በአዲስ አበባ የጤፍ ዋጋን ለማረጋጋት ለኹለተኛ ጊዜ የጤፍ ጨረታ ሊወጣ ነው

Views: 535

የአዲስ አበባ ህብረት ስራ ኤጀንሲ ዕለት ከዕለት እየጨመረ የመጣውን የጤፍ ዋጋ ንረት ለማረጋጋት ለኹለተኛ ጊዜ የጨረታ ሰነድ እያዘጋጀ መሆኑን አስታወቀ።
ከአቅርቦትና ፍላጎት አለመመጣጠን ጋር ተያይዞና ከዛም አለፍ ሲል ሆነ ብለው የዋጋ ንረት በሚፈጥሩ ኃይሎች በሚፈጠር ችግር በተለይ በመዲናዋ አዲስ አበባ በአንዳንድ ምርቶች ለአብነትም ጤፍ ላይ የዋጋ ንረት እያጋጠመ ነው ያሉት የአዲስ አበባ ህብረት ስራ ኤጀንሲ ምክትል ዳይሬክተር ሲሳይ አረጋ ኤጀንሲው ከዚህ በፊት በፈሳሽ የምግብ ዘይትና ሽንኩርት እጥረትና የዋጋ ንረት ወቅት እንዳደረገው ሁሉ አሁንም በአስሩም ክፍለከተሞች በሚገኙ የህብረት ስራ ማህበራትና የሸማቾች ሱቅ የሚዳረስ የጤፍ እህል ለማቅረብ እንዳሰበ ለአዲስ ማለዳ አስታውቀዋል።

በከተማው ውስጥ እያገጠመ ያለውን ከፍተኛ የሆነ የጤፍ ዋጋ ጭማሪን ለመቆጣጠር የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ የቁጥጥር ስርአት ዘርግቶ እያገዘ ነው ያሉት ሲሳይ በዚህም የእህል መጋዘኖችን የማየት፤ወፍጮ ቤቶችን የመፈተሸና ያለአግባብ ዋጋ የሚጨምሩትን የመቆጣጠር ስራ እየተሰራ እንደሆነ አስታውቀዋል።

የዋጋ ንረቱን ለማርገብ ክትትሉና ቁጥጥሩ ብቻውን በቂ ባለመሆኑ ኤጀንሲው ለመጀመሪያ ጊዜ ከወር በፊት ምርቱን ለሚያቀርቡለት ደርጅቶች ጨረታ እንዳወጣና ነገር ግን ጨረታው ውድቅ ሊሆን እንደቻለ ተናግረዋል።ለጨረታው መውደቅ አበይት መንስኤ የነበረው ጉዳይ ደግሞ የተዘጋጀውን የጨረታ ሰነድ ከኹለት ድርጅቶች ውጪ ሰነዱን ገዝቶ ሊወዳደር የፈለገ ድርጅትም ሆነ ተቋም ባለመምጣቱ ሲሆን ኹለቱን ሰነዶች የገዙትም ድርጅቶች ሰነዱን እንዳላስገቡ ምክትል ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።

ኤጀንሲው በጨረታ እንዲቀርብለት የፈለገው የጤፍ መጠን 100 ሺ ኩንታል ሲሆን ምንአልባት የመኸር ሰብል ካለመሰብሰቡ ጋር ተያይዞ አቅራቢዎች ያን ያህል የምርት መጠን አሁን ላይ ማቅረብ ሊቸግራቸው ይችላል በሚል ለኹለተኛ ጊዜ በሚወጣውና እስከ ጥቅምት 18/2013 ይከፈታል ተብሎ በሚጠበቀው ጨረታ ላይ አሸናፊዎች ጨረታውን ካሸነፉ በኋላ በኹለትና በሦስት የጊዜ ገደብ ውስጥ ምርቱን ሊያቀርቡ የሚችሉበት ሁኔታ እንደሚመቻች ኃላፊው ገልፀው ሰነዱንም ፍላጎት ያላቸው ተጫራቾች ይገዙ ዘንድ በተለያዩ የሚዲያ አማራጮች በስፋት ጥሪ ይቀርባል ብለዋል።

ምርቱ ከቀረበ በሗላ ወደ ተጠቃሚው ጋር በትክክል መድረሱንና ዝቅተኛ ገቢ ላላው ህብረተሰቡን እየተላለፈ እንዳለ በምን መልኩ ትቆጣጠራለቹ በማለት አዲስ ማለዳ ላነሳችው ጥያቄ ምክትል ዳይሬክተሩ ሲመልሱ “ምርቱ ወደ ሸማቾች ማህበር ከደረሰ በሗላ ማህበራቱ ከ50 ኪሎ በላይ ለአንድ ነዋሪ መሸጥ የማይችሉ ሲሆን የተገዛውንም ጤፍ እዛው በሚገኝ ወፍጮ ቤት ብቻ እንዲያስፈጩ በማድረግ የተፈጨን ዱቄት ብቻ ወደ ቤት እንዲወስዱ ይደረጋል” ብለዋል።ሆኖም ግን እንደ ህፃናት መርጃና አረጋውያን መንከባከቢያ ያሉ ድርጅቶች በልዩ ሁኔታ በደብዳቤ ከተቀመጠው ኮታ በላይ ይስተናገዳሉ ተብሏል።

ኤጀንሲው ለሚያከናውነው ተግባር ከልማት ባንክ ብድር ጠይቆ ወደ 80 ሚሊየን ብር የተፈቀደለት ሲሆን እስካሁንም 40 ሚሊየን ብር እንደተለቀቀለትና የተፈቀደውም ብድር የሀብረተሰብን ተጠቃሚነት ከማሰብ አንፃር ዝቅተኛ ወለድ የሚታሰብበት እንደሆነ አቶ ሲሳይ ለአዲስ ማለዳ ሀሳባቸውን ሰጥተዋል።

አዲስ ማለዳ በተለያዩ የከተማው አካባቢዎች እንዳደረገችው የገበያ ቅኝት ከሆነ አሁን ላይ በመሳለሚያ እህል በረንዳ አካባቢ ዝቅተኛ የዋጋ ተመን አለው ተብሎ የሚታሰበው ቀይ ጤፍ በኪሎ 39 ብር እየተሸጠ እንደሚገኝና ሰርገኛ 41 እንዲሁም ማኛና ነጭ ጤፍ ደግሞ ከ43 እስከ 45 ብር በኪሎ እየተሸጠ ይገኛል እንዲሁም በከተማው ደቡባዊ አቅጣጫ በሚገኙት ሰፈሮች ማለትም ቄራና ላፍቶ አካባቢዎች ከ43 እስከ 50 ብር ጤፍ በኪሎ እየተሸጠ እንደሚገኝ ለማረጋገጥ ተችሏል።

በምርቶቹ ላይ ከወር በፊት የነበረው ዋጋ በኪሎ ከስድስት እስከ 10 ብር ቅናሽ የነበረው እንደነበር ሀሳባቸውን ለአዲስ ማለዳ የገለፁ ሸማቾች ተናግረዋል። ዋጋውን ለማረጋጋት በሚሰራበትም ወቅት የጤፍ ዋጋ በከተማዋ ውስጥ በኪሎ በሰላሳዎቹ ቤት ውስጥ ሊሸጥ ይችላል ተብሎ እንደሚታሰብም አዲስ ማለዳ ከኤጀንሲው ያገኘችው መረጃ ያመላክታል።

ቅጽ 2 ቁጥር 102 ጥቅምት 7 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com