የኮቪድ-19 መከላከያ መመሪያ ሲፈተሸ

Views: 163

ዓለም የተፈተነችበት፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እድገቶች ከግስጋሴያቸው የገታ ብርቱ ቀበኛ፣ የሰው ልጅ ተፈጥሯዊ ግንኙነቶች እንዲሁም ማህበራዊ መስተጋብሮችን በእጅጉ ገድቦ ቁጥጥር ስር ያዋለ ውረርሽኝ ነው።

በአገረ ቻይና ውሃን ግዛት በወርሃ ታህሳስ 2012 መከሰቱ በግልጽ ለዓለም ህዝብ ይፋ ሆነ። ባልተገመተ እና ከአውሎ ንፋስ በፈጠነ ቅጽበት ዓለም አዳረሰ፣ ሚሊዮኖችን አጠቃ፣ በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ ዜጎችን ህይወት ቀጠፈ። ኮቪድ-19 ዓለም ከዚህ በፊት ካስተናገደቻቸው ወረርሽኞች ለመከላከል አዳጋች የሆነ እና እጅግ በፍጥነት የተስፋፋ ወረርሽን ነው ተብሎለታል።

የዓለም ሀያላን አገራትን አስጨናቂ ሆኖ የቀጠለው ኮቪድ-19 በዓለም ላይ የሰው ልጅ የቀድሞ እንቅስቃሴዎች እና ህዝባዊ ክዋኔዎችን በእጅጉ የገደበ በመሆኑ የዓለም አገራት ህዝባዊ እንቅስቃሴን የሚገቱ መመሪያዎችን እና እገዳዎችን ተግባራዊ አድርገዋል። አሁንም እያደረጉ ያሉ አገራት አሉ።
ኪቪድ-19 በእንቅስቃሴ ገደብ ሊገታ የማይችል በመሆኑ የስርጭት የኢትዮጵያ ጤና ሚኒስቴር እና ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲቱት “የኮቪድ-19 ወረርሽን መቆጣጠሪያና መከላከያ መመሪያ” አዘጋጅተዋል።

ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱና ኢንስቲቱቱ በመመሪያ ቁጥር 30/2013 የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመከላከልና ለመቆጣጣር የወጣ መመሪያ የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመከላከልና የሚያስከትለው ጉዳት ለመቀነስ ስለ ሚወሰዱ ክልከላዎች እና ግዴታዎች በህግ መወሰን አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በመድኃኒትና ምግብ አስተዳደር አዋጅ ቁጥር 1112/2011 አንቀፅ 72 ንዑስ-አንቀፅ (2)፣ በምግብ፣ መድኃኒትና የጤና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር አዋጅ ቁጥር 661 አንቀፅ 55 ንዑስ-አንቀፅ (3) እና የምግብ፣ የመደኃኒትና የጤና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር የሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 299/2006 አንቀፅ 98 መሰረት ዝርዝር መመሪያ አውጥቷል።

በመመሪያው ላይ “ማንኛውም አገልግሎት የሚሰጥ የመንግስታዊ እና የግል ተቋም አገልግሎቱን ለማግኘት ወደ ተቋሙ ለሚመጡ ተገልጋዮች በዚህ መመሪያ ወይም የሚመለከተው ዘርፍ በመመሪያ በሚያወጣው የጥንቃቄ እርምጃ መሰረት ቫይረሱን ለመከላከል የሚያስችሉ የንፅህና መጠበቂያ ቁሳሶችን የማቅረብ፣ ተገልጋዮች ሁለት የአዋቂ እርምጃ ተራርቀው የሚቆሙበትን ቦታ ምልክት የማድረግ እና ተገልጋዮች የአፍ እና አፍንጫ መሸፈኛ ማድረጋቸውን እና ሌሎች አስፈላጊ ጥንቃቄዎችን መተግበራቸውን የማረጋገጥ ኃላፊነት አለበት” ይላል።

ኮቪድ-19 ወደ ኢትዮጵያ መጋቢት ወር መጀመሪያ ላይ ተከስቶ እስካሁን ድረስ ስርጭቱን እየሰፋ ይገኛል። ቫይረሱ ወደ ኢትዮጵያ ከገባ ወዲህ የስርጭት አድማሱን ለመቀነስ የተለያዩ እርምጃዎች ሲወሰዱ ቆይተዋል። ከተወሰዱት እርምጃዎች ውስጥ የፌደራል መስሪያ ቤት ሰራተኞች በተራ ቢሮ እንዲገቡና ቀድሞ የነበረው መደበኛ የቢሮ መግቢያም ከጥዋቱ አንድ ስዓት ተኩል ገብተው ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት ከቢሮ እንዲወጡተደርጎ ነበር፣ ይህ የተደረገበት ምክንያት በወቅቱ የነበረውን የትራንስፖርት መጨናነቅ ለመቀነስ ነበር። እንዲሁም የትራንስፖርት አገልግሎት በግማሽ አንዲጫን እና ሆቴሎች ፣ሰፊ የህዝብ ፕሮግራሞች የተገቱበት ብሎም ለስድስት ወራት በመላው አገሪቱ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የታወጀበት ወቅት ሆኖ አልፏል።

መንግስት የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት በማሰብ ወስድኳቸው ያላቸው ያለፉት ውሳኔዎች አንደ መንግስት ሪፖርት የቫይረስን ስርጭት እንደቀነሰው ተጠቁሟል። ነገር ግን አሁንም ድረስ የቫይረሱን ስርጭት በእጅጉ እየሰፋ የመንግስት ትኩረት እየቀዘቀዘ፣ የህብረተሰቡ ጥንቃቄ በእጅጉ መዘናጋት የታየበት ሁኔታ ላይ መኖሩን አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው የኢትዮጵያ ህክምና ማህበር ፕሬዝዳንት ዶ/ር ተግባር ይግዛው ጠቁመዋል።

ዶ/ር ተግባር እንደሚሉት በአገሪቱ አሁን ላይ የሚታየው ሁኔታ የመንግስት እና የህብረተሰቡን መዘናጋት በእጅጉ የጎላ ይሁን አንጅ የቫይረሱ ስርጭት በእጅጉ እየሰፋ መምጣቱን ይናገራሉ። ለዚህም እንደ ማሳያ የሚነሱት የምርምራ ስራዎች የቀነሱበት ሁኔታ መኖሩን ገልጸው ያሳለፍነው ነሀሴ ወር አጠቃላይ የኮቪድ-19 ምርመራ ከሚደረግላቸው ሰዎች ውስጥ ሰባት በመቶ ያክሉ በቫይርሱ ይዛዙ እንደነበር አስታውሰው አሁን ላይ ከሚመረመረው ሰው ውስጥ 20 በመቶ ያክሉ በቫይረሱ አንደሚያዙ ዶ/ር ተግባረ ያስረዳሉ።

እንደ ዶ/ር ተግባር ገለጻ የማህበረሰብን ጤና ለማስጠበቅ ሶስት መሰረታዊ ነገሮችን ማገናዘብ ይጠይቃል ብለዋል። እነሱም የመጀመሪያ ህብረተሰቡ ጤናውን አንዲጠብቅ ስለ ቫይረሱ በቂ እውቀትና ግንዛቤ መኖር ሲሆን ኹለተኛ የተከሰተውን ወረርሽኝ ለመከላከል ቁርጠኝነት መኖር እንዲሁም ሶስተኛው ቫይረሱን ለመከላከል የሚወጡ መመሪያዎችን በተገቢው መንገድ ተግባራዊ ለማድረግ አስቻይ ሁኔታዎች መኖር ነው ይላሉ።

ዶክተሩ ያስቀመጧቸው ሶስት መሰረታዊ ነገሮች አሁን በወጣው “የኮቪድ-19 ወረርሽኝ መከላከልና መቆጣጠር የወጣ መመሪያ” ውስጥ ሊፈጸሙ የሚችሉ ብሎም የህብረተሰቡን ነባራዊ የአኗኗር ሁኔታ ያናዘቡ መሆን ይገባቸዋል ይላሉ። ለዚህም ካስቀመጧቸው ሶስት መሰረታዊ ነገሮች ውስጥ ምቹ ሁኔታዎችን መፍጠር የሚለውን መስፈርት ማሟላት እና አስቻይ ነገሮችን በመንግስት፣ በግለሰብ እና በተቋማት መፍጠር ይገባል ይላሉ።

አሁን ለወጣው መመሪያ ተግባራዊነት የሚመለከተው ሁሉ የድርሻውን ካልተወጣ እና የወጡት መመሪዎች ከማህበረሰቡ ነባራዊ, የኑሮ ሁኔታ ጋር የሚመጣጠኑ ካልሆኑ ብንመኘውም መመሪያው ተግባራዊ አይሆንም” ሲሉ ዶ/ር ተግባረ የሁሉም ድርሻ እና መመሪያው አስቻይ መሆን አለበት ይላሉ።

ሌላኛው አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው በኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲቱት የህግ ክፍል ኃላፊ መልኬ ታደሰ መመሪያው የተዘጋጀው በኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲቱት እና በኢትጵያ ጤና ሚኒስቴር መሆኑን በመግለጽ መመሪያውን ያወጣው ጤና ሚኒስቴር ከተጠሪ ተቋሙ ከህብረተሰብ ጤና ኢንስቲቱት ጋር ይሁን እንጅ ለመመሪያው ተግባራዊነት አንድ መስሪያ ቤት ሁሉንም ተደራሽ ማድረግ አይችልም ይላሉ።

መመሪያው ከኢትዮጵያ ህዝብ ነባራዊ የእለት ከእለት የኑሮ ሁኔታ ጋር የሚጣጣም ነው ወይስ በዘፈቀደ መመሪያ ተዘጋጅቷል ለማለት ነው የወጣው? ብለው የሚጠይቁ መመሪያውን የተመለከቱ ወገኖች ሀሳባችውን አዲስ ማለዳ ሰጥተዋል።

ከዚህ አንጻር አዲስ ማለዳ መመሪያውን በዝርዝር በመመልከት በተቋማት፣ በግለሰብ፣ በሆቴሎች እና በትራንስፖርት አገልግሎት መስጫ ቦታዎች በመመሪያው ላይ የተቀመጡ ድንጋጌዎችን በመያዝ ተግባራዊ እየሆነ ነው ወይ የሚለውን ጉዳይ ተመልክታለች።

አዲስ ማለዳ በትራንስፖርት ሰጭ ተሸከርካሪዎች ባደረገችው ቅኝት የተመለከተችው ነገር እና በመመሪያው ላይ በግዴታ የተቀመጠው እና በወንጀል ህግ እንደሚያስቀጣ ከተፈቀደው በላይ መጫን አንዱ ነው። ነገር ግን አዲስ ማለዳ ቅኝት ባደረገችባቸው የትራንስፖርት ሰጭ ተሸከርካሪዎች ላይ በተለይም በሀይገር ላይ ከፍተኛ የሚባል ከተፈቀደው ወንበር ልክ በላይ ከመጫን በላይ የሚቆመው ሰው ከአምስት እስከ አስር ሰው አንደሚሆን ተመልክታለች። ሌለው በዚሁ በትራንስፖርት ዘርፍ ማንኛውም ሰው ትራንስፖርት ሰልፍ ላይ አንድ የአዋቂ እርምጃ ርቀት ጠብቆ መቆም ግደታው እንደሆነ ተደንግጓል ነገር ግን ህብረተሰቡ ላይ የሚታየው ነገር በተቃራኒው በእጅጉ የመቀራረብ ሁኔታ ነው።

ኹለተኛው አዲስ ማለዳ ቅኝት ያደረገችው በተቋማት ነው። አዲስ ማለዳ ምልክታ ካደረገችባቸው ተቋሞች ውስጥ ሁለት የፌደራል መስሪያ ቤቶች ይገኙበታል። ተቋማትን በተመለከተ በመመሪያው ላይ ተቋማት ለተገልጋያቸው የኮቪድ-19 ቅድመ መከላከያ የሚባሉትን ውሃ፣ ሳሙና፣ ሳኒታይዘርና የሙቀት መለኪያ ሊኖራቸው እንደሚገባ እና ማንኛውን ወደ ተቋማቸው አገልግሎት ለማግኘት የሚመጣ ሰው የፊት መሸፈኛ(ፌስ ማስክ) ካላደረገ አገልግሎት እንዳይሰጡ ይደነግጋል።

ነገር ግን አዲስ ማለዳ ለቅኝት ወደ አንድ ፌደራል መስሪያ ቤት ባቀናችበት ወቅት በር ላይ የተቀመጠው ሙሉ ጥቁር ሱፍ የለበሰ ተቆጠጣሪ የአዲስ ማለዳ ተወካይ ወደ ተቋሙ መሪ ቢሮ እንዲወስደው በር ላይ የቆመውን እንግዳ ተቀባይ በጠቀበት ጊዜ ያለ ምንም ማቅማማት ተከተለኝ ብሎ ወደ መስሪያ ቤቱ የበላይ መሪ ቢሮ እስክንደርስ የፌደራል መስሪያ ቤት ተቋሙ በር ላይ በመመሪያው ላይ የተጠቀሱት ዝርዝር መከላከያዎች በር ላይ አልነበሩም።

አንደኛው የፌደራል መስሪያ ቤት አንደ መጀመሪያው መስሪያ ቤት አይሁን አንጅ ከሙቀት መለኪያ ውጭ ምንም አይነት ቅድመ መከላከያ ቁሳቁሶችአለማዘጋጀታቸውን አዲስ ማለዳ ታዝባለች።

ሶስተኛው የአዲስ ማለዳ የቅኝት ቦታ ሆቴሎች ላይ ሲሆን አንደኛው ሆቴል አዲስ አበባ ውስጥ አሉ ከሚባሉ ትልቅ ሆቴሎች ውስጥ አንዱ ነው። በሆቴሉ የመንግስት መስሪያ ቤቶች በብዛት ስብሰባዎች የሚካሂዱበት ሆቴል ነው። አዲስ ማለዳ በሆቴሉ ተገኝታ ቅኝት ባደረገቸበት ወቅት ግን ከሙቀት መለኪያ ውጭ የእጅ መታጠቢያ ውሃ፣ ሳሙና እና ሳኒታይዘር በመመሪያው ላይ መገኘት እነደሰለቻቸው ቢገለጽም በዚህ ትልቅ ሆቴል በር ላይ ግን አልነበሩም። በአንጻሩ አዲስ ማለዳ ቅኝት ባደረገችባቸው መካከለኛ እና አነስተኛ ሊባሉ በሚችሉ ሆቴሎችና ሬስቶራንቶች ላይ የፊት መሸፈኛ ጭንብል ያላደረገ ተገልጋይ በር ላይ ከመከልከል እና በአንድ ጠረጴዛ ላይ ከሶስት ሰው በላይ መቀመጥ አይቻልም ብለው ሲከለክሉ ተመልክታለች።

አራተኛ አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው ግለሰብን በመመሪያው ላይ ማንኛውም ግለሰብ ከቤት ውጭ በሚንቀሳቀስበት ጊዜ የፊት መሽፈኛ ጭንብል የማድረግ ግደታ አለበት ይላል። ሳያደርግ ሲንቀሳቀስ የተገኘ በወንጀል ህግ አንደሚቀጣ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲቱት የህግ ክፍል ኃላፊው መልኬ ለአዲስ ማለዳ አረጋግጠዋል። ነገር ግን አዲስ አበባ ህዝብ በሚበዛባቸው ቦታዎች ሁሉ በርካታ ግለሰቦች የፊት መሽፈኛ ጭንብላቸቀውን ከአፍና አፍንጫቸው ላይ ወደ አንገታቸው አውርደው ሲንቀሳቀሱ የተለመደ ሆኗል። አንደውም አንዳንዶች ይሄን ሁኔታ “ማስክ ባንገቴ” ሲሉት ይጠሩታል። ሌላኛው “ ማስክ በክርኔ” ይሉታል ይህ ደግሞ የፊት መሽፈኛ ጭንብላቸውን ክርናቸው ላይ አድርገው የሚንቀሳቀሱ ሰዎች ስም ነው።

አዲስ ማለዳ በቅንጭቡ ባደረገቻቸው ቅኝቶች ላይ በታዘበቻቸው ሁኔታቶች ላይ ዶ/ር ተግባረ መቶ በመቶ እንደሚስማሙ እና በባለድርሻ አካላት የሚታየው የትግበራ እንቅስቃሴ መመሪያው ከመውጣቱ ባሻገር ተግባራዊነቱ ላይ ክፍተት አንዳለ ይስማማሉ።

የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲቱት የህግ ክፍል ኃላፊው መልኬ የወጣው መመሪያ ተግባራዊነት ላይ ክፍተቶች አንዳሉ አምነው ለመመሪያው ተፈጻሚነት ሁሉም ባለድርሻ አካላት የድርሻውን መወጣት አለበት ይላሉ። ካልሆነ የዶ/ር ተግባረን ሀሳብ በመጋራት በአንድ ተቋም ስራ ብቻ የሚተገበር እንዳልሆነ ተናግረዋል። መልኬ አክለውም የጤና ሚኒስቴርና ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲቱት መመሪያውን ከማውጣትና ለህዝቡ ከማሳወቅ የዘለለ ሙሉ ድርሻ ሊወስድ የሚችል የክትትልና የማስፈጸም ስራ ብቻውን እንደማይሰራ ገልጸዋል። በመሆኑም ለመመሪያ ተግባራዊነት ጠቅላይ አቃቤ ህግ፣ ፌደራል ፖሊስ፣ ሰላም ሚኒስቴር፣ ተቋማትና ማኅበረሰቡ የመፈጸምና የማስፈጸም ስራውን ድርሻ መውሰድ እንደሚገባቸው ጠቁመዋል።

ቀድሞ በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት ታውጆ በነበረው አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተቋቁሞ የነበረው የኮቨድ-19 ወረርሽ የመከላከልና የመቆጣጠር ክንውኖችን የሚከታተለው ግብረ ሀይል ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ሲነሳ መፍረሱን የአዲስ ማለዳ የጠቆሙት መልኬ አሁን ላይ በግልጽ የወጣውን መመሪያ ለማስፈጸም የተቋቋመ ግብረ ሀይል ባይኖርም የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት የሚሰራ በጤና ሚኒስቴር “Multisectoral response tax force” የሚባል ግብረ ሀይል መቋቋሙን ጠቁመዋል።

እንደ መልኬ ገለጻ መመሪያውን ለማስፈጸም ቀድሞ ስራውን ሲሰራ የነበረው የሚኒስትሮች ምክር ቤት ግብረ ሀይል አሁንም ለመመሪው ተግባራዊነት የግትትልና የማስፈጸም ስራ መስራት እንዳለበት ጠቁመዋል። መመሪያው መሬት ላይ ወርዶ ተግባራዊ እንድሆን ከማድረግ አኳያ ለጤና ሚኒስቴር ለህብረተሰብ ጤና ኢንስቲቱት ሙሉ ሀላፊነቱን ከመተው ይልቅ ሁኑም በየድረሻው መስራት አለበት ብለዋል።

ለመመሪያው ተግባራዊነት ሁሉም ባለድርሻ አካላት የድርሻውን እንዲወጣ ከማድረግ አንፃር ጥብቅ ቁጥጥር ማድረግና የተቋሞችን ኃላፊነት መወጣት በትክክል መፈተሽ እንዳለበት ዶ/ር ተግባረ ጠቁመዋል። ዶ/ር አክለውም በመመሪያው ላይ የተቀመጡ ድንጋጌዎች ከማህበረሰቡ እንቅስቃሴ አንፃር ከባድ ሊሆኑ የሚችሉትን ምቹ ሁኔታዎችን ማመቻቸት ይጠይቃል ብለዋል።

በመመሪያው ክፍል አምስት ላይ የቀብር ስነ ስርዓት፣ የአስክሬን ማጓጓዝ እና የሀዘን ስነ ስርአት በተመለከተ “የቀብር ስነስርዓት አፈጻጸም በአጠቃላይ ከ50 ሰውሳይበልጥ፣ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ በማድረግና ሁለት የአዋቂ እርምጃ በመራራቅ መከናወን አለበት” ይላል። ዶ/ር ተግባረ ይሄን ድንጋጌ መነሻ በማድረግ ከህዝብ ማህበራዊ ክንዋኔ አንፃር ሊተገበሩ የማይችሉ መመሪዎችን በመፈተሸ ከባለ ድርሻ አካላት ጋር በመሆን መፈተሸ እንደሙገባ ጠቁመዋል።

በመመሪያው ላይ በዝርዝር የተቀመጡ ድንጋጌዎች ላይ ክፍተት ሊኖር እንደሚችልና ፍጽም አለመሆናቸወን ያነሱት መልኬ በበኩላቸው መመሪያውን መነሻ በማድረግ ተቋማት የየራሳቸወን ፕሮቶኮል በማዘጋጀተር ቫይረሱን መከላከል እንዳለባቸው ጠቁመዋል። መልኬ አንደሚሉት በየትምህርት፣ በትሪዝም፣ በሆቴልና በሌሎችም ተቋማት አንደየ ስራ ዘርፋቸው አመች ሁኔታዎችን ፈጥረው መከወን የተሻለ እንደሚሆን ጠቁመዋል።

የህብረተሰብ ጤናን በእጅጉ የፈተነወን ኮቪድ-19 ወረርሽኝ ለመከላከል የሚወጡ መመሪያዎችና እርምጃዎች በጥቅሉ የህብረተሰቡን የጤና፣ ማህበራዊ እና ምጣኔ ሀብታዊ ሁኔታዎችን ባበዛዘነ መልኩ በጥንቃቄ መከወን አንዳለባቸወን ዶ/ር ተግባረ መክረዋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 102 ጥቅምት 7 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com