መንግሥት በአምበጣ መከላከል ላይ ምን ድረስ ሄዷል?

Views: 271

መንግስት ከፍተኛ የሆነ መዘናጋት እያሳየ ያለበት ሁኔታ መሻሻል ቢኖረው በየዘርፉ ትክክክለኛውን አቅጣጫ ማስቀመጥ መለመድ አለበት በማለት መንግስት ተዘናግቷል የሚሉት በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ መምህር የሆኑት መስከረም አበራ ናቸው ፡፡አሁን ላይ እንደዚህ ከመራገቡ በፊት በአንበጣ ዙርያ ተደጋጋሚ ጥቄዎች እና ቅሬታዎች ጥቆማዎች ሲነሱ መንግስት በከፍተኛ መዘናጋት እና ቸልተኝነት አሳይቶበታል፡፡ ለምሳሌ የፀረ -ተባይ መርጫ አውሮፕላኖች ቁጥር ለመጨመር የታሰበውን ጉዳይ ቀደም ብሎ ማስፈፀም ቢቻል እና ቅድመ ጥንቃቄ ላይ ትኩረት ቢሰጥ መልካም ነበር ባይ ናቸው፡፡

ኢትዮጲያ አጠቃላይ በግብርናው ዘርፍ ላይ ህልውናዋ የተመሰረተ አገር እንደሞሆኗ ግብርናውን መንከባከብ እና መከታተል አስፈላጊ ነበር፡፡ እናም ቅድመ ጥንቃቄ ላይ ትኩረት ቢደረግ ከፍተኛ የሆነ ጉዳት ሳይደርስ መመለስ ይቻል ነበር፡፡ መስከረም እንደሚሉት ፀረ -ተባይ የሚረጩት አውሮፕላኖች ቀድመው ተዘጋጅተው እየጠበቁ ቢሆን ኖሮ መልካም ነበር፡፡ ነገር ግን አምበጣው መንሰራፋት በጀመረ ሰዓት ወደ ጥገና መግባቱ ጉዳቱ ከፍ እንዲል ከማድረጉም ባሻገር መዘናጋቱን ደግሞ ጎልቶ እንዲታይ አድርጎታል ሲሉ አስተያየታቸውን ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል፡፡

የግብርና ሚኒስቴር የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ የሆኑት አበራ ለማ በበኩላቸው ለአዲስ ማለዳ እንደገለፁት ደግሞ ተቋማቸው ከፍተኛ የሆነ ስራ እየሰራ እነደሚገኝ አንስተው ከነበሩት ላይ ሌሎች አዳዲስ የፀረተባይ መርጫ አውሮፕላን እየገቡ እየሆነ ብቻ ለመናገር ወደዋል፡፡

አሁን ባለው ሁኔታ በአማራ ክልል 80 ሺ ሄክታር የሚጠጋ መሬት ላይ የአንበጣ መንጋ ተከስቷል ፡፡ በአማራ ክልል ከመስከረም ወር መጀመሪያ ሳምንት ጀምሮ የተከሰተው የአንበጣ መንጋ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰ መሆኑን የክልሉ ባለስልጣናት እየተናገሩ ነው፡፡ የአንበጣ መንጋው በአንዳንድ ቀበሌዎች የተዘራ ሰብልን ሙሉ በሙሉ ያወደመ ሲሆን በአንዳንዶቹ ደግሞ የጉዳት መጠኑ ከ50 በመቶ በላይ መሆኑ ተገልጿል።

በአማራ ክልል በሚገኙ ሦስት ዞኖች፣ በስምንት ወረዳዎች እና በ66 ቀበሌዎች የአንበጣ መንጋ ወረርሽኝ መከሰቱን የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ምክትል ኃላፊ ተስፋሁን መንግስቴ መናገራቸው ይታወሳል፡፡በአማራ ክልል ከሚገኙት የኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር፣ ደቡብ ወሎ እና ሰሜን ወሎ ዞኖች በተጨማሪ ጉዳቱ ያን ያክል የከፋ ባይሆንም በሰሜን ሸዋ ዞን ቀወት ወረዳ በቅርቡ ወረርሽኙ መከሰቱንም ያብራራሉ። በእነዚህ አካባቢዎች ከ151 ሺህ ሄክታር መሬት በላይ አሰሳ ተደርጎ በ78 ሺህ 800 ሄክታር ላይ የአንበጣ መንጋው መከሰቱ መረጋገጡን ምክትል ቢሮ ኃላፊው ጨምረው ገልፀዋል።

ተስፋሁን ይህንን ከግንዛቤ በማስገባት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እየሰሩ መሆናቸውን ይናገራሉ። በየአካባቢው በተለያየ ጊዜ አንበጣው የተከሰተ ሲሆን፤ ነገር ግን በአብዛኛው ከመስከረም ወር የመጀመሪያው ሳምንት ጀምሮ የተከሰተ መሆኑንም ጨምረው ያስረዳሉ።

በራያ ቆቦ ወረዳ የአንበጣ መንጋው ለመጀመሪያ ጊዜ የተከሰተው መስከረም ስድስት ነው ያሉት የወረዳው አስተዳዳሪ መንገሻ አሸብር፤ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ሕብረተሰቡ በተለያዩ የመከላከያ መንገዶች ለመከላከል ጥረት ቢያደርግም በየቀኑ ከአፋር ክልል እየተፈለፈለ የሚመጣው አዲስ የአንበጣ መንጋ ከአቅም በላይ እየሆነ መምጣቱን ተናግረዋል። የአንበጣ መንጋው በወረዳው ከአፋር ክልል ጋር በሚዋሰኑ ዘጠኝ ቀበሌዎች የተከሰተ መሆኑን የተናገሩት መንገሻ፤ በወረዳው ወርቄ እና ያያ የሚባሉ ቀበሌዎች ላይ በሰብል ላይ ከፍተኛ ጉዳት አድርሷል ብለዋል። በእነዚህ ቀበሌዎች እስከ 500 ሄክታር ድረስ በሰብል የተሸፈነ መሬት በአበንጣው መጎዳቱንም ገልጸዋል።

የጉዳት መጠኑም ከ50 እስከ 100 በመቶ መድረሱን አስተዳዳሪው በማረዳት ፤እስካሁን ከ20 ሺህ ሄክታር በላይ ቅኝት በማድረግ ከግማሽ በላይ የሚሆነውን መከላከል መቻሉንም ገልጸዋል።

በሃርቡ ወረዳ በተመሳሳይ በዘጠኝ ቀበሌዎች ላይ የአንበጣ መንጋው ጉዳት ማድረሱን የሚናገሩት የወረዳው ዋና አስተዳዳሪ ዮሃንስ ተሰሜ እንደገለጹት፤ አንድ ቀበሌ ሙሉ በሙሉ የወደመ ሲሆን፤ በሌላ አንድ ቀበሌ ላይ ደግሞ ከ50 እስከ 100 በመቶ የሚሆን ሰብል ላይ ጉዳት ደርሷል ብለዋል።
አንበጣው በየጊዜው የሚጨምር እና የወረራ መጠኑም ከጊዜ ወደ ጊዜ የሚሰፋ በመሆኑ የአደጋውን አስቸጋሪነት ከፍ እንዳደረገው ዮሃንስ ገልጸዋል። ዮሃንስ አውሮፕላኑ ለርጭት ስምሪት የሚሰጠው ከሰመራ መሆኑን በማንሳት ይህም መጓተት ማስከተሉን ተናግረዋል። ይህ በቅርበት ለመወያየት አመች ስለማይሆን ወደ ኮምቦልቻ ቢቀየር የተሻለ መሆኑንም አመላክተዋል።

ሰመራ ላይ የነበረው አውሮፕላን መነሻው ከ25/01/13 ጀምሮ ወደ ኮምቦልቻ ተዛውሮ ሌላ አንድ ተጨማሪ አውሮፕላን መጨመሩንም የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ምክትል ኃላፊ ተስፋሁን መንግስቴ ተናግረው ነበር ። ነገር ግን የግብርና ሚንስትርም የመርጫ መሳሪያ የተገጠመላቸው ተሽከርካሪዎች እንደሚያቀርብ ቃል ገብቶ ነበር ያሉት ዮሃንስ፤ እስካሁን አለመላኩን ያነሳሉ።

በግብርና ሚንስትር በኩል “አብዛኛው ድጋፍ እየተደረገልን ነው፣ እርሱን ወደየ አካባቢዎቹ የማሰራጨት ሥራ እንሰራለን” ያሉት ምክትል ቢሮ ሃላፊው፤ አሁንም ግን አንበጣው መብረር ስለጀመረ ከሰው ኃይል ይልቅ በአውሮፕላን ርጭት መከላከል እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል። ከዛም ባለፈ ተጨማሪ አውሮፕላን እንዲመደብ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እየተነጋገርን ነውም ብለዋል።
የሃብሩ እና የራያ ቆቦ ወረዳ አስተዳዳሪዎች ችግሩ በየቀኑ እየጨመረ መሆኑን ገልጸዋል። የምንጩ ምክንያት ደግሞ የአንበጣው ዋና መፈልፈያው ቦታ አፋር ክልል በመሆኑ በየወረዳቸው የሰፈረውን የአንበጣ መንጋ መቀነስ ቢቻልም በየጊዜው ከክልሉ እየተፈለፈለ ወደ አማራ ክልል እየገባ መሆኑን ነው። ርጭቱ የአንበጣ መንጋው የተከሰተበት ቦታ ላይ መካሄድ አለበትም ብለዋል ሃሳባቸውን ሰጥተዋል።

ከአሁን በፊት የአንበጣ መንጋው በተከሰተበት አካባቢ የሚኖሩ አፋሮች፤ ኬሚካሉ ለከብቶቻችን ስጋት ይሆናል በሚል ፈቃደኛ እንዳልነበሩ የተናገሩት የራያ ቆቦ ወረዳ አስተዳዳሪ መንገሻ አሸብር፤ አሁን ግን እነሱም የችግሩ ሰለባ እየሆኑ በመምጣታቸው በቅርቡ ባደረጉት ውይይት ርጭቱ መካሄድ እንዳለበት መስማማታቸውን ይናገራሉ።

ምክትል ቢሮ ኃላፊው ተስፋሁን፤ እስካሁን ቅድሚያ ተሰጥቶት የነበረው በሰብል ላይ ጉዳት ሲያደርስ የነበረውን አንበጣ መከላከል መሆኑን በማስታወስ፤ በዚህም የተነሳ ወደ አፋር ሄዶ መፈልፈያው ቦታው ላይ መርጨት አለመቻሉን ገልጸዋል። አሁን ግን ሁለት አውሮፕላኖች ስለተመደቡ አንደኛውን ወደ አፋር በመላክ አንበጣውን ከመፈልፈያው የማክሰም እና የመከላከል ስራው እንደሚሰራ ገልጸዋል።

ከዛም በተጨማሪነት በትግራይ ክልል ደግሞ በ34 ሺህ ሄክታር ሰብል ማሳ ላይ የተከሰተ መንጋ በቀን 04/13 በትግራይ ክልል በ34 ሺህ ሄክታር የሰብል ማሳ ላይ የተከሰተን የአንበጣ መንጋ ለመቆጣጠር ጥረት እየተደረገ መሆኑን የአንበጣ መከላከልና የገቢ ማሰባሰቢያ ግብር ኃይል ማስታወቁ ይታወሳል።

የግብረኃይሉ አባል ገብረእግዛብሄር አረጋዊ ለኢዜአ እንደገለጹት የአንበጣ መንጋው በክልሉ በአራት ዞኖች ውስጥ በሚገኙ 45 ቀበሌዎች ተከስቷል ። መንጋው በተከሰተባቸው ቀበሌዎች በ32 ሺህ ሄክታር የማሽላ፣ ጤፍና ገብስ ሰብሎች ላይ ጉዳት እያደረሰ መሆኑን ተናግረዋል መንጋውን በቀላሉ መቆጣጠር ባለመቻሉ በሰብል ላይ እያደረሰ ያለው ጉዳት መቀጠሉን ጠቅሰዋል። “የአንበጣ መንጋ ክስተት በዚሁ የሚቆም ሳይሆን ተጠናክሮ እንደሚቀጥል በባለሙያ ትንበያ ተረጋግጣል” ብለዋል ።
በተያያዘም እነዚህ ጉዳዮች በማንሳት ደምስ ጫንያለው(ዶ/ር) የግብርና የኢኮኖሚ ባለሙያ ለአዲስ ማለዳ ይህ መሆኑ ኢኮሚውን ምን ያል እንዲጎዳ ያደርገዋል ስትል ጠይቃ የነበረ ሲሆን ፤ እርሳቸው እንደገለፁት ከሆነ ‹‹ህዝብን እና ፖለቲካን ለያይተን ማየት ነው ያለብን›› ምክንያቱም ህዝቡ እየተጎዳ ነገር ግን ወረቀት ላይ ባለ ነገር ዝቅተኛ ነው ከፍተኛ ነው እያልን ዝም ማለት የለብንም ብለዋል፡፡

በግብርና ሚኒስቴር በቅርቡ ባወጣው መግለጫን ጠቅሶ እንደነበረው አጠቃላይ ጉዳት ደርሷል ብለው ባወጡት መረጃ መሰረት እንኳን ብናይ 280 ሺህ ሄክታር በሰብል ከተሸፈነው መሬት እንደሆነ ተናግረው ነበር፡፡ ይህ መሆኑ ግን ጠቃሚ አይደለም፡፡ ምክንያቱም የቁጥር ማስረጃ ተጠቅመን መጨመረም መቀነስም ይቻላል ይላሉ፡፡ ነገር ግን መሆን ያለበት ለምሳሌ ‹‹አሁን አንበጣ በስፋት ከ ሰሜን ምስራቅ እና ደቡብ ምስራቅ አካባቢ አካለለ ቢባል በዛ አካባቢ ላይ ያሉት መሀበረሰቦች እና ቤተሰብ ተጎጂ ናቸው፡፡ ስለዚህ ጉዳቱ ከአንድ ቤተሰብ ችግር ነው የሚጀምረው ተረጂ ይሆናል፡፡ ቀጣይ ደግሞ ከአካባቢው ይፈናቀላል፡፡ እና ከመንግስት እርዳታ ጠባቂ ይሆናሉ፡፡ ይህም ማለት ደግሞ አንድ መንግስት ምን አልባት አደጋ ቢደርስ ብሎ ከሚይዘው መጠባበቂ በታች ሊሆን ይችላል ፡፡ያም ሆኖ ግን በአሁኑ ሰዓት በአንዳንድ አካባቢዎች ከፍተኛ የሆነ የጎርፍ አደጋ ተከስቶ ከፍተኛ ቁጥር ያለቸው ሰዎች ከቤት ንበረታቸው ተፈናቅለው ነበር፡፡ ይሄ ደግሞ ህልውናችንንን ያናጋዋል ›› ብለዋል፡፡

ከዛም በተጨማሪ ደምስ(ዶ/ር) እንደሚሉት የቤተሰብ ጉዳቱ ሊገለፅ የሚገባው ከተከሰተበት አካባቢ እና የማህበረሰቡ አኗኗር ሁኔታ ነው ሊሆን የሚገባው፡፡ ‹‹በቁጥር ስሌት ላይ አተኩረን ብዙ ሺህ ቁጥር ተረጂ እንዳናፈራ›› በማለት ተናግረዋል፡፡ ምክንያቱም ‹‹የምግብ ዋስትናችን በደናው ጊዜም አልተረጋገጠም ›› በማለት ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል፡፡

ቅጽ 2 ቁጥር 102 ጥቅምት 7 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com