የእለት ዜና

የበረሃ አንበጣ አስከፊ ጉዳት ከአርሶ አደር ማሳ

Views: 460

ተሾመ ላቀው ወጣት አርሶ አደር እና የሦስት ልጆት አባት ነው። ተሾመ ኗሪነቱ በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ኤፍራታ ግድም ወረዳ ጀብ ውሃ ቀበሌ ነው። አዲስ ማለዳ በአማራ ክለል በተወሰኑ ወረዳዎች ተከስቶ የአርሶ አደሩን ሰብል በከፍተኛ ሁኔታ አያወደመ የሚገኘውን የበረሃ አንበጣ በቦታው ተገኝታ ቅኝት ባደረገችባቸው በአራት ዞኖች ነው። በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን፣ ኦሮሞ ብሔረሰብ፣ በሰሜን ወሎ እና በደቡብ ወሎ ዞን ተጎጅ በሆኑ እንድ አንድ ወረዳዎች ላይ ነው።

ተሾመ ሁኔታውን እንዲህ ይገልጸዋል”የበረሃ አንበጣው በእኛ አካባቢ ከተከሰተ ቀናቶች ተቆጥረዋል። እኛ የምንገኝበት አካባቢ ለአፋር ክልል አዋሳኝ ቦታዎች የቀረበ በመሆኑ ከዚያ የሚነሳው መንጋ ነው እኛን ያጠቃን” ይላል። ተሾመ ቀጥሎም ባለፈው የመኸር ወቅት 30 ኩንታል የማሽላ ምርት ያገኘለት መሬቱ ላይ ያለማው ሰብል ሙሉ በሙሉ እንደወደመበት ይናገራል። በዚህም በአሁኑ ምርት ዘመን ወደ ቤቱ የሚስገባው ምንም አይነት የሰብል ምርት እንደሌለው እና ለወራት የደከመበት ሰብል ወድሞ የምርታማነት ተስፋውን ከንቱ አድርጎበታል።

ተሾመ አሁን ላይ በደረሰበት የሰብል ውድመት መጎዳቱን ተከትሎ ልጆቹን ለማስተማር እና የምግብ ፍጆታቸውን ለማሟላት ድጋፍ ያስፈልገኛል ይላል። ከዚህ ሁኔታ በመቀጠል የወደፊት ተስፋውን ሲገልጽ “ምናልባት ፈጣሪ ምሮን የበልግ ዝናብ የሰጠን እንደሁ ያኔ ለመቋቋም እንችላለን ካልሆነ ያው እንደምታየው የቀረው አገዳ ብቻ ነው ፌሬ የለም በተረጅነት እስከ ሚቀጥለው የምርት ዘመን መጠበቅ ነው።” ሲል ለአዲስ ማለዳ አስረድቷል። የበረሃ አንበጣ ከምንጬ ሊወገድ ካልቻለ ወደፊት በ ሚለሙ ስብሎች ላይም ጉዳት እንዳያደርስ የሚለው የተሾመ ሌላኛው ስጋት ነው።

በኤፍራት ግድም ወረዳ ከሚገኙ 27 ቀበሌዎች መኸል ኹለት ቀበሌዎች ላይ ጉዳት ደርሷል። በጉዳቱም 210 ሄክታር ሰብል ልማት መውደሙን የወረዳው ዋና አስተዳዳሪ ደምሰው መሸሻ ተናግረዋል። ዋና አስተዳዳሪው እነደገለጹት በአካባቢው የተከሰተው የበረሃ አንበጣ መነሻው ከአፋር ክልል መሆኑን ጠቁመዋል። አዲስ ማለዳ በቦታው በተገኘችበት ጊዜ የበረሃ አንበጣው በወረዳው ሌሎች ቀበሌዎች በመዛመት ላይ መሆኑን ከዋና አስተዳዳሪው አረጋግጣለች።

በአማራ ክልል ሰሜን ሽዋ አዲስ ማለዳ በቦታው ተገኝታ ቅኝት አስካደረገችበት ጊዜ ድረስ በዞኑ ካሉት 23 ወረዳዎች በዘጠኝ ወረዳዎች ላይ መከሰቱን ከዞኑ አደጋ ስጋት ጽ/ቤት ኃላፊ ቻለው ምንዳ አረጋግጣለች። ኃላፊው እንደሚሉት በዞኑ የበረሃ አንበጣ ከተከሰተባቸው ቦታዎች ውስጥ በከፍተኛ ሁኔታ ጉዳት የደረሰባቸው ምንጃር ሽንኮራ ወረዳ፣ አንኮበር ወረዳና ቀወት ወረዳ ናቸው ተብሏል። በወቅቱ ስርጭቱ በዘጠን ወረዳዎች ይሁን እንጅ በሌሎችም ወረዳዎች እየተዛመተ መሆኑን አዲስ ማለዳ አረጋግጣለች። የበረሃ አንበጣው ባለፈው 2012 ዓመትም በዞኑ በተለያ ወረዳዎች ተከሰቶ ጉዳት ማድረሱን ቻለው አስታውሰዋል።

አዲስ ማለዳ ቅኝት ያደረገችበት ኹለተኛው ዞን በአማራ ክልል ኦሮሞ ብሔረሰብ ዞን ነው። አዲስ ማለዳ በዞኑ በሚገኘው በጅሌ ጥሙጋ ወረዳ ሙጤ ፈጤ ተብሎ በሚጠራ ቀበሌ ተግኝታ ቅኝት ባደረገችበት ጊዜ የበረሃ አንበጣው ከፍተኛ መንጋ ያለው እና በእጅጉ አውዳሚ መሆኑን አረጋግጣለች። ጅሌ ጥሙጋ ወረዳ 22 የገጠርና 2 የከተማ ቀበሌዎች አሉ። በወረዳው ከሚገኙ 22 የገጠር ቀሌዎች የበረሃ አንበጣ በ17 ወረዳዎች ላይ ተከስቶ ሙሉ በሙሉ በሚባል ደፈረጃ በሰብል ልማት ላይ ጉዳት ማድረሱን የወረዳው ዋና አስተዳደሪ ጀማል ሀሰን ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል። የወረዳው ግብርና ጽ/ቤት ኃላፊ አብዱ መሀመድ በበኩላቸው በወረዳው ተከሰተው በረሃ አንበጣ መንጋ ስርጭት ከወረዳው ቁጥጥር ውጭ መሆኑን ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል። ኬሚካል ርጭትም በአውሮፕላን የተደገፈ መሆን ቢገባውን በወቅቱ በቦታው ላይ ከአርሶ አደሮች ጩኸት ውጭ ምንም ነገር አልነበረም። አዲስ ማለዳ በቦታው በተገኘችበት ወቅት በእጅጉ ከፍተኛ መንጋ ያለው የበረሃ አንበጣ ሰብል አውድሞ ዛፎች ላይ ሲሰፍር ተመልክታልች። ባለሙያው እንደሚሉት የመንጋው መነሻው በአቅራቢያው ከሚገኘው አፋር ክልል መሆኑን ጠቁመዋል።

የወረዳው ግብርና ጽ/ቤት ኃላፊ እንደገለጹት ከሆነ በአካባቢው እየደረሰ ያለው ሰብል ውድመት ከፍተኛ ቢሆንም የፌደራል መንግስት ትኩረት ሰጥቶ መፍትሔ ሊሰጥ አልቻለም ብለዋል። “መንጋው የተከሰተባቸውን ቦታዎች ለይታችሁ አምጡ ተብለን ብናሳውቅም አውሮፕላን ኬሚካል እርጭት በወቅቱ አልደረሰልንም” ሲሉ ተናግረዋል።

በወረዳው አዲስ ማለዳ ተገኝታ ቅኝት እስካደረገችበት ሰዐት ድረስ ከስድስት ሺሕ ሄክታር በላይ ሰብል መውደሙን ዋና አስተዳዳሪው ተናግረዋል። አካባቢው የበረሃ አንበጣ መነሻ ሆኗል ከሚባለው አፋር ክልል በቅርብ እርቀት ላይ ስለሚገኝ ስጋቱ ቀጣይነት እንዳለው ተናግረዋል።

የበረሃ አንበጣው ባደረሰው ጉዳት ምክንያት በወረዳው ዘጠኝ ሺሕ አባራዎች ሰብላቸው ሙሉ በሙሉ በመውደሙ መሰረታዊ ምግብና የተማሪዎች የትምህርት ቁሳቁስ እንዲሁም ለአርሶ አደሩ የመስኖ ልማት በግብዓት እና ምርጥ ዘር አቅርቦት እንደሚስፈልገው ዋና አስተዳዳሪው አሳስበዋል።

በአካባቢው ከተከሰተው ጉዳት በላይ ሌላ የወደፊት ስጋት የሆነው ጉዳይ የወረዳው ዋና አስተዳዳሪ ለአዲስ ማለዳ እንደገለጹት በወረዳው ላይ የአንበጣ መንጋው እንቁላል ሊፈለፍል እንደሚችል የግብርና ማለሙያዎች መጠቆማቸውን ተናግረዋል።

አዲስ ማለዳ ቅኝት ያደረገችበት ሦስተኛው ዞን በአማራ ክልል ደቡብ ወሎ ዞን ወረባቦ ወረዳ ሲሆን በወረዳው በረሃ አንበጣ የተከሰተው ከመስከረም 16/2013 ጀመሮ መሆኑን የወረዳው መንግስት ኮሙኒኬሽን ጽ/ቤት ኃላፊ ሳዳም ሽመልስ ተናግረዋል። በወረዳው ከሚገኙ 23 ቀበሌዎች በ17 ቀበሌዎች የበረሃ አንበጣ ተከስቶ ሙሉ በሙሉ የሰበል እና እንሰሳት መኖ ማውደሙን እንዲሁም አሁንም በሦስት ቀበሌዎች ላይ በረሃ አንበጣው የመዛመት ስጋት እንዳለ ጠቁመዋል።

በአካካባቢው የሚለማው ስብል ልማት በብዛት የማሽላ ስብል መሆኑን ከአርሶ አደሮች አንደበት ለማወቅ ተችሏል። መንጋው ከዘጠን ሺህ ሄክታር በላይ የማሽላ ሰብል አውድሟል።

መሀመድ ሲራጅ በወረባቦ ወረዳ የቀበሌ 17 ነዋሪ ናቸው። “በዘንድሮው ዓመት አምስት ሄክታር ማሽላ አልምቼ ይሄው አሁን በጣሳ አጥቼ ተቀምጫለሁ።” ሲሉ የጉዳታቸውን መጠን ለአዲስ ማለዳ አስረድተዋል። አዲስ ማለዳ በቦታው ላይ ተገኝታ ለማረጋጋጥ እንደቻለችው የአርሶ አደሮች ሰብል ወድሟል።

የአካባቢው ማኅበረሰብ በተከሰተው ጉዳት በመደናገጥ እንሰሳቶችን በርካሽ እየሽጠ መሆኑን የነገሩን ደግሞ አቦሌ ሰይድ የተባሉ አሮሶ አደር ናቸው። ይህም የሆነበት ምክንያት ማኅበረሰቡ በደረሰበት ጉዳት በመደናገጥ ካሁኑ የምግብ እህል ለመግዛት መሆኑ አቦሌ ለአዲስ ማለዳ አስረድተዋል።

የአካባቢው ማኅበረሰብ በደረሰበት ጉዳት ከፍተኛ የስነ-ልቦና ችግር ውስጥ መገባቱን የገለጹት የወረዳው ኮሙኒኬሽን ጽ/ቤት ኃላፊ ሳዳም መንግስት አስቸኳይ ድጋፍ እንዳደርግ ጠይቀዋል። ይህ ካልሆነ አሁን ላይ በማኅበረሰቡ ውስጥ በተለይም በወጣቱ ላይ የሚታየው ነገር ወደ ሌሎች ቦታዎች ለመሰድድ ሙከራ እያደረጉ በመሆኑ ከስደት ለመታደግ መንግስት ትኩረት ስጥቶ መስራት እንዳለበት ሳዳም አመላክተዋል። በወረባቦ ወረዳ ከሚኖረው 140 ሺሕ ዜጋ ውስጥ 54 ሺህ ያክሉ ለርሃብ አደጋ የተጋለጠ መሆኑን ሳዳም ተናግረዋል።

በወረዳው በደረሰው ከፍተኛ ጉዳት ማኅበረሰቡን ለማገዝ የተለያዩ ግል እና የመንግስት ተቋማት የብስኩት እና የምግብ ግብዓት ድጋፍ እያደረጉ መሆኑን ሳዳም ተናግረዋል።

አዲስ ማለዳ ቅኝት ያደረገችበት አራተኛው ዞን ሰሜን ወሎ ዞን ሲሆን በራያ ቆቦ ወረዳ እና ሀብሩ ወረዳ ተገኝታ የአርሶ አደሩን ጉዳት ተመለክክታለች።
45 ቀበሌዎች ያሉት የራያ ቆቦ ወረዳ አዲስ ማለዳ በቦታው ተገኝታ መረጃ አስከወሰደችበት ጊዜ ድረስ በ23 ቀበሌዎች ላይ የአንበጣ መንጋ ተከስቷል። 43 ሺህ 613 ሄክታር የሚታረስ መሬት ያለው ራያ ቆቦ የአፋር አዋሳኝ የሆኑት አምስት ቀበሌዎች ሰብላቸው ሙሉ በሙሉ በአንበጣ መንጋ ከጥቅም ውጪ ሆኗል። 10 ቀበሌዎች ደግሞ ከ50 በመቶ በላይ ሰብላቸው ሲጎዳ ቀሪ ስምንት ቀበሌዎች ከፊል ጉዳት ደርሶባቸዋል ተብሏል። አዲስ ማለዳ ከዚህ በፊት ቀድሞ የበረሃ አንበጣ የተከሰተባቸው ዘጠን ቀበሌዎች ከፉኛ መጎዳታቸወን መዘገቧ የሚታወስ ነው።

የራያ ቆቦ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ መንገሻ አሽብር ለአዲስ ማለዳ እንደተናገሩት ጉዳቱ አምራቹን ያራያ አርሶ አደር ላል ተጠበቀው ችግር ዳርጎታል ብለዋል። አዲስ ማለዳ በቦታው በተገኘችበት ወቅት የአማራ ክልል የምክር ቤት አባሎት የማኅበረሰቡን ጉዳት ለማየት በወረዳው የገጠር ቀበሌዎች ተገኝተቀው ቅኝት ሲደርጉ ተመልክታለች።
የአዲስ ማለዳ የተገኘችበት ሌላኛው ወረዳ ሀብሩ ወረዳ ሲሆን፣ በሰሜን ወሎ ዞን ሀብሩ ወረዳ የ28 ሺሕ አባወራዎች ሰብል ሙሉ በሙሉ መውደሙን የወረዳው ግብርና ጽሕፈት ቤት ለአዲስ ማለዳ አስታውቋል።

አዲስ ማለዳ በሀብሩ ወረዳ ቀበሌ 027 ተገኝታ ማረጋገጥ እንደቻለችዉ በአካባቢው ለምቶ የነበረው ጤፍ እና ማሽላ ሙሉ በሙሉ ፍሬዉ መበላቱን አረጋግጣለች። በሀብሩ ወረዳ 39 ቀበሌዎች ሲኖሩ 17 ቀበሌዎች ላይ የተከሰተው የበረሃ አንበጣ 9 ሺህ 100 ሄክታር ሰብል፣ 60 ሺህ ሄክታር ግጦሽ፣ 53 ሺህ ሄክታር ደን እና 60 ሺህ ቁጥቋጦ መውደሙን የወረዳው ግብርና ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ተመቼ ሲሳይ ለአዳስ ማለዳ ተናግረዋል።

ኃላፊው ለአዲስ ማለዳ እንደገጹት አንበጣዉ ሙሉ በሙሉ ውድመት ባደረሰባቸወሐ 17 ቀበሌዎች 141 ሺሕ 240 ዜጎች አስቸኳይ የምግብ ድጋፍ እንደሚስፈልጋቸው አረጋግጠዋል። አዲስ ማለዳ ያነገገረችው የቀበሌ 027 ወጣት አርሶ አደር ሀሰን ኑርዬ ሶስት ሄክታር ጤፍ አልምቶ ሙሉ በሙሉ እንደወደመበት ተናግሯል። አዲስ ማለዳ የወጣት ሀሰንን ሰብል መውደም በቦታዉ ተገኝታ አረጋግጣለች።

ኅብረተሰቡ ሳንሰደድ እና ልጆቻችን በረሃብ ሳይጎዱ መንግስትም ሆነ የኢትዬጵያ ህዝብ እንዲደግፋቸዉ ጥሪ አስተላልፈዋል። ኗሪዎቹ ለአዲስ ማለዳ አንዳሉት አካባቢው የበረሃ አንበጣ ከሚፈለፈልበት አፋር ክልል አጎራባች በመሆናቸው ከባለፈው 2012 የመኸር ወቅት ጀምሮ የችግሩ ሰለባ እንደነበሩ አስታውሰው ችግሩን መንግስት ከምንጩ እንዲያደርቅላቸው ጥሪ አቅርበዋል።

የበረሃ አንበጣ በኢትዮጵያ የተከሰተው በ2011 ሰኔ ወር ላይ ሲሆን ከተከሰተበት ጊዜ ጀምሮ በየጊዜው የመንጋ መጠኑን እየጨመረ በአርሶ አደሩ ሰብል ላይ ከፍተኛ ወድመት እያስከተለ ይገኛል። በኢትዮጵያ ከተከሰተ ኹለት ዓመት ያለፈው በረሃ አንበጣ መነሻው ከየመንና ሱማሌ ላንድ የነበረ ቢሆንም፣ ከወራት ወዲህ በኢትዮጵያ አፋር ክልል እንቁላልለ ጥሎ በመራባት በተለይ በአፋር ክልል አዋሳን ቦታዎች የሚገኙ ሰብሎችን በከፍተኛ ደረጃ እያወደመ ይገኛል። የግብርና ሚኒስቴር እንደሚለው ከሆነ የበረሃ አንበጣ አሁንም ካሳለፍነው መስከረም 2013 ጀምሮ ከየመንና ከሱማሌ ላንድ ወደ ኢትዮጵያ እየገባ ነው ተብሏል።

ቅጽ 2 ቁጥር 104 ጥቅምት 21 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com