የጤና ሚኒስቴር ምክረ ሐሳብ – በድፍረት ወይስ በዕውቀት!

Views: 128

የኮቪድ 19 ቫይረስ ወረርሽኝ ለዓለም እንግድነቱ አብቅቶ የተላመደና የተለመደ ይመስላል። ቫይረሱ የሰዎችን ሕይወት ከመቅጠፍ ወደኋላ ባይልና መድኃኒትም እስከ አሁን ያልተገኘለት ቢሆንም፣ ወረትና ስልቹነት የሚያጠቃው የሰው ልጅ የቫይረሱን ዜና እንደ መጀመሪያው ሰሞን የሚያስተናግደው አይደለም። ሕይወት መቀጠል አለበት በሚልም አስቀድሞ የተደረጉ የእንቅስቃሴ ገደቦች እየላሉ ይገኛሉ። ግዛቸው አበበም ይህን ሐሳብ በማንሳት፣ ከእንቅስቃሴ ገደብ ጋር በተገናኘ የትምህር ቤቶችን መከፈት ጨምሮ በኢትዮጵያ የጤና ሚኒስቴር እየተሰጠ ያለው ውሳኔ በብልሃት ነው ወይስ በድፍረትና በፖለቲካ ዕይታ እየተሄደ ያለው ሲሉ ጠይቀዋል።

በርካታ የዓለማችን አገራት የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ወደ አካባቢያቸው እንደገባ፣ አንዳንዶቹም ከመግባቱ በፊት ሕዝባቸውን ከእልቂት ለማዳን ያስችላሉ ያሏቸውን እርምጃዎች ወስደዋል። እነዚህ እገዳዎችን ያካተቱ እርምጃዎች ሕዝብን ለማዳን ሲባል የአገርን፣ የሕዝብን እና የግለሰቦችንም ጥቅሞች እንደ መሰዋት የሚቆጠሩ ናቸውና፣ ቀላል ሊባሉ የማይገባ ናቸው። ምክንያቱም ዕገዳዎቹ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎችን በሙሉ አስታጉለዋልና።

ቆየት ብሎ እነዚሁ አገራት ቀስ በቀስ እገዳዎችንና ክልከላዎችን እያላሉና አንዳንዴም ሙሉ በሙሉ እያነሱ፣ በአንድ በኩል ወረርሽኙ በሌላ በኩል የእንቅስቃሴ ገደቡ በአገርና በሕዝብ ላይ የሚያደርሱትን ጉዳት እያመዛዘኑ ኑሮን ለማስቀጠል ሲተጉ ታይተዋል። ረገብ አለ ብለውት የነበረው የወረርሽኙ ስርጭት የማገርሸት አዝማሚያ ሲያሳይም እንደገና ወደ እገዳዎችና ክልከላዎች ሲመለሱም ተስተውሏል።

ብዙዎቹ አገራት ዕገዳዎችን አንስተው የተለመደው እንቅስቃሴ በከፊል ወይም ሙሉ በሙሉ እንዲመለስ የፈቀዱት በኮቪድ 19 የሚያዙ ሰዎች እና በቫይረሱ የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር ጉልህ በሆነ መጠን መቀነሳቸውን ካረጋገጡ በኋላ ነው። ብዙዎቹ አገራት እገዳዎችን ሲያነሱ በአንዳንድ ጉዳዮች ላይ የተወሰኑ ገደቦችን በማስቀመጥና ጥብቅ ቁጥጥሮችን ማካሄድንም ታሳቢ አድርገው ነው። በተቃራኒው አሜሪካንና ብራዚልን የመሳሰሉ አገራት መሪዎቻቸውና ጥቂት የማይባሉ ዜጎቻቸው ጉዳዩን እንደ ጨዋታ በመቁጠር ሁሉንም ነገር ያለ ጥንቃቄና የሕክምና ባለሙያዎችን ምክር በመጻረርም ጭምር ስላካሄዱት ጠቅላላው ሕዝባቸው ከፍተኛ ዋጋ በመክፈል ላይ ይገኛል።

የጤና ሚኒስትር ሊያ ታደሰ አካሄድስ እንዴት ይገመገማል?

የኢትዮጵያ ጤና ሚኒስቴር መስከረም 8 ቀን 2013  እገዳዎች ያለ ገድብ እና ያለ ልዩነት እንዲነሱ ምክር ሐሳብ አቅርቦ ምክር ቤቱም ውሳኔ አሳልፎበታል። የዚህ እገዳ አነሳስ በጣም አስደንጋጭና ምክንያታዊነቱም ሚዛን የሚደፋ አይደለም። ምክንያቱም በኢትዮጵያ በበሽታው የሚያዙ ሰዎች ቁጥር እየጨመረና የሟቾች ቁጥርም ከፍ እያለ ባለበት ጊዜ ነው፣ ሁሉም እንቅስቃሴ ያለ ገደብ እንዲከፈት የተፈቀደው።

ከሕዝብ ብዛት አንጻር ሲታይ ኢትዮጵያ የምታካሂደው የኮቪድ-19 ምርመራ ዝቅተኛ ተብሎ የተመደበ ከመሆኑም በላይ፣ ምርመራ የሚደረግላቸው ሰዎች ቁጥር እየቀነሰ ከተመረመሩት ውስጥ በበሽታው ተጠቂ ሆነው የሚገኙት ሰዎች ብዛት ግን በመጨመር ላይ ነው። ይህን በመመልከት ብቻ የጤና ሚኒስቴር ምክረ ሐሳብና የምክር ቤቱ ውሳኔ በድፍረት ላይ ተመርኩዘው የተሰነዘሩ መሆኑን ያሳያል።

ከዚህ ቀደምም ወረርሽኙን የሚያስተላልፈው ሕዋስ በአፍ፣ አፍንጫና ዐይን ወደ ሰው አካል እንደሚገባ እየተነገረ፣ በሌላ በኩል በጤና ሚኒስትር ባለሙያዎችም ጭምር የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭንብልን የማጣጣል ዘመቻ በሰፊው እየተካሄደ ነበር። ወደ ታክሲና ከተማ አውቶብሶች ስንገባም በር ላይ እጃችንን በአልኮል እያጸዳን አፍና አፍንጫችንን ክፍት ትተን፣ አገር ሰላም ብለን እንድንጓዝ ያደረገን የጤና ሚኒስቴር ምክር እንደነበረ አይረሳም። አሁን ደግሞ ሌላ ከእውቀት የራቀ የድፍረት ምክረ ሐሳብ አቅርቦ እንዳይሆን መስጋት ተገቢ ነው።

ከፍተኛ የጤና ባለሞያ የሆኑ ባለሥልጣናት ወረረሽኙ ወደ ኢትዮጵያ ገብቶ ከአንድ ወር ላላነሰ ጊዜ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭንብልን በሰፊው መጠቀም ሳይበረታታና ሳይመከር የቆየው የማስክ ውጤታማነት አጠያያቂ ስለነበረ፣ በሳይንሳዊ ምርምር ያልተደገፈ ምክረ ሐሳብን ለሕብረተሰብ ማስተላለፍ አደገኛ ስለሆነ ነው ሲሉ ተሰምተዋል። ነገር ግን በኢትዮጵያ ይህን የመሰለ ቀልድ ከመሰማቱ ከስድስትና ከሰባት ወራት በፊት የቻይና የጤናው ዘርፍ ተመራማሪዎችና ምሁራን ማስክ ጠቃሚ መሆኑንና ቻይናን ከታደጓት ነገሮች እንዱ ማስክን በሰፊው መጠቀሟ መሆኑን ሲወተውቱና ሲያሳስቡ ነበር።

ቻይና እንግዳውን ወረርሽኝ የተጋፈጠችው የመጀመሪያዋ አገር ሆና ወረርሽኙን በውጤታማ መንገድ የተከላከለችና በጣም ዝቅተኛ የሆነ ጉዳት ብቻ አስተናግዳ ችግሩን በማሳለፍ ላይ ያለች አገር ነች። ስለሆነም ባለሙያዎቿ የሰጡት ምክር ችላ ሊባል አይገባውም።

የጤና ሚኒስቴራችን ሌላም የድፍረት ሥራ አስመዝገቧል። በኢትዮጵያችን በኮቪድ-19 ከተያዙ ሰዎች ምልክት አላሳዩም የተባሉት ወደየቤታቸው እየሔዱ ራሳቸውን እንዲያስታምሙ እየተደረገ ነው። ስንት ታማሚዎች ወደ ስንት አካባቢዎች እንደተላኩ በግልጽ የሚነገር ነገር የለም። እነዚህ ታማሚዎች ከበሽታው እስኪያገግሙ ወይም በሽታው ብሶባቸው የሐኪም ክትትልና የመሣሪያ ድጋፍ አስፈልጓቸው ወደ ሕክምና ማዕከላት እስኪሄዱ፣ በየቤታቸው ስንት ወራትን እንደሚያሳልፉ፣ እያንዳንዱን ዕለትና ሰዓት በቤታቸውና በአካባቢያቸው እንዴት አድርገው እንደሚያሳልፉት እየተከታተለ በሽታው እንዳይዛመት የሚሠራ ቡድን ስለመኖሩም የሚታወቅ ነገር የለም።

ወደየቤታቸው የሚሸኙ ታማሚዎች በቤታቸው ለእነሱ ብቻ የሚመደብ ክፍል መኖሩ ተረጋግጦ፣ ከሌሎች የቤተሰብ አባላትና ከጎረቤቶች ጋር ንክኪና ቅርርብ እንዳይኖራቸው የሚደርግ የቤትና የግቢ ሁኔታ ያላቸው ሰወች ናቸው ብለን ተስፋ እናድርግ። ነገር ግን ከእነዚህ ዓይነት ቤተሰቦች ስንቶቹ ናቸው ለታማሚው ለብቻው መጸዳጃና ሌሎችን መገልገያዎችን ሊያሟሉ የሚችሉት? ስንቶቹ ቤተሰቦችና ታማሚዎችስ ናቸው የቤታቸው ችግር ወደ ጎረቤቶቻቸውና ወደ አካባቢያቸው እንዳይዛመት እያደረጉ ወራትን የሚቆጥሩት? በጥቅሉ የጤና ሚኒስቴር ውሳኔ ብዙዎችን ለስጋት የዳረገና ብዙዎችን በማነጋገር ላይ ያለ የድፍረት ሥራ መሆኑ ሊረሳ አይገባም።

ሌላም አለ፤ በጣም ውስን በሆነ መጠን እና ብዙውን ጊዜም በአዲስ አበባና በክልል ከተሞች ከሚሞቱ ሰዎች በጣም ለጥቂቶቹ ብቻ ይደረግ የነበረው ከኮቪድ-19 ጋር የተያያዘ የአስከሬን ምርመራ ቆሟል። ይህ ምርመራ መደረግ የሚገባው ለሟቹ ጥቅም ተብሎ ሳይሆን ከሟቹ ቤተሰቦች ጀምሮ እስከ ጠቅላላው ሕዝብ ለበሽታው ያለውን ተጋላጭነትና የበሽታውን የመስፍፍት አድማስ በማወቅ የጥንቃቄ እርምጃዎችን ለመውሰድ ነው።

በአስከሬን ላይ የሚደረገው ምርመራ እንዲቆም የተላለፈው ውሳኔ አደገኛና አስደንጋጭ የድፍረት ውሳኔ ነው። ጤና ሚኒስቴር ከዚህ ቀጥሎ የሚሰነዝራቸውን ውሳኔዎች በግምትና በመሰለኝ ላይ ተመርኩዞ ለማድረግ እንደሚገደድም መገመት ይቻላል። ለዚህ ውሳኔ የቀረበው ምክንያት ሕብረተሰቡን ቅር እያሰኘ ነው የሚል ነው። ይህም በሚኒስቴሩና በኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ባለሥልጣናት ከተሰጡ ሙያዊ ያልሆኑ ምላሾች እንደ አንዱ ሆኖ ሊቆጠር የሚገባው የድፍረት ሰበብ ነው። ተጠያቂነት የሚያስከትል ችግር ወይም ወቀሳ ከመጣ ጉዳዩን በሕዝብ ላይ ለማላከክ ታስቦበት የተሰነዘረ ሰበብም ይመስላል።

ከላይ የተጠቀሱት እርምጃዎች የተወሰዱት ችግር ስለማያስከትሉና ከሕብረተሰብ ጤና አጠባበቅ አንጻር ተገቢነት ኖሯቸው ሳይሆን ወጭን በመፍራት መሆኑን መካድ አይገባም። በዚህ የጭንቅ ጊዜ መናፈሻዎችንና መዝናኛዎችን፣ ፏፏቴዎችንና የውሃ ጌጣ-ጌጦችን እየሠራ፣ ሥራው ያላለቀ ግንባታን በመመረቅ፣ ሰበብ እየፈጠረ ወታደራዊ ትርኢቶችን እና የዘፈን ድግሶችን በማካሄድ በቢሊዮኖች የሚቆጠር ብር የሚከሰክስ መንግሥት፣ የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመዋጋትና ችግሩን በተገቢ መንገድ ለመያዝ ገንዘብ አነሰው ሲባል ምን ማለት እንደሚገባ ግልጽ አይደለም።

በአጭሩ ከፍተኛ የድፍረት ሥራ እየተሠራ ነው ማለት ይቻላል። እነዚህ ጊዜ ቢሰጣቸውና ቢዘገዩ ምንም ችግር የማያመጡ፣ ነገር ግን ከፍተኛ ወጭን እየጠየቁ የሚካሄዱ ፕሮጀክቶችና ፕሮግራሞች ለጊዜው ገታ ተደርገው፣ ገዥው ቡድን በሙሉ ኃይሉ ወረርሽኙን ወደ መዋጋቱ ፊቱን እንዲያዞር የሚጠይቅ ባለሥልጣን፣ ሹመኛና ባለሙያ አለመኖሩ ‹ይህ ገዥ ቡድንና ለሕዝብና ለአገር ማሰብ አቁሟልን?› ብሎ ለመጠየቅ ያስገድዳል። በተለይም ‹የጤና ሚኒስትሯ ተልዕኮ ሕዝብን በሙያቸው ማገልገል ነው ወይስ የአገዛዙ ታማኝና ታዛዥ አገልጋይ ሆነው ሥልጣናቸውን ማስቀጠል?› ብሎ ለመጠየቅም የሚያሳሳ ነው።

ይህ በእንዲህ እያለ ነው የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ ምርጫ ማካሄድንና ትምህርት መጀመርን ጨምሮ ማሕበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎች ወደ መደበኛ ሁኔታቸው ከጥንቃቄ ጋር መመለስ እንደሚችሉ ለተወካዮች ምክር ቤት ምክረ ሐሳብ አቀረቡ የተባለውና ምክር ቤቱም ሐሳቡን የተቀበለው።

የጤና ሚኒስቴር ምክረ ሐሳብን ተከትሎ ጥቂት ሺሕ ስፖርተኞችን ከሚመራው ከዱቤ ጅሎ ስፖርት ኮሚሽን ጀምሮ ወደ 30 ሚሊዮን ለሚጠጉ ሕጻናት፣ ወጣቶችና ጎልማሶች ኃላፊነት የመውሰድ ግዴታ እስካለበት ትምህርት ሚኒስቴር ድረስ በእርግጠኝነት ሥራቸውን እንደሚቀጥሉ ተናግረው በማስነገር ላይ ናቸው። እንቅስቃሴዎቻቸውን ለመጀመር ዝግጅት እየጨረሱ መሆኑንም ፈጥነው ነው የነገሩን።

የፊልም ሠሪዎች ማሕበርም ከመስከረም 29/2013 ጀምሮ ሲኒማ ቤቶችን ከፍቶ ሥራ እንደሚጀምር ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል። ለመሆኑ በሽታው ከመስፋፋት ሳይገታ፣ የኮቪድ-19 ታማሚዎችና የሟቾች ቁጥር ሳይቀንስ ሙሉ በሙሉ እንቅስቃሴዎችን ያለ ገደብ የከፈተውና ለኢትዮጵያ አብነት ሆኖ እያገለገለ ያለው አገር የትኛው ይሆን?

 ልምድ ከማን?

ይፋ የተደረጉ የምርምር ውጤቶች የወረርሽኙ መንስኤ የሆነው ቫይረስ በአየር ላይ በጣም ለረዥም ጊዜ እንደሚቆይና ቫይረሱ ካለበት ሰው ከኹለት ሜትር በላይ የራቀ ሰውንም ሊያጠቃ እንደሚችል እያሳየ ነው። እናም ብዙዎችን በአንድ ክፍል ወይም ቦታ ለረዥም ጊዜ በሚያቆዩ ጉዳዮች ላይ ገደብ አለመኖሩ አጠያያቂ ነው።

በእርግጥ ባለሥልጣናት ነገሮችን የሚኮርጁት ግራና ቀኝ እያዩና እያመዛዘኑ አይደለም። ይልቁንም በጤና ሚኒስትሯ እና በምክር ቤቱ በተቀደደው ቦይ ለመፍሰስ ሰበብ የሚሆናቸውን ብቻ እየመረጡ ምክንያታዊ ለመምሰል ይከጅላሉ። ዱቤ ጅሎ እና በስፖርቱ ዘርፍ የተሰማሩ ከአቶዎች እስከ ዶክተሮች በኢትዮጵያ የስፖርት ውድድሮችን ለመጀመር በአውሮፓ የእግር ኳስና ሌሎች ስፖርታዊ ውድድሮች መካሄድን እንደ ማነሳሻ መቁጠራቸውን ነግረውናል።

ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ተመርጠው ጥሪ ከተደረገላቸው ወደ 40 የሚሆኑ ተጫዋቾች ውስጥ 36 የሚሆኑት መገኘታቸውና በነዚህ ተጫዋቾች ላይ የተካሄደው የኮቪድ-19 ምርመራ አምስቱ በበሽታው የተያዙ መሆናቸውን እንዳረጋገጠ ይፋ ሆኗል። በሁሉም የስፖርት መስኮች የሚካፈሉ ሁሉም ስፖርተኞች ቢመረመሩ ምን ያህሉ ይሆን በሽታው የሚገኝባቸው? ትምህርት ቤትንስ በሚመለከት፣ ሁሉም ተማሪዎች አስቀድሞ እንዲመረመሩ ቢደረግ ምን ያህሉ ይሆኑ ተጠቂዎች ሆነው የሚገኙት?

የጤና ባለሙያ በሆኑት በዶክተር ሊያ ታደሰ ምክረ ሐሳብና የፖለቲካዊ ‹አሻንጉሊትነት› ድራማ የመተወን በቂ ልምድ ባለው ምክር ቤት ውሳኔ፣ የኢትዮጵያችን ጥቂት ወይም ብዙ የኮቪድ-19 ተጠቂዎች ከጤነኞች ጋር ተቀላቅለው የሚሠሩበት፣ የሚማሩበት፣ የሚወዳደሩበትና የሚኖሩበት ዘመን ተጀምሯል። ቀጣዩ ነገር በዕድልና በአጋጣሚ የሚወሰን ነው።

የጤና ሚኒስትሯ መስከረም 8/2013 በተወካዮች ምክር ቤት ተገኝተው የኮቪድ-19 ወረርሽኝን በሚገባ መቆጣጠር በሚቻልበት ደረጃ ላይ መድረሱን ሲገልጹ የሕብረተሰቡ ግንዛቤና የማስክ አጠቃቀም በጥሩ ደረጃ ላይ መገኘቱን፣ በሽታውን በመመርመር በኩልም በአገሪቱ የመመርመሪያ መሣሪያ ማምረት መጀመሩን አልፎም አሳሳቢ ጉዳይ እንደሌለ አውስተው ነበር እገዳው እንዲነሳ አረንጓዴ መብራት ያበሩት። ከዚያኑ ዕለት ጀምሮ ጭፈራ ቤቶች፣ ሆቴሎችና መጠጥ ቤቶች፣ ካራምቡላ ቤቶችና ሌሎች ወጣቶችና ጎልማሶች የሚሰባሰቡባቸው ቦታዎች ከሚገባው በላይ በሰዎች ተሞልተው ውለው እያመሹና አንዳንዶቹም አምሽተው ሌሊቱን እያጋመሱ መሆኑ እየታየ ነው። ሌሊቱን ከማጋመስ አልፈው የሚያነጉስ ይታጡ ይሆን?

የሊያ ታደሰ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት ሥራ መጀመር ያለባቸውንና የሌለባቸውን፣ ያለ ገደብ ክፍት መሆን የሚገባቸውንና የማይገባቸውን ለመለየትም አልተጨነቀም። ሌላው ቢቀር መዝናኛ ስፍራዎች ሊያስተናግዱት ስለሚገባቸው የሰው ብዛትና ክፍት ሆነው ሊቆዩ የሚገባበትን ሰዓት በሚመለከት ምንም ዓይነት ገደብ አለመቀመጡ አስደንጋጭ ነው። በሺዎች በሚቆጠሩ ሰዎች ልቅነት ሲታይ በሚሊዮኖች የሚቆጠር ሕዝብ ችላ እያለ ነው ተብሎ ሲወነጀል ነበረ የከረመው። አሁን ደግሞ በእነዚሁ በሺህ የሚቆጠሩ ግለሰቦች ግዴለሽነት በሚሊዮኖች የሚቆጠር ሕዝብ ለአደጋ እየተጋለጠ ነው።

እነዚህ በሺሕ የሚቆጠሩ ሰዎች ወደየመሥሪያ ቤቱ፣ ወደየትምህርት ቤቱና ወደ ሌሎችም ሕዝብ ሥራ በሚሠራባቸውና አገልግሎት በሚያገኝባቸው ቦታወች እየሄዱ ስለሚቀላቀሉ የሚኒስቴር መሥሪያ ቤት ያስጀመረው ዘመቻ ‹እያንዳንድህ ራስህን አድን› የሚል ብቻ ሳይሆን፣ አለፍ ብሎ ‹እያንዳንድህ የራስህ ጉዳይ› የሚል ይመስላል። የትኛው ፈላስፋ ነበረ የሕዝብ ቁጥርን እንደ እርግማን የሚቆጥረውና የሕዝብ ቁጥር በግዙፉ የሚቀንሱ ዘዴዎችን በመጠቀም ብልጽግንና ሰላምን ማስፈን ይቻላል ያለው?

ዕገዳዎችን ባነሱ በርካታ አገራት ሆቴሎች፣ ሬስቶራንቶችና መጠጥ ቤቶችን የመሳሰሉ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ቀድሞ ማስተናገድ ከሚችሉት የሰው ብዛት ግማሹን ወይም ሩቡን ብቻ እንዲያስተናግዱና በምሽቱ የአገልግሎት ጊዜያውም የሰዓት ገደብ ተቀምጧል። ጎረቤታችን ኬንያ እንደ ኢትዮጵያ ዕገዳዎችን ያነሳችው ሰሞኑን ነው። ነገር ግን ከዕገዳው ጋር አልኮል መጠጥንም ከልክላ የቆየችው ኬንያ፣ የአልኮል መጠጡን ዕገዳ በብዙ ውዝግብ ስታነሳ፣ መጠጥ ቤቶችና ሌሎች መዝናኛ መሰል አገልግሎት ሰጪዎች ከምሽቱ ሦስት ሰዓት በኋላ ሥራቸውን እንዲያቆሙ ጥብቅ ትዕዛዛ አስቀምጣለች።

ጎረቤት ኬንያ ትምህርት የመጀመሩን ጉዳይ ስታነሳ ከካድሬዎችና ከሕክምና ሙያ ጋር ምንም ዝምድና የሌላቸውን ሹማምንትና ባለሥልጣናት እያንጋጋች ብዙ ስብሰባ ማካሄድ አላስፈለጋትም፣ ይልቁንም የሕክምና ባለሙያዎችን በስፋት አነጋግራለች። የባለሙያዎቿ ምክረ ሐሳብ ሲጨመቅ የኮቪድ-19 ባህሪ ተሟልቶ ተገማች ባልሆነበት በዚህ ጊዜ ትምህርት ቤቶችን መክፈት ‹ተማሪዎችን እንደ ቤተ-ሙከራ ኣሳማ ከመቁጠር ተለይቶ አይታይም› ብለው የነገሩን አደገኛነት በመግለጻቸው፣ የኬንያ መንግሥት ጉዳዩን በይደር ያቆየው ዘንድ ተገድዷል።

የጤና ሚኒስቴራችን ሁሉንም ያለ ገደብ ከፋፍቶ፣ ዕድልና አጋጣሚ በየትምህርት ቤቱና በየሰፈሩ የሚያመጡትን ነገር ማየቱን የመረጠ ይመስላል። ሌሎች የኢትዮጵያ ባለሥልጣን ተቋማትም እንደዚሁ። ቆየት ብሎ መጠየቅ ሲመጣ ‹ታዝዤ ነው፣ ተላላኪ ስለነበርኩ ነው› ማለት አዋጭ አይሆንም። እንደ ብልጣ ብልጥ ‹የቀድሞ› ኢሕአዴጋውያን ሥየተሰጠኝ ሥልጣን የእነ እንቶኔን ሥልጣን ለማራዘም ሲባል የተሰጠኝ ስለሆነ ስህተት እየተፈጠረ መኖሩ ግድ ነበረ።› …ወዘተ የመሰለ ኑዛዜ ጊዜው እያለፈበት ነው።

መስከረም 8/2013 ዕገዳወች እንዲነሱ፣ ምርጫን መካሄድንና ትምህርትም መጀመርን ጨምሮ ሁሉም እንቅስቃሴዎች ወደነበሩበት እንዲመለሱ ምክረ ሐሳብ ተሰጥቶ ሳምንት ሳይደፍን፣ ሚኒስትሯ መስከረም 11/2013 ሌላ መግለጫ ለጋዜጠኞች ሰጥተዋል። በዚህኛው መግለጫ ለምክር ቤቱ ዕገዳውን ለማንሳት ታሳቢ የተደረጉ በጎ ነገሮች ብለው ከሰነዘሯቸው ሐሳቦች የሚቃረቡ እውነታዎችን እያስቀመጡ ሕብረተሰቡ እንዲጠነቀቅ ተናግረዋል።

ከመመርመሪያ መሣሪያዎች ብልሽትና ከተፈላጊ ግብአቶች አቅርቦት እጥረት የተነሳ ምርመራ በተገቢው መጠን እየተካሄደ እንዳልሆነ፣ የሕብረተሰቡ ቸልተኝነት አሳሳቢ ደረጃ ላይ መሆኑን በመግለጽ ትኩሱን አለሎ ከእጃቸው ለማውጣት ሙከራ አድርገዋል። መስከረም 26/2013 የሩብ ዓመት ሪፖርት ሲያቀርቡም፣ መንግሥት ወረርሽኙን ለመዋጋት ከፍተኛ ገንዘብ መከስከሱን ሲናገሩ የሕብረተሰቡ ቸልተኛነት የመንግሥት ጥረት ውጤታማ እንዳይሆን እያደረገ ነው ሲሉ ውንጀላ አሰምተዋል።

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የታወጀባቸውን ጊዜያት በሙሉ የብልጽግና ቡድን ሥልጠና፣ ግምገማ፣ ንቅናቄ መፍጠር፣ አምስት ቢሊዮን ችግኝ መትከል፣ የግድቡ በውሃ መሙላት ደስታ መግለጫ፣ የሙዚቃ ድግስ ወዘተ እያለ ከአራት በላይ ሆኖ መሰብሰብ ክልክል ነው የሚለውን ሕግ ሲጥስና ሌሎችም እንዲጥሱት ሲያስደርግ በዝምታ ያለፉት ሚኒስትሯ፣ ሕዝብን መወንጀላቸው ለትዝብት የሚዳርጋቸው ነው። ተጠያቂነትን ወደ ሌላ ለማሸጋገር እንደ መጣርም ይቆጠራል። ለፖለቲካ ታማኝነት ሲሉ ሙያዊ ኃላፊነታቸውን መወጣቱን እንደ ትኩስ የብረት አለሎ ቆጥረውታል። እናም ወደ ሌላው እየወረወሩት ነው።

ትኩሱን አለሎ በቶሎ ወደ ሌሎች ለመወርወር ቸኩሎ የታየው ሌላው ትምህርት ሚኒስቴር ነው። የክልል ትምህርት ቢሮ ኃላፊዎችን ጠርቶ ትምህርት መጀመር እንደሚቻል፣ ነገር ግን ትምህርት የሚጀመረው የትምህርት ቢሮ ኃላፊዎች በስራቸው የሚገኙ ትምህርት ቤቶች በሙሉ ኮቪድ-19 ችግር በማይፈጥርበት ሁኔታ ውስጥ መገኘታውን ሲያረጋግጡ መሆኑን ነግሮ ሸኝቷቸዋል። የትምህርት ቢሮዎች ኃላፊዎችም ትኩሱን አለሎ ይዘው ሄደው የወረዳና ትምህርት ጽሕፈት ቤት ኃላፊዎችን፣ ዳይሬክተሮችን፣ የመምህራን ማሕበር ወኪሎችን፣ ወላጆችን ወዘተ…. ጠርተው ኃላፊነቱን ወደ ትምህርት ቤት ዳይሬክተሮች የማሸጋገር ሥራ በመሥራት ላይ ናቸው።

የትምህርት ቤት ዳይሬክተሮች ትኩሱን አለሎ ወደ ሌላ ወርውረው እርፍ የማለት ዕድሉ ባይኖራቸውም፣ ከወላጆችና ከመምህራን ጋር አለሎውን እየተቀባበሉ ጊዜአቸውን እየገፉት ነው። ልማታዊ ጋዜጠኞች ትምህርት ቤቶችን ጎበኘን እያሉና በየትምህርት ቤቱ የሚገኙ እነሱን መሰል ልማታዊ ካድሬዎችን በማነጋገር ትምህርት ለመጀመር እንቅፋት የሚሆን የጎላ ችግር እንደሌለና ዝግጅቶችን እየተጠናቀቁ መሆኑን እየነገሩን ነው።

በሕወሐት/ኢሕአዴግ ስርዓት የዳበረው ከላይ የተወረወረን ትዕዛዝ፣ ያለምንም ማመዛዘንና ያለ አንዳች ጥያቄ እንደወረደ ለመተግበር የመጣደፍ ባህል በኢሕአዴጉ ብልጽግናም ቀጥሏል። ብልጽግና የሚባለው ቡድን ያስተዳድራቸዋል በሚባሉት በአዲስ አበባና በክልሎች ከሚገኙ የመንግሥትና የፓርቲው ሚዲያዎች በሚሰሙት ወሬዎች መሰረት፣ ጤና ሚኒስትሯ እና ትምህርት ሚኒስትሩ ያወረዱት መመሪያ በቀጥታ ተግባራዊ ከመሆን ፍንክች እንዳይል ተደርጎ ነገሮችን ሁሉ በታማኝ ካድሬአዊ ጥንቃቄ ለመተግበር ሥራዎች እየተሠሩ መሆናቸውን መረዳት ይቻላል።

ሐኪሞችና ወታደሮች መስዋዕትነትን እንደተጋፈጡት ሁሉ መምህራንም ሊጋፈጡት ይገባል ከሚለው የቆራጥ ታጋዮች ቀረርቶዎች ጀምሮ፣ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭንብልን፣ ሳኒታይዘርን እንዲሁም በየክፍሎቹና በግቢው የሚረጩ ኬሚካሎችን አሟልተን ሥራችንን በስኬት እናካሂዳለን እስከሚሉ የካድሬ ቱሪናፋዎች እንደ ዋዛ እየተስተጋቡ ትምህርት ይጀመር የሚለው የባለሥልጣናት መመሪያ ሊተገበር እየተቸኮለ ነው።

የሕክምና ማዕከላት የማስክ እጥረት እሮሮዎች ጋብ ሳይሉ፣ የመዲናዋ የአዲስ አበባ ዋና ዋና መንገዶች አንድ ጊዜ ብቻ በጸረ- ተሕዋስ ኬሚካል ተረጭተው መድገም ባልተቻለበት ሁኔታ በየትምህርት ቤቱ፣ ለዐስር ወራት የኮቪድ-19 መከላከያ ቁሳቁሶችና ኬሚካሎች እንዴት እንደሚሟሉ ሊነግሩን ግዴታ አለባቸው፤ የጤና ሚኒስትሯ እንዲሁም የእሳቸውን ምክር ሃሳብ እንዳለ ተቀብለው መመሪያ በመስጠት እፎይ ሊሉ የሚሞከሩት የትምህርት ሚኒስትሩ። እስከ አሁን ምንም ያላሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩስ የሚሆነውን ሰምተው ይሆን?

ትምህርት ሚኒስቴር ትምህርት ቤቶች በሦስት ዙር እንደሚከፈቱ ያሳወቀ ሲሆን፣ በአንደኛው ዙር በገጠር ቀበሌዎችና ወረዳዎች፣ በኹለተኛው ዙር በዞንና በክልል ከተሞች፣ በሦስተኛው ዙር በአዲሰ አበባና በዙሪያዋ የሚገኙ ትምህርት ቤቶች እንደሚከፈቱ አሳውቋል። ይህ ተራ የወጣው የቫይረሱ ስርጭት ከፍተኛ የሆነባቸውን ለማዘግየት ታስቦ ነው ተብሏል። ከዚህ ጋር ኮቪድ-19 ለመከላከል የሚያስችል ቁመና ላይ የማይገኙ ትምህርት ቤቶች እንደማይከፈቱ ተነግሯል።

ይህ የሦስት ዙር አከፋፈት የታማሚዎችን ቁጥር መሰረት ያደረገ ነው ቢባልም፣ በተቃራኒ ደግሞ የተሻለ ግንዛቤ ያገኘ ሕዝብ በሚኖርባቸውና ለኮቪድ-19 ምርመራም ሰፊ ዕድል አግኝተው በቆዩ አካባቢዎች ያሉ ትምህርት ቤቶችን አዘግይቶ በጣም አናሳ ግንዛቤ ያለባቸውንና ለኮቪድ-19 ምርመራም ያነሰ ዕድል ባላቸውን አካበቢዎች የሚገኙ ትምህርት ቤቶችን ያስቀደመ ሆኖ ይታያል።

በአንዳንድ ስብሰባዎች ላይ አሳሳቢው ጉዳይ የተማሪዎች ጤንነትና ትምህርት ቤት ውለው ወደ ቤተሰቦቻቸው ምን ይዘው ይመለሳሉ የሚለው ነገር ቢሆንም፣ በአንዳንድ ስብሰባዎች ላይ በኹለትና በሦስት ፈረቃ የሚሠሩ መምህራን ድካም፣ ቅዳሜ ለመሥራት ስለሚገደዱ መምህራን መብት፣ መምህራኑም ጭምር ለችግሩ ተጋላጭ ሊሆኑ እንደሚችሉና የመሳሰሉት ጉዳዮች እየተወሱ ነው። አሳሳቢው ነገር የመምህራኑ ጉዳይ ብቻ በሚስመስል ሁኔታ ‹መምህራን እንደ ሐኪሞች፣ ፖሊሶችና ወታደሮች መስዋዕት ለመሆን መዘጋጀት ይገባቸዋል› እየተባለ ዞሮ ዞሮ ጉዳዩ ጠቅላላውን ሕብረተሰብ የሚነካ መሆኑ ተሸፋፍኖ ሊታለፍ እየተሞከረ ነው።

መስከረም 20/2013 ቢቢሲ አማርኛ ላይ ሐሳባቸውን እንዲያጋሩ የተጋበዙ አንድ በአዲስ አበባ የሚገኝ ትምህርት ቤት ዳይሬክተር ምዝገባ ይካሄድ ከተባለበት ጊዜ ጀምሮ ወደ ኹለት ሺሕ ተማሪዎች የተመዘገቡ መሆኑን ገልጸዋል። ትምህርት ይጀመራል በመባሉም ደስተኛ አለመሆናቸውንና ነገሩ በጣም አደገኛ እንደሆነ ተናግረዋል።

ቪኦኤና ቢቢሲ ላይ ሐሳባቸውን እንዲሰነዝሩ ዕድሉን ያገኙ ወላጆች የሰነዘሯቸው ሐሳቦች ግልጽ የሚያደርጓቸው ኹለት ነጥቦች አሉ። አንዱና ዋነኛው ነጥብ በአዲስ አበባ የሚኖሩ ወላጆችና በክልሎች የሚገኙ ወላጆች ስለ በሽታው ያላቸው ግንዛቤ በጣም የተለያየ መሆኑ ነው። ኹለተኛው ደግሞ የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ኢትዮጵያ መግባቱን ተከትሎ ወላጆች ለልጆቻቸው ያደረጉት ጥንቃቄና ጥበቃ በኑሮ አቅማቸው ላይ የተመረኮዘ መሆኑን ነው። ስለዚህ ትምህርት የመጀመሩን ጉዳይ በሚመለከት የያዙት አቋምም በዚህ ላይ የተመረኮዘ ነው።

ከአዲስ አበባ ሐሳባቸው ከሰነዘሩት ወላጆች ብዙዎቹ በበሽታው አደገኛነትና ገዳይነት ላይ ተመርኩዘው አስተያየታቸውን ሲሰጡ፣ የክልል ወላጆች በአብዛኛው ‹ልጆች እስከ መቼ ሳይማሩ ቁጭ ይላሉ፣ ልጆች ለሥነልቦና ችግርና ለድብርት እየተጋለጡ ነው።› ወዘተ… በማለት አስተያየት ሰንዝረዋል። ከአዲሰ አበባ ውጭ አስተያየት ከሰጡ ወላጆች ውስጥ አንድ የአምቦ አባት ብቻ ነገሩን አክብደው በማየት ‹ሀብታም አገራት ያልቻሉትንና እያለቁበት ያለውን በሽታ መዳፈሩ ተገቢ አይደለም› ብለዋል። እኚህ ወላጅ ‹…በበሽታው የተያዘ ሰው ምልክት ሳያሳይ ለረዥም ጊዜ ይቆያል በሚባልበት ጊዜ፣ ልጆች ከየቤታቸው ወደ ትምህርት ቤት ምን ይወስዳሉ፣ ከትምህርት ቤት ወደ ቤታቸውስ ምን ያመጣሉ ተብሎ ውሳኔው በጥልቀት መታየት ነበረበት…› ብለዋል።

በባህርዳር ከተማ ኮንዶሚንየም ውስጥ የሚኖሩ አንድ አባት የኮንደምንየም ኑሮ በብዙ መንገድ ለመራራቅ የሚመች እንዳልሆነና በእሳቸው አመለካከት ትምህርት ቤት በመከፈቱና ባለመከፈቱ መካከል ልዩነት እንደሌለ፣ በመኖሪያው አካባቢ ልጆችን አብረው ከመዋል ማገድ እንደማይቻል ተናግረዋል። እናም ልጆቹ ከሌሎች ልጆች ጋር አብረው መዋላቸው ካልቀረ ትምህርት ቤት ቢውሉ ይሻላል ባይ ናቸው።

በተመሳሳይ በተለያየ ከተማ የሚገኙ ወላጆች ልጆቻቸውን ትምህርት ቤት መላክ በአንድ ጎን የሚስማሙበት ሲሆን፣ ስጋቱም የተለያቸው አይመስልም።

በተመሳሳይ አንድ የአዲስ አበባ ነዋሪ፣ ከኬጂ እስከ 10ኛ ክፍል የሚማሩ አራት ልጆች እንዳሏቸው ጠቅሰው 5ኛ እና 10ኛ ክፍል የደረሱትን ወደ ትምህርት ቤት እንደሚልኩ ኬጂ እና 1ኛ ክፍል የሆኑትን ግን የትምህርት ቤቶቹ ሁኔታ በማየት ሙሉ በሙሉ አስተማማኝ መሆናቸውን ማረጋገጥ እንደሚፈልጉና ቆየት እንደሚያደርጓቸው ተናግረዋል።

‹‹ልጄን ትምህርት ቤት ብልከው በበሽታው ሊያዝም ላይያዝም ይችላል። ነገር ግን ልጄ በበሽታው ተይዞ ከሚሞት ባይማር ይሻላል›› ያሉ ወላጆችም አሉ። በድምሩ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ዓለም ዐቀፍ ችግር መሆኑ እንደታወጀ፣ በአፍሪካ ወደ 30 ሚሊዮን የሚሆኑ ሰዎች በበሽታው ሊጠቁ እንደሚችሉና ከእነዚህ ውስጥ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ለህልፈት እንደሚዳረጉ ጊዜ የተጠቀሰለት ግምት ተቀምጦ ነበረ። ይህ የተፈራው ነገር ሳይደርስ ጊዜው አልፏል። ይህን መሰሉ የግምት መዛነፍ ለጤና ሚኒስትራችን የድፍረት ውሳኔ በር ከፍቶ ይሆን?

ግዛቸው አበበ በሙያቸው መምህር ናቸው። በኢሜይል አድራሻቸው gizachewabe@gmail.com ላይ ሊገኙ ይችላሉ፤

 

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com