የእለት ዜና

የጥቅምት ወር ትሩፋቶች

Views: 705

አገራችን አትዮጵያ በአለም ላይ ብቸኛዋ የአስራ ሦስት ወር ፀጋ ባለቤት አገር መሆንዋ ይታወቃል። እነዚህም ከመስከረም እስከ ጷግሜ ያሉት አስራ ሦስቱ ወራት ታዲያ የመጠሪያ ስማቸውን በየወራቱ ካለው የአየር ሁኔታና መሰል ጉዳዮች ጋር ተያይዞ የተሰጣቸው ሲሆን፤ ወራቱንም አስመልክቶ በጥንት ሊቃውንቶች ዘንድ የተነገሩ፤ እስካሁንም ድረስ በትውልዱ እየተነገሩ የዘለቁ የተለያዩ አባባል እና ስነ-ቃሎችም ይገኛሉ።

እኛም በዛሬው የጥበብ እና ሕይወት መሰናዷችን አሁን የምንገኝበት የጥቅምት ወር እንደመሆኑ የወሩን የስያሜ መነሻ፣ ባህሪ እንዲሁም ከወሩ ጋር ተያይዘው ስለሚነገሩ ጥንታዊ አባባል እና ስነ-ቃሎች በጥቂቱም ቢሆን ዳሰሳ ልናደርግ ወደድን። መልካም ቆይታ

ጥቅምት
የክረምቱ ወራት አልፎ በ አዲስ አመት ሲተካ ምድር በፀደይ ወር የልምላሜ ፀጋ ትፈካለች። በክረምቱ ወቅት የነበረው ዝናብና ጭጋጋማ አየርም በመስከረም ወር ቀስ በቀስ እየተወገደ ከጥቅምት ወር መባቻ አንስቶ መሉ ለመሉ መሬቱ ፍሬ ማፍራት ይጀምራል። ሜዳው፣ ሸንተረሩና መስኩ ሁሉ በለምለም ሳር እና በደማቅ አበቦች ተሸፍኖ ይታያል።

የጥቅምት ወር ታዲያ የአበቦች መፍኪያ፤ ቡቃያዎች እሸት ማፍሪያ ወቅት በመሆኑ በተለይም በገበሬው ዘንድ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ወር ነው። ንቦች በየአካባቢው የበቀሉ አበቦችን መቅሰም ጀምራሉ፣ ከብቶች የሚግጡት ሳር ለምለም ነውና ጠግበው ከወዲህ ወዲያ ይቦርቃሉ፣ ገበሬዎችም የቡቃያውን ማሸት የማሩን በቀፎ ውስጥ መሰራት እየተመለከቱ፤ ከሌሎቹ ወራት የበለጠ ጥቅምን እንደሚያገኙ በማሰብ ውስጣቸው በደስታ ይሞላል። ይህንንም ለማሳየት ይመስላል ወሩ ጥቅምት የሚል ስያሜን የተሰጠው። ጥቅምት የሚለው የወሩ መጠሪያ የግዕዝ ሥርወ ቃሉ ‹ጠቀመ› የሚል ሲሆን፤ ሠራ ወይንም ጠቃሚ ጊዜ የሚል ትርጓሜን ይይዛል።

ወሩ በመስከረም ወር ያቆጠቆጡ አበቦች ሙሉ ለሙሉ የሚያብቡት፤ ንቦችም አበባውን ቀስመው ማርን መስራት የሚጀምሩበት ወር እንደመሆኑ ገበሬው ወደ ቀፎው የገባውን ማር ለመቁረጥ የሚዘጋጅበት ወቅት ነው። የጥቅምት ማር ደግሞ በመድሃኒትነቱ የሚመረጥ መሆኑን ብዙዎች ይናገሩለታል።

‹ጥቅምት የማር እመቤት ናት፤ ያውም የማር እሸት› ይላሉ ካህሳይ ገ/እግዚአብሄር ህብረ ብዕር በተሰኘው መጽሐፋቸው ፤ በተለያዩ የአገራችን ገጠራማ አካባቢዎች ስላለው የማር አቆራረጥ ስርዓትም ሲያስረዱ፤ ‹‹በአገር ቤት ማር እንዲሁ በተገኘ ዕለት አይቆረጥም። ለምሳሌ፦ በጥቅምት ወር የሚቆረጠው ጥቅምት 17 ቀን በቅዱስ እስጢፋኖስ ዕለት ሲሆን በኀዳር ወር ደግሞ ኀዳር 12 ቀን በቅዱስ ሚካኤል ቀን ነው። ጥቅምት 17 ቀን የአበባ ወቅት የሚያበቃበት ቦታውን ለፍሬ የሚያስረክብበት ጊዜ ነው ተብሎም ይታመናል።›› በማለት በቀፎው ውስጥ የተሰበሰበውን ማር ለመቁረጥ አመቺውን ጊዜ ያስረዳሉ።

በጥቅምት ወር በመላው የአገራችን ክፍሎች ወደሚገኙ ገጠራማ አካባቢዎች ለጉብኝትም ይሁን እግር ጥሎት በስራ ጉዳይ የሄደ ሰው በሚያየው ልምላሜ እና ተፈጥሯዊ ውበት እጅግ እረክቶና መንፈሱ ታድሶ እንደሚመለስም እሙን ነው።

‹‹ጥቅምት ገበሬው የድካሙን የልፋቱን ዋጋ የሆነውን የምስራች የሚቀምስባት፣ ጥጆች የሚፋፉባት የአበባና የፍሬ ብቻ ሳይሆን የምርት ሲሳይ የሚታፈስባት ወርም ናት። ኧረ እንደ ጥቅምት የታደለ ማን አለ? ሌላው ቢቀር በጥቅምት ወር የተቆረጠ ዛፍ አይነቅዝም።›› በማለት ካህሳይ የጥቅምትን ወር የልምላሜ ትሩፋቶችን በመፅሃፋቸው ያስረዳሉ።

ከዚህም በተጨማሪ በጥቅምት ወር የገበሬው ጎተራ ስለሚጎድል ቡቃያው ደርሶ እስኪሰበሰብ ድረስ ያለውን ይቆጥባል። ቡቃያው የደረሰ እና ወደ ጎተራ የገባ ጊዜ በቆሎውን፣ ስንዴውን፣ ማሽላውን ዘንጋዳውን እያማረጠ በደስታ በክረምቱ ወራት የተጎዳወን ሰውነቱን መጠገን ይጀምራል። ቢሆንም ‹‹ልጅን በጡት እህልን በጥቅምት›› እንዲሉ በጥቅምት ወር በቂ ምርትን የሰበሰበ ገበሬ ያገኘውን ምርት ሳያባክን በሥርዓቱ ቆጥቦ በመያዝ እስከ ሰኔና ሀምሌ መጠቀም ይኖርበታል። አለበዚያ መልሶ ለርሀብ እና ችግር መጋለጡ የማይቀር ነው።

ወርሓ ጥቅምት (ዘመነ ጽጌ)
በአገራችን በተለይም በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ዘንድ የመስከረምና የጥቅምት ወራት የአበባ ወራት (ዘመነ ጽጌ) በመባል ይታወቃሉ፡፡ ይህም ወቅት ሜዳና ሸንተረሩ በውብ አበቦች አሸብርቆና ለዓይን ግቡእ ሆኖ የሚታይበት ነው፡፡ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሥርዓተ አምልኮ መሠረትም ከመስከረም 26 እስከ ጥቅምት 6 ቀን ያለው ወቅት ‹ዘመነ ጽጌ፤ ወርኀ ጽጌ› ተብሎ ይጠራል፡፡ በግእዝ ቋንቋ ‹ጸገየ› ማለት ሲሆን ትርጓሜው ‹አበበ፤ አፈራ፤ በውበት ተንቆጠቆጠ፤ በደም ግባት አጌጠ፤ የፍሬ ምልክት አሣየ› እንደ ማለት መሆኑን ታደለ ገድሌ (ዶክተር) ‹ዘመነ ፅጌ› በሚል ርዕስ በፃፉት ፅሁፍ ላይ ይገልፃሉ።

ዘመነ ጽጌ (ወርሓ ጽጌ) የሚከበረው ምድር በልምላሜና በውበት በምትንቆጠቆጥበት በዚህ ወቅት ነው፡፡ በየሳምንቱ እሑድ ከእኩለ ሌሊት ጀምሮ ማኅሌተ ጽጌ የሚቆሙትና ለሰዓታት ፀሎትን የሚያደርሱት ካህናት ቅድስት ድንግል ማርያምን በአበባ፣ በትርንጎ፣ በሮማን፣ በእንጆሪ እንዲሁም በሌሎች ለምለም እፅዋቶች እየመሰሉ ለፈጣሪ መዝሙርና ምስጋናን እንደሚያቀርቡም ታደለ በፅሁፋቸው ያስረዳሉ፡፡

ለአርባ ቀናት ያህል የሚቆየው የዘመነ ጽጌ (ወርኃ ጽጌ) ወቅት መታሰቢያነቱ ለድንግል ማርያምና ለኢየሱስ ክርስቶስ እንደሆነም በእምነቱ ተከታዮች ዘንድ ይገለፃል። ቅድስት ድንግል ማሪያም ልጇን ይዛ ከዮሴፍና ከሰሎሜ ጋር በምድረ ግብጽ ሲሰደዱ የደረሰባቸውን እንግልት፣ መከራና ስቃይ ለማስታወስ፤ እንዲሁም ከግብፅ ምድር ወደ ናዝሬት የተመለሱበትን ወቅት ለመዘከር ሥነ-ስርአቱ ይከወናል። በዚህ ወቅትም ምእመኑ በተራ በተራ የጥቅምት ወር ካፈራቸው ልዩ ልዩ አዝርት እና አትክልቶች እየቆረጠ ምግብ በማብሰልና ጠላን በማዘጋጀት ማህሌት ቆመው ከሚያድሩ ካህናት እና ከቤተክርስትያኒቱ ምእመናት ጋር እየተገባበዘ ዘመነ ጽጌን ያሳልፋል።

የጥቅምት ወር መገለጫ ሥነ-ቃል እና ጥበባዊ ስራዎች
የጥቅምት ወር ከልምላሜ ፀጋው በተጨማሪ በማለዳው ውርጭ፣ በምሽቱ ቅዝቃዜና በለሊቱ ቁርም ጭምር በደንብ ይታወቃል። እንዲሁም ቀን ቀን የሚወጣው ጠራራ ፀሀይም ሌላኛው የጥቅምት ወር መገለጫ ነው።

የዚህም የወቅቱ የአየር ሁኔታው ነፋሻማነትና መቀዝቀዝ ያለውን ጥቅም ካህሳይ በዚሁ ‹ህብረ ብእር› በተሰኘው መፅሃፋቸው ላይ ሲያስረዱ እንዲህ ይላሉ ‹በክረምት ወራት ውሃ ጠግቦ የባጀው መሬት ጠፈፍ እንዲል፣ ያሸተው አዝመራ ጎምርቶ፣ አፍርቶ በቶሎ እንዲደርስ (እንዲበስል) ነፋሱ አስፈላጊ ነው። የጥቅምቱ ነፋስ ታዲያ ብቻውን አይመጣም። ውርጭና ብርድን በአጃቢነት ይዞ ነው ከተፍ የሚለው።›› በማለት የወቅቱ ነፋሻማነት ለአዝመራው በቶሎ መድረስ ያለውን አሉታዊ ፋይዳ ያስረዳሉ።

ታዲያ ለዚህም ነው የጥቅምት ወር በመጣና የቅዝቃዜው ነገር በታሰበ ቁጥር በብዙዎቻችን ዘንድ የሚታወቀው አንድ አባባል በህሊናችን ጓዳ ብቅ የሚለው። ‹‹በጥቅምት አንድ አጥንት››

መቼም ይህ ሥነ-ቃል ጥቅምት ሲመጣ በብዙዎቻችን ዘንድ የሚነገር ሥነ-ቃል ነው። ታዲያ አጥንትን ለጥቅምት ወር ብቻ ማን ሰጠው በሌሎቹስ ወራት አጥንት አያስፈልግም ወይ የሚል ጥያቄ የሚያነሳ አይጠፋምና ለምን እንዲሀ እንደሚባል እንመልከት።

ነገሩ እንዲህ ነው ቅድም ከላይ ለመግለፅ እንደሞከርኩት የጥቅምት ወር ብርድ እጅግ በጣም ከፍተኛ ነው። ይሄንንም ብርድ ለመቋቋም ታዲያ ኃይልና ሙቀት ሰጪ ምግቦችን ሰውነታችን ማግኘት እንደሚገባው ይነገራል። ከእነዚህም ኃይልና ሙቀት ከሚሰጡ ምግቦች ውስጥ ደግሞ አንዱ ስጋ ነው። በመሆኑም የብርዱን ወቅት ተቋቋሞ ለማለፍ የስጋን አስፈላጊነት በማንሳት በጥቅምት አንድ አጥንት ይባላል። ታዲያ አጥንት ለመጋጥ አቅሙ የማፈቅድለትም በአጥሚት ሆነ በሌሎች ትኩስ እና ሰውነትን ሊያበረቱ በሚችሉ ምግቦች ወቅቱን እንዲያልፍ ይመከራል።

ነገር ግን ይሄ ብቻ አይደለም። የጥቅምትን ወር ምክንያት በማድረግ የሚነገሩ አባባሎች ብዙ ናቸው። ‹ትምህርት በልጅነት፤ አበባ በጥቅምት ያምራል›፣ ‹ልጅን በጡት፤ እህልን በጥቅምት›፣ ‹አትትረፊ ያላት ወፍ፤ በጥቅምት ትሞታለች›፣ ‹ውሃ የጥቅምት ነበርሽ ማን በጠጣሽ፤ ምክር የደኻ ነበርሽ ማን በሰማሽ›፣ ‹ያልታደለች ወፍ በጥቅምት አይኗ ይጠፋል› እኚህና ሌሎች እኚህን የመሳሰሉ ተረት እና አባባሎች በጥቅምት ወር ተዘውትረው ሲነገሩ ይሰማል።

ከዚህም በተጨማሪ ስለ ጥቅምት ወር ልምላሜ በግጥሞች፣ በመፅሀፍቶች፣ በሙዚቃዎች ብዙ የተባለ ሲሆን ለዚህም ‹‹የጥቅምት አበባ›› በሚለው የንዋይ ደበበ ዘፈን እንደ አንድ ማሳያ ያገለግለናልና እስኪ ግጥሙን በጥቂቱ ወደ እናንተ ላድርስ የዜማውን ነገር ለእናንተው ትቼዋለው።

የጥቅምት አበባ፤ የጥቅምት አበባ፤
የጥቅምት አበባ ነሽ አሉ፤
አወድሽው አካሌን በሙሉ።
የጥቅምት አበባ፤ የጥቅምት አበባ፤
የጥቅምት አበባ ለሽታ፤
ለኔ ግን ጣልሽብኝ ትዝታ።
ንብ ሆኜ መጥቼ እንዳይሽ፤
ፈገግ ብሎ ይቆየኝ ጥርስሽ፤
እመጣለሁ ጠብቂኝ በርሬ፤
ታዲያ ላልመለስ አፍሬ፤
ተጣልቷል አይኗ ከአይኔ ጋር፤
አስታርቁኝ እንዴት ይነጋል፤
ንገሯት አለሁ ትበለኝ፤
በእሷ ነው እረፍት የማገኝ……

እያለ የጥቅምት አበባን ውበት፣ የንቦቹን ወቅቱን ጠብቆ ማር መስራት በአጠቃላይ የወቅቱን ልምላሜና ድምቀት በልዩ ሁኔታ በዜማ ይገልፀዋል።
ኮሮና፣ የጎርፍ አደጋ፣ ፖለቲካዊ አለመረጋጋት እንዲሁም የአንበጣ መንጋ ስጋት እና የዘንድሮው የጥቅምት ወር
የዘንድሮው ጥቅምት እንደወትሮዎቹ የጥቅምት ወራት ሁሉ ልምላሜን የታደለና ለገበሬውም መልካም ተስፋን በመያዝ የደረሰ አይመስልም። በኮሮና ወረርሺኝ ሳቢያ እንቅስቃሴዎች በመገደባቸውን ምርታማነት መቀነሱ ይነገራል። በተጨማሪም በተለያዩ የአገሪትዋ ክፍሎች ተከስቶ የነበረው የጎርፍ አደጋ የገበሬውን ማሳ በእጅጉን ያበላሸ፣ አርሶ አደሩን ከቤት ንብረቱ ያፈናቀለ፣ ከብቶቹን ያጠፋና ጎተራውንም ያራቆተ ነበር። በተጨማሪም በየአካባቢው በሚከሰቱ ኹከት እና ብጥብጦች ሳቢያ የብዙሃን ህይወት ጠፍቷል፣ ቤት ንብረት ተቃጥሏል እንዲሁም የደረሰ ማሳ ወድሟል።

ከዚህ ሁሉ በላይ ግን በአሁኑ ሰአት በአገራችን በስፋት እየተሰራጨ የሚገኘው የአንበጣ መንጋ የገበሬውን ማሳ ያበላሸና በከፍተኛ ደረጃ ምርታማነቱን እያሳጣው የሚገኝ ጉዳይ ሆኗል። ጠቅላይ ሚኒስቴር አብይ አህመድ ባሳለፍነው ሳምንት እንደተናገሩት ከሆነ የአንበጣ መንጋው በአሁኑ ሰዓት በአጠቃላ በ240 ወረዳዎች ላይ የተከሰተ ሲሆን በእነዚህም ወረዳዎች ውስጥ በሚገኙ 750 ቀበሌዎች ላይ መንጋው በሰብል ላይ ጉዳት አድርሷል።

በእነዚህም አካባቢዎች በድምሩ 4 ሚሊዮን ሔክታር ታርሶ እንደነበር የጠቆሙት ጠ/ሚኒስቴሩ ከዚህም ውስጥ 420 ሺህ ሔክታር የሚሆን ሰብል ውድመት እንደደረሰበት አስታውቀዋል።

ታዲያ ይህ ሁሉ እየሆነ ባለበት ወቅት ስለ ጥቅምት አበባ፣ ስለ ልምላሜ እና ስለ አጥንት ማውራቱ ተገቢ ባይሆንም፤ እኛ ግን ለአገራችን መልካሙን ሁሉ እየተመኘን የወቅቱን ቀደምት ታሪክና የአየር ሁኔታ ለማስታወስ ያህል ይሄን አለን። ፈጣሪ በአገራችን ላይ አጥንት የሚሰብረውን አጥፍቶ የሚጠግነውን ያብዛልን። ሰላም

ቅጽ 2 ቁጥር 103 ጥቅምት 14 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com