ጥቅምት 2 እና የአድዋ ጉዞ

Views: 50

ይህ መስከረም 17 ቀን 1888 የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት ዳግማዊ አፄ ምኒልክ የጣሊያን ጦር ኢትዮጵያ በመውረር በቀኝ ግዛቱ ስር ለማዋል ማሰቡን በማረጋገጣቸው፤ በጣሊያን የወረራ ዝግጅት በመቆጣት የኢትዮጵያ ሕዝብ ለጦርነት እንዲዘጋጅ ያሳሰቡበት የክተት አዋጅ ነው።

አዋጁም ንጉሠ ነገሥቱ በሚመሩትና በሚያስተዳድሩት የሸዋ ጠቅላይ ግዛት እንዲሁም በየግዛቱ ባሉ የጦር መሪዎቻቸው፣ መኳንንቶች፣ የጦር አበጋዞች፣ በራሶች እንዲሁም በደጅ አዝማቾች በኩል በዛው ወቅት በየአካባቢው ላለው ኢትዮጵያዊ ሁሉ እንዲነገርም አስደረጉ። ከዚያም የንጉሡን የክተት አዋጅ ሰምቶ ከየአካባቢው የተሰባሰበው ጦር ወደ ሰሜን ዘመቻ ለማድረግ ጥቅምት 2 ቀን 1888 ኹለት ሰዓት ሲል ከአዲስ አበባ የአራዳ ጊዮርጊስ መናገሻ ፅጌ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተክርስትያን ላይ የቅዱስ ጊዮርጊስን ታቦት በመያዝ ወደ ዘመቻው ለመትመም ተነሳ።

አሁን 2013 ላይ እንገኛለን። ጀግኖች አያቶቻችን የዳግማዊ አፄ ምኒልክን ጥሪ ተቀብለው ወደ አድዋ ዘመቻ ጉዞ የጀመሩበት የጥቅምት 2 ታሪካዊ ቀንን ለማስታወስ በአገራችን የተለያዩ ክፍሎች ልዩ ልዩ መሰናዶች ይሰናዳሉ። ከእነዚህም መሰናዶዎች መካከል ዘንድሮ ለ8ተኛ ጊዜ ወደ ወደ አድዋ የእግር ጉዞ የሚያደርገው ጉዞ አድዋም ይገኝበታል።

ይህም መሰናዶ የፊታችን ሰኞ ጥቅምት 2/2013 በኢትዮጵያ ቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን አዳራሽ የሚከናወን ሲሆን፣ በዕለቱም የጉዞ አድዋ ስምንት ተጓዦች ምዝገባ በይፋ ይጀመራል። በጉዞ ዓድዋ 7 ለተሳተፉ ተጓዦችም የክብር ሜዳልያ ሽልማት እንደሚበረከት ከጉዞ አድዋ መሥራቾች መካከል ያሬድ ሹመቴ ለአዲስ ማለዳ አስታውቋል።

ያሬድ ከአዲስ ማለዳ ጋር በነበረው ቆይታ በኮቪድ 19 ምክንያት ጥንቃቄን ታሳቢ በማድረግ በእለቱ እንደ ከዚህ ቀደሙ ሰፋ ያለ ዝግጅት ባይኖርም፣ የተለያዩ ኪነ-ጥበባዊ መሰናዶዎች፣ አምና ለተጓዙ ተጓዦች የክብር ሜዳልያ ሽልማት፣ በወቅቱ የሚገለፅ የማዕረግ ሽልማት እንዲሁም የክብር እንግዶች በዓሉን አስመልክቶ መልዕክቶች ከመድረኩ የሚያስተላልፉበት ዝግጅት እንዳለ ጠቁሟል። በዋናነት ግን እለቱን የሚያወሱና የሚዘክሩ ልዩ ልዩ ዝግጅቶች እንደሚቀርቡ ገልጿል።

‹‹የምንኖርበት ዘመን ሁልጊዜ እንቅፋቱ እና መከራው ይበዛል።›› የሚለው ያሬድ፣ አሁንም እንደሱ አይነት ምልክቶች እየተስተዋሉ እንደሚገኙ በማንሳት ጥሩ ታሪክ አንድነትን ተላብሰን ጀግንነትን ያሳየንበት ጊዜ የሚያስታውሰን ነገር እንደሚያስፈልገንም ያስረዳል። ‹‹የእኛ ቅድመ አያቶች የሠሩትን ታሪክ እኛ እራሱ ሠራነው ብለን ኮርተን እንድንናገር የሚያስችል ወኔና ብርታት የሰጡንን አያት ቅድመ አያቶቻችንን ማስታወስ ያለብን ወቅት እንደሆነ ለማሰብም ጭምር ሁልጊዜም ቢሆን ጥቅምት ኹለትን እያከበርን አድዋን እያጎላን እንሄዳለን።›› በማለትም ይገልፃል።

ይህንን ታሳቢ በማድረግ እለቱን መዘከር ከጀመሩ ስድስት ዓመታት መቆጠራቸውን የሚያነሳው ያሬድ፣ ‹‹የአድዋን ድል ያገኘነው አንድ ሆነን ስንነሳ ነው›› በሚል መሪ ቃል ከጉዞ አድዋ ሦስት አንስቶ እስካሁን ባሉት ዓመታት እለቱ እየታወሰና በተለያዩ ደማቅ ዝግጅቶች እየተከበረ መዝለቁን ያወሳል። ድሮ መዘጋጃ ሜዳ የሚባለው ስፍራ ላይ ተከልሎ የነበረውን ቦታ በመቀበል አሁን ወደ የአድዋ ማእከልነት እንዲቀየር እየተሠራበት እንደሚገኝም አንስቶ፣ ለዚህም የማእከል ግንባታ ጉዞ አድዋ ትልቅ አስተዋፅኦ እንዳለው ገልጿል። በቦታው ላይ ማዕከሉ እንዲገነባ የመሠረት ድንጋይ የተጣለውም 2012 በዚሁ ታሪካዊ ቀን ጥቅምት ኹለት መሆኑንም ያስረዳል።

የ1888ቱ ጥቅምት ኹለት ለ2013 ጥቅምት?

‹‹እንዳንድ ጊዜ ታሪክ እራሱን ይደግማል ይባላል። ሁልዜም የአገር አንድነትን የሚያጠፉ፣ የመለያየት፣ የመነቃቀፍ እና የመቃቃር የሚመስሉ ምልክቶች ይታያሉ። እነዚህ ምልክቶች በሚኖሩበት ጊዜ አድዋን ማስታወስ በጣም ብልህነት ነው። የአድዋን ድል ለየት የሚያደርገው የአብሮነት እና ህብረት ፋይዳ የታየበት መሆኑና መጨረሻውም ከድል ጋር አብሮ መሰፋቱ ነው። ታዲያ ከታሪኩ የሚማር እና የኋላውን አገናዝቦ እውቀትን የሚጨብጥ ትውልድ፣ ከዚህ የበለጠ ወደፊት ለመሻገር እና ቀጣይ ሕይወቱን ቀና ለማድግ አይቸገርም። አለበዚያ አሁንም ለውድቀት ምልክት ሊሆኑ የሚችሉ ጉዳዮች በዙሪያችን እያንዣበቡ መሆናቸው በገሃድ የሚታይ እውነት ነው።

በመሰረቱ ቀድሞ የነበረ አንድነት አሁን ተሸረሸረ እና እየጠፋ ነው የሚለውን ንግርት እኔ አልቀበለውም። ቀድሞም ቢሆን ልዩነት ነበረን።›› ይላል ያሬድ። ይሄንንም በመቀጠል እንዲህ ሲል ያስረዳል፤

‹‹የአድዋ ድል ከመምጣቱ በፊት ሁሉም በየነገድና ጎሳው ተከፋፍሎ ዘመነ መሳፍንትንም አሳልፈናል። አፄ ቴዎድሮስ ኢትዮጵያን አንድ ለማድረግ ሲነሱ በጦር ኃይል ነው አንድ ያደረጉት። ያ ማለት ወደ አንድነት እና ህብረት ለመምጣት ሁሉም ፍቃድ ኖሮት አይደለም ወደ አንድነት ማእከሉ የገባው። የሚችል ተዋግቷል የተሸነፈው ደግሞ ገብሮ በኢትዮጵያ አንድነት ስር ገብቷል።

የአድዋን ለየት የሚያደርገው በአፄ ምኒልክ ጥበብ በየግዛቱ የነበሩትን አስተዳዳሪዎች፣ መኳንንቶች፣ ራሶች እና ደጅ አዝማቾችን ወደው በኢትዮጵያ አንድነት ስር እንዲጠቃለሉ ባደረጉት ሙከራ ነው። ከዚህም ባሻገር ውጊያ እንኳን የገጠሟቸውን የአውራጃ አስተዳዳሪዎችን መልሰው በየቦታቸው ላይ እየሾሙ አንድነትን ለመምጣት በጣም ከፍተኛ የሆነ ጥረት አድርገዋል። እና እንዲሁ ዝም ተብሎ እኛ ኢትዮጵያዊያን ጠላት ሲመጣ አንድ እንሆናለን የሚለው ንግግርም ልክ ነው ብዬ አላምንም። እንዳየሁትም ሆነ ከንባብ እንደተረዳሁት ትክክለኛ መሪ ያስፈልጋል።›› ሲልም ሕዝብን በአንድ ቦታ ላይ በማሰለፍ የአገር አንድነትን ለማስቀጠል የመሪነት ጥበብ እና ሆደ ሰፊነት እንደሚጠይቅ ያስረዳል።

የ2013 ጉዞ ዓድዋ ከነባራዊ እውነቶች አንጻር

ዘንድሮውን 125ኛ ዓመት የአድዋ ድል በዓል የካቲት 23 የሚታሰብና የሚከበር ሲሆን፣ የጉዞ አድዋ መርሐ ግብርም ለ8ተኛ ጊዜ ‹አድዋ የአፍሪቃ ድል!› በሚል መርህ በጥር ወር መግቢያ ይጀመራል ተብሎ ይጠበቃል። ታዲያ በዓሉም ሆነ ጉዞው እንደ ወትሮው ሁሉ በልዩ ድምቀትና ታሪካዊ ስርዓት እንዳይከናወን በዓለም ዐቀፍ ደረጃ የተከሰተው አስከፊው የኮሮና ወረርሽኝ እና ወቅታዊው የአገራችን የፖለቲካ ጉዳይ ተግዳሮት አይሆንበትም ወይ በማለት አዲስ ማለዳ ለያሬድ ሹመቴ ጥያቄን አቅርባለች።

ያሬድም ይሄንን ሲመልስ እንዲህ ይላል ‹‹ዳግማዊ አፄ ምኒልክ በ1888 መስከረም 17 ባስተላለፉት የክተት አዋጅ ላይ ‹እኔም የአገሬን ከብት ማለቅ የሰውን መድከም ዐይቼ እስካሁን ዝም ብለው፤ ደግሞ እያለፈ እንደ ፍልፍል መሬት ይቆፍር ጀመር።›› የሚል አለ። ይሄ ከ1881 እስከ 1888 ድረስ በጣሊያን እና በኢትዮጵያ መካከል የነበረውን ፖለቲካዊ ቁርሾና የሉዓላዊነት መደፈር ጉዳይ ጋር ተያይዞ ያለውን ነገር በጣም አለሳልሰው ይዘውት እንደነበር ያሳያል።

በተጨማሪም በወቅቱ በዓለም ዐቀፍ ደረጃ ትልቅ ወረርሺኝ ተከስቶ 500 ሚሊዮን ሰዎች በበሽታው ተይዘው ከዛ ውስጥ 50 ሚሊዮን የሚሆን ሕዝብ ያለቀበት ክስተት ተከስቶ ነበር። ያ ክፉ ቀን የመጣበት ወቅት እንደነበርና የታሪኩ አንድ አካል እንደነበረ ያሳያል። ስለዚህ ያኔም እንደ አሁኑ የኮሮናን ወረርሺኝ የሚመስል በሽታ ዓለም ላይ ተከስቶ የነበረበት፣ የርሀብ፣ የአንበጣ፣ የጎርፍና መሰል አሁን የምናያቸው አይነት ችግሮች ነበሩ። ስለዚህ የታሪኩ አንዱ አካል እንደነበሩ መታዘብ ያስፈልጋል።›› በማለት በየትኛውም ተግዳሮት ውስጥ ቢሆን በጥንቃቄና በፅናት ዓላማን ማስፈፀምና ለድል መብቃት እንደሚቻል ያስረዳል።

በተጨማሪም ተጓዦች የጥንቃቄ መርህ የሚባሉትን መርሆች በመከተል መጀመሪያ ሁሉም ጉዞው ላይ የሚሳተፉ ሰዎች የጤና ምርመራ እንዲያደርጉ እንደሚደረግና፤ ከአዲስ አበባም ሲነሱ ሁሉም ሰው ከቫይረሱ ነፃ መሆኑን ማረጋገጫ እንዲይዝ እንደሚደረግ ያሬድ ይጠቅሳል። ምናልባትም የተጓዦች እጥረት ሊከሰት ይችላል ለሚለው ከኹለትና ሦስት ዓመት በፊትም ፖለቲካዊ አለመረጋጋቶች ኖረው እና ልክ ያልሆኑ ዘመቻዎችም ተከፍተው ሕዝብ እንዲፈራ እና እንዲረበሽ በሚደረግበት ወቅት፣ ጉዞ አድዋ ላይ የተጓዥ እና ተመዝጋቢ ቁጥር መጨመሩን እና የበለጠ ፍላጎቱ እያደገ እንጂ እየቀነሰ እናዳልመጣ ያወሳል። የአቅም ውስንነት ከሌለ በቀር የፍላጎት መቀነስ ይታያል ብሎ እንደማያስብም ያስረዳል።

‹‹ነገር ግን›› ይላል ያሬድ፣ ‹‹ነገር ግን ሁሉንም ጉዞ ላይ የሚደረጉ ነገሮች ከውሀ አጠቃቀም ጀምሮ፣ በየቤቱ ሰዎች ምግብ ሲሰጡን፣ ሰው እኛን ለመቀበል ተሰብስቦ ሲመጣ፣ እግር ካላጠብኩኝ የሚለውም ምስኪን ሕዝብ ብዙ ነው። ሰው ቤት ውስጥ ሄዶ ማደር አለ። እነዚህን እነዚህን ነገሮች ለንክኪ ሊያጋልጡ ስለሚችሉ አስፈላውን ጥንቃቄ ወስዶ የጥንቃቄ መርሆውን በተከተለ መንገድ ጉዞውን ለማድረግ የሚጨምረው ተጨማሪ ወጪ አለ። እርሱን በቻልነው አቅም የሚያግዙንን ሰዎች ካበዛን እንወጣዋለን ብዬ አስባለሁ። ግን ያው አድዋ ፈተና እንደመሆኑ ከፈተና በኋላ ያለውን ድል ለማጣጣም ተዘጋጅተናል።›› ሲል የኮሮና ቫይረስን በሚመለከት የሚኖረውን ጥንቃቄ ያስረዳል።

‹‹ዘንድሮ የምናደርገውን የዓደዋ ጉዞ በአገራችን እየታየ ካለው የፖለቲካ አለመረጋጋት ጋር በማያያዝ እንዴት ልታደርጉት ነው የሚል ጥያቄን ብዙዎች ያነሳሉ።›› የሚለው ያሬድ፣ እንደግል ያለውን ሐሳብ ሲያስረዳ ‹‹ያን ያህል ችግር ይገጥመናል የሚል ጥርጣሬ የለብኝም። ችግር ቢገጥመንም እንኳን አድዋ እንደመሆኑ የአድዋ ድል ከመገኘቱ በፊት ትግል እንደነበር ሁሉ ይሄን በመገንዘብ በትግሉ የአባቶችን መከራ መቀበል ያን ያህል ችግር ያለው ነገር እንዳልሆነ አምነንበት ነው የምንገባው። ያም ሆኖ ግን ምንም አይነት ችግር ይኖራል ብለን አናስብም።

ምክንያቱም አሁን ያለው የፖለቲካ ግለት እና የእርስ በእርስ ንትርክ በእኔ እምነት በፖለቲከኞች መሀል የተደረገ ውዝግብ ነው። ይህም አይደለም ሕዝብ ለሕዝብ የሚደረግ ግንኙነትን ይቅርና፣ ፖለቲከኛው ከሕዝብ ጋር የሚያደርገውን ግንኙነት በራሱ ችግር ውስጥ ይከተዋል ብዬ አላስብም። ምክንያቱም እኛ ከየትኛውም የፖለቲካ አስተሳሰብና ከየትኛውም የፖለቲካ ቅርፅ ውስጥ ያለን አይደለንም። የሕዝብ ጉዞን የምንጓዝ ነን። ስለዚህ የሕዝቡን ጉዞ ሕዝቡ አያደናቅፈውም ብቻ ሳይሆን በኹለት ጎራ የተሰለፉ የፖለቲካ ኃይሎች ራሱ አያደናቅፉትም። ምክንያቱም ከሕዝቡ ጋር ፀብ አላቸው ብዬ አላምንም።›› ሲል የፖለቲካው አለመረጋጋት ያን ያህል በጉዞቸው ላይ የሚያሳርፈው ተፅዕኖ አለመኖሩን ይገልፃል።

አክሎም ‹‹በሰሜንም ይሰለፍ በደቡብ ከጉዞ አድዋ ጋር ችግር ያለበት የፖለቲካ ኃይል አለ ብዬ አላምንም። ሌላ ለብሽሽቅ አንዳንድ ሰዎች አሁን እዛ ብትሄዱ እንደዚ ይሆናል እንደዛ ይሆናል የሚሉ አሉ። ከዚህ በፊትም ተብለን እናውቃለን። ግን እኛ የምናውቀው የትግራይ ሕዝብ የኢትዮጵያ ህዝብ አካል ብቻ ሳይሆን የጥንታዊት ኢትዮጵያ መሰረት የተጣለበት፣ ጥንስሱ የተሟሸበት፣ ሁሉም ተቦክቶ የተጋገረበት ነው። የ3000 ዓመት ታሪክ ስንል መነሻው እና እንብርቱ እዛ ነው የሚለው ለሽንገላ አይደለም። እዛ ሄደንም ዐይተነዋል። አልጋውን ለቆ የሚያሳድር፣ መሶቡን ገልብጦ የሚያበላ ሕዝብ ነው። የመጨረሻ ፍቅፋቂም ብትቀር፤ የመሶቡ ክርክር ምልክት ያረፈበት የመጨረሻ እንጀራ እንኳን ሳይሰስት የሚያቀርብ ሕዝብ ነው።

ስለዚህ በእኛ እምነት ችግር በምንም ተዓምር ሊኖር አይችልም። እንግዲህ አሁን ባለው ጉዳይም ዙሪያ ባለኝ መረጃ መሰረት ከሕዝቡ ጋር እንዳትገናኝ የሚል ሕግ አልወጣም። ስለዚህ በሕግም በሞራልም የሚከለክለን ነገር የለም። እንደውም የበለጠ ፍቅርን የምናፀናበት፣ የበለጠ መተሳሰብን የምናሳይበት፣ እንደዚህ አይነት የችግር ሰዓት ላይ ብንችል እንደ ጋሞ አባቶች ቄጤማ ቆርጠን ሳር ጎዝጉዘን በፖለቲከኞቹ መሃል ያለውን ቁርሾ ለማላላት ሕዝቡ እንደማይነጣጠልን እንደማይለያይ ማሳየት ከቻልን ፖለቲከኞቹ ልባቸው ይመለሳል ብዬ አስባለሁ።

ስለዚህ እንደውም እስካሁን ካደረግነው ጉዞ በተለየ የአድዋን ትልቅ ተልዕኮ ያነገበ ጉዞ፤ በኢትዮጵያ ችግር ላይ ብቻ ሳይሆን በአፍሪካ ተስፋ ላይ ጭምር ተመርኩዘን ለማድረግ አስበናል።›› ሲልም በምንም አይነት ሁኔታ ውስጥ ቢሆን ጉዞውን የሚያስቀር ነገር አለ ብሎ እንደማያስብ ያስረዳል።

የጉዞ አድዋ ተጓዦች ቁጥር

ዘንድሮው በኮቪድ 19 ምክንያት ለወራት ለጉዞ አድዋ ገቢ መሆን የሚችሉ ሥራዎች አለመሠራታቸውን የሚያስታውሰው ያሬድ፣ በዚህም ሳቢያ በጣም አነስተኛ በጀት ላይ እንደሚገኙ ይገልፃል። ቢሆንም ግን በተቀሩት ጊዜያት ውስጥ የሚያግዙ ሰዎች ከመጡ የመጣውን ሰው ሁሉ ይዘን ለመሄድ ነው ፍላጎታችን ሲልም ያስረዳል።

የመጀመሪያው የጉዞ ዓድዋ መርሃ ግብር 5 ተጓዦችን፣ በኹለተኛው 6፣ በሦስተኛው 12፣ በአራተኛው በጣም ሁከት የነበረበት ወቅት ስለነበር 8፣ ከዛ 25፣ ከዛ 48 ሰው፣ በ2012 ሰባተኛው የጉዞ አድዋ መርሃ ግብር ደግሞ 63 ተጓዦች በጉዞው መሳተፋቸውን ያሬድ ጠቅሷል። የአሁኑን የተጓዦች ቁጥር መወሰን የሚቻለው የጥር ወር መጀመሪያ ላይ እንደሆነና የዚህም ምክንያት ደግሞ ብዙ ሰው ተመዘግቦ ሐሳቡን ሊቀይር፣ ላይመቸው፣ በምርመራ ሊወድቅ እንዲሁም በሌሎች ብዙ አይነት ጉዳዮች ሳቢያ ለጉዞው ብቁ ላይሆን ስለሚችል መሆኑን ያስረዳል።

የጉዞ ዓድዋ ግብና ስኬት

ጉዞ ዓድዋ ወደ ታሪካዊው የዓድዋ ተራራ የሚያደርገውን ጉዦ ከጀመረበት ከዛሬ 8 ዓመት በፊት አንስቶ እስካሁን ባደረጋቸው እንቅስቃሴዎች የሚፈለገው ያህል ተፅዕኖ መፍጠር ችሏል ወይ? በማለት አዲስ ማለዳ ላነሳችው ጥያቄ ያሬድ ተከታዩን ብሏል።

‹‹አንድ ትንሽዬ ጠጠር አንድ ኮረት ትነካለች፣ ያ ኮረት አንድ አሎሎ ነገር ይነካል፣ አሎሎው ድንጋይ ይነካል እያለ ትልቁ አለት መጨረሻ ሊንቀሳቀስ ይችላል። ስለዚህ ክብሪቱን እንደመለኮስ ጉዞ አድዋ፤ ለዚህ ላለንበት ዘመን እንቅስቃሴ የአድዋ ድል የበለጠ ክብር እና የበለጠ ቦታን እንዲይዝ ለማድረግ፤ በትውልድ ውስጥ የወጣቱ ርዕሰ ጉዳይ ለማድረግ ትልቅ ሚና አለው ብለን እናምናለን።

ባሰብነው ልክም በየዓመቱ እያደገ መሄዱንም አስተውለናል። ግን እኛ ብቻ ነን ይሄን ያደረግነው ብለን አናስብም። ምክንያቱም እኛ ይሄን ጉዞ ከጀመርን በኋላ ብዙ ሰዎች ውስጥ መነሳሳት በመፈጠሩ የሁሉም ድምር ውጤት ነው። ከኛ በቀደመው ጊዜ በተለያዩ የኪነጥበብ ሥራዎች የአድዋ ድል በየትውልዱ ላይ እንዲኖር ያን ችቦ እንዳይጠፋ እያቀጣጠሉ ያቀባበሉ አሉ።

እነ ሎሬት ፀጋዬ ገ/መድህን፣ ጋሽ አባተ መኩሪያ፣ እጅጋየሁ ሽባባው፣ ቴዲ አፍሮ እና መሰል የጥበብ ሰዎች የአድዋ ስሜት ከማህበረሰቡ እንዳይጠፋ ሲያደርጉ ቆይተዋል። ከዛ በኋላ ነው እኛ የምንመጣው። ስለዚህ እኛም እራሱ እንደው ለትውልዳችን ምልክት ለመሆን ያክል የተወሰነ አስተዋፅኦ እያደረግን ነው እንል ይሆናል እንጂ፣ የእነዚህ ሁሉ ተያያዥነት ያላቸው ሥራዎች አካል ነው ብዬ አምናለሁ። ግን በእኔ እምነት የአድዋ ድል በዓል የበለጠ ትኩረት እያገኘ መጥቷል።›› ይላል።

አሁን ያለው ችግር አድዋን ለመበሻሸቅ የሚጠቀሙበት ሰዎች መኖራቸው ነው የሚለው ያሬድ፣ ይልቁንም የአድዋ ድልን የኔ ብቻ ድል ነው በማለት ሁሉም ወደ ሰፈሩ ለመጎተት የመሞከር ነገር መታየቱ መሆኑን ያስረዳል። ይህ ደግሞ የጎንዮሽ ጉዳት እንዳለው ሁሉ በአንድ በኩል ጥሩ ነው ብየየ አስባለው በማለት እንደ ምክንያትም ይህን ይላል፤

‹‹ድሉ የኔ ነው ብሎ እንዲቀበለው ማድረጉ ቀላል ነገር አይደለም። ግን የሁላችንም ነው፣ የእኛ ነው የሚል መንፈስ አሁንም መነገር ያለበትና ሊባል የሚገባው ነገር ነው። ዳግማዊ አፄ ሚኒልክ የምናደንቅበት ብልህነታቸውን የምናሞግስበት አንደኛው ምክንያት እነዛን ሁሉ ታላላቅ የጦር ጀብደኞች አንድ ቦታ ማሰለፍ መቻላቸው ነው። እንደ ጉዞ አድዋም በጠቅላላ የምናምነው እንደዚህ ነው። ሕዝቡን ለአንድ ዓላማ ማሰለፍ ነው ከባድ እንጂ መተኮስ አይደለም።

ያንን ችለውበታል በሚል ነው አድናቆታችን። በዛ ውስጥ የሁሉም ጀግኖች ድርሻን የሚያጎላ መልክ አለው ብዬ አስባለሁ። ለዚህም ነው ጉዞ አድዋ ላይ ሁሉም ተጓዥ ጉዞውን በሚጨርስበት ጊዜ ካነበበው፣ ከተማረው በመንገዱ ላይ ካገኘው እውቀት እና ታሪክ በመነሳት አንድ የጀግና ሥም እንዲወስድ እና ራሱን በመሰየም እንዲያስተዋውቅ ለማድረግ የምንሞክረው። አድዋ የሁላችንም ነው ካልን ሁሉንም የሚያጠቃልል ታሪክ መሠራት አለበት ብለን ስለምናምን ነው።›› ሲል አብራርቷል።

‹‹በዋነኛነት ለአገራችን ሰላም ለአገራችን ህብረት እያንዳንዱ ግለሰብ ሚና እንዳለው ማሰብ አለበት።›› የሚለው ያሬድ፣ ‹‹ኢትዮጵያ ለእኛ ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካም ብርሀን ልትሆን የምትችል አገር ነች። የአፍሪካ ህብረት መቀመጫነት እድልን እራሱ ብዙዎች እየፈለጉት ሳለ እኛ አግኝተነው አልተጠቀምንበትም። ስለዚህ የእኛ እቅድ ወደፊት የአድዋ ድል የአፍሪካዊያን ድል ነው እያልን እያወራን ሌሎች አፍሪካዊያን እንዲሳተፉበት ማድረግ ነው። ይሄንንም ቢያንስ በ10ኛው የዓድዋ ጉዞ ላይ ለማሳካት የኹለት ዓመት ዝግጅት ብናደርግ ጥሩ ነው ብለን እናስባለን።›› ሲል ለወደፊት የተሰነቀውን ግብም አመላክቷል።

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com