ወሲባዊ ጥቃት አድራሾች በኅብረተሰቡ እንዲገለሉ የሚያደርግ ስርዓት ሊዘረጋ ነው

Views: 213

ብሔራዊ የጥቃት አድራሾች መረጃ ሥርዓት የወሲብ ጥቃት ፈጻሚ ወንጀለኞችን ለመያዝ፣ ለመቆጣጠር ለመከታተል እና ብሎም በሕብረተሰቡ እንዲገለሉ ማድረግ የሚያስችል ስርዓት እየተዘጋጀ ነው።

የሴቶች ወጣቶችና ሕጻናት ሚኒስቴር በሕጻናት፣ በወጣቶች እና ሴቶች ላይ የሚፈጸመውን ጥቃት ለመከላከል ቅንጅታዊ አሠራርን መሰረት ያደረገ የብሔራዊ ጥቃት አድራሽ መረጃ ሥርዓት እየተዘጋጀ መሆኑን ሚኒስቴሩ ለአዲስ ማለዳ አስታውቋል፡፡

ሥርዓቱን ወደ ተግባር ለማስገባት በአሁን ወቅት በጥናት ላይ እንደሚገኝ በሴቶች፣ወጣቶችና ሕጻናት ሚኒስቴር የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አድነው አበራ ለአዲስ ማላዳ አስታውቀዋል።

ጥቃት አድራሾችን ለመቀነስም ከትምህርት ተቋማት፤ከጸጥታ እና ፍትህ ተቋማት እንዲሁም በማህበራዊ ጉዳይ ላይ ከሚሰሩት ተቋማት ጋር በጋራ እንደሚሠራም አድነው ገልጸዋል።

እየተዘጋጀ ስላለው ሥርዓት የሚገልጹት አድነው፤ አንድ ግለሰብ ጥቃት በሚፈጽምበት ወቅት በወንጀል ተጠያቂ ቢሆንም ነጻ በሚሆንበት ጊዜ ግን ከማህበራዊ ነገሮች ላይ እንዲገለል ያደርገዋል ነው ያሉት፡፡

ይህም ማለት ጥቃት አድራሹ አካል፤ ጥቃት ከመፈጸሙ በፊት ቆም ብሎ እንዲያስብ ስለሚያርገው እንደሆነ ታምኖበት ነው ብለዋል።
ጥቃት አድራሹ ግለሰብ በማሕበራዊ ሕይወቱ መገለል አለበት ሲባልም በምን ዓይነት አገልግሎት መሳተፍ የለበትም ወይም አገልግሎት እንዳያገኝ የሚደረግ ሲሆን የአገልግሎቶቹ ዓይነቶች የትኞቹ ናቸው የሚለው ግን በጥናት የሚመለስ እንደሆነ አድነው ጠቁመዋል።

ነገር ግን ግለሰቡ የሚያጣው አገልግሎት ምንደው ነው? የሚለው ከሕግ ጋር የማይጣረስ እንዲሆን በደንብ እያጠናን ነው ሲሉ አድነው አስታውቀዋል።
‹‹አንድ ግለሰብ አንድ ጊዜ ካጠፋ፤ እንዴት ኹለት ጊዜ ሊቀጣ ይችላል የሚያስብል ጥያቄም የሚያስነሳ ሲሆን ይህንንም በጥናት ውስጥ እንዴት መመለስ እንዳለበት እየመከርንበት እንገኛለን›› ብለዋል – አድነው።

ምንም እንኳን ሥርዓቱ ይህንን ዓላማ ያድርግ እንጂ ነገሩን ከሰብዓዊ መብት አንጻርም ማጤን እንደሚያስፈልግ አድነው አስረድተዋል።ሥርዓቱን ተግባራዊ ለማድረግም በአሁን ወቅት ጥናት ከማድረግ ጎን ለጎንም እየተመከረበት እንደሚገኝም ጠቁመዋል፡፡

ጥቃት አድራሾቹን ለመያዝ፣ለመቆጣጠርና ለመከታተል የሚያግዝ የመረጃ ቋት ከማዘጋጅት በተጨማሪ ከወረዳ ጀምሮ እስከ ፌደራል ድረስ የሚገኙ የተለያዩ ተቋማትም በስራው ላይ ተሳታፊ ይሆናሉ ተብሏል።

ምንም እንኳን አንድ ሠው ወንጀም ከፈጸም የሚጠየቅ ቢሆንም በሴቶች ወጣቶችና ሕጻናት ሚኒስቴር በኩል ለማስተማሪያ ይሆን ዘንድ በዚህ መቆም የለበትም ብለን እየሠራን እንገኛለን ይህም የሚፈጸመውን ጥቃት ለመከላል እንደሚረዳ ስለታለመነበት ነው የታቀደው ብለዋል።

የኮቪድ-19 ወረርሽ በኢትዮጵያ መከሰቱን ተከልትሎ በሴቶችና ሕጻናት ላይ የሚደርሰው ጥቃት እቀዱን ለማዘጋጀትም ምክንያት ሆኗል።
የሕግ ባለሙያው አወል ሱልጣን በበኩላቸው ሰዎች ወንጀል ሲፈጸወሙ ቅጣት እንደሚተላለፍባቸው ኹሉ መጀመሪያ ማሕበረሰቡን ወንጅል ከመፈጸም እንዲቆጠብ ማስተማር መቅደም እንዳለበት ለአዲስ ማለዳ ገለጸዋል፡፡

አስቀድሞ በሥነልቦና ላይ መሠራት ከተቻለም ጥቃቱን መቀነስ እንደሚቻል ጠቁመዋል። ለምሳሌ እንኳን ይላሉ አወል ፤በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ምክንይት የቤት ውስጥ ጥቃቶችን እንዲሁም ወስባዊ ጥቃትን ሲፈጸሙ እንደነበር አንስተዋል።

እንዲህ ዓይነት ጥቃት መፈጸማቸውን ተከትሎ ሴቶች ወጣቶችና ሕጻናት ሚኒስቴር ለመከላከል እየሄደበት ያለው ነገር ጥሩ ነው ብለዋል፡፡
አስቀድሞ ማስተማር ቅድሚያ የሚሰጠው ነገር ቢሆንም ጥፋተኛ ሆኖ ማረሚያ ከገባ በኋላ የግለሰቡ ሥነ ምግባር እንዴት ነው የሚለውን ማረሚያ ቤቱ የሚመልሰው በመሆኑም ከማረሚያ ቤቶች ጋርም በጋራ መስራት ያስፈልጋል ሲሉ አወል ሃሳባቸውን ያክላሉ።

ይሁን እንጂ ሚኒስቴሩ የወጠነው እቀድ አንድን ጥቃት አድራሽ ግለሰብ በማህበራዊ ኑሮ እንዴት መገለል እንዳለበት እናሳያለን ብሎ መስራት በራሱ ሌላ ችግር የሚፈጥር ሊሆን ስለሚችል በጣም በጥንቃቄ መደረግ አለበት ነው ያሉት።

ሃሳቡ ምንም እንኳን የሚደገፍ ቢሆንም ጥንቃቄ የሚያስፈልግ ነገር እንደሆነ የህግ ባለሙያው አወል አሳስበዋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 102 ጥቅምት 7 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com