ድርግም ብሎ ብልጭ ያለው “ኢሳት”

Views: 263

የሳተላይት አገልግሎት ክፍያ ለመፈጸም እጁ በማጠሩ ምክንያት የኢሳት ቴሌቪዥን ከባለፈው ሳምንት ዓርብ፣ ጥቅምት 6 ጀምሮ በድንገት ስርጭቱ መቋረጡ የብዙዎችን ቀልብ ስቦ ከርሟል፤ መነጋገሪያ ብቻ ሳይሆን መከራከሪያም ጭምር በመሆን።

የስርጭት መቋረጡ ካስደሰታቸው መካከል በብዛት የዘውግ ፖለቲካ አቀንቃኞች ይገኙበታል። እንደዚህ ዓይነት የብዙኀን ድምጽ መሆን ያልቻለ ቴሌቪዥን ይዋል ይደር እንጂ እንደሚያቋርጥ ጠንቋይ መሆን አይጠይቅም ሲሉ ተሳልቀዋል። በድሮ ዝናና ክብር እስትፋስ መቀጠል እንደማይቻልም አስረግጠዋል። እፎይታ እንደተሰማቸውም አልደበቁም።

በኢሳትን ስርጭት መቋረጥ ደስታቸውን የገለጹት የዘውግ ፖለቲካ አቀንቃኞች ብቻ ሳይሆኑ በኅብረ ብሔራዊነት ወይም በዜግነት ፖለቲካ እናምናለን የሚሉት ጭምር ናቸው። በዚህ ጎራ የሚመደቡት አንዳንዶቹ ከዚህ ቀደም ኢሳትን በቃል ብቻ ሳይሆን በገንዘባቸውም ጭምር ይደግፉ የነበሩ ይገኙበታል። የኢሳት ተልዕኮ በሕወሓት የሚመራውን መንግሥት ከሥልጣን ለማስወገድ በመሆኑ ጣቢያው መዘጋት የነበረበት በኢትዮጵያ የፖለቲካ ለውጥ ከመጣበት ከመጋቢት 2010 ጀምሮ መሆኑ በማንሳት ክርክራቸውን አቅርበዋል።

ሌሎቹ በዜግነት ፖለቲካ የሚያምኑ ነገር ግን የኢሳት ተቃዋሚዎች፣ ጣቢያው በፊት በመንግሥት ላይ ያራምድ የነበረውን ጠንካራ ተቃውሞ በመተው ተንሸራቶ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አስተዳደር የፕሮፓጋንዳ መሣሪያ ሆኗል ሲሉ ይከሳሉ። ከኢቲቪ በበለጠ የመንግሥት ጠበቃነቱን በተግባር አስመስክሯል ሲሉ የመንግሥት ክፍተቶችን ባለመዘገብ፣ የሚፈጸሙ ኢ-ሰብኣዊ ድርጊቶችን ትኩረት በመንፈግ እና ጭፍን ድጋፍ ለመንግሥት ማሳየቱ ተንበርካኪነቱን ማሳያ ናቸው ሲሉ አብጠልጥለዋል። የሳተላይት ስርጭቱ መቋረጡም የጊዜ ጉዳይ ነበር እንጂ ተጠባቂ መሆኑን በመግለጽ ተመልሶ እንዳይመጣም ተመኝተዋል።

ታሪኩ ወዲህ ነው በማለት ስለቴሌቪዥን ስርጭቱ መቋረጥ ጥብቅ መረጃ እንደደረሳቸው የቀድሞ የጣቢያው ባልደረባ ምናላቸው ሥማቸው በፌስቡክ ገጻቸው አስፍረዋል። “ኢሳት ከአየር የወረደው በገንዘብ እጥረት አይደለም” የሚሉት ምናላቸው፥ የገጠመውን የተዓማኒነት ችግር ለመመለስና ከለውጡ ኀይል ጋር ግንኙነት የለውም የሚለውን መልዕክት ለማስተላለፍ የታለመ ነው ሲሉ ጽፈዋል። በጽሑፋቸው ማሳረጊያም የአንድ ዘውግ በሥም በመጥራት ኢሳት የዛ ዘውግ ጠል መሆኑን ጠቅሰዋል።

በርግጥ ከላይ እንደተገለጸው የኢሳት መቋረጥ ያስደሰታቸው ድምጽ ብቻ አልነበረም የተሰማው። መቋረጡ ክው ያደረጋቸው ብዙዎች ነበሩ። “አንድ ብቸኛ የነበረንን ድምጽ ተቀማን” ሲሉ ሀዘናቸውን የገለጹ ይገኙበታል። ጽንፈኛ የብሔርተኛ ፖለቲካ እንዲሁም ጽንፈኛ የዜግነት ፖለቲካ አቀንቃኞች መፈንጫ የሆነውን የአየር ሞገድ ገትሮ የያዘልን ብቸኛ ልሳናችን ተዘጋ ሲሉ ተቆጭተዋል።

የኢሳት ሳተላይት ስርጭቱ ይቋረጥ እንጂ በይፋዊው ‘ዩቲቲዩብ’ ገጻቸው ላይ በተለይ በብዙዎች ዘንድ ተወዳጅ የሆነው “እለታዊ” ቀጥሏል። ከጋዜጠኞቹ አንዱ ምርኩዛችን ላላቸው ደጋፊዎች “እናንተ ስትደክሙ ኢሳት ይደክማል፣ እናንተ ስትጠነክሩ ኢሳትም ይጠነክራል” የሚል መልዕክት አስተላልፏል። ታዋቂዎቹ የጣቢያው ባልደረቦችም በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ አየር እንመለሳለን ሲሉ ተስፋቸውን ገልጸው ነበር።

በርግጥም ደጋፊዎቹ በቁጭት ብቻ ሳይወሰኑ በተቋቋመው ‘ጎ ፈንድ ሚድ ሚ’ ከሃምሳ ሺሕ ዶላር በላይ በኻያ አራት ሰዐት ውስጥ ማሰባሰብ ተችሏል። በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ፈጣሪ የሆኑት ስዩም ተሾመና ናትናኤል መኮንን እንዲሁም ሌሎች የድጋፍ ዘመቻው አካል በመሆን በአራት ቀናት ውስጥ ከ190 ሺሕ ዶላር በላይ እንዲሰበሰብ፤ በተመሳሳይ በአገር ውስጥም በባንክ በኩል ድጋፍ እንዲደረግ ቀስቅሰዋል። መጠኑ አይታወቅ እንጂ በአገር ውስጥም በርከት ያለ ብር መሰብሰቡ አመላካቾች ታይተዋል። ሥሙ ያልተገለጸ አንድ ሰው ብቻውን 50 ሺሕ ብር ልገሳ ማድረጉን የሚያሳይ የባንክ ደረሰኝ በስፋት በማኅበራዊ ትስስር አውታሮች ተዘዋውሯል።

በርግጥም ኢሳት ያልተጠበቁ የድጋፍ ምላሾችን ከዓለም ዙሪያ ማግኘት የቻለ ሲሆን ተጽዕኖው ምን ያክል ለመሆኑም ምስክርነት ሰጥቷል።
በአስገራሚ ፍጥነት ሐሙስ፣ ጥቅምት 12 ወደ ሳተላይት ቴሌቪዥን ዳግም የተመለሱት የኢሳት ፕሮግራሞች ብዙዎችን አስፈንድቋል። “የእለታዊ” አዘጋጆች በከፍተኛ መደመም የሕዝቡን ድጋፍ ያመሰገኑ ሲሆን ድጋፉም መቀጠል እንዳለበት አሳስበው መደበኛ መርሃ ግብራቸውን አስተላልፈዋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 103 ጥቅምት 14 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com