ሥልጣን ማጋራት ወይስ ውጥረትን ማርገብ?

Views: 169

በበርካታ አገራት በገዢው ፓርቲ እና በተፎካካሪዎች መካከል ውጥረት ሲነግስ እና አለመረጋጋቶች ሲገዝፉ የሚወሰዱ እርምጃዎች ማግባባት እስከሚያስችሉ ድረስ ይለያያሉ። በአንዱ አገር የሰራው በሌላው አገር ለተፈጠረው ችግር አይነተኛ መፍትሔ ነው ተብሎ እንደማይታሰብ ሁሉ ከአገር አገር እና ከሁኔታዎች አንጻር ውጥረቶችን ማርገቢያ ዘዴዎች ይለያያሉ። ከዓመታት በፊት በጎረቤት አገር ኬንያ ሥልጣንን ማጋራት የተባለ መንገድ ተግባራዊ ተደርጎ በኹለት ወራት ውስጥ የ1 ሽሕ ንጹሐንን ሕይወት የቀጠፈ ሲሆን ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ሰዎችንም ካፈናቀለ በኋላ አገሪቱን ወደ ተስተካከለ ቁመና መልሷታል። በቅርብ ደግሞ በኢትዮጰያ በመንግሥት በኩል አዳዲስ ሹመቶችን ከወደ ተፎካካሪ ፓርቲ አመራሮች ዘንድ እየተመለከትን ነው። እነዚህን እና መሰል ጉዳዮችን በተመለከተ የአዲስ ማለዳው ኤርሚያስ ሙሉጌታ በጉዳዩ ላይ የተጻፉ ዓለም አቀፍ ጥናቶችን፣ የዘርፉን ባለሙያዎች እና ፖለቲከኞችን በማናገር የሐተታ ዘማለዳ ጉዳይ አድርጎታል።

በአንድ አገረ መንግስት ውስጥ አገር እንደ አገር ለመቀጠል የሚስፈልጓትን በአመዛኙ ማካተት እንደሚኖርባት በርካቶች የሚስማሙበት፤ አለፍ ሲልም አልተሟሉም ብለው የሚዋቀሱበት ላቅ ሲልም የሚታገሉበት ጉዳይ ነው። በዋናነት በአንድ አገር ውስጥ አገርን ከሚያስተዳድረው የስልጣን ባለቤቱ መንግስት ባለፈ በሰላማዊም ሆነ ከዛ በተቃራኒው በሆነ መንገድ የሚቃወሙ እና ለአገር መልካምነት የሚታትሩ አካላትም መኖራቸው እሙን ነው። ግድ አገርን እያስተዳደረ የሚገኘው መንግስት ብቻ ለአገር ዕድገት እና ልማት ያስባል ወይም የሚስተካከለው አካልም የለም ማለት አይደለም።

ይህ ታዲያ አንዳንድ አገራትን በተለይም ደግሞ በአፍሪካ ውስጥ የሚገኙ አገራትን ወደ ለየለት እና ዘመን ተሸጋሪ ወደ ሆኑ አለመረጋጋቶች ሲከቱም ተስተውለዋል። በዚህም የተነሳ ደግሞ አፍሪካ በዚህ አይነት የዕርስ በርስ ግጭቶች ማስተማሪያ እና ምሳሌ መስጫ አህጉርም ሆና የኖረች አሁንም ቢሆን ይህን ጉዳይ በጉያዋ አቅፋ የምትኖር የሰላም ዕጦት ተምሳሌትም ናት። በአደጉት እና በበለጸጉት አገራት ይህን አይነት ችግሮችን እና በመንግስት እና በተቀናቃኝ ወገኖች መካከል የሚደረጉ አለመግባባቶች በሰለጠነ መንገድ ይፈታል፣ በሀሳብ ይረታል፣ እንደተራራ የገዘፈው ችግር እንደ ጉም በኖ ይጠፋል። እንደ አለመታደል ሆኖ በአፍሪካ ይህን አይነት ችግር አፈታት ያውም በችግር አፈታት ረገድ ዘለግ ያሉ ዓመታትን የኖሩ ቱባ ባህል እና ልምድ ባለቤት የሆነችው አፍሪካ ግን የሰከነ ግጭት አፈታት አካሔዶቿን ወደ ጎን አድርገው ነፍጥ ያነሱ ዜጎቿ ቀላል አይደሉም።

የተፈጥሮ ሀብቷን ለማሟጠጥ ተግተው የሚሰሩ እና ከሌሎች አህጉራት ወደ አፍሪካ የሚተሙት ዜጎች ከአህጉሪቱ ግጭት ትርፋቸውን የሚያጋብሱ እስኪመስሉ ድረስ አካሔዳቸው ለየቅል ነው። ከዚህም ጋር በተያያዘ እጅግ አስገራሚ በሆነ ሁኔታ በአልማዝ እና በሌሎች ምድር ላይ ውድ በሆኑ ማእድናት የበለጸገችው ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎን እንደ ማሳያ እናንሳ። ከማያባራ የእርስ በርስ ጦርነት ጋር በተያያዘ የደቀቀው ምጣኔ ሀብቷ በአስገራሚ ሁኔታ ዕድገት ሚያሳይበት እና በተለይም ደግሞ ዕርስ በርስ ጦርነቱ በሚያይልበት ወቅት በአገሪቱ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ደግሞ በእጅጉ እንደሚያንሰራራ ጥናቶች በተደጋጋሚ ሲያስነብቡን ቆይተዋል። ይህን ተገን ያደረጉ አካላትም ግጭቱን ከድጡ ወደ ማጡ እንዲሆን እና አድሮ ቃሪያ የሆነ አካሔድ እንዲፈጠር ከማድረግም እንደማይቆጠቡ በርካታ ጉዳዮች አመላካች ናቸው።

በዘጠነኛው እና በአፍሪካ የደኅንነት ጉዳዮች ላይ አበክሮ የሚያወያየው ጣና ከፍተኛ ጉባኤ ላይ አወያይ የነበሩት ብሪያን ታሙካ ለአዲስ ማለዳ እንደተናገሩት በተለያዩ አገራት በዋናነት በአፍሪካ በርካታ አህጉር አቀፍ ሰላም እና መረጋጋት እንዲሁም ደኅንነትን ማዕከል ያደረጉ ውይይቶች በተደጋጋሚ ለዘመናት መደረጋቸውን ይጠቅሳሉ። ነገር ግን አሁንም በአፍሪካ የትኛውም ቀጠና ላይ ጉዳትን የሚያስከትሉ እና የጥይት ድምጽ የማይሰማባቸው ጠርዞች አለመኖራቸው ደግሞ ጉዳዩ ምን ይሆን ? ወይም ደግሞ በተሳሳተ ጉዳይ ይሆን እንዴ እየተወያየን ያለነው? ምናልባትም ደግሞ እንደ መፍትሔ የተቀመጠው ምክረ ሀሳብ ነባራዊ ሁኔታን ያላማከለ እና በእጅጉ የሚራራቅ ሊሆን ይችላል ብለን መገምገም ይኖርብናል ሲሉ ይናገራሉ።

እንደ ፓን አፍሪካዊው እና አማካሪው ብሪያን ገለጻ አሁንም በአፍሪካ ከአስር አገራት በላይ ከባድ አለመረጋጋቶች እና ከፍ ሲለም እስከ መንግስት ግልበጣ የደረሱ አገራዊ ሰላም ማጣቶች መከሰታቸው የመሻሻል ጭላንጭል አለመኖር አመላካች ነው፡፡ ከአህጉራዊው ተቋም አፍሪካ ሕብረትም ዘንድ ወደ አገራት የሚተላለፈው ውሳኔ ጠንካራ አለመሆን ለሚከሰቱት አለመረጋጋቶች እንደ አቀጣጣይ እንጂ እንደ መቆጣጠሪያ አለመሆን ዋነኛው ጉዳይ መሆኑን ያነሳሉ። ብሪያን በኢትዮጵያ ያለውን አዲሱን አመራር በተመለከተ እየተከተለ ያለውን አካሔድ የሚደነቅ እንደሆነ እና አብዛኛውን በሳይንሳዊ መንገድ በመከተልም ግጭቶችን ወደ ተካረረ መንገድ ሳይሄዱ በአጭር የመቅጨት አካሔድ እንደሚታይበትም አንስተዋል።

ስልጣን ማጋራት
በአፍሪካ አገራት ያልተለመደ እና ተቃዋሚ ድርጅቶች በስልጣን ላይ ያለውን መንግስት ወደ ዘብጥያ ወይም ወደ መቃብር ካላሰናበቱ ወንበር ለመያዝ የማያልሙባት አሕጉር መሆኗን ከታሪክ ድርሳናት እና ከነባራዊ ሁኔታ እንዲሁም በዕድሜያችን ካየናቸው ክስተቶች መናገር የምንችለው ጉዳይ ነው። ከላይ ለመግለጽ እንደተሞከረውም በግጭቶች አትራፊው ማንም እንዳልሆነ እናያለን። እንደ ብሪያን ገለጻ አፍሪካ ከፍተኛ ችግር ውስጥ ሆና ዘመናትን ለመኖር የተገደደችበት አንዱ እና ዋነኛው ምክንያት ከተቃዋሚ ቡድኖች ጋር መንግስታት ቁጭ ብለው በመነጋገር ጉዳዩን ለመፍታት አለመቻላቸው እንደሆነ ይጠቁማሉ። በርካታ ደም መፋሰሶች እና ውድ እና ክቡር የሆነው የሰው ሕይወት መጥፋት ጋር በተያያዘ ከፍተኛ ኪሳራ በየዓመቱ የምትጋፈጠው አፍሪካ ከረፈደ ችግሮችን ለመፍታት መነሳቷ እንደሆነም አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው በርካታ የሰላም እና ደኅንነት ከፍተኛ ተመራማሪዎች ይናገራሉ።

በሰላም እና ደኅንነት ሳይንሳዊ አካሔድ ግጭቶችን እና አለመግባባቶችን ከማርገቢያ መንገድ ስልጣንን ማጋራት አንደኛው እና የተሻለው አማራጭ እንደሆነ ይነገራል። በሉክዘምበርግ ዩኒቨርስቲ የሰላም እና ደህንነት ተመራማሪው ሚካኤል ሞችታክ ለንባብ ባበቁት ‹‹ስልጣንን ማጋራት እና ዲሞክራሲን ማጎልበት በአፍሪካ ፤ የኬንያ ልምድ ›› በሚል ጽሑፋቸው ስልጣንን ማጋራት በራሱ ውጤታማነቱ የፖለቲካ ቀውስን ከመቋቋም አንጻር ከፍኛ ሆነ ሚና እንዳለው ይናገራሉ። በአንዳንድ ስፍራዎች ላይ ይህን አይነት ስልጣን ማጋራት በጥናት እየተካሔደበት እንደሆነ በጽሑፋቸው ሚያሳዩት ሚካኤል ነገር ግን የፖለቲካ ልሒቃንን በማግባባት እና በማስማማት ብሔራዊ አንድነትን በማምጣት አገር ለማስቀጠል አይነተኛ መፍትሄ እንደሆነ ይነገራል።

ባለፉት ጥቂት አስርት ዓመታት ስልጣንን ማጋራት ጽንሰ ሀሳብ በድህረ ግጭት ውስጥ የሚገኙ ከሰሀራ በታች ያሉ ማኅበረሰቦችን እና የተከፋፈሉ ቡድኖችን በማስታረቅ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው ይነገርለታል። ስልጣን ማጋራት ማለት በተቋም ደረጃ የሚተገበር እና በፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል የሚደርግ ሰላም እና ዲሞክራሲን ለማግኘት የሚኬድበት አንደኛው አቅጣጫ መሆኑን እና በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብም ዘንድ ከፍተኛ ሆነ ተቀባይነት እንዳለው በፈረንጆች 2017 በአንትሬፕ ዩኒቨርስቲ የተደረገ ጥናት ያመላክታል።

ይሁን እንጂ ጥናቶች የስልጣን ማጋርትን በተመለከተ ሰላም እና ዲሞክራሲ ግንባታን ለማምጣት አይነተኛ መፍትሔ ነው ብለው የዘመሩለትን ያህል በሌላ ጽንፍ ደግሞ ድምዳሜውን ፉርሽ የሚያደርጉ አካላት አልታጡም። በእርግጥ ሰላም ማምጣቱን ጉዳይ ባይጠራጠሩም ነገር ግን ለዲሞክራሲ ግንባታ ግን በጭራሽ የማይገናኝ ጉዳይ እንደሆነ ያስቀምጣሉ። ከዚህም ጋር አያይዘው የስልጣን ማጋራት ጉዳይ እንኳንስ ለዲሞክራሲ ግንባታ እርዳታ ሊያደርግ ቀርቶ እንዲያውም ግንኙነታቸው ራሱ ውስብስብ ነው ወደሚል ድምዳሜም ይደርሳሉ።

ለአብነት የሚካኤልን ጥናት ብናነሳ ፤ በኬንያ የተደረገውን የስልጣን ማጋራት ጉዳይ ማየት እንችላለን። በኬንያ ከዓመታት በፊት በኡሁሩ ኬንያታ እና በራኤላ ኦዲንጋ መካከል የፈጠረ አለመግባባትን በአጭር ጊዜ ለመፍታት የተሄደበት መንገድ አንደኛው ስልጣንን የማጋራት ጉዳይ እንደነበር ሁላችንም የምናስታውሰው ጉዳይ ነበር። በእርግጥ በኹለቱ ወገኖች መካከል የተፈጠረው ውጥረት በደጋፊዎቻቸው ዘንድ ጠንክሮ በመታየቱ ከፍተኛ የሆነ ደም መፋሰስ እና በአገረ ኬንያም ከባድ ውጥረት ውስጥ ተገብቶ እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው።

በፈረንጆች 2007 በተደረገው አገራዊ ምርጫ ተከትሎ በተፈጠረው አለመግባባት በከፍተኛ ውጥረት እና ግጭት የታመሰችው ኬንያ በቀጣዩ ዓመት በፈረንጆች 2008 ላይ ውጥረቱ አይሎ ነበር። በዚህም ሳቢያ በኹለት ወራት ጊዜ ውስጥ 1 ሽሕ ሰዎችን ለሞት ዳርጎ 600 ሽሕ ሰዎችን ደግሞ ከቀያቸው እንዲፈናቀሉ አድርጓል። ይህን ኹነት ተከትሎም በ ፈረንጆች 2008 ላይ ልሂቃን የስልጣን ማጋራትን በሚመለከት የመግባቢያ ሰነድ ፈርመው ከጥፋት አካሔድ ኬንያን መልሰዋል። ይህን ኹነት አንስተው በቅርቡ በኢትዮጵያ ውስጥ የሚካሔዱ ጉዳዮችን የስልጣን ማጋራት ጭላንጭል እና አዝማሚያ ሊኖር ይችላል ሲሉም ሰላም እና ደኅንነት አማካሪው ብሪያን ይናገራሉ። ‹‹በኢትዮጵያ በርካታ መልካም ጅማሬዎች መኖራቸውን መመስከር እችላለሁ›› የሚሉት ብሪያን በተፎካካሪ ፓርቲዎች አመራሮች ላይ በቅርቡ ተደረገውን የመንግስት እና ሕዝብ ሹመትን በሚመለከት ጭላንጭሎች መኖራቸውንም ይናገራሉ። ‹‹በብልጠት የተሰራ ውሳኔ ይመስላል›› የሚሉት ብሪያን በተለይ ደግሞ እዚህም እዛም የሚፈጠሩትን ችግሮች በጊዜ ለመፍታት ከወዲሁ የታሰበበት እንደሚመስልም ብሪያን ለአዲስ ማለዳ አስታውቀዋል።

በፈረንጆች 2008 በኬንያ የተፈረመው ስልጣን ማጋራት ሒደት ሕገ መንግስትን በሕዝበ ውሳኔ እንዲሻሻል እና የኹለቱም ፖለቲካ ድርጅቶች ድምጽ እኩል የተሰማበት እንደነበር በ2010 የፈረንጆች ዓመት ላይ ውጤቱ ታይቶ ነበር። ይህንንም መሰረት አድርጎ ከአምስት ዓመታት በኋላ አገራዊ ምርቻ ያካሄደችው ጎረቤት አገር ኬንያ በእጅጉ ሰላማዊ ነው የተባለ እና ከቀዳሚው ምርጫ ጋር ለውድድር የማይቀርብ እንደሆነ በ2013 ላይ የታየው ውጤት ይመሰክራል ሲል በፖርቱጋል ሊዝበን ዩኒቨርስቲው ተመራማሪ አሌክሳንደር ዲ ሶሳ በጽሑፉ ያትታል።

በኢትዮጵያ ይህን አይነት አጋጣሚዎች ናቸው የሚያስብሉ መነሻ እና አመላካች እንቅስቃሴዎችም እየተካሄዱ እንዳሉ ሚገልጹ ከብሪያን በተጨማሪ ቁጥራች ዘለግ ያለ ነው። የዐብይ አሕመድ (ዶ/ር) መንግስት ወደ ስልጣን ከመጣበት የመጀመሪያው ወቅት ጀምሮ በርካታ ጉዳዮች ሲካሄዱ የተስተዋሉ ሲሆን ከእነዚህም ውስጥ ታዲያ ከተፎካካሪ ፓርቲዎች የተወጣጡ አመራሮች በተለያዩ የኃላፊነት ስፍራዎች መቀመጣቸው እንግዳ ነገር እንደሆነ በተለይም ደግሞ በኢትዮጵያ ውስጥ ከነበረው ነባራዊ ሁኔታ አንጻር መሻሻሎችን ማሳያ እንደሆነ ተነግሮለታል። ከመጀመሪያው ወራት የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) ሊቀመንበር መረራ ጉዲና (ፕ/ር) በመንግስታዊው እና ቀደምት የመገናኛ ብዙኃን በሆነው የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን በቦርድ አባልነት ሲሾሙ፤ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ ፓርቲ (ኢዜማ) ሊቀመንበር እና በሌሉበት ሞት ተፈርዶባቸው የነበሩት ብርሀኑ ነጋ (ፕ/ር) በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ውስጥ የቦርድ አባልነት በመሆን ነበር እንግዳው ነገር ጀመረው። ይህን እና መሰል ጉዳዮችን እስከ ቅርብ ጊዜ በትኩረት ሲከታተሉ የነበሩት ብሪያን የስልጣን ማጋራት ጥቂት ጭላንጭል የመኖሩን ጉዳይ ያስረዱት።

ነገርግን ከዚህ በተቃራኒው ደግሞ በአሁኑ የኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ ላይ አስተያየታቸውን የሚሰጡት እና በአጽንኦት የሚከታተሉት ነአመን አሸናፊ ‹‹በጭራሽ የስልጣን ማጋራት ጉዳይ አይደለም ›› ሲሉ ይጀምራሉ ። በቅርቡ የሮማን ገብረሥላሴን ከታላቁ ሕዳሴ ግድብ ሕዝባዊ ማስተባበሪያ ዋና ዳይሬክተርነት መነሳትን ተከትሎ በምትካቸው የትግራይ ትብብር ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ትዴት) ሊቀመንበር አረጋዊ በርሔ (ዶ/ር) መተካት እንዲሁም ከቅርብ ጊዜያት በፊት የፖሊሲ ጥናት ዳይሬክተር ሆነው የተሾሙት የሶሻል ማኅበራዊ ፓርቲ ሊቀመንበር በየነ ጴጥሮስ (ፕ/ር) ሹመትን አዲስ ማለዳ አንስታ ነበር ጥያቄ ያቀረበችው። ነአመን ሲመልሱም ‹‹በጭራሽ የእነዚህ ሰዎች ሹመት ወይም ወደ ሕዝብ እና መንግስት ሥልጣን መግባት የስልጣን ማጋራት ጅማሮን አያሳይም ወይም አያመላክትም።

ምክንያቱ ደግሞ ግለሰቦቹ የተሾሙበት ስፍራ ምንም ድምጻቸው የሚሰማበት ወይም በከፍኛ የመንግስት ውሳኔዎች ላይ ሊሳተፉ የሚችሉበት ባለመሆኑ ስልጣን ተጋርተዋል ማለት አይቻልም›› ሲሉ ያክላሉ። ይሁን እንጂ እንደ ነአመን ገለጻ በመንግስት በኩል እየተደረገ ያለው ይህ ሹመት ወይም የተፎካካሪ ፓርታዎች ሊቀመናብርት ሹመት በመጪውን ምርጫ ምክንያት ሊፈጠር የሚችለውን ከፍተኛ ውጥረት እና ሕዝባዊ ቁጣ ለማርገብ ከወዲሁ እየተተገበረ ያለ የመንግስት እርምጃ እንደሚሆን ግን አልጠራጠርም ሲሉ ነአመን ሀሳባቸውን ይገልጻሉ። በኢትዮጵያ ውስጥ በጥቂቱም ቢሆን የስልጣን መጋራት የነበረበትን ዘመን የሚጠቅሱት ነአመን ‹‹በ1983 የሽግግር ወቅት በኢትዮጵያ ውስጥ የተቋቋመው የሽግግር መንግሥት እና ቻርተር ላይ እንደ ኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) እና ሌሎች ተፎካካሪ ፓርቲዎች የተሳተፉበት እና ድምጻቸው በትክክል የተካተተበት ኹነት በመሆኑ በወቅቱ የስልጣን ማጋራት የታየበት እና በኃላ ላይ በ1987 ወደ ሕገ መንግስት ያደገው ይኸው ቻርተር በመሆኑ በእርግጥም በትጥቅ ትግሉ ወደ ሥልጣን የመጣው መንግስት በተወሰነ መልኩ ሥልጣን አጋርቶ ነበር ማለት እንደሚቻል ነአመን ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

በተወሰነ መልኩ ነአመንን ሀሳብ የሚጋሩት ደግሞ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የሰላም እና ደኅንነት ጥናት ተቋም ውስጥ በተመራማሪነት እና እያገለገሉ የሚገኙት ኤልያብ ጥላሁን ‹‹ሥልጣን ማጋራት ማለት በሦስቱ የመንግስት አካላት ማለትም ሕግ አውጪ ሕግ ተርጓሚ እና ሕግ አስፈፃሚ ላይ መሳተፍ ማለት ነው›› ሲሉ ሀሳባቸውን ይገልጻሉ። በእርግጥ በቅርቡ የተሾሙት እና ወደ ፊት መስመር የመጡት የተፎካካሪ ፓርቲ አመራሮች ጉዳይ ይበል የሚያሰኝ ቢሆንም ነገር ግን ስልጣን ለማጋራት ነው የሚባልበት ደረጃ ላይ አለመሆናቸው ግን ከሦስቱም የመንግስት አካላት ውስጥ አለመሆናቸው አመላካች ነው ሲሉም ኤልያብ ሀሳባቸውን ይገልጻሉ። ይሁን እንጂ መንግስት ሥልጣን ለማጋራት ጅማሬዎችን እያሳየን ነው ለማለት የሚያስችሉ አካሔዶችንን ግን በጭላንጭልም ቢሆን ሊያሳይ የሞከረበት ሁኔታ እንዳለም መረዳት ያስፈልጋል ይላሉ ኤልያብ።

‹‹ለምሳሌ በየነ ጴጥሮስን (ፕ/ር) በፖሊሲ ጥናት ዳይሬክተርነት ሲሾሙ የራሳቸው ሀሳብ እና ፖሊሲን በማጥናት እና በማጎልበት ወደ ፖሊሲ አውጪዎች ለመላክ በሚደረግበት ሒደት ላይ አይካቱትም ወይም ግብዓታቸው አይኖርም ማለት ስለማይቻል በተዘዋዋሪ በሕግ ማውጣቱ ላይ ተሳትፏቸው ጉልህ ሊሆን ይችላል›› የሚል ሀሳብ እንዳቸውም ከአዲስ ማለዳ ጋር በነበራቸው ቆይታ ተናግረዋል። በአረጋዊ በርሔ (ዶ/ር) ሹመት ላይ ደግሞ አስተያየታቸውን የሚሰጡት ኤልያብ ምናልባትም ‹‹የጠላቴ ጠላት ወዳጄ ነው›› በሚል አካሔድ የተሾሙ ሊሆኑ እንደሚችሉም እንደሚገምቱ ይናገራሉ።

ከዚህ በተለየ ደግሞ የአረጋዊ በርሔን ሹመት በተመለከተ አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው አስተያየት ሰጪዎች እንደሚሉት ኃላፊነታቸው ሕዝብ ማስተባበር እና ለአንድ ብሔራዊ ለሆነ አላማ ማሰለፍ ነው። ዘላቂነት በሌለው እና በተወሰነ ጊዜ ውስጥ የሚቋጭ እና ከዛም በኋላ ኃላፊነታቸው የሚደመደም በመሆኑ እዚህ ግባ የማይባል ኃላፊነት ምክንያት ስልጣን ማጋራት ነው ሊባል እንደማይችልም ሀሳባቸውን ይሰነዝራሉ።

ጥናቶች እንደሚያመላክቱት ስልጣን ማጋራት ተከፋፍለው የነበሩ ቡድኖችን የሚያቀራርብ እና በአንድ አገር የዲሞክራሲ ግንባታ ላይ የሚኖረው ሚና ከፍተኛ እንደሆነ ይነገርለታል። አስተያየታቸውን ከመስጠት ያልተቆጠቡ ግን ደግሞ ስማቸውን እንዲጠቀስ ፈቃደኛ ያልሆኑ በመንግስት የከፍተኛ የኃላፊነት ሥፍራ ላይ ያገለገሉ ግለሰብ ከአዲስ ማለዳ ጋር ቆይታ አድርገዋል።

በቆይታቸውም መንግሥት በአንዳንድ ጉዳዮች ላይ ከባድ እርምጃዎችን መውሰድ እያለበት ግን ደግሞ የሰነፈበት ወይም በግድ የለሽነት ያለፋቸው ትልቅ ዋጋ የሚያስከፍሉ ጉዳዮች መኖራቸውን ይናገራሉ። በዚህም ሳቢያ ታዲያ መጪው የአገራዊ ምርጫ ሂደት እና ከዛ ቀጥሎ ያለው ኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታም እንደሚያሳስባቸው ያትታሉ። ይሁን እንጂ ከወዲሁ ደግሞ በሌላ ወገን እየተሰሩ ያሉ እና ነገሮችን ለማለስለስም ሆነ እጅግ በሚገርም ፍጥነት ሰዎችን በስልጣን በሚመስል ግን ደግሞ የእውነት ባልሆነ ሁኔታ እንዲሳተፉ ተደርጓል፡፡ በዚህም ተከታዮቻቸውን በምርጫ ማግስት በመንግሥት ላይ እንዳይነሱ እንደሚያደርግ እና ምርጫው ሰላማዊ ሆኖ እንዲያልፍ ያሰበ ተግባር እንደሆነ ይናገራሉ።

በርካታ ጉዳዮችን በተለይም ደግሞ የስልጣን ማጋራት ኹነት እየተደረገ ወይም ወደዛው መንገድ እየተሔደ ነው ወይ የሚል ጥያቄ አዲስ ማለዳ ላደ,ቀረበችው ጥያቄም ምላሽ ሲሰጡ፤ ‹‹በእርግጥ ወደዛ የሚሔድበት ጉዳይ አይኖርም። ምክንያቱ ደግሞ በኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን የበዛው ፖለቲካ ፓርቲዎችን ጉዳይ ሚታወቅ ሲሆን ስልጣንን ከማን ጋር ተጋርቶ ከማን ጋር ይተዋል የሚለው ጉዳይ መነሳት አለበት›› ሲሉም ይናገራሉ። በብሔር እና በጎሣ ለተዋቀረው ፖለቲካ ድርጅቶች ስብስብ አንዱን የፖለቲካ ፓርቲ አቅርቦ እና በመንግስት አካላት ላይ እንዲሳተፉ አድርጎ ሌላውን መተው ወይም ሳይሳተፉ ማስቀረት ወደ ባሰ ብጥብጥ እና መከፋፈል የሚመራ ጉዳይ እንደሆነም ይጠቁማሉ።

የኬንያን ጉዳይ ከቅርብ ዓመታት ኹነትነቱ በተጨማሪ በጉርብትናውም ባለው ቅርበት ምክንያት አድርገው ለምሳሌነት የጠቀሱት አስተያየት ሰጪው፤ ‹‹ኬንያ እንደዛ ከባድ የሆነ ውጥንቅጥ ውስጥ ሲገቡ ዘግይተውም ቢሆን ያለውን ጉዳይ በስልጣን ማጋራት ሲያረግቡት በወቅቱ በአለመረጋጋቱ ላይ ዋነኛ ሚና የነበራቸው ድርጅቶች ውስን በመሆናቸው ምናልባትም ገዢው ፓርቲ እና ሌላ ተቀናቃኝ ቡድን እንጂ እንደእኛ በዛ ያሉ ፓርቲዎች ባለመሆናቸው ጉዳዩን እንዲረግብ እና ስልጣን ማጋራቱን ተጠቅመውበታል ብየ አምናለሁ›› ሲሉ ያስረዳሉ።

ነገር ግን በኢትዮጵያ ከበዛው የፓርቲዎች ቁጥር ባለፈ እና በዋናነት ግን ስልጣንን ለማጋራት ሕገ መንግሥቱ ላይ ማሻሻያዎች ሊሰሩ እንደሚገባ እንደ ቅድመ ሁኔታ የሚቀመጥ መሆኑንም አስተያየታቸውን ለአዲስ ማለዳ ሰጥተዋል። ‹‹በሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት እንደፈለገ እና እንዳሻው ከነገ ጀምሮ ሥልጣን አጋራለሁ ብሎ መነሳት አይችልም። ምክንያቱም የተያዘው እኮ አገርን መምራት እና ሕዝብን ማስተዳደር እንጂ የልጅ ጭዋታ አይደለም። በተደጋጋሚ ሌሎች ጉዳዮች ማለትም በሕገ መንግስት ማሻሻል እና በሽግግር መንግሥት ምስረታ ዙሪያ የሚነሱ ጉዳዮች መኖራቸውን እናያለን እያየንም ነው። ነገርግን ከመንግሥት ወገን የሚሰጠው ምላሽ እንደ እኔ ተገቢ ነው ባይ ነኝ። ምክንያቱም ለኹሉም ጥያቄዎች እርምጃዎችን በመውሰድ የሚመለስ ከሆነ እና አሁን ባለንበት ደረጃ ደግሞ የጥያቄዎች ብዛት እልፍ ከመሆኑ ጋር ተዳምሮ በቅጡ ያልረጋውን መንግሥት ወደ ባሰ ውጥንቅጥ እንደሚከተው አልጠራጠርም›› ሲሉም አስተያየታቸውን ይደመድማሉ።

በአሁኑ ወቅት በየትኛውም ኢትዮጵያ ጥግ ላይ ትላልቅ የሆነ ኩርፊያ መኖሩ በራሱ መጪውን ምርጫ በአገር አቀፍ ደረጃ አስፈሪ እንዲያደርገው ምክንያት እደሆነ አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው የፖለቲካ ሳይንስ እንዲሁም የሰላም እና ደኅንነት ባለሙያዎች ያስረዳሉ። ከዚህም ጋር ተያይዞ በእውኑ መንግሥት የተከተለው መንገድ ወደ ሥልጣን ማጋራት ከሆነ አገሪቱን ከማረጋጋት ይልቅ ወደ ለየለት ውጥንቅጥ ውስጥ የሚያስገባ ጉዳይ ነው የሚሆነው ብለው የሚሞግቱ አልጠፉም።

በኢትዮጵያ አራተኛው አገራዊ ምርጫ ላይ ከፖለቲካ ፓርቲዎች ዘንድ በወቅቱ አገር ሲያስተዳደር የነበረው ፓርቲ (ግንባር) ኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ግንባር (ኢሕአዴግ) ጋር ባደረጉት ውይይት እና ክርክር መንግሥት ሥልጣን መማጋራት እንደሚኖርበት ሞግተው ነበር። ይሁን እንጂ ይህን ጉዳይ በቀላሉ ማለፍ ባይፈልግም በወቅቱ በነበረው አካሔድ ግን ይህን ጥያቄ በሙሉ በመድፈን ነበር ሊያልፈው የወደደው። በእርግጥ በወቅቱ ከመድረክ የጋራ ፖለቲካ ፓርቲዎች ስብስብ ዘንድ ኢህአዴግ ሥልጣን ሊያጋራ ይገባዋል በሚል የተቀነቀነውን ሀሳብ ከግንባሩ በኩል ተወያይ የነበሩት ሴኮ ቱሬ ምላሽ የሰጡበትን አጋጣሚ ኢትዮጵያ ዛሬ የተሰኘው ድረ ገጽ እንዲህ አስቀምጦት ነበር ‹‹መድረክ በክርክሩ የኦፍዲኑን አቶ ገበየሁ አያቶንና የሕብረቱን አቶ ወንድሙ ኢብሳን ያቀረበ ሲሆን፤ አቶ ገበየሁ – መንግሥት ሥልጣን ሊያጋራ ይገባል የሚለውን የመድረክን አቋም አንጸባርቀዋል። ኢህአዲግ ሥልጣን ማጋራት “የሕልም እንጀራ ነው” እያለ መሳለቁ ይታወቃል›› ሲል አስነብቦ ነበር።

በእርግጥ መንግስት ሥልጣን ያጋራ ይሆን?
አሁን ኢትየጵያ ባለችበት የፖለቲካ ሁኔታ ላይ መንግሥት ሥልጣን ሊያጋራ ይችላል ወይ ተብሎ የሚጠየቅበት አጋጣሚ ጥቂት አይሆንም። የሰላም እና ደኅንነት ባለሙያው ኤልያብን ሀሳብ በዚህ ላይ እናምጣው እና መንግሥት በእርግጥም ሥልጣን ለማጋራት የሚችለበት ወይም ደግሞ የሚፈልግበት ደረጃ ላይ ነው ብለው እንደማያምኑ ይናገራሉ። ነገር ግን አንዳንድ አስጨናቂ እና ከፍተኛ ትችቶች በሚጋረጡበት ወቅት ግን ይህን አይነት አካሔድ ሊጠቀም እንደሚችል ግምታቸውን ያስቀምጣሉ። ነገር ግን አሁን በሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት ሥልጣን ከማጋራት ይልቅ ኃይል ዕርምጃዎችን በመውሰድ ነገሮች ለማርገብ እንደሚጥር ደግሞ ነአመን አሸናፊ ለአዲስ ማለዳ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል። ‹‹በጭራሽ መንግሥት ሥልጣን ያጋራል ብየ አላምንም። በሆነ መንገድ እንኳን ከተፎካካሪ ፓርቲዎች ወደ መንግሥት ኃላፊነት ሥፍራ ብቅ የሚሉ ካሉ በእርግጥም እንደተባለው ወይ እብዛም ድምጻቸው የማይሰማበት ወይም ደግሞ ውስጥ ውስጡን በገዢው ፓርቲ አባልነት መዝገብ ላይ ያሉ ሊሆኑ እንደሚችሉም ይታሰባል›› ሲሉ ነአምን ይናገራሉ።

በመጀመሪዎቹ የለውጡ ወራት በኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ውስጥ ከገዢው ፓርቲ ያልሆኑት ጀነራል ከማል ገልቹ የክልሉ አስተዳደር ሰላም እና ግንባታ ቢሮ ኃላፊ ሆነው ሲያገለግሎ መቆየታቸው የሚታወስ ነው። ከማል በኃላፊነት ሥፍራቸውም ሕዝብ ማገልገል ፖለቲካ ልዩነታቸው እንደማያግዳቸውም ሲናገሩ የተደመጡበት ሁኔታ እንደነበር አይዘነጋም። ይህ ታዲያ መንግሥት በወቅቱ ሥልጣን ለማጋራቱ ምናልባትም በሥልጣን ማጋራት የራሱ የሆነ ሳይንሳዊ ፍቺ በመመርኮዝ ለጥቂት ጊዜያትም ቢሆን ተጋርቶ ነበር የሚል ጥያቄም የሚያስነሳ ነው። ይሁን እንጂ ከማል በተመደቡበት የኃላፊነት ቦታ ላይ መቆየት ሳይችሉ ቀርተው በፈቃዳቸው መልቀቃቸው እና ወደ ፓርቲያቸው ሙሉ ጊዜያቸውን እንዳዞሩም የሚታወስ ሲሆን በአሁኑ ሰዓት ሙሉ በሙሉ ከብልጽግና ፓርቲ ጋር ለመስራት መስማማታቸው ታውቋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 103 ጥቅምት 14 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com