ለማ ጉያ፤ የለማዊነት ማሳያ ከ1921-2013

Views: 716

ሥዕል ቀደምት ታሪካዊ መነሾ ያለው የሥነ-ጥበብ ዘርፍ ነው። የሰው ልጅ ከጥንት ዘመን አንስቶ እንደመግባቢያናነትና ስሜቱን መግለጫነት ይጠቀመበት እንደነበርም ቀደምት ድርሳናትና የታሪክ ልሂቃን ያስረዳሉ።

የአገራችን የሥነ-ሥዕል ታሪክም እረጅም ዘመንን ያስቆጠረ ሲሆን በሥዕል ሥራዎቻቸውም በአገር ውስጥም ሆነ በአለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ተወዳጅነትንና እውቅናን ያተረፉ ታላላቅ ባለሙያዎችም ተፈጥረውበታል፤ እየተፈጠሩበትም ይገኛሉ።

በዚህ የሥነ-ሥዕል ጥበብ ታሪክ ውስጥ ታዲያ በሥራዎቻቸው ደማቅ አሻራ ካስቀመጡና ልዩ የሆነ ጥበባዊ እይታን በምጥን የቀለማት ውህደት ውስጥ የማሳየት ፀጋን ከታደሉ እውቅ ሠዓሊያን መካከል አንዱ ደግሞ የክብር ዶክተር ሎሬት አርቲስት ሻንበል ለማ ጉያ ናቸው።

ሠዓሊ ለማ ጉያ ከ65 አመታት በላይ ባስቆጠረው የሥነ ሥዕል ሙያቸው ከ10 ሺህ በላይ የሚሆኑ የሥዕል ሥራዎችን የሰሩ ሲሆን በተለይም በፍየል ቆዳ ላይ የሚነድፏቸው ምስለ አካሎች (ፖርትሬት) ከሌሎች የሥዕል ባለሙያዎች እንዲለዩ ያደረጉና በብዙዎች ዘንድ አድናቆትን ያተረፉላቸው ስራዎቻቸው ናቸው።
ታዲያ እኚህ እውቅ እና ስመጥር የአገራችን የኪነጥበብ ባለሙያ ባደረባቸው ድንተኛ ህመም ምክንያት በህክምና ሲረዱ ቆይተው በተወለዱ በ92 አመታቸው ባሳለፍነው ሳምንት ሰኞ ጥቅምት 16 ቀን 2013 ከዚህ አለም በሞት ተለይተውናል።

ሐሙስ ጥቅምት 16 ቀን ረፋድ ላይ የፌደራልና የክልል ከፍተኛ ባለስልጣናት፣ የተለያዩ አገራት አንባሳደሮች፣ አድናቂዎችና ወዳጅ ቤተሰቦቻቸው በተገኙበት በቢሾፍቱ ስቴዲየም በተከናወነ ይፋዊ የክብር የስንብት መርሃ ግብር፤ ከቢሾፍቱ ከተማ በ7 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው አደአ ሊበን ወረዳ ዳሎ ቀበሌ ቅዱስ ገብርኤል ቤተክርስቲያን የክብር ሥርዓተ ቀብራቸው ተፈፅሟል።

አዲስ ማለዳም በእኚህ እውቅ የጥበብ አባት ህልፈተ ህይወት የተሰማትን ከፍተኛ ሀዘን በመግለፅ ለቤተሰቦቻቸው፣ ለአድናቂዎቻቸውና ወዳጅ ዘመዶቻቸው ሁሉ መፅናናትን እየተመኘን ተጨልፎ ከማያልቀው የሠዓሊው የህይወት ታሪክና ሥራዎች በጥቂቱ ልናስቃኛችሁ ወደድን።

የታላቁ የጥበብ አባት ትውልድ እና እድገት
የክብር ዶክተር ሎሬት አርቲስት ሻንበል ለማ ጉያ ከአባታቸው ጉያ ገመዳና ከእናታቸው ማሬ ጎበና በቀድሞው ምስራቅ ሸዋ አድአ ሊበን ወረዳ ደሎ በሚባል ቀበሌ ውስጥ ነሐሴ 12 ቀን 1921 ተወለዱ።

በልጅነታቸው እናታቸው የእጅ ስራ አዋቂና ባለሙያ ነበሩና ለማ እንደማንኛውም የየአካባቢው ሕፃናት ሁሉ የህፃንነት እድሜያቸውን ተጫውተውና ተሯሩጠው ከማሳለፍ ይልቅ የእናታቸውን ፈለግ በመከተል የቅርፃ ቅርፅ ሥራን አጥብቀው ይወዱና አዘውትረውም ይሰሩ እንደነበር ይነገራል።

በዚህም ለሙያው በነበራቸው ከፍተኛ ፍቅርና በሸክላ ውጤቶች በሚሰሯቸው የሰው፣ የእንስሳትና የቁሳቁስ ቅርፆች ቤተሰባቸውንም ሆነ የአካባቢውን ሰዎች በማስደነቃቸውና ትኩረትን በመሳባቸው በአካባቢው ማህበረሰብ ጫና ወደ ዘመናዊ ትምህርት ቤት እንዲገቡ እድሉ ተመቻቸላቸው። በአስራ አምስት አመታቸውም ከሚኖሩበት ቀበሌ በአስር ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሚገኘው በቀድሞው አጠራር አፄ ልብነ ድንግል ትምህርት ቤት በመግባት ትምህርታቸውን ጀመሩ።

በጊዜውም እስከ ሰባተኛ ክፍል ድረስ ይሰጥ የነበረውን ዘመናዊ ትምህርት በ1943 አጠናቀው ቶሎ ሥራ በመያዝ ቤተሰባቸውን ለመርዳት በነበራቸው ከፍተኛ ፍላጎት የተነሳ ናዝሬት (በድሮ ስሙ) ዓፄ ገላውዴዮስ ተብሎ በሚጠራው የመምህራን ተቋም በመግባት በመምህርነት ሠልጥነው ሥራ ጀመሩ። ነገር ግን መልሰው ሥራቸውን በማቋረጥ ወደ ትውልድ ቀያቸው ተመለሱ።

የየዛን ጊዜው ብርቱ ወጣት ለማ ጉያ ታዲያ ከሕፃንነታቸው አንስቶ በልባቸው የሰረፀውን የዕደ-ጥበብ እና የሥነ-ሥዕል ሙያ ለማሳደግ ብሎም ስለሙያው ጠለቅ ያለና በቴክኖሎጂ የታገዘን እውቀት ለመገብየት ምን ማድረግ እንደሚገባቸው ሲያሰላስሉ ቆይተው እንደ ድንገት አንድ መላ በህሊናቸው ብልጭ ይልላቸዋል።
ይኸውም ከእንጨት በመስራት በቀለማት ያስዋቡትን የአውሮፕላን ሞዴል በየሳምንቱ መጨረሻ ወደ ቢሾፍቱ ለሚመጡት ንጉስ ኃይለሥላሴ ማሳየትና ትኩረታቸውን መሳብ ነበር። ሃሳባቸውም ተሳክቶላቸው በአንድ ወቅት ኃይለስላሴ ለጉብኝት ወደ ቢሾፍቱ በሄዱበት ጉዜ ከንጉሱ ፊት ቀረቡ።

ንጉሱም የለማን ሥራ አይተው እጅግ በመደነቃቸው ምን እንዲደረግላቸው እንደሚፈልጉ ይጠይቋቸዋል። ስለዚህ ጉዳይ ደራሲና ተርጓሚ ታደለ ገድሌ (ዶ/ር) ከሠዓሊ ለማ ጉያ ጋር በአንድ ወቅት የነበረውን ቆይታ በማስታወስ ባሰፈረው ፅሁፍ ላይ ለማ ለንጉሱ ጥያቄ ‹‹ግርማዊ ሆይ አየር ኃይል ያስገቡኝ›› ብለው መመለሳቸውንና ጃንሆይም ግራ አዝማች ሣህሉ ድፋየን ጠርተው ‹‹በል በአስቸኳይ ለጄነራል አሰፋ አያና ንገርና ይህንን ልጅ ያስገባው›› በማለት መመሪያ መስጠታቸውን እንዳጫወቱት ይገልፃል።

በተጨማሪም በዛኑ ወቅት ንጉሱ 60 ብርም ጨምረው የሰጧቸው ሲሆን በብሩም አንዲት ላም ገዝተው ለቤተሰቦቻቸው እንደሰጡ፤ ላሚቷም ከንጉሱ በተሰጠ ብር የተገዛች በመሆንዋ ሳትሰረቅና በማንም ሳትነካ ለአመታት እንደኖረች እንደነገሩትም ያስታውሳል።

በወቅቱ ወደ አየር ሃይል የመግባት መሻታቸውን ለንጉሱ በድፍረት የገለፁት ለማ ጉያም የንጉሱን ይሁንታ በማግኘት የአየር ሃይል ማሰልጠኛ ተቋምን ተቀላቅለው በአውሮፕላን መካኒክነት ሙያ ስልጠናን ጀመሩ። በዛውም ማታ ማታ ደግሞ በእንግሊዝ መምህራን እንግሊዘኛ የመማር እድልንም አገኙና እንግሊዘኛውን በማቀላጠፍ መናገርም ለመዱ።

በአየር ሃይል ማሰልጠኛ ተቋሙ የሚሰጠውን ስልጠና ካጠናቀቁና ለኹለት አመታት በማሰልጠኛው ካገለገሉ በኋላ በ1945 በወጣት ዕጩ የፖሊስ ኃይል ሰልጣኝነት /ካዴት/ የሚሰጠውን ስልጠና በማጠናቀቅ በ1950 በከፍተኛ ውጤት ተመረቁ።

በወቅቱ ከማሰልጠኛው በከፍተኛ ውጤት የተመረቁት ለማ በምርቃታቸው እለት ከንጉሱ እጅ አቪያ የተሰኘ የወርቅ ሰዓት ከተሟላ የስዕል መሳያ ቁሳቁሶች ጋር በስጦታ መልክ እንደተበረከተላቸው የህይወት ታሪካቸውን እና ስራቸውን አስመልክቶ በብርሃን መኮንን በተፃፈውና በኢትዮጵያ ብሔራዊ የባህል ማዕከል የዕደ-ጥበብና ኪነ-ጥበብ ሥራዎች ማበልጸጊያ ዲይሬክቶሬት መጋቢት 2009 በወጣው ፅሁፍ ላይ ተገልጿል።

አስከትለውም ለማ አስመራ ከተማ በሚገኝው የአየር ሃይል ጣቢያ በመምህርነት እንዲሁም በጦር መሀንዲስነት ሙያቸው ማገልገላቸውን ቀጠሉ። በዚህም ወቅት ከሥራ ባልደረቦቻቸው ጋር በመሆን ከአስመራ ወደ ደቀመሀሪ በሚወስደው አቅጣጫ 40 ኪ.ሜ ርቀት ላይ በምትገኘውና በተራራ በተከበበችው በ‹‹አሊ›› ግዛት የጦር ፓይለቶችን ስለ ቦምብ አጣጣል፣ ኢላማ አመታትና የቦምብ አጠቃቀም የተግባር ትምህርት አስተምረዋል።

ሠዓሊ ለማ ጉያ ከሰለጠኑበት የአየር ሃይል ሙያ በተጓዳኝ ወደዚህ ሙያና ስራ ለመግባት በር የከፈተላቸውን የሥነ-ጥበብ ሙያ ሳይዘነጉ በአስመራ የኢጣሊያኖች የስዕል ትምህርት ቤት ከደሞዛቸው እየቆረጡ ከፍለው በመማር የሙያ ማዳበር ሥራቸውን የቀጠሉ ሲሆን በተለይም በፖርትሬት በመልክአ ምድር በቁሳቁስ (Still-Life) ሥራዎች መጠቀምን በመማር በተፈጥሮ የታደሉትን እውቀት ሊያዳብሩ መቻላቸውን ሠዓሊው የክብር ዶክትሬት ማዕረግን ከጅማ ዩኒቨርሲቲ በተቀበሉበት የሰኔ 27/2007 የምረቃ ሥነ ሥርዓት ላይ የቀረበው ግለታሪካቸው ያስረዳል።

በተለይም በአየር ሃይል በነበራቸው ቆይታ ለአየር ሃይሉ አባላት የሥዕል ኤግዚቢሽኖችን በማቅረብ በአንድ በኩል በወታደራዊ ትምህርቱ የተሰጣቸውን ግዳጅ እየተወጡ በሌላ በኩል ለአባላቱ የሥዕል ሥራዎችን በማሳየት ለሥነ-ሥዕል ጥበብ የነበራቸውን ልዩ ፍቅር አሳይተዋል። በ1950 እና በ1952 በአስመራ ከተማ ኹለት ኤግዚቢሽኖችን ያሳዩት ለማ በአየር ሃይል ውስጥም በፎቶ ክፍልና በህዝብ ግንኙነት መኮንን የኃላፊነት ቦታ ላይ ሠርተዋል።

የሠዓሊ ለማ የሥነ-ሥዕል ጉዞ
የክብር ዶክተር ሎሬት አርቲስት ሻንበል ለማ ጉያ እናት ማሬ ጎበና ከሚሰሩት የሸክላ ሥራ በተጨማሪ፤ የተለያዩ ቀለማት ያላቸውን የአፈር አይነቶች በመደባለቅ የተለያዩ የሰዎችንና የእንስሳቶችን ሥዕሎች በቤታቸው ግድግዳ ላይ ይስሉና ለቤቱም ልዩ የሆነ ውበትና ድምቀትን ይፈጥሩ እንደነበር ይነገራል።

ይህንንም እየተመለከቱ ያደጉት ለማ ለሥዕል ያላቸው ፍቅር እለት ከእለት እየጨመረና የእናታቸውን የቀለማት ውህደት እና የአሳሳል ዘይቤ በጥልቀት በመመልከት የሰው፤ የእንስሳት እንዲሁም የተለያዩ ቅርፃ ቅርፆችን በመሳል፤ በህፃንነት እድሜያቸው የሥዕል ሥራቸውን አሀዱ ብለው ጀመሩ። ቀስ በቀስም በትምህርትና በተለያዩ ስልጠናዎች ችሎታቸውን ከጊዜ ወደ ጊዜ በማሻሻል በሀገራችን የሥነ-ጥበብ ታሪክ ላይ የራሳቸው ደማቅ ዱካ ማሳረፍ የቻሉ ታዋቂና ዝነኛ የሥዕል ባለሙያ ለመሆን በቅተዋል።

እዚህ ጋር እናታቸው ማሬ ጎበና ለዛሬዎቹ የሠዕሊ ለማ ጉያ ውብ እና ድንቅ የሥዕል ሥራዎች ያበረከቱት የአርዓያነት መሰረትም ከፍተኛ እንደነበር ልብ ማለት ያሻል። ለዚህም ይመስላል በሌላ ሙያ ላይ ከተሰማሩት የለማ ጉያ አንዱ ወንድም ተሰማ ጉያ በስተቀር ሌሎች ወንድሞቻቸውም በዚሁ የሥነ-ጥበብ ዘርፍ ላይ ተሰማርተው ሠዓሊዎች የሆኑት። ሠዓሊ፣ ገጣሚና ደራሲ አሰፋ ጉያና ሠዓሊና በአዲስ አበባ የሥዕል ትምህርት ቤት መምህር የሆኑት ቱሉ ጉያም የእዚሁ ሙያ ባለቤቶች ናቸው።
ሠዓሊ፣ ገጣሚና ደራሲ አሰፋ ጉያ ‹ሰምና ወርቅ› በተሰኘውና በ2012 ባሳተሙት መጽሐፋቸው ላይ እውቁ ገጣሚ፣ ደራሲና ባለቅኔ ሎሬት ፀጋዬ ገብረ መድህን በአንድ ወቅት ለሠዓሊ ለማ ጉያና ቤተሰቦቹ በጻፉት ደብዳቤ የሚከተለውን ማለታቸውን አስፍረዋል።

‹‹ለማ ጉያ ስዕላዊ አፈ ታሪክ፥ ስዕላዊ ተረትና ምሳሌ ትስላለህ። የአበው ጨዋታ ያነፀህ፥ ሕዝባዊነትህን በብሩሽህ ይፋና ቀላል በሆነ የቀለማት ፊደል ታስተጋባለህ፥ ድንቅ የሰፊው ህዝብ ስዕላዊ እንቆቅልሽህ፥ በተለይ ‹‹ቋንጣ›› ዘረፋ፥ በብኩንነት መርገምቱ፤ ‹‹አቦል ቡና›› በህዝባዊ ጭውውቱ ግልጥ ምዕራፎችህ ናቸው።
ቱሉ በለማ ፈለግ እየተራመድክ ርቀሃል እንጂ አንተም እንደ ወንድምህ የሰፊው ሕዝብ ባህል እና ልምድ ስዕላዊ ተረተኛ ነህ። ‹‹አክፋይ››፥ ‹‹ጉግስ›› እና ‹‹ሰርግ›› ያልካቸው ከህብረተሰቡ ህይወት ማረሚያ ነጥቦች ጋር የተቀረጹ፥ ልምድና ወጎችን በተረት አዘል ጭውውት እንደማውጋታቸው፥ የሙከራዎችህ ጥሩ ምሳሌዎች ናቸው።

አሰፋ ግን ከስዕል ወደ ስነ ግጥም፥ ከግጥም ወደ ስነ ስዕል በመሸጋገር አለም አቀፍ ችግሮችን ለማብሰር የመጣርህን ያህል እንደከባድ ርዕሶችህ ሁሉ የስራህም ፍሬ በዚሁ ክብደት ውስጥና ሥር ተውጠዋል። ጥረትህ በጣም ጥሩ ነው። የውስጣዊ አላማህን ግዙፍነት በብሩሽህ ለመቀመር የሚፈጅብህ እድሜና ግን እሩቅ በመሆኑ ሙከራህን አታቋርጥ። ወንድማችሁ ፀጋዬ ገ/መድህን ፲/፬/፸፭።›› ይላል። ሎሬት ፀጋዬ ገ/መድህን ለእውቁ ሠዓሊ ለማ ጉያና ወንድሞቹ የፃፉት ደብዳቤ።

ተፈጥሮአዊ የአሳሳል ዘይቤን የሚያዘወትሩት ሠዓሊ ለማ ጉያ በአገራችን ዘመናዊ የምስል ቴክኖሎጂ ባልተስፋፋበት ወቅት የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦችን የአለባበስና የአኗኗር ዘይቤን የሚገልፁ፤ በተለይም የኦሮሞን ህዝብ ትውፊትና ባህልን የሚያጎሉ ሥዕልች በመሳልና በማሳተም በመላው አገሪቱ እንዲዳረሱ በማድረጋቸው ይታወቃሉ።

በይበልጥ ግን ሠዓሊ ለማ ጉያ ላለፉት 65 ዓመታት በፍየል ቆዳ ላይ የሳሏቸውና በቁጥርም ከ10 ሺህ በላይ እንደሚሆኑ የሚነገርላቸው የሥዕል ሥራዎቻቸው ከፍተኛ የሆነ አድናቆትና ዝናን እንዳተረፉላቸው ይነገራል።

በተለይም ከእርሳቸው ቀደም ብሎ በቆዳና በብራና ላይ የተሰሩ በርካታ የፈጠራ ሥራዎች ቢኖሩም እርሳቸው ግን የፍየል ቆዳ ሙሉ ለሙሉ ፀጉሩ ሳይነሳ ተፈጥሯዊ ወዝና ውበቱን እንደጠበቀ የፊትን ገፅ በላዩ ላይ በቀለም በመስራት ብዙዎችን አስደምመዋል።

ከእነዚህም ሥዕሎች ውስጥ በዋናነት የኢትዮጵያና የአፍሪካ መሪዎች፣ ዲፕሎማቶች፣ የታዋቂ ሰዎች፣ የብሄር ብሄረሰቦችን አኗኗር፣ ወግና ባህል እንዲሁም የተለያዩ የአገራችን ገፀ ምድሮችና የተፈጥሮ ሐብቶች የሚያሳዩ ተወዳጅ ሥራዎች ይገኙበታል።

ለማ ጉያ ብሩሽና ቀለማቸውን በማዋሃድ የሠሯቸው የሥዕል ሥራዎች እጅግ በርካታ ቢሆኑም በተለይ ግን ‹‹የሸክላ ገበያ››፣ ‹‹የደንከል ልጃገረድ››፣ ‹‹ቋንጣ››፣ ‹‹አቦል ቡና››፣ ‹‹እሬቻ››፣ ‹‹ዋርካ››… የሚል መጠሪያ የተሰጣቸውና ሌሎችም ሥራዎቻቸው የማህበረሰባችንን ባህል እና ወግ መሰረት ያደረጉ ዘመን ተሸጋሪ ሥራዎች በመሆናቸው በብዙዎች ዘንድ አድናቆትና ሙገሳን ያተረፉባቸው ሥራዎች ናቸው።

በተለይ በሕዝብ ዘንድ ትልቅ አድናቆትን ካሰጣቸውና በሹማምንቱ ዘንድ ልዩ ትርጉምና አቃቂርን በማስወጣት ከየወቅቱ አዛዦች ጋር እንዲላተሙ ካስደረጓቸው የበኩር ስራዎች ውስጥ ሳትጠቀስ የማታልፈው ‹‹ቋንጣ›› የተሰኘችው ሥዕላቸው ነች። ‹‹ቋንጣ›› ሥዕል የአፍሪካን የሀብት ምዝበራ ወይም ሙስናን ፍንትው አድርጋ የምታሳይ ሥራ እንደሆነች ብዙዎች ይናገሩላታል።

በ1968 ከአየር ሃይል በጡረታ የተገለሉት አርቲስት ለማ ጉያ ቀሪ ህይወታቸውን ለሥነ-ጥበብ በማዋልና በተለይም በአገራችን የሥነ ጥበብ ማሳያ ጋለሪዎችን በስፋት አለመኖራቸውን በማስተዋል ከ3ዐ በላይ የውጭ አገራት ዲኘሎማቶችን ጋብዘው ሥራዎቻቸውን በማሳየት የሥዕል ማሳያ ማዕከል እንዲመሠረት አድርገል።
ይህም ‹‹የአፍሪካ አርት ጋለሪ›› የሚል መጠሪያ የተሰጠውና በቢሾፍቱ ከተማ የሚገኘው የአርቲስት ለማ ጉያ የሥዕል ሥራዎች ማሳያ ማዕከል መታሰቢያነቱን ለኔንሰን ማዴላ በማድረጉ በግቢው ውስጥ ሀውልት ተሰርቶ የቆመላቸው ሲሆን አራት የማሳያ ቤቶችን በመገንባት ማሳያዎቹ ምንጊዜም ለተመልካች ክፍት ሆነው በለማ ጉያ የሥዕል ሥራዎች ቀጣዩ ትውልድ እንዲማር እየተደረገ ይገኛል።

ማህበራዊ አበርክቶትና የክብር ሽልማቶች
የክብር ዶክተር ሎሬት አርቲስት ሻንበል ለማ ጉያ የኪነ-ጥበብ ብቻ ሳይሆን በጨዋታ አዋቂነታቸውም በብዙሃን ዘንድ ተወዳጅነት ያተረፉ ሰው ናቸው። የቅንነት፣ ጨዋነት፣ ደግነትና አርቆ አስተዋይነት መንፈስን እንደተላበሱ የሚነገርላቸው ለማ ጨዋታ ሰውን ሁሉ የሚያከብሩና ከፍተኛ የሆነ የአገር ፍቅር ስሜት የነበራቸው እንደነበሩ የቅርብ ጓደኞቻቸውና ወዳጅ ዘመዶቻቸው ይመሰክሩላቸዋል።

በሕይወት ዘመናቸው ወደ 1ዐ ሺህ የሚጠጉ የስዕል ውጤቶችን ለአገራቸው ያበረከቱትና፣ በግብርና፣ በማስተማር፣ በውትድርና በአየር ኃይል አባልነት ያገለገሉት አርቲስት ለማ ጉያ በመሠረቱት ‹‹የአፍሪካ አርት ጋለሪ›› ግቢ ውስጥ የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በመክፈት አገራዊ ግዴታቸውን ሲወጡም ቆይተዋል።
ከተለያየ ጊዜ የውጭ አገራት ዜጐች የሚበረከቱላቸውን የሥዕል መጽሐፎቶችም ለኢትዮጵያውያን በሚስማማ መልኩ በመተርጎም፤ በአገራችን ታሪክና በሥዕሉ ዘርፍ የመጀመሪያ የሆነውን ‹‹የሥዕል ያለአስተማሪ መጽሐፍ›› ተርጉመው በትምህርት ሚኒስቴር ወጪ ታትሞ በመላው አገሪቱ ባሉ ትምህርት ቤቶች እንዲሰራጭ በማድረግ ታሪክ ምንጊዜም ሊያስታውሰው የሚችል አሻራን አስቀምጠዋል።

ለማ ጉያ በሥራቸው በተለያዩ ጊዜያት ከተለያዩ አገራት መሪዎች ልዩ ልዩ ሽልማቶችን የተቀበሉ ሲሆን በቀድሞው የደቡብ አፍሪካ ፕሬዝዳንት ጃኮብ ዙማን ጥሪንም በመቀበልም በገዢው ፓርቲ (ኤኢንሲ) ዓመታዊ ስብሰባ ላይ ለሦስት ጊዜያት የመሳተፍን እድል አግኝተዋል።

የቀድሞው የሊቢያ መሪ ኮሎኔል ሙአመር ጋዳፊ የራሳቸው ምስል ያለበትን የወርቅ ሽልማትም ሸልመዋቸዋል። የቀድሞው የኩባ መሪ ፊደል ካስትሮም ኩባን እንዲጎበኙ ተጋብዘዋቸው የክብር ሽልማትን ከፊደል ካስትሮ እጅ ተቀብለዋል። በተጨማሪም ከቀድሞውና ከአሁኑ የሴኔጋል ፕሬዝዳንቶች ዳካር ድረስ ተጋብዘው የገንዘብና የክብር ሽልማቶች ተቀብለዋል።

ሠዓሊ ለማ ጉያ ተመሳሳይ ሙያ ካላቸው ልጆቻቸው እና ወንድሞቻቸው ጋር በመሆን በተለያዩ የአለም አቀፍ እና የአገር ውስጥ መድረኮች ላይ ሥራዎቻቸውን አቅርበዋል። ከአገር ውጪ በአሜሪካ፣ ስዊዲን፣ እንግሊዝ፣ ኬንያ፣ ናይጄሪያ ሴኔጋልና ሌሌች አገራት ውስጥ ያሳዩ ሲሆን ሦስት ትውልድ የተናገሩ የጥበብ ሥራዎች በሚል በሰሜን አሜሪካ የውስጥ ቅርስ ማህበር ተሸላሚም ሆነዋል።

የጅማ ዩንቨርስቲ ሴኔት ሰኔ 15 ቀን 2007 ባስተላለፈው ውስኔ መሰረት ለክቡር አርቲስት ለማ ጉያ ገመዳ የክብር ዶክትሬት በሥነ ጥበብ ዘርፍ እንዲሰጥ በአንድ ድምፅ ውሳኔን አሳልፏል። በ(ፖርትሬት) የሥነ-ጥበብ ሥራዎቻቸውም ‹‹ለማዊነት›› የሚል ሥያሜን አሰጥቷቸዋል።

ክቡር ዶክተር ሎሬት አርቲስት ሻንበል ለማ ጉያ በትዳር ለ56 ዓመታት በጋራ ከኖሩት ባለቤታቸው ወ/ሮ አስቴር ሦስት ሴቶችና ኹለት ወንድ ልጆችን በድምሩ አምስት ለጆችን ያፈሩ ሲሆን ከእነሱም ውስጥ አራቱ የአባታቸውን የሥነ-ጥበብ ሙያ ተከትለው በመስራት ላይ ይገኛሉ።

እነሱም ትዕግስት ለማ ጉያ (ክብርት ሴክረተሪ)፣ ነፃነት ለማ ጉያ (ሠዓሊና የግራፊክስ ዲዛይን ባለሙያ)፣ ሠላማዊት ለማ ጉያ (ሠዓሊ፣ መምህርት እና የሙዚቃ ባለሙያ-በአሜሪካ)፣ ደረጀ ለማ ጉያ (ሠዓሊ፣ የሲኒማቶግራፈርና የፕሮዳክሽን ባለሙያ) እንዲሁም ዳዊት ለማ ጉያ (ሠዓሊ) ሲሆኑ፤ ሠዓሊ ለማ ጉያ ስምንት የልጅ ልጆችንም አይተዋል።

በኑሯቸውም ሆነ የሥዕል ሥራዎቻቸውን ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ እስከ እድሜ ማምሻቸው በትጋት የሠሩት የቀለም አባት የክብር ዶክተር ሎሬት አርቲስት ሻንበል ለማ ጉያ ለአገር እና ለሕዝብ ብዙ ሠርተዋል። «ይህቺ ናት አገሬ፤ ይህቺ ናት ኢትዮጵያ» እያሉም ኢትዮጵያን እና ኢትዮጵያዊነትን ለአለም ህዝብ አስተዋውቀዋል። ከሥዕል ሥራዎቻቸው ባሻገርም ለህዝባቸውና ለአገራቸው ነፃነትም የታገሉ ነበሩና ትውልድ ዘለአለም ሥራዎቻቸውንና መልካም ምግባራቸውን ሲዘክር ይኖራል።

ቅጽ 2 ቁጥር 104 ጥቅምት 21 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com