ዶናልድ ጆን ትራምፕና ያለፉት አራት ዓመታት የንግሥና ዘመናቸው

Views: 151

ግራ አጋቢና ተወናብደው አወናባጅ ናቸው ይሉዋቸዋል ።ሰውየው ሁሌም ቢሆን የፈለጉትን ለመናገር አያመነቱም ። ብዙዎች ሰውየው ነጋዴ እንጂ የፖለቲካ ሰው አይደሉም ቢላቸውም በነጩ ቤተ መንግስት አራት አመታትን ለማሳለፍ ችለዋል ። አብርሃም ፀሀየም ዶናልድ ጆን ትራምፕ ባለፉት አራት ዓመታት የንግሥና ዘመናቸው ውስጥ ግድየለሽ ንግግራቸውን በአለምቀፍ ደረጃ ያለቸውን ተቀባይነት ማጣት የአለም ትልቅ ስጋት የሆነው የአየር ንብረት ለውጥ እና የኮረና ቫይረስ ላይ ያላቸው ግድየለሽ ምላሽ እና ሌሎች ባህሪያቸውን ለማሳየት ሞክሯል

የመጀመሪያዋ አራት ዓመታቸው እያለቀች ነው። አዛውንቱ ሰው ቀጣዩን አራት ዓመትም ነጩ ቤት መቆየት አለብኝ፤ አሜሪካንን ትልቅ የማድረግ ህልሜ የበለጠ ይሳካል እያሉ ነው። ባላንጣቸው ጆ ባይደን ደሞ የሚለቁላቸው አይመስሉም። እስከመጨረሻዋ ደቂቃ ድረስ ዕጣ ፈንታው የማይለየው የአሜሪካ ፕሬዚደንታዊ ምርጫ አሁንም እንደቀድሞው የዓለምን ቀልብ እንደያዘ ነው። ለዚህ ነው አሜሪካኖቹ ኑ የዓለምን መሪ እንምረጥ የሚሉት። እኚህ አነጋጋሪ ፕሬዝደንት ግማሽ የስልጣን መቆያ ዘመናቸውን እያጠናቀቁ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ምን ዓይነት ሰው ነበሩ የሚለውን ጥያቄ ይዘን ስለርሳቸው ጥቂት እንባባል።

ዶናልድ ጆን ትራምፕ እና ‘ፌክ ኒውስ’
ዶናልድ ጆን ትራምፕ በቢዝነሱ ዓለም ስኬታማ ናቸው። በንግዱ ውጣ ውረድ ላይ በጠረባ ተመተው መኪና ውስጥ እስከማደር ደርሰው የነበሩ ቱጃር ናቸው። ለህልማቸው ሟች እንደሆኑ የሚነግርላቸው የነጩ ቤተ መንግስት አለቃ ገና በሰላሳ ዓመት ዕድሜያቸው አሜሪካንን እንደሚመሩ ተናግረዋል። ተወደዱም አልተወደዱ ግን ይኸው በዘገየ ዕድሜአቸው ፕሬዝዳንት ሆነዋል።

ሰውየው ህልማቸውን ይኑሩ እንጂ በፖለቲካው ግን እምብዛም የተሳካላቸው አይመስልም። አሜሪካንን ከቀረው ዓለም ጋር ከማዋደድ ይልቅ ማቀያየም የያዙ ይመስላል። እኛም ቤት ይኸው ነገር ይዘው ከተፍ ብለዋል። መቼም ከሳቸው አፍ የተነገረ በመሆኑ እምብዛም ዋጋ ባንሰጠው ይሻላል እንጂ አባባ ዓመለኛ ናቸው ሰውየው ምርጫው ላይ ማትረፍ የፈለጉት ነገር ያለም ይመስላል። የሆነ አካል አስደስተው ነጩ ቤት ለመቆየት የቀመሩት የድምጽ ስሌትም ይሆናል እንጂ ንግግራቸው ከእኛነታችን ሊያወርደን አይገባም። በስሜትም ጭምር! ራስ ላይ በርትቶ መስራቱ ያዋጣል። በሌላ ላይ ከመደገፍ ይልቅ በራስ እግር ለመቆም መፍጨርጭር ግድ የሚልበት ዘመን ላይ ስለመሆናችን ማሳያ ነው። የፖለቲካና የምጣኔ ሃብት ምህዳሩን በማስፋት ሁሉም እንዲጫወት መፍቀድ ተገቢ ነው።

ዋና ነገራችን ስለእኚህ አወዛጋቢ ሰው መነጋገር ነውና አንድ በአንድ እያነሳሳን ማንነታቸውን እንመልከት። ከላይ በንዑስ ርዕሳችን ላይ ስላስቀመጥነው ፌክ ኒውስ /fake news/ ወይም ያልተገባና ትክክለኛ ያልሆና ዜና እና መረጃ እናውራ። ይህ የፌክ ኒውስ ጉዳይ መግዘፍ የጀመረው ዶናልድ ጆን ትራምፕ ፕሬዚደንት ከሆኑ ጊዜ ጀምሮ ነው። እሳቸውን የተመለከተና አሉታዊ የመሠላቸውን ጉዳይ ለማውገዝ የሚጠቀሙበት ቃላት it is fake news የሚል ነው። ከጋዜጠኞች ምንጭ ተጠቅሶ ሲጠየቁ ጭምር የሰማችሁት የተቀነባበረ ዜና እንጂ እኔ ይህንን አላልኩም ወይም አላደረኩም ዓይነት መልስ በመስጠት ጉዳዩ ፌክ ኒውስ ነው በማለት ያሳርጉታል።

ትራምፕ ያዳበሩት ይህ ‘ፌክ’ ነው የማለት አነጋገር ወደሌሎች ሀገራት መሪዎች እየተስፋፋ መሆኑን አጥኚዎችእየዘገቡት ይገኛል። የፊሊፒንስ፣ የሳዑዲ ዓረቢያ፣ የታይላይንድና የባህሬን መሪዎች በምሳሌነት ተጠቅሰዋል። እነርሱም እንደትራምፕ መካድ ጀምረዋል ተብለዋል። ለሚቀርብባቸው መረጃ ሁሉ “ይሄ ሆን ተብሎ የተቀናበረና አግባብነት የሌለው መረጃ ነው” እያሉ ማምለጥ እንደጀመሩ ተስተውሎባቸዋል። ትራምፕ በመሪዎች ደረጃ ሊስፋፋ የሚችል ወረርሽኝ አስነስተዋል ማለት ይቻላል።

አጥኚዎች እንደገለጹት ዶናልድ ትራም ፕሬዝዳንት ከሆኑ ጀምሮ ከኹለት ሺህ ጊዜ በላይ ፌክየሚለውን ቃል ተጠቅመዋል። ጉግል ባሰላው ስሌትም ይህ ቃል በዓለም ላይ ወደ አንድ ነጥብ አንድ ቢሊየን ጊዜ በገጹ ላይ ጥቅም ላይ ስለመዋሉ ይፋ አድርጓል። ሰውየው ለዓለም ያወረሱት ቃል መሆኑ ነው።

የ’ሲቪክ ሶሳይቲ ግሩፕ’ የተሰኘው ተቋም ግን ቃሉን በዋዛ እያለፈው አይደለም። የዚህ ቃል አጠቃቀም ዴሞክራሲን የሚያቀጭጭ፣ ተጠያቂነትን እና ኃላፊነትን ወደኋላ የሚያስቀር የማምለጫ መንገድ እየሆነ ነው ሲል አትቷል። ትክክለኛ መረጃዎችን ጭምር ልክ እንዳልሆነና አግባብ ያልሆነ ዜና ነው በሚል መሪዎችም ሆኑ ሌሎች በየደረጃው የሚገኙ አካላት እያጭበረበሩበት ነው ሲል ቅሬታውን በማሰማት ላይ ይገኛል። ወደሀገራችን ጉዳይ ስንመጣ አሁን በቀደም በኛ ላይ የሰነዘሩትን አስተያየት ደግመው ቢጠየቁ ፌክ ነው ሊሉ ይችላሉ። ለማንኛውም የትራምፕ አንደበትና እጅ ከኛ ላይ እንዲነሳ፤ እንዲሁም ሌሎች ረጃጅም እጆችሞ እንዲሰበሰቡ ወይም ከመውሰድ ይልቅ ለመስጠት እንዲዘረጉ ሲባል ከቀረርቶና ሽለላው በላይ በይበልጥ አቅማችን ላይ ልንሰራ ይገባል። ራሳችንን በውስጥም ሆነ በውጪ ያለን ልኬት በዓለምአቀፍ ደረጃና በጊዜው ሚዛን መሆኑን ማረጋገጥ አለብን። ያለበለዚያ ያወጣነው መግለጫ ሰሚ የለውም፤ በየቴሌቪዥን መስኮቱ አንዳንድ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ተቆጡ በሚለው ዜና የሚደነግጥ ብቻ ሳይሆን የሚያይ አይን አይኖርም። ያላጠናቀቅናቸው ብቻ ሳይሆኑ አዳዲስ የጨመርናቸው የውስጥ የቤት ስራዎች አሉብን።

የፖለቲካ ተንታኝ የሆኑትና የጀርመን ድምጽ ያናገራቸው አቶ የሱፍ ያሲን እንዳሉት ኢትዮጵያ ከአሜሪካ፣ ከግብፅም ይሁን ከሌላ ሥፍራ የሚደረግባትን ጫና ለመቋቋም የውስጥ አንድነቷን መጠበቅ፣ ካለፈዉ ስሕተቶቿ መማር፣ ዕድሎችዋን በቅጡ ማወቅና መጠቀም ይገባታል ብለዋል።

የዶናልድ ጆን ትራምፕ ተቀባይነት ከአሜሪካ ውጪ
በ13 ሀገራት ውስጥ ተቀባይነታቸው ምን እንደሚመስል በተሠራው ጥናት ለምሳሌ በእንግሊዝ 41 በመቶ ሆኖ ተገኝቷል። ይህም ከ20 ዓመታት ወዲህ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ያስመዘገበው አነስተኛ ቁጥር ነው። በፈረንሳይም 31 በመቶ ሲሆን እንደአውሮፓ ከቆጣጠር ከ2003 ወዲህ የተመዘገበው አነስተኛ ቁጥር ነው። በጀርመን በተመሳሳይ መልኩ የቀነሰ ሆኖ 26 በመቶ ተመዝግቦባቸዋል። ከዚህ የተቀባይነታቸው መውረድ ጎን ለጎን የ13 ሃገራት ህዝቦችን በመጠየቅ በተሰራው ጥናትም ትራምፕ አልቀናቸውም። ከዓለማችን ኃያላን ሃገራት መሪዎች መካከል ለዓለማችን ትክክለኛ ስራ በማበርከት ተጽእኖ ይፈጥራሉ የተባሉት በደረጃ ተሰልቶላቸዋል። ከተጠያቂዎቹ በተሰበሰበው መረጃ መሠረት ምን ያህል እንደሚተማመኑባቸው በመቶኛ እንደሚከተለው ቀርቧል፤
የጀርመኗ ሜርኬል 76 በመቶ
የፈረንሳዩ ሜርኬል 64 በመቶ
የእንግሊዙ ጆንሰን 48 በመቶ
የሩሲያው ፑቲን 23 በመቶ
የቻይናው ዢ 19 በመቶ
የአሜሪካው ትራምፕ 16 በመቶ ሆነው እንደየደረጃቸው ሰፍረዋል።

የተጠየቁት 13 ሀገራት ለንጽጽሩን ሚዛናዊነት በየራሳችን ለመጥቀስ አስፈላጊ ስለሆነ እንጥቀሳቸው። አውስትራሊያ፣ ቤልጂየም፣ ካናዳ፣ ዴንማርክ፣ ፈረንሳይ፣ ጀርመን፣ ጣሊያን፣ ጃፓን፣ ኔዘርላንድ፣ ደቡብ ኮሪያ፣ ስፔን፣ ስዊድን፣ እንግሊዝ ናቸው። እነዚህ ሀገራት ከአሜሪካ ጋር ጠበቅ ያለ ግንኙነት ያላቸው ሆኖ ምናልባትም አሜሪካ ላይ ተስፋ ሊያደርጉ ይችላሉ የተባሉ ዜጎች ያሉባቸው ሀገራት ናቸው። ውጤቱ ግን አሉታዊ ተደርገው ከሚሳሉት የሩሲያና የቻይና መሪዎች እንኳን ዝቅ ያለ ግምት እንዲያገኙ ሆነዋል። ትራምፕ ከስረዋል!

ፕሬዚደንት ትራምፕ በኮረና ቫይረስ ስርጭት መግታት ላይም አሜሪካውያኑ ራሳቸው አልተማመኑባቸውም። መሪያቸው ወረርሽኙን ሊያቆሙት ይችላሉ ብለው የሚያምኑት ከ15 በመቶ አይበልጡም። “የኮቪድ 19 ምንጭ ቻይና ናት፤ የአለም ጤና ድርጅት ኃላፊነቱን በአግባቡ አልተወጣም” ወዘተ… የሚሉት የትራምፕ አጀንዳዎች ጊዜ አልፎባቸዋል። እውነታው ሰው መሞቱ ብቻ ነው። አሜሪካውያን እየረገፉ ነው። ምጣኔ ሃብቷ ከዕድገት ተገቷል። ዜጎቹ የሚፈልጉት ይህንን የሚገታላቸው አሰራር ነው። የወረርሽኙ ተጠያቂ ማን እንደሆነ የማወቅ ጉዳይ አሁን ላይ አንገብጋቢያቸው አይደለም። በዚህ ረገድ ግን ፕሬዚደንቱን የሚያምነው ኢምንት ነው።

የፓሪሱ አየር ንብረት እና ዶናልዶ ጆን ትራምፕ
ዓለም በአየር ንብረት ሳቢያ እየተመሳቀለች ነው። የወደፊቱ ደግሞ ከዚህ ይብሳል። በካርበን ልቀት ቻይና ግንባር ቀደም የብክለት አስተዋጽኦ እያደረገች ነው። ቀጥሎ አሜሪካ ናት። ዓለም ለዚህ ምን ይበጃታል እየተባለ ውይይትና ክርክሮች እየተደረጉ ባሉበት ወቅት አወዛጋቢው አለቃ ከሰብዓዊነት ይልቅ ወትሮም የቢዝነስ ነገር ላይ የኖሩ ናቸውና 200 ሀገራት የሚደግፉትን የፓሪሱ የአየር ንብረት ስምምነትን ሀገራቸው ጥላ እንድትወጣ አድርገዋታል።

ያስቀመጡት መልስ የሀገሬ አምራቾች ላይ የሚፈጥረው ተጽእኖ የአሜሪካ ምጣኔ ሃብትን ይገድላልና በፍጹም አላደርገውም የሚል ሆኗል። እውነታው ግን ይህ የአየር ንብረት እስካልተስተካከለ ድረስ ዓለማችንን ከምቹ የመኖሪያ ስፍራነት ሊያርቃት ይችላል። በበጋ ወቅት በከፍተኛ የሙቀት መጠን መጨመር ምክንያት አዛውንቶች መቋቋም አቅቷቸው እየሞቱ እንደሆነ ይታወቃል። ሌላ ማሳያ እንመልከት የጣሊያን ገበሬዎች ኪዊ የተሰኘው ተክላቸው ላለፉት ስምንት ዓመታት ምን እንደሚያወድመው ባለማወቅ ግራ ተጋብተዋል። ከቻይና ቀጥሎ በዚህ ተክል አብቃይነት አንደኛ የሆነችው ጣሊያን ከሀገሪቱ 20 በመቶ የሚሆነው ተክሏ ወድሟል።
በሽታው ቅጠሉን ያበሰብስና በአስር ቀናት ውስጥ መሬት ይወድቃል። በዚህ ጊዜ እነዚህ ኪዊ የተሰኙት ፍራፍሬዎች በቀጥታ ለጸሐይ ብርሃን ይጋለጡና ይበላሻሉ። ከዚህ ጎን ለጎን የኪዊ ተክል ስሩ እየበሰበሰ በአንድና በሁለት ዓመት ውስጥ ይወድቃል። ገበሬውቹ ሞርያ ይሉታል – ‘ገዳይ’ ማለት ነው። ሳይንቲስቶች ምንም መፍትሄ ማግኘት እንልቻሉም ተናግረዋል።

በመላምት ደረጃ ይህ ከ2012 ዓ. ም ጀምሮ አውዳሚ እየሆነ የመጣው በሽታ እንደተመራማሪዎች ገለጻ ዐፈር ውስጥ በሚፈጠሩ ባክቴሪያና ፈንገስ እንዲሁም የኦኮስጅን መጠን መዛባት ነው ቢሉም ከዚህ በተጨማሪም በተለይ በይበልጥ እየታመነበት ያለው የዓለም የአየር ጸባይ መለወጥ ያመጣው ጣጣ ነው እያሉ ነው። የበጋ ወራቱ ሙቀት 30ዎቹ ዲ.ሴ.ግ ውስጥ የገባ ሲሆን ለኪዊ ተክል ግን ከ25 – 27 በላይ እንዲሆን አይመከርም ተብሏል። ዝናብን በተመለከተም በከፍተኛ መጠን እየተመዘገበ በመሆኑ እሱም ለተክሉ አስቸጋሪ ሆኖበታል ተብሏል። ዶናልድ ትራምፕ ለካርበን ልቀት አስተዋጽኦ እያደረጉ ያሉትን አምራቾች ለመታደግ በሚል ስለሌላው ዓለም ግዴለሽነታቸውን በይፋ አሳይተዋል። ዞሮ ዞሮ ዳፋው ለሷ መድረሱ የማይቀር ቢሆንም።

እስራኤል
የአሜሪካ በርካታ መሪዎች ከአይሁዳዊቷ ሀገር ጋር ጥብቅ ትስስር እንዳላቸው ይታመናል። የመካከለኛው ምስራቅ ሚዛን አስጠባቂያቸው ናት። የእስራኤል ጥቅም የአሜሪካ ጥቅም ተደርጎ ይወሰዳል። እስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትሯ ጎልዳ ሜየር ምዕራብ ጀርመን ላይ ተዘጋጅቶ በነበረው የዓለም የኦለምፒክ ውድድር ላይ አትሌቶቿን በአሸባሪዎች ባጣች ጊዜ የተናገሩት ንግግር “እኛ ብቻችንን ነን፤ የሚደርስብንንም ብቻችንን ተጋፍጠን እናሸንፈዋለን” ብለዋል። እንዳሉትም ለሞሳድ በሰጡት የቤት ስራ ከግድያው ጋር እጁ ያለበትን እያንዳንዱን ሰው በያለበት የዓለም ክፍል የየሀገራቱን ፈቃድ ሳይጠይቁ ለቅመው ጨርሰዋቸዋል። ከዚህች በወታደራዊና በቴክኖሎጂ የፈረጠመችና እንዳሻት የሆነች ሀገር ጋር ግን አሜሪካ ምን ጊዜም አለች። በይፋ መኖሯን ያሳወቁት ግን ትራምፕ ይመስላሉ።

በእንጥልጥል የቆየውና ብዙ ሀገራት እጃቸውን የሰበሰቡበት የእስራኤል ዋና ከተማን ከቴላቪቭ ወደኢየሩሳሌም መዞር የተቀበሉትና እንደሀገር ዕውቅና የሰጡት ዶናልድ ትራምፕ ናቸው። በኢየሩሳሌም ላይ የይገባኛል ጥያቄ ያላትን ፍልስጤም የራስሽ ጉዳይ ብለው አስቀይመዋታል። ትራምፕ ብልህነት ለሚፈልገው የዲፕሎማሲ ጉዳይ መርህ የሚከተሉ አይመስልም። እስራኤል በቅርቡ ከሱዳን ጋር ስምምነት ማድረጓን ጨምሮ ከዚህ በፊት ከባህሬንና የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ጋር ያስማሙት ትራምፕ ናቸው። ይህ እንኳን በመጠኑ የተሻለ ስራ የሰሩ ቢያስብላቸውም ዓላማቸው ግን በብዙ ጉዳዮች ከአሜሪካ ጋር ሚስጥራዊ ስምምነት ላላት እስራኤል ያደላ እንደሆነ ብዙ ተንታኞች ያስረዳሉ።

በማያልቅ ጦርነት ውስጥ አንሳተፍም
ትራምፕ ይህን ያሉት ከሶሪያ ጦርነት እጄን አንስቻለሁ ብለው ጦራቸውን ለማውጣት በወሰኑበት ጊዜ ነው። ታላቅ ሀገራት መቋጫ በሌለው ጦርነት ውስጥ አይዋጉም (Great nations do not fight endless wars) በሚል ጠብ የሚል ምክንያት በሌለው ንግግር ፊቴን ከሶሪያ ላይ አንስቻለሁ ሲሉም ተደምጠዋል። የሶሪያም ሆነ ተመልካች ያጣው የየመን ጦርነት እንዲሁም ሊቢያና ሌሎች ሀገራት ውስጥ ጭምር ያለው ውጊያ አሜሪካ እጇ የለበትም ወይም አታውቀውም ማለት ዘበት ነው። ጥቅም ካላት በከፍታና በማይነቃነቅ ወንበር ላይ ለዘመናት የምታስቀምጣቸው መንግስታት አሉ፤ ካልመሰላት ደግሞ አንድ ቀንም እንዳያድሩ የምታደርግ ጣልቃ ገብ ናት። የጀመረችውን ወይም ያስጀመረችውን ጦርነትም ሳትጨርስ ትታ ለመውጣት ወደኋላ የማትል ነገሯን ላየ ክፋቷ አይጣል ነው ያስብላል።

የኢራኑን የጦር አለቃ ጄኔራል ቃሲም ሱሌይማንን ምንም ይፋዊ ጦርነት ውስጥ ሳትገባ ነጥላ ገድላቸዋለች፤ ትራምፕ እኔ ነኝ ከማለት ያገዳቸው አልነበረም። አስገድዶ መድፈር ማለት ይሄ ነው። ተቆጪ የሌላት ሀገር ናትና! ከዚህ በላይስ ጣልቃ ገብነትና ሉዓላዊነትን መድፈር የታለ?! ስደተኞችን በተመለከተም ከሰባት ሙስሊም ሀገራት ወደሀገሬ ማንም ሰው እንዳይመጣ ሲሉ ዓለም ላይ የኃይማኖት ልዩነት ያለምንም ይሉኝታ የፈጠሩ ግዴለሽ መሪ መሆናቸው የተገለጸበት አካሄዳቸው ነበር።
ወደ 17 ከሚጠጉ ሀገራት የሚመጡ ስደተኞች ላይም ጥብቅ ህግ አውጥተዋል። ሜክሲኮን በአጥር ከመለየት አንስቶ ወላጅና ልጆችን እስከመለየት የደረሰ የስደተኞች ክልከላ ህግ በማውጣት ለምስኪን ስደተኞች ምቹ ባለመሆንና ከላይ በጠቃቀስናቸው ማንነት ይህንን አራት ዓመታት አሳልፈዋል። ይቀጥሉ ይሆን? አብረን የምናየው ይሆናል።
በአብርሃም ፀሀየ

ቅጽ 2 ቁጥር 104 ጥቅምት 21 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com