የእንጦጦው ፓርክ ፕሮጀክት – ከሥነ ምህዳሩ የተስማማ ልማት

Views: 333

ትናንሽ የሚመስሉ ነገር ግን ዘልቀው መቀጠል የቻሉ የእድገት ምጣኔ ልዩነቶች ጎልቶ የሚታይ የኢኮኖሚ ልማት ልዩነት ያመጣሉ የሚሉት ሽመልስ አረአያ (ዶ/ር)፣ የእንጦጦ ፓርክ ፕሮጀክትን አንስተዋል። በዚህም በእንጦጦ የተሠራው የልማት ሥራ በዘላቂነት ኑሯቸውን የሚያሻሽልላቸው የማኅበረሰብ ክፍሎች እንደመኖራቸው፣ ፕሮጀክቱ ቀጣይነትን ከሚያረጋግጡ የልማት ሥራዎች የሚመደብ ነው ሲሉ ያክላሉ። ይህንንም ከምጣኔ ሀብት ጽንሰ ሐሳብ እንዲሁም ከባለሞያዎች ትንታኔ ጋር አገናኝተው እንደሚከተለው ሐሳባቸውን አስፍረዋል።

ይህን ጽሑፍ እንድጽፍ መነሻ የሆነኝ በአንድ ዓመት ተገንብቶ ለአገልግሎት ክፍት የተደረገው የእንጦጦ ፓርክ ልማት በማስመልከት በፋና ቴሌቪዥን ‹እንጦጦ – ነገን ዛሬ ማያ› በሚል ርዕስ የተላለፈው ድንቅ ዘጋቢ ፊልም ተከትሎ፣ ወደ አንዱ የዲያስፖራ ሚድያ ዞር ስል ይህን ፕሮጀክት ከወቅቱ የአንበጣ ወረርሽኝ ጋር በማነፃፀር የቅደም ተከተል ችግር እንዳለበት በማንሳት የተደረገ ማጥላላት በመመልከቴ ነው። እናም እንዲህ ዓይነት ፕሮጀክቶች የሚኖራቸው ኢኮኖሚያዊ አንድምታ የሳይንሱን ንድፈ-ሐሳቦች በመከተል እንዲሁም ከአገራት ተሞክሮ ጋር በማስማማት ለአንባቢ ግልጽ አድርጎ ለማቅረብ በመሻት ነው።

በመሆኑም ይህን የመሰሉ ፕሮጀክቶች ለዘላቂ የኢኮኖሚ እድገት (sustainable economic growth) መረጋገጥ የሚኖረውን አንድምታ እንመረምራለን። መነሻ እንዲሆነን ግን ዓለም ላይ እናተኩር።

ዓለም የተለያየ የምጣኔ ሀብት ቅርጽና መጠን ያላቸውን አገራት አቅፋለች። አንዳንድ አገራት በጣም ሀብታም ሲሆኑ አንዳንዶቹ ደግሞ በጣም ደሃዎች ናቸው። ሌሎች በርካታ አገራት ደግሞ በዚህ ኹለት ጥግ ጥጋቸውን በያዙ አገራት መካከል ተሰድረው የሚገኙ ናቸው። የአንዳንዶቹ ኢኮኖሚ በፍጥነት ሲያድግ፣ የአንዳንዶቹ ደግሞ በጭራሽ እያደገ አይደለም። የአንዳንዶቹ እድገት እንዲያውም ቁልቁል የሚያዘግም ይሆናል።

በጥቅሉ የዓለም አገራት በኢኮኖሚ አቅማቸው በተለያየ ወቅት በሚኖር አሰያየም በረድፍ ተከፍለው ይቀመጣሉ። በቀዝቃዛው ጦርነት ወቅት የአንደኛው ዓለም (First World)፣ የኹለተኛው ዓለም (Second World) እና የሦስተኛው ዓለም (Third World) ተብለው ተከፍለዋል።

የሦስተኛው ዓለም ረድፍ ከአሜሪካ አልያም ከሶቬየት ህብረት ጎን ያልተሰለፉ አገራትን የሚያመላክት ነበር። ዛሬ ‹ሦስተኛው ዓለም› ተብለው እየተገለፁ ያሉት አገራት ያልዳበረ ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊ፣ አካባቢያዊ እና ሌሎች ጉዳዮች ያሏቸው አገራት ናቸው። ይህ የደረጃ ምደባ በአገራት መካከል የሥልጣን ተዋረድ ያመለክታል ተብሎ በምርምር ነክ ጽሑፎች ላይ ሲጻፍ እምብዛም አይስተዋልም።

አሁን ባለንበት ወቅት የሚያገለግለው ደግሞ የተባበሩት መንግሥታት የአገራት የኢኮኖሚ ልማት አከፋፈል – ያደጉ ኢኮኖሚዎች (developed)፣ በሽግግር ላይ ያሉ ኢኮኖሚዎች (transition) እና ባለአዳጊ ኢኮኖሚዎች (developing countries) ይሰኛሉ።

አገራት የኢኮኖሚ እድገት ማረጋገጥ ዋነኛው ግባቸው ነው። ኢኮኖሚ ብዙ ነገር ስለሚሸከምም እድገትን ማረጋገጥ የግድ አስፈላጊ ነው። የአገር ሉዓላዊነት ለማስከበር የዳበረ ኢኮኖሚ ባለቤት መሆን አስፈላጊነቱ አያጠያይቅም። በመሆኑም የኢኮኖሚ እድገትን ለማምጣት መንግሥታት ይጠቅማል ያሉትን የፖሊሲ መሣሪያ ሁሉ ይተገብራሉ።

በትንሽ መጠን የሚመዘገብ እድገት ትሩፋቱ ብዙ ነው። ለምሳሌ ስለኢኮኖሚ እድገት በሚመለከት ለተማሪዎች መማሪያነት በተጻፉ መጽሐፍት እንደተጠቀሰው በ2.5 በመቶ የእድገት ምጣኔ ሳያቋርጡ የሚያድጉ አገራት በየ28 ዓመቱ ኢኮኖሚያቸው በእጥፍ እንደሚጨምር በቀላል ሒሳብ ማየት ይቻላል። በተመሳሳይ እድገቱ የሦስት በመቶ መጠን ሲኖረው ኢኮኖሚው ከ23 ዓመት በኋላ በእጥፍ ይመነደጋል። በተመሳሳይ ወቅት አነስተኛ የሕዝብ ቁጥር እድገት ብቻ እንዲኖር ማድረግ ከተቻለ የነፍስ ወከፍ ገቢ በየኻያ ዓመቱ በእጥፍ ማሳደግ ይቻላል እንደ ማለት ነው።

ከአጠቃላይ የኢኮኖሚው ጥቅል ገቢ (GDP) ይልቅ የነፍስ ወከፍ ገቢ የአገራት የኢኮኖሚ ጥንካሬን በማመላከት ቁልፍ ነው። ይኸውም አገራት ለኑሮ ባላቸው ምቾት የሚለያዩት በነፍስ ወከፍ ገቢ በመሆኑ ነው። የዘመኑ እውነታ እንደሚያሳየውም በአሜሪካ እና በምዕራብ አውሮፓ የሚገኙት አገራት የነፍስ ወከፍ ገቢ በአማካይ ከሰሃራ በታች ካሉ የአፍሪካ አገራት ጋር ሲወዳደር ከሠላሳ ስድስት እጥፍ ይበልጣል።

እንዲህ ዓይነቱ ልዩነት የሚከሰተው ለረጅም ዓመታት ከሚኖር የኢኮኖሚ እድገት የተነሳ ነው። ለምሳሌ በአሜሪካ እ.ኤ.አ. በ1870 2 ሺሕ 244 ዶላር የነበረው የነፍስ ወከፍ ገቢ፣ በ1990 ወደ 19 ሺሕ 840 ዶላር የደረሰው ኢኮኖሚው በየዓመቱ በአማካይ በ1.75 በመቶ ብቻ ማደግ በመቻሉ እንደሆነ ተገልጾ ይገኛል። በመሆኑም በእንደዚህ ትናንሽ በሚመስሉ የእድገት ምጣኔ ልዩነቶች ሳይቀር (እድገቱ ሳይቋረጥ ማስቀጠል የተቻለ ከሆነ ነው) በጣም ጎልቶ የሚታይ የኢኮኖሚ ልማት መራራቅ ይፈጠራል ማለት ነው።

Robert Barro የተባለ የሃርቫርድ ዩኒቨርሲቲ የምጥኔ ሀብት አዋቂ እ.ኤ.አ በ1999 “Economic Growth” በሚል ርዕስ ባሳተመው መጽሐፉ፣ ኢትዮጵያን በምሳሌነት ተጠቅሞ ለንፅፅር ያቀረበበትን ሃቅ፣ አንድ ኢትዮጵያዊ ሲያነበው ያጥወለውለዋል። ‹‹ኢትዮጵያ ብትወጣ ብትወርድ፣ የአሜሪካን የ1990 የኢኮኖሚ አቅም ለማሳካት ከሦስት መቶ ዓመታት ያላነሰ ጊዜ ይፈጅባታል›› ይላል።

ይህንን ያነበብኩት በወቅቱ መንግሥት ኢኮኖሚውን በ11 በመቶ ማሳደግ ችያለሁ እያለ ይህንን ከተቃረነ ጋር ግብግብ እየገጠመ የነበረበት ነው። የዓለም የገንዘብ ድርጅት (IMF) ደግሞ እድገቱ ከሰባት በመቶ አይበልጥም ስላለ መንግሥት የሚይዘው የሚጨብጠው አጥቷል። በአገሪቱ ነዋሪ ዘንድም ግርታ በማየሉ ወደ አገራቸው ለጉዳያቸው የመጡ ዲያስፖራዎችን እየተከታተለ ‹እንዲህ አትመስለንም ነበር፣ አገራችን አሁን ስናያት ለካስ ተለውጣለች› እያስባለ በየሚድያው እያሰማን የነበረበት ወቅት ነው።

የመጽሐፉ አቀራረብ ተአምር ስለሆነብኝ የኢኮኖሚያችን እድገት በዓለም የገንዘብ ድርጅት ምጣኔ እንኳን ቢሆን ከላይ የትንሽ እድገት ትሩፋት ባየንበት እንዴት የአሜሪካንን የ1990 የነፍስ ወከፍ ገቢ ለማሳካት ዳገት ይሆንብናል የሚለው ይመላለስብኝ ነበር። በዚህም በመምህርነት ተቀጥሬ ከምሠራበት ዩኒቨርሲቲ በየወሩ በሚታተም መጽሔት ላይ ‹እውን ኢትዮጵያ አድጋለች?› በሚል ርዕስ ባሳተምኩት አንድ አጭር ጽሑፍ፣ በሰባት በመቶ ሳታቋርጥ ማደግ ብትችል ከግማሽ ምዕተ ዓመት ያላነሰ ጊዜ እንደሚፈጅባት ጻፍኩኝ።

ያንን በመጻፌ ከዩኒቨርሲቲው የበላይ አመራር ከሌሊት እንቅልፌ እያባነነ የሚያስነሳኝ ተግሳፅ ለማስተናገዴ ምክንያት ሆኖኛል። እንደ ባለሥልጣኑ ግልምጫ ‹ሃምሳ ዓመት ድረስ የማን ጎፈሬ እናበጥራለን› ነው። አቤት የካድሬ ግልምጫ ግን አያምጣው!

የኢኮኖሚ እድገት ልዩነት ምንጭ ምንድነው?
የኢኮኖሚ እድገትን በሚመለከት በተደጋጋሚ የሚነሳ ተለምዷዊ ጥያቄዎች አሉ። ‹ሀብታም አገሮች ምን ያህል ሀብታም ናቸው፣ ድሆችስ ምን ያህል ድሆች ናቸው? ሀብታም እና ድሃ አገሮች ምን ያህል በፍጥነት ያድጋሉ?› የመሳሰሉት ከጥያቄዎቹ ዋነኞቹ ናቸው። እነዚህን ጥያቄዎች ለመመለስ Robert Solow የተባለ አሜሪካዊ የምጣኔ ሀብት ምሁር እ.ኤ.አ. በ1956 “A Contributions of the Theory of Economic Growth” በሚል ርዕስ ድንቅ ጽሑፍ አሳትሞ ነበር።
የጸሐፊው ንድፈ ሐሳቦች ዋና ትኩረት፣ የካፒታል ክምችት (investment) እንዲሁም የቴክኖሎጂ ሽግግር ቀጣይነት ያለው የኢኮኖሚ እድገት በማረጋገጥ ሂደት ወሳኝ አንቀሳቃሽ ሞተር መሆናቸውን ማመላከት ነበር። ጸሐፊው ለዚህ ሥራው እና ቀጣይ የኢኮኖሚ እድገት በሚመለከት ግንዛቤያችን እንዲያድግ ላበረከተው አስተዋፅዖ በሚል እ.ኤ.አ. በ1987 በኢኮኖሚክስ የኖቤል ሽልማትም ተበርክቶለታል።

በተመሳሳይ የበለፀጉት አገራት አሁን ላሉበት የኢኮኖሚ ደረጃ በምን ቀመር/ፎርሙላ ለዚህ እንደበቁ የተጻፉ ሰነዶች ያብራራሉ። ለምሳሌ በሰሜን ምሥራቅ እና ደቡብ ምሥራቅ እስያ አገራት መካከል ሰፊ የሆነ የኢኮኖሚ ልማት ልዩነት (development gaps) እንዳለ ጆ ስቱድዌል (Joe Studwell) የተባለ እንግሊዛዊ ጸሐፊ ከፍተኛ አድናቆት በተቸረው “How Asia Works” በሚል ርዕስ እ.ኤ.አ በ2013 ባሳተመው መጽሐፉ ማስረጃዎችን በማጣቀስ አስደማሚ የሆነ ንፅፅራዊ የኢኮኖሚ ልማት ልዩነት ትንተና አቅርቧል።

ይህንን መጽሐፍ ቢሊየነሩ ቢልጌትስ በሥሙ የተቋቋመው ፋውንዴሽን ውስጥ የሚሠሩ ሠራተኞቹ እንዲያነቡት እስከማሳሰብ ደርሷል። እንደ ስቱድዌል አገላለፅ፣ በምሥራቅ እስያ አገራት መካከል ዋናው የኢኮኖሚ ልማቱ ልዩነት ከነባራዊ ሁኔታ ጋር የተስማማ ፖሊሲ ማውጣትና ይህንንም በጥብቅ ዲሲፕሊን መፈፀም የመቻል እና ያለመቻል ጉዳይ ብቻ እንደሆነ አብራርቷል።

ከዚህ ባለፈ መልክአ ምድር፣ የአየር ጠባይ እንዲሁም ባህል የጎላ ሚና እንደሌላቸው ገልጿል። በአጭሩ ‹የዘራኸውን ታጭዳለህ› እንደማለት ነው። ስለዚህም ሰሜነኞቹ ከነባራዊ ሁኔታቸው የሚስማማ ፖሊሲ አውጥተው በጠንካራ ዲሲፕሊን ሲያስፈጽሙ፣ የደቡቦቹ እስያዎች ደግሞ አብዝተው በዓለም ዐቀፍ የፋይናንስ ተቋማት በሚቀርብላቸው ከነባራዊ ሁኔታቸው የማይታረቅ ‹ምክር› እየተመሩ የሚፈልጉትን የኢኮኖሚ እድገት ማረጋገጥ አልተቻላቸውም። በዚህም ምክንያት አሁን ላሉበት ዝቅተኛ የኢኮኖሚ ደረጃ (በተነጻጻሪነት) ተዳርገዋል።

በአጭሩ ሲቀመጥ አገራት የስኬታቸው እንዲሁም የክስረታቸው መነሻም መድረሻም ፖሊሲ እና ፖሊሲ ብቻ እንደሚመለከት በሚገባ አስምሮበታል።
የሸቀጦች እና አገልግሎቶች ምርት በመጨመሩ የተነሳ የኢኮኖሚ እድገት ይከሰታል። የተጠቃሚዎች ሸመታ መጨመር፣ የዓለም ዐቀፍ ንግድ ማደግ (የወጪና ገቢ ንግድ ልዩነት) እና በካፒታል ወጪዎች የሚተገበሩ የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች እድገት ተደምረው የአንድ አገር ሸቀጦች እና አገልግሎቶች ምርት ደረጃ ላይ የእድገት ለውጥ ሲያመጡ ስለኢኮኖሚ እድገት እያወራን ነው ማለት ነው።

በመሆኑም በቀጣይነት ኢኮኖሚው የበለጠ እንዲያድግ የሚያግዙ አምራችና የመሠረተ-ልማት ተቋማት ግንባታ ሚናቸው ከፍተኛ መሆኑን ያመላክታል። ይህንን የምርት እድገት ለመጨመር ኢንቨስትመንት መስፋፋት አለበት። በመሆኑም የኢንቨስትመንት መጨመር የኢኮኖሚው የማምረት አቅም በማሳደግ የኢኮኖሚ ዕድገትን ያፋጥናል።

ስለዚህ ኢኮኖሚን ለማሳደግ እንዲሁም የሥራ ዕድልን ለመጨመር የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች ሚና ትልቅ ነው። አገራዊ የኢኮኖሚ ግቦችን ለማሳካት የሚወጡ የልማት ፖሊሲዎች ወደ መሬት የሚወርዱት በፕሮጀክት መልክ ተመንዝረው ነው። ፕሮጀክት በተወሰነ ቦታ፣ የተወሰነ ግብ፣ የተወሰነ በጀት ተመድቦ በተወሰነ ጊዜ እንዲጠናቀቅ በጥድፊያ የሚሠራ ሥራ ነው።

ለምሳሌ ከአዲስ አበባ ሐዋሳ የሚያገናኝ የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክት ወይም በርዕሱ እንደተመለከተው የእንጦጦ ፓርክ ፕሮጀክት ለአብነት መጥቀስ ይቻላል። የፕሮጀክቶች ድምር አፈፃፀም የአገሪቷን ጥቅል ፖሊሲ ስኬት አልያም ውድቀት አመላካቾች ሊሆኑ ይችላሉ። ለእነኚህ ፕሮጀክቶች ማስፈፀሚያነት የተመደበ የካፒታል ሀብት ሳይባክን ለታለመለት ግብ ብቻ መዋል ስላለበት ሁነኛ የፕሮጀክት ክትትልና መቆጣጠሪያ ስርዓቶች (monitoring and evaluation system) በመዘርጋት ከፍተኛ ቁጥጥር ሊደረግበትም ይገባል። የአገራት ተሞክሮ እንደሚያሳየውም በዓለም ላይ የፋይናንስ ቁጥጥር እና አመራር ስርዓት ሳያደርግ ያደገ አገርም ማግኘት አዳጋች ነው።

በሁሉም አገር የመንግሥት ሚና የአገሪቱ ኢኮኖሚ አቅጣጫውን ሳይስት እድገት እንዲያስመዘግብ ውጤታማ የሆኑ የተለያዩ መደበኛ የፖሊሲ መሣሪያዎችን በመጠቀም የመሪነት ሚናውን መወጣት ነው። በተጨማሪም ግዙፍ የሆኑ ኢንቨስትመንቶችንም ያከናውናል። እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አዳጊ አገራት የሚገኘውን ውስን የመሠረተ ልማት ተቋማት ለማስፋፋት መንግሥት ዋናውን ሚና ይጫወታል።

ከእነኚህ የመሠረተ-ልማት ዝርጋታዎች በተጨማሪ በኢኮኖሚው ውስጥ ንቁ ተሳታፊ መሆን እንዳለበትም እንዲሁ አያጠያይቅም። በመሆኑም በኢትዮጵያ በየዓመቱ የመንግሥት ኢንቨስትመንት በከፍተኛ መጠን እያደገ ይገኛል። መንግሥት ወጪው ሲጨምር በባንኮች ውስጥ ያለውን የብድር አቅርቦት ለብቻው ስለሚጠቀም የግሉን ክፍለ-ኢኮኖሚ እንዲቀጭጭ ስለሚያደርግ (Crowding-out effect) የግል ኢንቨስትመንት እንዳያድግ እንቅፋት ሆኗል በሚል ትችት የሚሰነዝሩ አሉ።
መንግሥት በኢኮኖሚው ውስጥ በጉልህ መሳተፍ እንዳለበት የሚወተውቱ አካላት ደግሞ የሚያቀርቡት መከራከሪያ ነጥብ አለ። ይህም የግሉ ክፍለ-ኢኮኖሚ ገበያው በሚፈልገው ልክ ምርትና አገልግሎት ሙሉ ለሙሉ አሟልቶ የማቅረብ ክፍተት ያለበት በመሆኑ፣ (ትርፍ የማያስገኝ ከሆነ አምርቶ የማቅረብ ፍላጎት ስለማይኖር) የፍላጎቶች አለመሟላት ስለሚያጋጥም የገበያ ጉድለት (market failure) ይከሰታል የሚል ነው።

ይኸውም የግሉ ዘርፍ ትርፍን በሚያስገኙ ተግባራት እንጂ ለብዙኀኑ ሕዝብ አገልግሎት የሚያበረክቱ ኢንቨስትመንቶችን የሚያከናውን ባለመሆኑ፣ በኢኮኖሚው መንግሥት ንቁ ተሳታፊነት (ጣልቃ ገብነት) ሊኖረው እንደሚገባ እንደማስረጃነት ይጠቅሱታል። ይህ ማለት ግን በአዳጊ አገራት መንግሥት ድርብ ኃላፊነት ስላለበት ይህንን መወጣት እንዳለበት ለማመላከት እንጂ፣ ሁሉንም የኢንቨስትመንት ተግባራት ብቻውን መሥራት ከቻለ ህብረተሰቡ ይጠቀማል ለማለት አይደለም። የንግድ ውድድር (libralized market) ባለመኖሩም ህብረተሰቡ የሚጎዳበትም አግባብ ይኖራል።

የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ለማስተርስ ዲግሪ መመረቂያቸው “AFRICAN DEVELOPMENT: DEAD ENDS AND NEW BEGINNINGS” በሚል ርዕስ ባዘጋጁት የጥናት ጽሑፋቸው ስለዚሁ ጉዳይ እንዲህ ሲሉ አብራርተዋል፤ ‹‹በማደግ ላይ ባሉ አገራት ውስጥ ጥልቅ የሆኑ የገበያ ጉድለቶች እንዲሁም ተቋማዊ ክፍተቶች የተንሰራፋባቸው በመሆኑ እጅግ በአስከፊነቱ በሚገለፅ የድህነት አዙሪት ውስጥ እንዲገኙ ምክንያት ሆኗል። በመሆኑም በገበያ ሕግ የመጫወቻ ዘዴዎች በመታገዝ ብቻ የተፋጠነ ልማት ማምጣት ስለማይቻል የመንግሥት ሚና ጉልህ ብቻ ሳይሆን የግድ አስፈላጊም ነው››

በመሆኑም መንግሥት የቁጥጥርና የመሪነት ሚናውን በአግባቡ እየተወጣ ከግሉ ዘርፍ ጋር ፕሮጀክቶችን በማቀድና በመፈፀም ተባብሮና ተቀናጅቶ ቢሠራ ለዘላቂ እድገት የሚኖረው ፋይዳ ከፍተኛ ነው። ይህም በእንጦጦው ፓርክ ፕሮጀክት በተግባር ታይቷል። በዚሁ ወደተነሳሁበት የእንጦጦ ፓርክ ልማት የሚኖረው ፋይዳ መዳሰስ ተገቢ ነው።

የአዲስ አበባ ፓርኮች ግንባታ ትሩፋቶች
በአገራችን አረንጓዴ ኢኮኖሚ (Green Economy) እንደዚሁም ዘላቂነት ያለው ልማት ማረጋገጥ የሚሉ ቃላት ተደጋግመው ሲጠሩ እንሰማለን። በዓለም ዐቀፍ ደረጃም በምርምር ጽሑፍ ህትመትና የአገራት ልማት ትብብሮች መካከል በሚደረጉ ግንኙነቶች፣ እነዚህ ቃላት ሲደጋገሙ ይሰማል። ለአብነትም በተባበሩት መንግሥታት ይፋ የተደረጉት የዘላቂ ልማት ግቦች (Sustainable Development Goals -SDGs) ‹ለሁሉም የተሻለ እና ቀጣይነት ያለው ልማት ለማምጣት የሚያስችል ንድፍ› ተብለው የተቀየሱ 17 እርስ በእርሳቸው የተሳሰሩ ግቦች ስብስቦች ናቸው።

‹ዘላቂነት› የሚለው አገላለጽ የሚያመለክተው የወቅቱ ትውልድ ወደፊት የሚመጡትን ትውልዶች ለኑሮ የሚያስፈልጉ ነገሮች የመጠቀም መብት በጉልህ ሳይነካ የአሁን እና የወደፊት ፍላጎቶች ሚዛን በመጠበቅ ፍላጎቱን ማሟላት ለማመላከት ነው። ይህንንም የዘላቂነት ትርጉም ግልፅ ለማድረግ እርስ በእርስ የተሳሰሩት አስራ ሰባቱ የተባበሩት መንግሥታት የልማት ግቦች በሦስት ዋና ዋና ምሰሶዎች ማለትም፡- ኢኮኖሚያዊ፣ አካባቢያዊ እና ማህበራዊ ልማት ስር ተሰድረው ይቀርባሉ።
የእነዚህን ሦስት ምሰሶዎች መደበኛ ባልሆነ አገላለፅ በሰዎች (people)፣ በመሬት (earth or environment) እና በትርፍ (economic benefits) ፍላጎት መካከል ሚዛን ማስጠበቅ መቻል ‹ቀጣይነት› አልያም ‹ዘላቂነት› ተብሎም ይገለፃል።

በመሆኑም ቀጣይነት ላለው እድገት ተግባራዊ የሚደረጉ ፕሮጀክቶች የዘላቂነት ልማት መስፈርቶችን ማሟላት ይኖርባቸዋል። ኢኮኖሚን ማሻሻል ወይም ማሳደግ መሠረታዊ ነገር እንደሆነ ከላይ ዐይተናል። ምክንያቱም ያለ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ በምድር ላይ ሕይወትን ማኖር አንችልም። ይህም በመሆኑ የወቅቱ ትውልድ በሚከውናቸው ኢኮኖሚ-ነክ ሥራዎች (ማለትም የማምረት [production] አልያም የመጠቀም [consumption decisions]) ወደፊት ለሚመጡት ትውልዶች (future generations) ወይም ከአካባቢ (የተፈጥሮ ሀብት) ጥበቃ ጋር የሚያያዙ ተጽዕኖዎች ይኖሩታል።

ስለሆነም በኢኮኖሚ፣ በአካባቢ እና በትውልዶች (societies) መካከል ሚዛን ማምጣት እጅግ ወሳኝ ነው። ለአብነት የፕላስቲክ ከረጢት እዚህም እዚያም ሲጣል አካባቢን ከማራቆት አልፎ የግብርና ምርት የሚያደናቅፍ በመሆኑ አንዳንድ አገራት ይህን ምርት በገበያ እንዳይሸጥ እስከማገድ ደርሰዋል። ፕላስቲኩን ማምረት ለዜጎች የሥራ እድል ቢፈጥርም ቀጣይነት የምንለው ልማት ለማረጋገጥ አያግዝም።

ለማህበራዊ ዘላቂነት (Social sustainability) መስፈርት መሳካት ፕሮጀክቶች ድሃ-ተኮር ሆነው የአብዛኛው ድሃ ማህበረሰብ ሕይወት የሚቀይሩ መሆን አለባቸው። አካባቢያዊ ዘላቂነት (environemtnal sustainability) ስንል የሚተገበረው ፕሮጀክት የውሃ፣ የአፈርና የአየር ጥራት እንዲጠበቁ እንዲሁም ብዝኀ ሕይወትን የሚያስፋፋ መሆን አለበት።

በእነኚህ ሦስት ምሰሶዎች መካከል አንዱን ብቻ አንጠልጥሎ ሌሎቹን ጥሎ የሚጠበቅ ሚዛን አይኖርም። ለምሳሌ የምግብ ምርትን ለማሳደግ ደን ሲመነጠር የሚታረሰው መሬት ጨምሮ ለጊዜው ምርት ያድጋል። ሆኖም ግን በደን ምንጣሮ የተነሳ በነፋስና በጎርፍ የአፈር መከላትና በሂደት ለምነት መቀነስ የኋላ ኋላ ምርትና ምርታማነት መቀነሱ ስለማይቀር ለህብረተሰቡ አስፈላጊ የሆነው የምግብ አቅርቦት ማረጋገጥ አዳጋች ያደርገዋል።

በመሆኑም እንዲህ ያሉትን የተፈጥሮ ሀብትን የሚያራቁቱ፣ በሂደትም ለምርት እድገት መቀነስ ምክንያት የሚሆኑ የዜሮ ድምር ኢንቨስትመንቶች ቀጠይነት/ዘላቂነት የሚያረጋግጡ የልማት ሥራዎች ልንላቸው አንችልም።

ከላይ ለመግለጽ እንደሞከርኩት ከሰሞኑ በእንጦጦ ለመመረቅ የበቃው የጠቅላይ ሚኒስትሩ ፕሮጀክት ኢኮኖሚን፣ አካባቢንና የድሆችን የኑሮ ሁኔታ በዘላቂነት የሚያሻሽል እንደመሆኑ ቀጣይነት ከሚያረጋግጡ የልማት ሥራዎች የሚመደብ ነው።

ከዚህ በተጨማሪም እንደአገር የነበረብን ፕሮጀክቶች በዕቅድ መሰረት ሠርቶ የማጠናቀቅ ድክመት እርምት የተወሰደበት፣ ለትውልድ ተሻጋሪ የሆነና ከአካባቢው ስነ-ምህዳር ጋር የተስማማ (Eco-friendly) በመሆኑ የሚያስገኘው አስተዋጽኦ እንዲሁ በቀላሉ መታየት የለበትም። በመሆኑም ከሦስት የዘላቂ ልማት ምሰሶዎች ጋር በማያያዝ ሳይንዛዛ ለአብነት እንዲሆን የእነዚህ ፓርኮች ፋይዳ መዳሰስ እንችላለን።

ከሁሉ በላይ አገሪቷ በምትመራበት የጎሳ/ብሔር ፖለቲካ ስርዓት የተነሳ ዜጎች በገዛ አገራቸው በማንነታቸው የተነሳ እጅግ አሳዛኝ ለሆነ ጥቃት እየተጋለጡ ባለበት በዚህ ወቅት፣ የሰውን ልጅ ክቡርነት ለማመላከት በምስለ-ሰብ ዲዛይን ተግባራዊ የተደረገው ፕሮጀክት ላስተዋለ መልዕክቱ ቀላል አይደለም። በአራቱም የአገሪቱ አቅጣጫ ኋላቀር በጎሳ ላይ የተመሠረተ ስርዓት መሠረት እንዲይዝ ተደርጓል።

ይህ እኩይ ሥራ ለዓመታት የተለፋበት እንደመሆኑ የዘመናዊው ዓለም የደረሰበት በዜግነት ላይ የተመሰረተ የፖለቲካ ስርዓት (የተለያዩ ባህሎቻችንና ቋንቋዎቻችን የሚያበለጽግ ሆኖ) መሬት ለማስያዝ እንዲያመላክቱ ከተቀረፁ ፕሮጀክቶች ውስጥ አንዱ ነው።

ስለዚህም የፕሮጀክቱ ፍፃሜ ተከትሎ በአንድ አቅጣጫ የሚዥጎደጎደው ማጥላላት ስንመረምር በአገሪቷ ለዓመታት በልዩነት ላይ የተመሠረተ የፖለቲካ እሳቤ ተቋማዊ ቁመና እንዲኖረው የተለፋበት እኩይነት የሚደረምስ በመሆኑም ጭምር ነው። በመሆኑም በዚህ እሳቤ የተቀረፀውና በፍጥነትም ተጠናቅቆ ለሕዝብ ክፍት የተደረገው የእንጦጦ ፕሮጀክት ለአገር አንድነትና ሥልጡን ለሆነ ፖለቲካ መሰረት ከሚጥሉ ቋሚ ማሳያዎች እንደ አንዱ ይመደባል።

በሌላ በኩል የእንጦጦ ደን ልማት ለአካባቢው ነዋሪዎች ለዘመናት በቁጥቋጦ ለቀማ ላይ ብቻ እንዳይንጠላጠሉ ዘላቂ የሆነ ኢኮኖሚያዊ ጥቅም በማስገኘቱ፣ ኑሯቸውን ስለሚያሻሽል ዘላቂነት የሚያረጋግጥ ፕሮጀክት እንደሆነ መረዳት ይቻላል። ይህን ፕሮጀክት ይፋ ባይደረግ የአካባቢው ነዋሪዎች ለዘመናት ተለምዷዊ በሆነው የሥራ እንቅስቃሴያቸው ቢቀጥሉ በቁጥቋጦ ለቀማው ላይ ብቻ ሊቆሙ አይችሉም።

በመሆኑም ደኑ ለሁሉም ቁጥቋጦ ለቃሚ ክልከላ የሚደረግበት እንዳለመሆኑ (እንዲህ ያሉት በዘርፉ አገላለጽ Comon-Pool Resources ይባላሉ) እየተመናመነ ስለሚሄድ የቁጥቋጦ አቅርቦት ማድረግ እየተሳነው ይመጣል። በመሆኑም ከቁጥቋጦ ለቀማ ወደ ተደራጀ የደን ምንጠራ መሸጋገሩ የጊዜ ጉዳይ ብቻ ይሆናል።
በተለያዩ ጥናቶች እንደቀረበው በሕዝብ ቁጥር እድገት የተነሳ በዚያው ድህነት ስለሚስፋፋ (ድሃ ብዙ ስለሚወልድ የሕዝብ ቁጥር እድገትና ድህነት መሳ ለመሳ ስለሚጓ) ለዚህ ውድመት ከፍተኛ አስተዋፃኦ የሚያበረክት ስለመሆኑ እርግጥ ነው። እንግዲህ የሚሆነውን በአጭሩ ለመግለጽ የGarrett Hardin ግሩም ገለፃ የሆነው “tragedy of the commons” እዚህችው ጋር ማምጣት መረዳቱ ግልጽ ያደርገዋል።

በመሆኑም የአዲስ አበባ ሳንባ የሚባለው ጥቅጥቅ የእንጦጦ ደን ታሪክ ሆኖ ይቀራል ማለት ነው። ነገር ግን ተግባራዊ በተደረገው ፕሮጀክት የተነሳ የአካባቢው ነዋሪዎች በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ቋሚ የሆነ ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ስለሚያገኙና እንደቀድሞው ኑሯቸው በደን ምርት (forest products) ላይ ብቻ ስለማይንጠለጠል፣ ለተፈጥሮ ሀብቱ ጥበቃ መጠናከር ጉልህ ድርሻ ይኖረዋል።

ይህም የሚያሳየው ድህነት (Poverty) እና የአካባቢ ውድመት (Environmental degradation) የጠበቀ ዝምድና ያላቸው መሆኑን ነው። የአካባቢው ነዋሪዎች የኑሮ ሁኔታቸው እየተሻሻለ ሲሄድ ጫካውን ከማውደም ተጨማሪ ዛፎችን የመትከል ተግባራት መከወን እንደሚችሉ መረዳት ለተሳነው፣ የምዕራባውያን አገራት በአረንጓዴ የመሸፈናቸው ምስጢር የኢኮኖሚ ልማት መረጋገጥ መሆኑ አልተገለፀለትም ማለት ነው።

ሲጠቃለል ፕሮጀክቱ በሺዎች ለሚቆጠሩ ዜጎች ተቀጥረው የሚሠሩበት የሥራ ዕድል ያስገኛል። በዚህ ፕሮጀክት ምርትና አገልግሎት ይቀርብበታል። የኢኮኖሚ እድገት ለማምጣት ለሚደረገው ርብርብም የማይናቅ አስተዋፅኦ ያበረክታል። አካባቢው በመልማቱ የተነሳ በተዘዋዋሪ ለአካባቢው ነዋሪዎች የሚከፈቱ የኢኮኖሚ (የገበያ) እድሎች ይኖራሉ።

ሌላው መንግሥት ፕሮጀክቱን ከግሉ-ዘርፍ ጋር በመናበብ ተቀናጅቶ የከወነው እንደመሆኑ የመንግሥትና የግሉ ክፍለ-ኢኮኖሚ ቅንጅት (Public Private Partnership – PPP) ውጤታማነቱ የተረጋገጠበት ነው። በመሆኑም በቀጣይም በሌሎች ፕሮጀክቶች ይህንን መልካም ተሞክሮ ለማስፋፋት ይረዳል።
የፕሮጀክቱን መጠናቀቅ ተከትሎ በግንባታው የተሳተፉት ባለሀብቶች ለግንባታው ያወጡትን ወጪዎች በቶሎ መመለስ ስላለባቸው ‹እጄን እግሬን!› ሳይሉ በባለቤትነት መንፈስ ወዲያውኑ አገልግሎት የማቅረብ ሥራቸውን ለማከናወን መጀመራቸውም ታይቷል። በዚህም ፕሮጀክቱ በመንግሥት ብቻ የተገነባ ቢሆን በዚህ ፍጥነት አገልግሎት ለመስጠት ዝግጁነት ማየት ይቻል ነበር ወይ ብሎ መጠየቅ ተገቢ ነው።

መንግሥትም በዚህ የተነሳ (በተለይ የሞቀ ገበያ ባለበት አዲስ አበባ አቅራቢያ እንደመመሥረቱ) በግብር እና በሚያቀርባቸው አገልግሎት የሚሰበስባቸው ገቢዎች በቀላሉ የሚታዩ አይሆንም። ይህንንም ገቢ በመጠቀም በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ለሚያከናውናቸው ሌሎች ፕሮጀክቶች አስፈላጊ የሆነውን የፋይናንስ አቅርቦት ያስገኝለታል።

በፓርኩ የሚሰጡት አገልግሎቶች ባደጉት አገራት የተለመደ አይነት ሲሆን (የቤተ-መንግሥት ለጎብኝዎች ክፍት መሆኑ ሲታከልበት) ከፍተኛ ቁጥር ያለው የቱሪስት ፍሰት ስለሚጨምር፣ ለቱሪዝም ዘርፉ እድገት ተጨማሪ ሲሳይ ያስገኛል።

ፕሮጀክቱ ከዲዛይኑ እስከ ትግበራው አንድም የውጭ እጅና ሀብት ያላረፈበት እንደሆነ በዘጋቢ ፊልሙ መጠቀሱንም ሰምቻለሁ። በዚህም በህዳሴው ግድብ ፕሮጀክት ግንባታ እንደታየው ከተባበርን በራሳችን እውቀትና ሀብት ተዓምር እንደምንሠራ ዳግም የተመለከትንበት ነው። በአገራችን ሰላምና መረጋጋት ሰፍኖ ሁሉም ወደ ሥራ ቢሰማራ በአጭር ጊዜ ቀጣይነት ያለው እንዲሁም በሁሉም ዘንድ ተዓማኒነት የሚኖረው እድገት ማምጣት እንችላለን።

በእንዲህ አይነት የሚጠናቀቁ “ነገን የሚያመላክቱ” ፕሮጀክቶች ቀጣይነትን ስለሚያረጋግጡ ተደምረው አገርን ያሳድጋሉ። በመሆኑም ባለንበት የድህነት ምድብ ላይ ሆነን አንቀርም። ይህንን ፕሮጀክት ግንዛቤው ካለን አቃልለን የምናየው አይደለም። በመሆኑም ፕሮጀክቱን አስጀምረው እስኪፈፀም በሚገባ ተከታትለው ለመሩት ድምፃዊዋ ቻቺ ታደሰ በእንባ ታጅባ ‹ዶ/ር ዐቢይ አመሰግንሃለሁ› እንዳለችው፣ አገር ሠሪዎችን እያገዝን ማበርታት አለብን። ምስጋና ለሚገባው እናመስግን። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ እኔም እንደ አንድ ዜጋ ይህን ስላሳዩን አመሰግኖታለሁ።

ሽመልስ አርአያ (ዶ/ር) በጀርመን አገር ከሚገኘው ጊሰን ዩኒቨርሲቲ በኢኮኖሚክስ የዶክትሬት ዲግሪ አግኝተዋል። ከዚህ ቀደም በሐዋሳ ዩኒቨርስቲ በመምህርነት አገልግለዋል። በኢሜይል አድራሻቸው araya.gedam@gmail.com ይገኛሉ።

ቅጽ 2 ቁጥር 102 ጥቅምት 7 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com