የእለት ዜና

የአቻምየለህ ታምሩ ጽሑፍ ‹ግድፈቶች› – እንዳነበብኩት

ጁሀር ሳዲቅ (ጋዜጠኛ) በማኅበራዊ መገናኛዎች መስከረም 22 ቀን 2013 የወጣውንና በአቻምየለህ ታምሩ ‹ገዳ እና ኢሬቻ› በሚል ርዕስ የተጻፈው ጽሑፍ ላይ የታዘበውን ያነሳል። ‹ግድፈቶች› ያላቸውንም ነቅሶ ለጸሐፊውና ለአንባብያን ይህን አድርሱልኝ ብሏል።

ለአቻም የለህ ታምሩ፤
አቻምየለህ ታምሩ በማህበራዊ ድረገፁ ላይ የሚያሰፍራቸውን ጽሑፎች አያቸዋለሁ። አርብ መስከረም 22 ቀን 2013 ያስነበበውና ‹ገዳ እና ኢሬቻ› የሚል ርዕስ ያለው ጽሑፉ ለዚህ አስተያየት መነሻዬ ነው።

በጽሑፉ የገዳን ወደ ስርአተ ትምህርት መምጣት ተከትሎ ‹ገዳ› ለትምህ ርትነት ብቁ አይደለም በማለት ጽፏል። እንዲሁም ሙስሊሙንም ማህበረሰብ የሚያስቀይም፣ ሙስሊሙን እንደመጤ አድርጎም አፄዎች ለሙስሊሙ ባለዉለታ እንደሆኑ ዐይኑን በጨዉ አጥቦ ለመጻፍ ይሞክራል።

ከዚህ ጽሑፍም ዋና ዋና ሰበዞቹን በመምዘዝ የአቻም የለህ ታምሩ ግድፈቶች ለማሳየት እሞክራለሁ። ለመጻፍ ያነሳሳኝም ጽሑፉ ፅንፍ የረገጠ ጥላቻን የሚሰብክ ሆኖ ስላገኘሁት ነው። በጽሑፉ ካሰፈራቸዉ ዉስጥ የሚከተሉት ይገኙበታል፤
1. ኦሮሞ ኢሬቻን አዲስ አበባ ሊያከብር አይገባውም፤
2. ኦሮሞ ምስጋና የሚለዉ የሸዋ አማራ ገበሬዎች ፈጣሪያቸውን ለማመስገን የሚጠቀሙበትን ነው።
3. ኢሬቻ እና ገዳ የኦሮሞ አይደለም፤ የባሬንቱ ነው፤
4. ኦሮሞ ኢትዮጵያን ወረረ፣
5. ኢሬቻ በዪኔስኮ መመዝገብ የለበትም
6. የኦሮሞ ብሔርተኞቹ እነ ፕሮፈሰር መሐመድ ሐሰን፣ ዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ፤ ቡልቻ ደመቅሳ፤ ይልማ ደረሳ፤ ፕሮፌሰር ተሰማ ታዓ፤ ወዘተ እንደነገሩን ደግሞ ኦሮሞ ከብት በማርባት የሚተዳደር የነበረ ሲሆን፣ የእርሻ ሥራ የጀመረው ዛሬ በሰፈረበት አካባቢ ከረጋ በኋላ ከ17ኛውና ከ18ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ወዲህ ነው፤ የሚሉት ዋናዎቹ ናቸዉ ።

አቻምየለህ በጽሑፎች በአብዛኛው የሚያጣቅሳቸው ምንጮች ራሱ ከሚፈልገው የሚቀዳ ሲሆን፣ የጽሑፎቹ ይዘቶች በእስልምናና ክርስትና፣ በኦሮሞና በአማራ እንዲሁም በትግሬና በአማራ መካከልም የብሔር ቁርሾ ቁስሎችን የሚነካካ፣ የሕዝቦችን አብሮነት የሚሸረሽር ነው። በዚህ ከቀጠለና በርታበት ከተባለ መላውን የአማራ ወጣት ይመርዛል፤ መላዉ የኦሮሞ ወጣት ያቄማል፣ የትግራይ ወጣትም እንዲሁ።

የታሪክ ተመራማሪና አስተማሪ መሆን እንዲህ ነው ብዬ አላምንም። አቻምየለህ ታምሩ ብዙ ጽሑፎቹ ላይ ራሱ ብቸኛ የአማራ ታሪክ ደራሲና ተመራማሪ አድርጎ ነዉ የሚቆጥረው። እሱና እንደነ ፕሮፌሰር ሕዝቅኤል ጋቢሣ የሚጽፉት ጽሑፍ አማራ እና ኦሮሞ ሰላም እንዳይወርድላቸዉ ካደረጉ ምክንያቶች መካከል መስለዉ ይታዩኛል።

አቻምየለህ በመጀመሪያ አማራ የሚለዉ ብሔርም ሆነ ሴሞች የመጡት ከመካከለኛው ምሥራቅ ነው የሚሉ የዜና መዋዕል ወይም የክብረ ነገሥትና ፍትሀ ነገሥቶችን እንደሚቀበል በተለያየ ጽሑፎቹ ይገልፃል።

በበኩሌ እንደሱ ጠርዝ ረገጥ የታሪክ አስተማሪዎች ወይም መጽሐፎች አይደለም ያስተማሩኝም፣ ያነበብኩትም። ኢትዮጵያዊ ታሪክ ነዉ የተማርኩት። ስለዚህ የኢትዮጵያ ሕዝብ ነባር ሕዝብ ነው ብዬ አምናለሁ። ትግሬ፣ ጉራጌ፣ ኦሮሞ፣ ስልጤ፣ ሲዳማ፣ ሶማሌ፣ አርጎባ፣ ሽናሻ፣ ቅማንት ወዘተ ነባር ነን። ነገር ግን እምነቶቻችን ከመካከለኛው ምሥራቅ ነው የመጡት።

አዎ! ግን ይህ ማለት ሕዝቡ መጤ ነው ማለት አይደለም፤ ሀላስ!። በዚህ ነው የማምነው። አቻም የማይዋጥለት ከሆነ ሊሞግተኝ ይችላል። በመጀመሪያ ኩሾች ኢትዮጵያን ተቆጣጥረዉ እንደነበር በታሪክ ድርሳኖች ተጽፏል።

ኦሮሞ ኢትዮጵያን ወረረ የሚለውም አያስማማም። በመጀመሪያ ኦሮሞ እዚህ ነበር። ከዚህ መጣ የሚል ተጨባጭ መረጃ፣ ይህ ነው የሚባል ቦታም የለም። ኦሮሞ ከመስፋፋቱ በፊት በገናሌ ወንዝ ዳርቻ ለብዙ እልፍ ዘመናት ኖሯል። ለዚህ ደግሞ አባ ባህርይም ኦሮሞ ወደ ደቡቡ አካባቢ ሊኖር እንደሚችልና የእሳቸዉ ጽሑፍም ኦሮሞ ወደ መኻል ሲስፋፋ የተጻፈ መሆኑን ይገልፃሉ።

በተጨማሪ ፕሮፌሰር ፍቅሬ ቶሎሳ፣ አሰፋ ጃለታ፣ ፕሮፌሰር አስመሮም ለገሰ፣ ነጋሶ ጊዳዳ፣ ጀርመናዊዉ Eike Hberland የዉጭ ጸሐፍትም ስለ ኦሮሞ ሕዝብና ባህል አብራርተውታል። በየትኛዉም ዓለም የሕዝብ መጠኑ እየጨመረ ሲመጣ መስፋፋት ይኖራል። በተለይ ድሮ ሁሉም ጉልበት ብቻ በሚጠይቅበት ወቅት፣ ኦሮሞም ያንኑ በመጠቀም ወረራ ሳይሆን መስፋፋትን አካሂዷል። ይኸውም በተመሳሳይ በዓለም ደረጃ ተካሂዷል። ያውም መስፋፋቱን በግድ በጦርነት ለማድረግ ተሞክሮ፣ ለአንደኛዉና ለኹለተኛው የዓለም ጦርነት መንስኤ የሆነዉ ይኸዉ ‹እኔ ብቻ!› የሚል ቅጥ ያጣ ፍላጎት ነው።

ከዚህ በብዙ ዘመን የራቀዉ የኦሮሞ መስፋፋትን ወረራ አስመስሎ ማለፍ እጅግ እብሪተኝነትና ፀያፍ ነው። ለኦሮሞ መስፋፋት ምክንያቱም ራሱ አምባገነኑ ንጉሣዊ ስርአት መሆኑ መካድ የሚቻል አይደለም። ንጉሦቹ ከ12ተኛው ክፍለ ዘመን አንስቶ የሙስሊም ሱልጣኔቱን ለማስገበርና ከግዛታቸው ስር ለማድረግ የሄዱበት መንገድ ለጦርነቱ ምቹነትን ፈጥሯል። እናም በአፄ ሠርፀ ድንግል እና ከዛ በፊት በነበረው ጊዜ ኦሮሞ አልገብርም ማለቱ መንስኤዎቹ ናቸዉ ብዬ አምናለሁ።

በወቅቱ ሊያስገብር የሚፈልገው የሚጠቀመዉ ጉልበት ስለሆነ ሌላዉ ተገዳዳሪ ጉልበት ካለዉ አሻፈረኝ በማለት ይገጥማል። ኦሮሞም ይኸንኑ ነው ያደረገው። ይሄ ለአርብቶ አደሮቹ የኦሮሞ ማህበረሰብ ጥሩ አጋጣሚ ፈጥሯል። {በሰላማዊም አመፃም} ተስፋፍቷል። ለረዥም ዘመንም በኦሮሞም ይሁን በሌላ ብሔሮች መካከል የተፈጠረ ብሔር ተኮር ነገር እንዳልነበር ምስክሮች ነን።

ነገር ግን ልክ በአማራም እንደ አቻምየለህ ዓይነት ‹ተራኪ፣ የተረት ተረት አባቶች› በኦሮሞም መካከል በመወለዳቸው ምክንያት፣ ወንድም በወንድሙ ላይ ገጀራ እስኪያነሳ፣ ሰብአዊነት እስኪጠፋ ሰብከዋል። ይኸዉ አሁንም እየሰበኩ ነው። ይሄ ኦሮሚያ አካባቢ ላለ አማራም ይሁን ሌላ ብሐየር የሚጠቅም ሳይሆን በእጅጉ የሚጎዳ ተግባር ነው።

እኔ ለአቻም ያለኝ ጥያቄ ይህ ነው፤ ኦሮሞ ኢትዮጵያዊ ካልሆነ ምናዊ ነው? ወደ መጡበትስ ይሂዱ እያለ ይሆን? ስሜት ታሪክ አይሆንም፤ ሆኖም አያዉቅም። እናም አቻምየለህን ታረም እላለሁ።

በመቀጠል ‹ኢሬቻ› የሚለዉ ቃል አማርኛ ነው በማለት የነ ከሳቴ ብርሀን የመዝገበ ቃላቶች ፍቺ ያቀርባል። ሆኖም በምንጭነት ያቀረባቸው ፍቺዎች የኦሮሞ አባቶች ከሚሉት የተለየ አይደለም። ‹‹ምስጋና የሚያቀርቡበት›› ነው። እሱ ግን አጣሞ ኦሮሞዎች ለሸዋ ገበሬዎች ሰብላቸዉ ለምርት በደረሰ ወቅት ምስጋና ለማቅረብ የሚጠቀሙበት ነው በማለት ኦሮሞ ገበሬ ሳይሆን ሥራ ፈት ነው ይለናል።

ምክንያቱም እነ ፕሮፌሰር መሐመድ ሐሰን፣ አስመሮም ለገሠ፣ ነጋሶ ጊዳዳ ወዘተ ብሔርተኞች ካለ በኋላ፣ ኦሮሞ ከብት አርቢም አይደለም በማለት የጻፉትን ይተቻል። እሺ ምን ነበር ታዲያ? አቻምየለህ ታሪክ እንደማህበራዊ ሚዲያ ወጀብ ይመስለዋል፤ ማንም የቀረበለትን ዝም ብሎ የሚጋት ይመስለዋል።

ገዳ እና ኢሬቻ የኦሮሞ አይደለም በማለት ለመለያየት ይጥራል። አጥኚዎቹ ባህል ይወራረሳል፣ ያድጋል፣ ይጠፋል በማለት ያስቀምጣሉ። በኢትዮጵያዊያን መካከል ብናይ የባህልና የቋንቋ መወራረሶች አሉ። ለምሳሌ ኩሽ የሆኑት የመመሳሰል ባህሪ ሲኖራቸው፣ የሴሞችም በጣም የተቀራረቡና የተጋመዱ መሆናቸዉ የቋንቋ አጥኚዎቹ ገልጸዋል። በባህልም የአማራና የትግሬ ባህል ከአለባበስ እስከ በዓላት፣ አሸንዳና ሻደይ የጉራጌ ኖቀ መዉሰድ ይቻላል።

የግዕዝ፣ የአማርኛ እና የትግርኛ፣ የጉራጌ ቋንቋዎች ቅርርብ ዝም ብሎ የመጣ ሳይሆን በጋራ የመጣንበት እሴታችን ጭምር ነው። ኦሮሞ ኢሬቻ ከባሬንቱ ወርሶት ነው ላለው፣ ባሬንቱዎችም ኢሬቻን እንደራሳቸው ቢያከብሩት ምን ችግር አለው? ነገር ማዋሰድ ካልሆነ በቀር፣ ሙስሊሞች በአብረሃም ነብይነት፣ በኖህ፣ በሙሴ፣ በሰለሞን ነብይነት ያምናሉ። ክርስትያኖችም እንደዛው። ታድያ ምን ተፈጠረ? ምንም፤ ሀላስ!።

ኢሬቻ ኦሮሞዎች ፈጣሪያቸዉን ዋቃነወ የሚያመሰግኑበት ስርአት ነው። ነገር ግን በራሱ በሚመቸው አዙሮ በአማርኛ የፈሰሩትን ተፍሲር/ትርጉም ተንትኖ ሲያበቃ፣ ኢሬቻ ከመስቀል መከበር በኋላ የሚከበር ስለሆነ እንዴት ሊሆን ይችላል ይላል? ለምን አይከበርም? ቢከበር ምን ችግር አለው?

አማራ ገበሬዎች ፈጣሪያቸዉ ለማመስገን እንጂ፣ ኦሮሞ ኢሬቻ ፈጣሪን ለማመስገን አይደለም ይላል። ምክንያቱም ከመስቀል በኋላ ስለሆነ ነው። አያችሁ! ግን እሱ ራሱ ባነሳው ነጥብ እሸት የሚበላበት ነው ይላል። ነገር ግን ጊዜው በክረምቱ ወራት የሚታረስበት፣ የሚታረምበት እንጂ ደርሶ እሸት የሚበላበት አይደለም። ፍራፍሬ እንዳንል ከእሸት ጋር ብዙ ልዩነት አለው። የኦሮሞ ኢሬቻ የሚተረጎመዉ ከክረምቱ የጎርፍ የጭቃ እና የዝናብ የአየር ሁኔታ ወደ ክረምቱ መዉጫ ስላሸጋገረዉ የሚያመሰግንበት በዓል ነው። ይህንን ማጣመም አግባብ አይደለም።

አቻምየለህ ይቀጥላል፤ ኢሬቻ በዩኔስኮ መመዝገብ የለበትም ይላል። ያሳዝናል። ከአንድ ምሁር ነኝ ባይ/ኢትዮጵያዊ የማይጠበቅ ነው። ኢሬቻ በዩኔስኮ በቅርስነት ቢመዘገብ ለአገራችን ሌላ የቱሪስት ገቢ ያመጣል፣ ያስተዋዉቃል እንጂ ምን ጉዳት አለው? ይሄ ተራ ስሜት የወለደዉ እንጂ ምሁራዊ ዕይታ ነው ብዬ አላምንም ።
አለፍ ብሎ ‹ኢሬቻ የሚከበረዉ ሆራ አርሰዴ እንጂ አዲስ አበባ አይደለም።› ይላል። እስከዛሬ እዉነት ነዉ ኢሬቻ የሚከበረዉ ሆራ አርሰዴ በሚገኘዉ ዝዋይ ሀይቅ ዳርቻ ነው። ነገር ግን ሁሉም ባህሎች መዉጣት፣ መታየት፣ መዋብ፣ ማማር አለባቸው። ጠቃሚ እሴት እስከሆኑ ቢቻል የተደበቁ ባህሎች ካሉ ቢወጡ፣ እንደውም ባህልን እያሳደጉ መሄዱ መልካም እንጂ መጥፎ አይደለም። ከዚህ አኳያ ባህሎቹ ለከተማ ሕዝብ ነዉ የሚተዋወቁት።

ለምሳሌ ሻደይና አሸንዳ በከተማ ደረጃ በአዲስ አበባ መከበር የጀመሩት ከኢሕአዴግ በኋላ ነው። ታዲያ ለአሸንዳና ሻደይ የተገባችው ሸገር አዲስ አበባ፣ ኢሬቻን እንዴት አላስተናግድም ትላለች፤ እንዴትስ ላታስተናግድ ትችላለች? በእምነት ብንወስደው መስቀል፣ አረፋ፣ ገና፣ ፋሲካና ኢድ አል ፊጥር በዓላት የሚከበርባት አዲስ አበባ፣ እንደምን ለኢሬቻ እምቢ ልትል ይቻላታል? ይሄ ጭቆና ነው የሚሆነው።

በ1960ዎቹ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎቹ መሪ ትንታጉ ዋለልኝ መኮንን ጽሑፍ ለአቻምየለህ ለከት አልባ ቃላቶች በቂ ነው። ዋለልኝ ኢትዮጵያ ዉስጥ የባህል የብሔር የሀይማኖት እኩልነት እንደሌለ ከገለፀ በኋላ፣ የ80 ብሔሮቿ ኢትዮጵያ ባህል እያለ የነበረው የአማራና የትግሬ፣ ዘፈኑም እንደዛዉ በማለት ሁሉን ዐቀፍና ዴሞክራሲያዊ መንግሥት ያስፈልገናል ብሎ ይሞግታል።

ይህንን ማስታወስ እወዳለሁ። ዛሬ ጽንፍ በረገጠ መልኩ ፖለቲከኞቹ ዘዉረዉ ቢጠቀሙበትም አስተሳሰቡ አካታች ኢትዮጵያዊነትን ነው። ለዛሬዋም ሆነ ለነገዋ ኢትዮጵያ የሚበጀዉ ሁሉም መደማመጥ ሲችል፣ የሁሉም ባህልና እምነት በእኩልነት መንፀባረቅ ሲችል ብቻ መሆኑን ለማስረገጥ እወዳለሁ። በዴሞክራሲ እሳቤ ደግሞ ሰዎች ባህላቸውን፣ እምነታቸዉን የትም ቢሆን መለማመድ ይችላሉ።

ካልሆነ ከሰብአዊ መብት ድንጋጌ ጋርም ይጋጫል። ስለዚህ የኦሮሞ ኢሬቻ ከሌሎች የሚለይበት አንዳች ምክንያት የለም። ምንም ልዩነት ሳይደረግ መከበር አለበት፤ አበቃ!። ሌላ ብሶት መዘርገፍ አያስፈልግም። አቻም እጅግም ደፈር ብሎ ኦሮሚያ ውስጥ የሚኖረው ዘጠና በመቶው ኦሮሞ አይደለም ይለናል። ለዚህ ምላሽ ራሱ በምንጭነት የጠቀሳቸዉ አባ ባህርይ ናቸው። እርሳቸውም እንዲህ ብለዋል፤ ‹‹አማራ በሰሜን ሀይማኖትና ቋንቋዉን በማስፋት ሌሎችን አማራ እንዳደረገዉ…›› (ገፅ 106-107) ብለዉ ይገልጹታል። ስለዚህ ጥርት ያለ አማራ ማነዉ? አቻምየለህ፤ ተመራመርበት።

ማሳረጊያ
ምናልባት አቻምየለህ አሁን በሥልጣን ላይ ያሉ አመራሮች ፖለቲካዊ እንዲሁም ነባራዊ ሁኔታዎቻቸው ላያምረው ይችላል። መላው የኦሮሞ ሕዝብ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ወይም የሽመልስ አብዲሳ አድናቂ አይደለም። ስለዚህ የአመራርና የሕዝብ ነገሮችን መለየት የግድ ይላል። ነገር ግን አቻምየለህ በአንድ ሙቀጫ ሁሉንም ይወቅጠዋል።

እሺ ሁሉም ለእርሱ ተመሳሳይ ስዕል ካላቸዉ ማን ይምጣለት? ወርደን እዚህ መገኘታችን ያሳዝናል። አቻምየለህ የተነሳበት ዓላማ አዲስ አበባ ወይም እሱ የሚላት የአፄ ዳዊቷ በረራ ለማብራራት ሰፊዉ የኦሮሞ ሕዝብ ባይተዋር ማድረግ፣ ግጭት ቀስቃሽ የጥላቻ ስብከት ካልሆነ በቀር የዛሬ የአዲስ አበባችን ጉዳይ ሰባኪዉ እንደሚለዉ ወይም ሌሎች የኦሮሞ ብሔርተኞች እንደሚሉት ዓይነት አይደለም። የአዲስ አበባ ሕዝብ አስተዳደራዊ ጥያቄ እንጂ የብሔር ጥያቄ አይደለም፤ ወደዛ መገፋትም የለበትም።

Comments: 2

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

 1. አቶ ጁሀር!
  የመጀመሪያው መልእክቴ፣ ጋዜጠኛ እንደመሆንህ እንደዚህ ከእውቀትና ከእውነት የፀዳ ጽሑፍ ይዘህ መቅረብህ አስገምቶሀል።
  ሁለተኛው መልእክቴ፣ በርግጥ አማራ ፣ ትግሬ ሲዳማ፣ ጉራጌ ፣ ሀድያ ወዘተ የኢትዮጵያ ነባር ነገዶች ናቸው ። ኦሮሞ ግን በ16ኛው ክፍለ ዘመን የኢትዮጵያን ክፍሎች ወርሮ ነው የገባው። በዚህ ወረራ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ነባር ነገዶች እንደተጨፈጨፉ የውጭ ፀሐፊዎች ሳይቀሩ ፅፈውታል። ዶር ነጋሶ ጊዳዳ በፅሑፋቻቸው ላይ በኦሮሞ ወረራ የተነሳ አሁን ወለጋ በተባለው የኢትዮጵያ ክፍል ብቻ 20 የሚሆኑ ነባር ነገዶች በገዳ ጨፍላቂነት አንደጠፉ ፅፈዋል። የኦሮሞን ወረራ በሚመለከት የኦሮሞ ፋሽስት ደርጅቶች ገና በግብፅ ሲመሰረቱ ጀምሮ ይሄን በታሪክ የተደገፈውን እውነት በመካድ (እነ ፕሮፌሰር መሐመድ ሐሰንን ጨምሮ) ኦሮሞ ከመጀመሪያውም ኢትዮጵያ ውስጥ ነበር በማለት ሲቀላምዱ ኖረዋል ።
  3ኛ መልእክቴ፣ ገዳ ከኦሮሞ ውጭ ያሉትን ነገዶች ጨፍላቂ ለመሆኑ እላይ እንደ ማሳያ ጠቅሻለሁ።የዛሬዎቹ አባገዳዎችም፣ በኦሮሚያ የሚኖሮትን ወደ 15 ሚሊየን የሚጠጉ አማሮች በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው እንዳይማሩ እየከለከሉ (በአማራው ክልል ኦሮሞው በራሱ ቋንቋ ይማራል፣ እራሱን ያስተዳድራል ፣ ይሄ ነው ትክክለኛወደ አብሮ መኖር!!!!) እራሱን እንዳያስተዳድር እየተከለከለ፣ አባገዳዎች በሚመሩት ቄራዎች እየተገደሉ ገዳን በአዲስ አበባ
  ትምህርት እንዲሰጥ መደገፍ ፣ አብሮ በሰላም መኖርን ሳይሆን ሌሎችን ነገዶች ጨፍልቆ ሃብታቸውን ለመዝረፍ ብቻ ነው። የኦሮሞ ሕዝብ ላለፉት 400 ዓመታት ከነባር ነገዶች ጋር አብሮ በመኖር ነባር ሆኗል ። በመሆኑም ይዋል ይደር እንጂ፣1 የኦሮሞ ነገድ ፣እነዚህን የግብፅ ቅጥረኛ ፋሽስት ልጆቹን አንቅሮ እንደሚተፋቸው ጥርጥር የለኝም ። የሕወሓትንም እጣ ፈንታ በቅርቡ ማየታችን አይቀርም ። 2 ይዋል ይደር እንጂ እውነተኛዎቹ ኢትዮጵያውያን ተባብረው እነዚህን የግብፅ ቅጥረኛ ፋሽቶች አሽቀንጥረው መጣያቸው ደርሷል ።

 2. ይድረስ ለጁሀር ሳዲቅ፣
  በእርግጥ ጋዜጠኛነት ትልቅ ክቡር ሙያ ነው።በዚህም ላይ ሙያውን እንዳያሳንስና የሐሰት መዘክር እንዳይሆን ጥንቃቄ ያዘለ ተግባር መሆን ይገባዋል ። በእርግጥ የአንድን ሰው ሀሳብ ለመንቀፍ እንዲያው ቢያንስ አንድ መስፈርትን ማሟላት ግድ ይላል ። የተጻፈው ስህተት ለመሆኑ አጣቃሽ ዋቢ ጽሑፎችን ማቅረብ ግዳጅ ነው ። ይሄንን ለመጻፍ ያነሳሳኝ በአቶ አቻምየለህ ታምሩን ነቅፈህ ባወጣኸው ጽሑፍ ነው።
  በመጀመሪያ የአቻምየለህ ጽሑፍ ምንጩ ምን መሆኑን መረዳት ተገቢ ነው። ያለፈውን 40አመት በላይ አዲሱ ትውልድ ኢትዮጵያ በደፈናው ሀገር መሆኗን እንጂ፣ሀገርነቷ ከምን እንደመነጨ ምንስ እሴቶቿ እስካሁን ፣ምንም ብዙ የውስጥም የውጭም ጥቃት ቢገጥማትም፣ ሊያቆያት እንደቻለ አይነገርም ። በተለይ ባለፈው 30 አመት ተረኛ ነን ባይ ገዢዎች የኢትዮጵያን ህልውና ለማጥፋት ብዙ ሴራ ሲያካሂዱ፣ዋናው በአንደኛ ደረጃ ያደረጉት ዘመቻ ወጣቱን ትውልድ ታሪክ የለሽ ማድረግ ነው ፣ብሎም የሀሰት ትርክት መጋት ነው። ይሄን በሀሰት የተወላገደ ትምህርት ሲሆን ማቃናት ፣አለበለዛ ነቅሎ መስመር ማስያዝ ያስፈልጋል ።
  አቶ አቻምየለህ ይሄን የተንሸዋረረ ታሪክ ለማስተካከል የታሪክ ሀላፊነት ወስዶ እየሰራ ነው።ይሄን የዘር ፓለቲካ ፣ተረኛ ነን የአሁኑ ባዮች አይጥማቸውም ። እኔንም የነርሱ የሀሰት ትርክት አይጥመኝም። ለዚህም ነው አቻምየለህ እራሱ እንፈለገው ያጣቀሰው ሳይሆን ፣በጽሑፍ ያገኘውን መረጃ አሰባስቦ ያቀረበው። እንግዲህ አንድ ጸሐፊ ብቁነቱን የሚያሳየው ምን ያህል መረጃ ከእናት ማህደር ፈልፍሎ ማግኘትና ለአንባቢ ማቅረቡ ነው። ለዚህም ነው የጸሑፍና የመጻህፍት ጠቃሚነቱ። በልምድ በአፈታሪክ የሚተላለፍ አለ፣ለዚህም ነው አፈታሪክ ለሰሚው ደስ የሚል ነገር ግን በዋቢ መረጃነት ቦታ የሌለው።
  ምናልባት ሀገር ወጥ ጸሐፊዎች ተሳሳቱ ቢባል እንኳን ፣የኢትዮጵያን ታሪክ ብዙ የውጭ ጸሐፊዎች በተለያዩ ዘመናት የታሪክ ቅርስ ትተዉልናል። ምናልባት ለዚህ ነው ተረኞች ባዮችና ደጋፊዎቻቸው ፣አቻምየለህ ጎርጉሮ ያወጣውን ሰነድ የሚጠሉት። እስካሁን እንቻቻል ተብሎ በትዕግስት ቢታለፍም ፣ የፍርሀት መስሎ ብሎም እንደ እውነት ስለተቆጠረ፣ አንንዳዴም “ዝም አይነቅዝም ” ጽንፈኞችን ለትልቅ የታሪክ ስህተት ዳርጓቸዋል።
  አቶ ጁሀር ፣አቶ አቻሜለህ ጵንፍ የረገጠ የጥላቻ ሰባኪ ብለህ ያቀረብከው 6ት ነጥቦች፣አንዲያው አንዱን እንኳን በማስረጃ አቅርበህ አላሳየህም። ይባስ ብለህ እስላሞች መጦች ናቸው ብሏል ብለህ ትወነጅላለህ። ከዚህ የበለጠ የሀይማኖት ጥላቻን መንዛት አፀያፊ መሆኑን ልትገነዘብ ይገባል። አርሱ የፃፈውን በማንኛውም ጊዜ ከማህደር አውጥቶ ማንበብና ማመሳከር ይቻላል።
  ከዚህ ሁሉ ይልቅ ለምን አሁን በኢትዮጵያችን የሚካሄደውን የዘር ፓለቲካ ከነፅንፈኞቹ አታወግዝም።ላንተ ሕዝቅኤልና ሽመለልስ ብቻ ናቸዉ ፅንፈኘፀኞቹ። ይሄ ብቻ ያለህበትን የቆምክለትን ጎራ ይመሰክራል ።
  እሬቻና የገዳ ሰርአት ብዙ ተብሎለታል። ዋናው ችግሩ ግን ፣ሕዝብ ላይ በግድ ለመጫን መሞከሩ ነው። ኢሬቻ አዲስ አበባ መከበሩ አይደለም ቁም ነገሩ፣ አዝሎት የመጣው የሀሰት ታሪክ ነው ችግሩ። ይሄንንም የአዲስ አበቤ ነባር ነዋሪ ያውቀዋል አስተማሪ አይሻም። የገዳ ሰርአትን እንደ አንድ በመካከለኛው ክፍለ ዘመን ጊዜ በተወሰነ ህብረተሰብ ክፍል የአገዛዝ ደንብ ለመሆኑ ሊጠቀስ ይችላል። በየትምህርት ቤቱ አቅርቤ በግዳጅ አስተምራለሁ ማለት የበታችነትን ስሜት ወደር የሌሽ ማድረግ ነው።
  አሁን በኦሮሞ ፅንፈኞ ችግራቸው አሣ ጎርጓሪ ዘንዶ ያወጣል ስለሆነባቸው ነው። በታሪክ ሰነድ ማቅረብ የማይሳካላቸውን በጉልበት ለመትገበር ተያይዘውታል። ያልገባቸው ነገር እንዳለፉት መንግስታቶች የጉልበት አገዛዝ ተቃዋሚ ጉልበት መፍጠሩን ከራሳቸውም ታሪክ አልተማሩም። ማንኛቸውም የጨቋኝ ስርአት በዓለም እንዳየነው ማንኛውም መጨረሻው አላማረም። የጀርመኑም ሂትለር ከነ ግብረአበሮቹ ራሳቸውን አጥፍተዋል፣የኢራቁ ሳዳም መሬት ምሶ ቢገባም ሕዝብ ጎትቶ አውጥቶ ለሞት ዳርጎታል፣ የሊቢያው ጋዳፊ ጥጋብ ወጥሮት ያዙኝ ልቀቁኝ እንዳላለ ሁሉ የመሬት ቱቦ ውስጥ ተደብቆ ያመፀው ሕዝብ አውጥቶ በጥፊ ሲያቀልጠው ዓለም መስክራለች ፣መጨረሻውንም እናውቃለን።ወደ ሀገራችን ስንመጣ የደርግ ፈላጭ ቆራጭ መንግስቱ ጨለማ ተገን አድርጎ ወደ ግዞት ሔዷል እርሱም በህይወት እያለ የሞት ሞት ተከናንቧል ። ህውሐቶች እንደ አይጥ ሹክክ ብለው መቀሌ ከትመዋል ። የነርሱ ሞት ደሞ የጉዲፈቻ ልጃቸው ሲዘባነን ማየት ነው። እንግዲህ ለሁሉም ጊዜ አለው። ያሁኑም ተረኞች መጨረሻችንን አሳምርልን ብለው ንስሃ ካልገቡ ዕጣ ፈንታቸው አስከፊ ነው የሚሆነው።
  እንግዲህ አቶ ጁሀር፣ አቶ አቻምየለህምን ሳይሆን ፅንፈኛ ወገኖችህን ብትመክር የተሻለ አማራጭ ነው።በዃላ እንዲህ አልመሰለኝም ነበረ ብሎ ቢንጫጩ ትርፉ ጉዳት ነው።

This site is protected by wp-copyrightpro.com