቻ ሳይሆን በዓለም ዐቀፍ ደረጃ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እያደረገ ያለ እና ዕውቅና ያለው ነው። ይህ በእንዲህ እንዳለ የዓለም ዐቀፍ ትምባሆ መቆጣጠሪያ ማዕቀፍ በኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ ተዘጋጅቶ በተወካዮች ምክር ቤት ቀርቦ እንዲፀድቅ በማድግና የፀደቀውም ሕግ በአፍሪካ አህጉር ጥብቅ ከሚባሉት አንዱ እንዲሆን በማድረግ ሂደት ውስጥና በመቀጠልም ጠንካራ የእሴት ታክስ በተወካዮች ምክር ቤት ቀርቦ እንዲፀድቅ ጉዳዩ የሚመለከታቸውን በማስተባበርና ሂደቱን በመምራት ረገድ ላበረከትነው ከፍተኛ አስተዋፅኦና ሚና ነው በአጋሮቻችን ሥም ሽልማቱን የተቀበልነው።

ዕውቅናው ወደፊት ጠንክረን እንድንሠራ የሚያበረታታ፣ በዚህ ረገድ ያለንን አስተዋፅኦና እውቅና ከፍ የሚያደርግ ነው።

 ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ትኩረት እየተሰጣቸው አይደለም። ብዙ ቁጥር ያለው ሰውም እየተጎዳበት ነው። በኢትዮጵያ ያለው ነባራዊ ሁኔታስ ምን ይመስላል? ምን መደረግ አለበት ይላሉ ?

በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ በየዓመቱ ሕይወታቸውን ከሚያጡ ሰዎች መካከል 52 በመቶ የሚሆኑት የሚሞቱት ተላላፊ ባልሆኑ ሕመሞችና ድንገተኛ አደጋ ምክንያት ነው። ተላላፊ ያልሆኑ ሕመሞች በአገራችን በኢትዮጵያ ተገቢውን ትኩረት ባለማግኘታቸው አገሪቷ በየዓመቱ በእነዚህ ሕመሞች 31 ቢሊዮን ብር ወይም 1.8 በመቶ የሚሆነውን አጠቃላይ አገራዊ ምርት /GDP/ በየዓመቱ ታጣለች።

እነዚህ ሕመሞች በአብዛኛው አስቀድመው መከላከል የሚቻል ቢሆንም በቂ ትኩረት አላገኙም። በኢትዮጵያ ከዓመታዊ የጤና በጀት ተላላፊ ላልሆኑ ሕመሞችና አደጋ የሚመደበው ከ15 በመቶ ያነሰ ሲሆን፣ ከውጭ አገር ከሚገኘው እርዳታም ለተላላፊ ያልሆኑ ሕመሞችና አደጋ የሚውለው አንድ በመቶ ብቻ ነው። እንግዲህ ይህ የሚያሳየው ተላላፊ ያልሆኑ ሕመሞች ማለትም በልብ፣ በደም ብዛት፣ በመተንፈሻ  አካላት፣ ስኳር፣ ካንሰር ላይ መሥራት ምን ያህል አስቸጋሪ እንደሆነ ነው።

ተላላፊ ያልሆኑ ሕመሞች የጤና ችግር ብቻ ሳይሆኑ የልማት ችግር በመሆናቸው መንግሥትም ሆነ ህብረተሰቡ ትኩረት ሰጥቶ ሊከላከላቸውና ሊቆጣጠራቸው ይገባል። በአሁኑ ወቅት በከተማ በወጣቶች ዘንድ ያለው የጫት፣ የመጠጥ፣ የትምባሆ፣ የአደንዛዥ ዕፅ ተጠቃሚነት በህብረተሰቡ ዘንድ ስለጤናማ አመጋገብ፣ ክብደት መጨመር፣ በቂ የሆነ የአካል እንቅስቃሴ አለማድረግ፣ ትምባሆና አልኮል አስመልክቶ ያለው የግንዛቤ ችግር እጅግ አሳሳቢ እየሆነ ነው።

ስለሆነ ህብረተሰቡ ጤናን በተመለከተ ጤናማ አማራጭ እንዲከተልና ጤናማና ደስተኛ ሆኖ እንዲኖር ማስተማር ማሳወቅና ማብቃት ይጠይቃል። ይህ ደግሞ የአንድ አካል ሥራ ብቻ ስላልሆነ በአገር ዐቀፍ ደረጃ ተቀናጅቶና ተባብሮ መሥራትን ይጠይቃል።

የኢትዮጵያ  ዳያስፖራ ኤጀንሲ የፕሮጀክት ግምገማ ወቅት ማህበሩ ቅሬታ እንደነበረው ይታወቃል። ቅሬታው ምን ነበር? ምን ያህል አግባብስ ነበር?

የኢትዮጵያ ዲያስፖራ ፈንድ በአገራችን የተለያዩ ዘርፎች እንድንወዳደር ግልፅ ማስታወቂያ አውጥቶ ባቀረበው ጥያቄ መሠረት ከ4ዐዐ በላይ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች መካከል 22 የምንሆነው መመረጣችንን በጽሑፍ አሳውቆን ነበር። በመቀጠል ሌላ ማጣሪያ እንደሚደረግ ገለፁልን። በዚሁ መሠረት እያንዳንድ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት የተመረጠበትን ኘሮጀክት ተግባራዊ ለማድረግ ያለውን ዝግጁነት፣ የውስጥ አደረጃጀቱን፣ ሕጋዊ አሠራሩን፣ ኘሮጀክቱን ሥራ ላይ ለማዋል ያለውን ልምድና ብቃት የሚያጣራ አማካሪ ድርጅት ተመድቦ የማህበራችን አጠቃላይ ይዞታ ተገምግሞ (Organizational Capacity Assessment-OCA) ጥሩ ውጤት ማግኘታችን ተገለፀልን።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ውጤቱ በሚገለፅበት ቀን ምሳ ሰዓት ያልተጠበቀ የኢሜል መልዕክት ደረሰን። ይኸውም የመጀመሪያው ስምምነት የሚፈፀመው ከአምስት መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ብቻ እንደሆነና የተቀረነው 17 በቀጣይ እንደሚጣራ ተገለፀ። ይህ ያልተጠበቀና ዱብ ዕዳ ነው የሆነብን። በተለይ እንደኛ ላለነው በተላላፊ ያልሆኑ ሕመሞች ላይ ለምንሠራ ድርጅት ያቀረብነው ኘሮጀክት በኦሮሚያና በደቡብ ክልል ከሦስት ዓመት በላይ ሥራ ላይ አውለን  ከፍተኛ ልምድ ያገኘንበትን የማህፀን ጫፍ ካንሰር በጋምቤላ፣ በቤንሻንጉልና አፋር ክልል ሥራ ላይ ለማዋል ነበር።

የማሕፀን ጫፍ ካንሰር አስቀድሞ መከላከል የሚቻልና ክትባት ያለው ሕመም ሆኖ ሳለ በዚህ ሕመም ብዙ መሥራት እየቻልን ለመሥራት ዝግጁ ሆነን ኘሮጀክቱ መያዙ በጣሙን ቅር አሰኝቶናል።

የካንሰር ቅድመ ምርምራ እንዲጀመር ማህበሩ የነበረው አስተዋጽኦ ምን ነበር? ምርመራው መጀመሩ ምን ፋይዳ አለው? አሁንስ ምን ደረጃ ላይ ይገኛል?

የማሕፀን ጫፍ ካንሰርን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በሚደረገው ጥረት አስቀድሞ መከላከሉ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያደርጋል።  በዚህም የጤና ሚኒስቴር ከአጋር ድርጅቶች ጋር በመተባበር ዕድሜያቸው 14 ዓመት ለሚሆናቸው ልጃገረዶች በሙሉ በአገር ዐቀፍ ደረጃ የመጀመሪያ ዙር ክትባት እንዲሰጥ ተደርጓል።

ኹለተኛው ዙር ቀደም ሲል መሰጠት የነበረበት ሲሆን፣ በኮቪድ 19 ምክንያት ሳይሰጥ የቆየ በመሆኑ በቅርቡ ይሰጣል ተብሎ ይጠበቃል። ይህ የክትባት ዘመቻ ተጠናክሮ ከቀጠለ አብሮ ለሌሎች ሴቶች ከሚሰጠው የግንዛቤ ማስጨበጫ ጋር ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያደርጋል። ሕመሙንም ለመከላከልና እንደተከሰተ ለማወቅ ስለሚያስችል በማሕጸን ጫፍ ምክንያት በሴቶች ላይ የሚደርሰውን ስቃይ ለመቀነስና ታክመው የሚድኑበትን ዕድል ለማሳደግ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያደርጋል።

የካንሰር ሕክምና ተቋማትን ለመገንባት እንዲሁም የሕክምና ባለሙያዎችን ቁጥር ለማሳደግ ምን እየተደረገ ነው?

ሶሳይቲያችን ያለው አቅም ውሱን ቢሆንም፣ በካንሰር ላይ ትርጉም ያለውና ዘላቂ ሥራ ለመሥራት የመንግሥት በተለይ የጤና ሚኒስቴር አስተዋፅኦ ከፍተኛ መሆኑን ጠንቅቆ ይገነዘባል። በዚህም የጤና ሚኒስቴር በተላላፊ ያልሆኑ ሕመሞችና በካንሰር ላይ በተለይ ያለበትን የአቅም ውሱንነት በመገንዘብ ከአጋር ድርጅት ባገኘነው ድጋፍ አንድ ከፍተኛ ባለሙያ ቀጥረን እኛ ደመወዙን እየከፈልን ለሦስት ዓመት ከ1ዐ ወራት ሙሉ ጊዜውን በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር እንዲሠራ አድርገናል።

በዚሁም ጊዜ አገራችን ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ የብሔራዊ ካንሰር መቆጣጠሪያ ዕቅድ እንዲኖራትና ዕቅዱም በጀት እንዲመደብለት በተደረገው ጥረት ከፍተኛ አስተዋፅኦ አድርገናል። ለዚሁም ለደመወዝና ልዩ ልዩ ወጪዎች ከዘጠኝ ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ አድርገናል።

ዕቅዱ በአፍሪካ አህጉር በጀት ከተመደበላቸው ጥቂት ዕቅዶች አንዱ ለመሆን በቅቷል። በዚህም መሠረት ዛሬ በመቀሌ፣ በጎንደር፣ በጅማ፣ በሀዋሳና በሀሮማያ ትልልቅ የካንሰር ማዕከላት ከመሠራታቸውም በላይ እያንዳንዱ ከ1ዐዐ ሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጡ ስድስት የጨረር መሣሪያዎች /ራዲዮቴራፒ/ እንዲሁም አንድ ሺሕ 3ዐዐ በላይ የማህፀን ጫፍ መመርመሪያና ማከሚያ መሣሪያ መግዛት፣ በቅዱስ ጳውሎስም የካንሰር ልኅቀት ማዕከል ለማቋቋም በተደረገው ጥረት ከፍተኛ አስተዋፅኦ አድርገናል።

የባለሙያዎችንስ ቁጥር ከማሳደግ አንጻር ምን ጥረት እየተደረግ ነው?

እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ በኢትዮጵያ የነበሩትን የካንሰር ስፔሻሊስቶች ወይም ኦንኮሎጂስቶች አራት ብቻ ነበሩ። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የካንሰር ባለሙያዎች ትምህርትና ሥልጠና በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ መስጠት በመጀመሩ የካንሰር ስፔሻሊስቶችና ነርሶች ቁጥር እየጨመረ ነው።

በአሁኑ ወቅት የስፔሻሊስቶቹ ቁጥር ከ5ዐ በላይ ደርሷል። በውጭ አገር በመሠልጠን ላይ ከሚገኙት አንድ ላይ ቁጥሩ እየጨመረ ይገኛል።

 የሳንባ ካንሰር ቅድመ ምርመራና መቆጣጠር ፕሮጀክት በኢትዮጵያ እንዲጀመር የማቴዎስ ወንዱ ካንሰር ሶሳይቲ ምን አስተዋጽኦ  አድርጓል?

ቢ.ኤም.ኤስ.ኤፍ. (BMSF) በአራት አፍሪካ አገሮች ውስጥ ሲያካሄድ የቆየውና የሳንባ ካንሰር ላይ አተኩሮ የሚሠራውን ፕሮጀክት ኢትዮጵያን አምስተኛ አገር አድርጎ ሥራ ላይ እንዲውል የተደረገው ጥረት ተሳክቷል። ፕሮጀክቱ ሥራ ላይ ለማዋል ማቲዎስ ወንዱ የኢትዮጵያ ካንሰር ሶሳይቲ /ማወኢካሶ/ የቢኤምኤስኤፍ በኢትዮጵያ ዋና አጋር በመሆን ከቢኤምኤስኤፍና ከጤና ሚኒስቴር ጋር ለሦስት ዓመት የሚቆይ የፕሮጀክት ስምምነት ተፈራርሟል።

በአራት ክልሎች ውስጥ ማለትም በአማራ፤ በኦሮሚያ፤ በአፋር ክልሎችና በአዲስ አበባ አስተዳደር ውስጥ ተግባራዊ የሚደረግ ፕሮጀክት ነው። ለዚህም ማወኢካሶ ከአምሬፍ (AMREF)፤ ከኩዋም (CUAMM)፣ ከሜሪጆይ (Mary Joy) እና ከኢትዮጵያ ቶራሲክ ሶሳይቲ (ETS) ጋር የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርሟል።

በፕሮጀክቱ የሳንባ ካንሰርን አስቀድሞ ለመከላከል፤ በወቅቱ የመመርመርና ተገቢውን የሕክምና አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችለውን አቅም በተለያዩ ሆስፒታሎች ውስጥ የሚገነባ፤ ባለሙያዎች የማሠልጠን፤ የተመረጡ ጥናትና ምርምሮችን የማካሄድ፤ የሳንባ ካንሰር ሕሙማን ስቃይ ለመቀነስና ታክመው የሚድኑበትን ዕድል ከፍ ለማድረግ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያደርጋል።

በዚህም በሶሳይቲያችን አመራር ሠራተኞች ሥም ቢኤምኤስኤፍ የከበረ ምስጋና እናቀርባለን። ይኽ ድርጅት ሶሳይቲያችን እዚህ ደረጃ እንዲደርስ የአቅም ግንባታ ድጋፍ ያደረገና ለሦስት ዓመት በማሕፀን ጫፍ ካንሰር ላይ በኦሮሚያ፤ በደቡብ ክልልና በአዲስ አበባ ውጤታማ ሥራ አብሮን የሠራ ነው። በአፍሪካ አህጉር በተለይ በካንሰር ላይ ትርጉም ያለው ድጋፍ ሲያደርግ ውጤታማ  በመሆኑም ትብብራችንን አጠናክረን እንቀጥላለን።

 የመስከረም ወር ወርቃማው የሕጻናት ካንሰር ወር ተብሎ ይዘከራል። ለመሆኑ የሕጻናት ካንሰር ዋና ዋና ምልክቶችን ለአንባቢያን ቢጠቁሙሉን?

እንደ ራስ ምታትና በተደጋጋሚ ጠዋት ጠዋት ማስመለስ፣ በተከታታይ ክብደት መቀነስ፣ በየጊዜው በኢንፌክሽን መጠቃት እና አቅም ማጣት፣ የማየት አቅም በድንገት መዳከም እና የታችኛው የዐይን ክፍል ነጭ መሆን ሕጻናት ላይ ከሚታዩ ምልክቶች መካከል ናቸው።

 የህብረተቡ ንቃተ ሕሊና እና የመንግሥት ድጋፍ ምን ይመስላል?

ተላላፊ ያልሆኑ ሕመሞች በአጠቃላይና ካንሰር በተለይ አዋጪ የሚሆነው ቢቻል አስቀድሞ በመከላከል፣ ካልሆነ ሕመሙ እንደያዘ ቶሎ ታውቆ ተገቢውን ሕክምና እንዲያገኝ ማድረግ ነው። ካንሰር ከተሰራጨ በኋላ አክሞ ለማዳን በጣሙን አስቸጋሪ ነው።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ህብረተሰቡ ስለካንሰር ያለው ግንዛቤ በጣም ዝቅተኛ ነው። ካንሰርን አስቀድሞ መከላከልም ሆነ ከያዘም አክሞ ለማዳን ጨርሶ እንደሚቻል ስለማያምኑና አንዳንዶቹም የእግዚአብሔር ቁጣ አድርገው ስለሚያስቡ ያለውን ችግር ይበልጥ አወሳስበውታል።

እንደ እውነቱ ከሆነ እስከ 4ዐ በመቶ የሚሆኑትን የካንሰር አምጪ ምክንያቶችን አስቀድሞ መከላከል ይቻላል። ይህንንም ለማድረግ ጤናማ አመጋገብ፣ ጥራጥሬ ፍራፍሬና አትክልት ላይ ያተኮረ አመጋገብ መከተል፣ ከቁመት ጋር ተመጣጣኝ የሆነ ክብደት መያዝ፣ በቂ የአካል እንቅስቃሴ ማድረግ፣ ከትምባሆና አልኮል መጠጥ፣ ከጫት ወዘተ.. መቆጠብ ይጠቅማል።

ካንሰር እንደያዘ በወቅቱ ከተደረሰበትና ተገቢውን ሕክምና ካገኘ የመዳን ዕድሉ ከፍተኛ ነው። በዚህ ረገድ በጤና ሚኒስቴርና አጋር ድርጅቶች በአገር ዐቀፍ ደረጃ እየተደረገ ያለው ጥረት የሚያበረታታ ቢሆንም፣ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት። በዚህም ህብረተሰቡን ከካንሰር ሕመም አስቀድሞ እንዲከላከል የማድረግ ሥራ፣ ከዚያም ሕመሙን በወቅቱ መርምሮ ለማወቅና ተገቢውን ሕክምና ለመስጠት ይበልጥ ተቀናጅቶ መሥራትን ይጠይቃል።

 

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com