የእለት ዜና

የ“ኢሱ” የኢትዮጵያ ጉብኝት አንድምታዎች

Views: 227

በሳምንቱ መጀመሪያ ሰኞ፣ ጥቅምት 2 ለብዙዎች ድንገቴ የሆነው የኤርትራው ፕሬዘዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ የሦስት ቀናት ጉብኝት አዲስ አበባ ሳይሆን ባልተለመደ መልኩ ጅማ ላይ አቀባበል ተደርጎላቸው ጀምረዋል። ፕሬዘዳንቱ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ጋር በመሆን በጅማ የቡና እርሻን፣ የጅማ ዩኒቨርሲቲን፣ የኮይሻን ኤሌክትሪክ ኀይል ማመንጫ ግድብ፣ የታላቁን ሕዳሴ ግድብ እንዲሁም የኢፌዴሪ አየር ኀይልን ጎብኝተዋል። ወደ መዲናችን አዲስ አበባ በመምጣትም የእንጦጦ ፓርክን የጉብኝታቸው አካል አድርገዋል።

የኤርትራው ፕሬዘዳንት ጉብኝት የመገናኛ ብዙኀን ቀልብን የሳበ ከመሆኑም ባሻገር በተለይ የኢትዮጵያንና የኤርትራን እንዲሁም የአፍሪካ ቀንድን ትኩረት አድርገው መልከዓ ምድራዊ ፖለቲካውንና የምጣኔ ሀብት ትስስሩን የሚተነትኑ ባለሙያዎችም ሆኑ ተርታው ዜጋም የተለያዩ አንድምታ ሰጥቶታል።

የኹለቱ አገሮች ግንኙነት ከኹለቱ መሪዎች ወዳጅነት በዘለለ የሕግ ማዕቀፍ ተበጅቶለት ሊያዝ እንደሚገባው ሲያሳስቡ ተደምጠዋል። በተለይ በመሪዎቹ ደረጃ ግንኙነቱ መጀመሩ መልካም ቢሆንም ግንኙነቱ ተቋማዊ እንዲሆን በሚመለከታቸው አካላት በትኩረት ሊሠራ ይገባል ሲሉም አክለዋል። በተለይ በኤርትራ ውስጥ ነፃነትና ሰብኣዊ መብት አለመጠበቅና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ለማካሄድ፤ ሐሳብ እንኳን በነፃነት መግለጽ በማይቻልበት ሁኔታ ከመሪዎቹ የርስበርስ ተደጋጋሚ ጉብኝት ለሕዝቡ ምንም ጠብ ያለ ነገር የለም ብለው ጠንከር ያለ ትችት የሰነዘሩም ቁጥራቸው ቀላል አይደለም።

በሌላ በኩል የፕሬዘዳንቱ ጉብኝት በፌደራል መንግሥትና በትግራይ ክልል በሚመራው ሕወሓት መካከል ያለው ፍጥጫ ወደ ከፋ ደረጃ በመደረሰበት ወቅት መደረጉ አንድምታው ሌላ ነው ሲሉ አንዳንዶች ሐሳባቸውን አንሸራሽረዋል። ሕወሓት’ን በተለይ ሽማግሌ አመራሩን ትንፋሽ አሳጥቶ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ የሚኖረውን ሚና የበለጠ ለማዳከምና ወደ ታሪክ መዝገብ ለመክተት የታቀደ ነው ሲሉ የጉብኝቱ ምክንያት ነው ያሉትን ሰንዝረዋል።

ይህንን ሐሳብ በማጠናከር አሜሪካዊው የቀድሞ አምባሳደር፣ የአፍሪካ ቀንድ ረዳት ውጪ ጉዳይ ሚኒስትር በመሆን ያገለገሉት እንዲሁም የ“The Mind of the African Strongman” እና በቅርቡም “US Policy Toward Africa” መጻሕፍት ደራሲ ኸርማን ጄ. ኮህን፥ የፕሬዘዳንት ኢሳያስን ጉብኝት አስመልክቶ በቲውተር ገጻቸው ላይ “ወቅታዊው የኤርትራ ፕሬዘዳንት የኢትዮጵያ ጉብኝት ለትግራይ ክልላዊ መንግሥት ባለሥልጣናት በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የሚመራውን የኢትዮጵያን ማዕከላዊ መንግሥት ለመገዳደር ወታደራዊ ኀይል ለመጠቀም እንዳያስቡ ጠንካራ መልዕክት ለማስተላለፍ ነው” በማለት አስፍረዋል። መልዕክታቸውም በብዙዎች የማኅበራዊ ትስስር ተጠቃሚዎች ተጋርቷል፤ መነጋገሪያ ሆኖም ከርሟል።

በሌላ በኩል ደግሞ የጉብኝቱ ዋና ፋይዳ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ያጋጠሟቸውን አገራዊ ተግዳሮቶች ሆን ተብሎ ትኩረት ለማስቀየስ ነው በማለት ክርክራቸውን በአመክንዮ ለማስደገፍ ላይ ታች ሲሉ የከረሙ አሉ። አንደኛው፤ ሰሜን ኢትዮጵያ በተለይ ትግራይና አማራ ክልሎች ውስጥ የሚገኙ የአርሶ አደሮች ሰብል በአስደንጋጭ መልኩ በአንበጣ መንጋ መወረርና የሰብሎች መውደም የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ መንግሥት ቸልታ ውጤት በመሆኑ ጉብኝቱ በትኩረት ማስቀየሻነት ተጠቅመውታል የሚል ነው።

ኹለተኛው መከራከሪያ ነጥብ ደግሞ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በቤኔሻንጉል ክልል ውስጥ በሚገኙ የተወሰኑ ወረዳዎች በተደጋጋሚ የጸጥታ መደፍረስ ማጋጠሙና ብሔርን ለይቶ የንጹኀን ዜጎች ሕይወት በአሰቃቂ ሁኔታ መቀጠፉ የጠቅላይ ሚኒስትሩን መንግሥት ፈተና ላይ የጣለ በመሆኑ ጉብኝቱ የብዙኀንን ቀልብ እንዲገዛ በማድረግ ተግዳሮቱን ትኩረት አልባ ሆኖ እንዲዳፈን በመሣሪያነት ተጠቅመውታል በማለት ሐሳባቸውን አንጸባርቀዋል።

የሆነው ሆኖ ፕሬዘዳንት ኢሳያስ እና የልዑክ ቡድናቸው በኢትዮጵያ ያካሄዱትን የሦስት ቀናት የሥራ ጉብኝት አጠናቀው ወደ አገራቸው በተመለሱ በጥቂት ደቂቃዎች ልዩነት፥ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በፌስቡክ ገጻቸው ጉብኝቱም ሆነ በልዩ ልዩ የኹለትዮሽና ቀጠናዊ ጉዳዮች ላይ ያተኮረው ውይይት ውጤታማ ነበር ሲሉ ጽፈዋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 102 ጥቅምት 7 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com