በኢትዮጵያ ያሉ ሁሉም ለይቶ ማቆያዎች ተዘጉ

Views: 628

የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ወደ አገራችን መግባቱ ከተረጋገጠበት መጋቢት 4/2012 ጀምሮ አገልግሎት ሲሰጡ የነበሩ ሁሉም የውሸባ ማቆያዎች ‘የኳራንታይን’ ቦታዎች መዘጋታቸውን የጤና ጥበቃ ሚኒስትር ለአዲስ ማለዳ አስታውቋል።

ኮቪድ 19 ወደ ሃገራችን መግባቱ ከተረጋገጠበት ጊዜ ጀምሮ ሃገሪቱ በዘጠኙም ክልሎች እና ሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች 148 ለይቶ የማቆያ ስፍራዎች እንደነበሩ ሚኒስትሩ ገልጿል።እነዚህ ስፍራዎች ዩኒቨርሲቲዎች ትምህርት ቤቶች እንዲሁም በጎ ፈቃደኛ የሆኑ ግለሰቦች በስጦታ ያበረከቷቸው የተለያዩ ህንጻዎች የነበሩ ሲሆን አሁን ሁሉም አገልግሎት መስጠት አቁመዋል።ሲሉ የኳራንታየን ቡድን መሪ የሆኑት ህሊና ገዛኸኝ ለአዲስ ማለዳ አስታውቀዋል።

በአገሪቱ 69 ሺሕ 21 የሚደርሱ ሰዎች በለይቶ ማቆያ አንደነበሩ ነው የተነገረው። በመዲናችን አዲስ አበባም 28 ሆቴሎች እና ሰባት ትምህርት ቤቶች የሳይንስና ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩትን ጨምሮ በለይቶ ማቆያነት ሲያገለግሉ ቆይተዋል። በነዚህ ቦታዎች 34ሺህ 700 ያህል ሰዎች ነበሩ።

የጤና ጥበቃ ሚንስቴር ከመስከረም 8 ጀምሮ የማቆያ ቦታዎች ስራ እንዲያቆሙ ውሳኔ ላይ ቢደርስም ተግባራዊ የሆነው ግን ሚንስቴሩ መመሪያውን ይፋ ካደረገበት መስከረም 25 ቀን ጀምሮ ነው።በዚህ መመሪያ ላይ በከፍተኛ ሁኔታ ተጋላጭ የሆኑ ስዎች የሚገኙባቸው ቦታወች እና የኮሮና ህሙማን የሚገኙባቸው ስፍራውችን በአካል ሄዶ መጎብኘት እንደማይቻል እንዲሁም ሆቴሎችና የጉብኝት ተቋማት እና የትራንስፖር ግልጋሎት ሰጭዎች የፊት መሸፈኛ ጭምብሎችንና ሌሎች መከላከያ ቁሳቁሶችን ማቅረብ አላባቸው ተብሏል።

አሁን ያለው አሰራር በቫይረሱ ተይዘው ጽኑ ህሙማን የሆኑት ብቻ ወደ ህክምና ቦታዎች ይላካሉ ምልክቶች የታዩባቸው ግን በቤታቸው እንዲያገግሙ ይደረጋል። ለይቶ ማቆያዎች የተዘጉበት ምክንያት ሲያብራሩ ሁሉም በኮሮና ቫይረስ ምክንያት ተዘግተው የነበሩ ትምህርት ቤቶች በመከፋታቸውና ማንኛውም ወደ ሃገር ውስጥ የሚገባ ተጓዢ 120 ሰዓት ወይንም አምስት ቀን ያላለፈው የምርመራ ውጤት ይዞ ወደ ሃገር እንዲገባ እየተደረገ በመሆኑ ነው ብለዋል ህሊና ለአዲስ ማለዳ።

ማንኛውም ወደ ሃገር ውስጥ የሚገባ ተጓዥ አምስት ቀን ያላለፈው የኮቪድ 19 የምርመራ ውጤት ካልያዘ አየር መንገዱ የማይጭን ሲሆን ይህ ካልሆነ ደግሞ አየር መንገዱ ኃላፊነቱን ይወስዳል ሲል ነው ሚንስቴሩ ያስታወቀው። በስደት ላይ የቆዩና ወደ ሃገር የገቡ ተጓዦች የምርመራ ውጤት ማምጣት ስለማይችሉ የሰላም ሚንስቴር ሃላፊነቱን ወስዶ እየሰራ ይገኛል።

በድንበር ለሚገቡ ሰዎች ልክ በቦሌ አለማቀፍ አየር መንገድ ለሚመጡ ተጓዦች እንደሚደረገው የመለየት ስራ እየተሰራ ይገኛል። ድንበር አቋራጭ ተሽከርካሪዎችን የሚያሽከረክሩ አሽከርካሪዎችና ረዳቶች፣ የኢትዮ ጂቡቲ የባቡር ትራንስፖርት አሽከርካሪዎችና ረዳቶች ን ተግባራዊ ሊያደርጓቸው የሚገቡ ግዴታዎችና ኃላፊነቶች በተመለከተ መመርያው ሰፊ ማብራሪያ ሰቷል። በማብራሪው የመንግስት የሥራ ቦታዎች እና በሌሎች መንግስታዊ ባልሆኑ ተቋማት ሁሉ ሁለት የአዋቂ እርምጃ ተራርቀው ሰዎች አንዲቆሙ ነው በአጽኖት የተነገረው።

በዚህ ሁኔታ ውስጥ ግን ቫይረሱ ስርጭት 95% ደርሷል ነው የተባለው። ኢትዮጲያም ቫይረሱ ቀድሞ ከተገኘባት ቻይና በመቅደም በዓለም አቀፍ ደረጃ በ85,718 ተጠቂዎች 49ኛ ደረጃ ላይ ስትቀመጥ ቻይና በ85,611 50ኛ ደረጃን ይዛለች።

በኢምባሲዎች በኩል የሚመጡ ዲፕሎማቶች የምርመራ ውጤት ሳይዙ ከመጡ ናሙና በመስጠት ከአየር መንገዱ መውጣት እንደሚችሉ ነገር ግን ራሳቸውን ለ 7 ቀናት በቤት ውስጥ አግልለው ማቆየት እንዳለባቸው ተነግሯል ::

ቅጽ 2 ቁጥር 102 ጥቅምት 7 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com