የእለት ዜና

እምቦጭን በአንድ ወር ዘመቻ

የእምቦጭ አረም የጣና ሐይቅ ላይ መታየት ከጀመረበት 2004 ጀምሮ እምቦጭን ለማጥፋት የተደረጉ በርካታ እንቅስቃሴዎችእንደነበሩ የሚታወስ ነው። ይሁን እንጂ ውጤታማነታቸው እዚህ ግባ የሚባል ባይሆንም ሐይቁን ግን በጥቂቱም ቢሆን በነብስ እንዲቆይ ያደረገው ነበር።
ይህን መጤ አረም ግን ከዚህ ቀደሙ በተለየ ሁኔታ ለአንድ ወር የሚቆይ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሰው የሚሳተፍበት እና ሐይቁን ከአደጋ ለመታደግ የሚደረግ ርብርብ ተጀምሯል በዚህም 90 በመቶ የሚሆነውን አረም ለማስወገድም ታቅዷል። ከዘመቻውም ባለፈ ግን ዘላቂነቱን ለማረጋገጥ አዲስ የአሰራር ስርዓት በመዘርጋት በሐይቁ ዳርቻ አነስተኛ የግብርና ስራዎች እየተተገበሩ ሐይቁን እግረ መንገድ ከአረሙ መጠበቅ የሚል ነው። በዚህም ታዲያ በዘመቻው ያሳተፈውን ሰፊ ቁጥር ያለውን ሰው ታዲያ በዘላቂነት አቅፎ የሚይዝ ስርዓትም እንደሆነ ተጠብቋል። ጣና ሕልውናውን ለሰው ልጆች ብቻ ሳይሆን አቅፎ ለያዘው የብዘሀ ሕይወት ጭምር ሲል ሊመልስ ግድ ያለው ይመስላል።

ጣና ሐይቅ እምቦጭ በሚባል መጤ አረም መወረሩ ከታወቀ ዘጠኝ ዓመታት ተቆጥረዋል። ለመጀመሪያ ጊዜ መጤ አረሙ ሐይቁን መውረሩ የታወቀው በ2004 ነበር።አሁን በሀይቁ ዙሪያ በሦስት ዞኖች ማለትም በደቡብ ጎንደር መዕከላዊ ጎንደር እንዲሁም ሰሜን ጎንደር የሚገኙ 30 ቀበሌዎችን እና አንድ ከተማ አስተዳደርን ጨምሮ የሀይቁ 4300 ሄክታር በላይ የሚሆነው የሐይቁ አካል በእምቦጭ አረም ተወሯል። ባለፉት ዘጠኝ ዓመታት ሐይቁን ከዚህ ወራሪ አረም ለመታደግ አልፎ አልፎ ዘመቻዎች ቢደረጉም እምቦጩ ግን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየሰፋ የሐይቁን መግቢያ በሮች ጥቅጥቅ አድርጎ ዘግቷል። በተለይ በሐይቁ ሰሜንና ሰሜን ምስራቅ አቅጣጫ የሚገኙት የፎገራ ሊቦከምከም ጎንደር ዙሪያና ደምቢያ ወረዳዎች ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰ ይገኛል።

ለእምቦጭ አረም የጣና ሐይቅ ምቹ የሆነበት ምክንያት ደለል ገበሬዎች እህል ለመዝራት የሚጠቀሙበት ማዳበሪያ እና ከሆቴሎች የሚወጡ ፍሳሾች መሆናቸውን ጥናቶች ያስረዳሉ።እንዲሁም በአንድ ወቅት ጠቅላይ ሚንስትሩ እምቦጭ ጣና ሀይቅን በከፍተኛ ደረጃ ለማጥቃቱ የጉና ተራራ የደን ሽፋን መሳሳትና በዝናብ ወቅት የሚኖረው ከፍተኛ ጎርፍ ጠራርጎ የሚወስዳቸው አፈርና ሌሎች ግብዓቶችን ወደ ጣና ሀይቅ መግባታቸው ለመጤ አረሙ እድገት የጎላ አስተዋፅኦ አበርክቷል ብለዋል፡፤
የጣና ሐይቅ ተፋሰስ 21 ወረዳዎችን እና 347 ቀበሌዎችን ያዳርሳል።በሐይቁ ውስጥ 20 ደሴቶች እና ገዳማት ይገኛሉ።ሐይቁ ኢትዮጲያ ካሏት የተፈጥሮ ጨው አልባ ውሃማ አካላት መካካል 50 በመቶ ያህሉን ይሸፍናል። አንዳንድ ጥናቶች እንደሚያሳዩት ከሆነ ከሦስት ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ዜጎች ኑሯቸው የተመሰረተው በጣና ሃይቅ ዙሪያ ነው። በሐይቁ ዙሪያ የሚገኙ አርሶአደሮች ሕይወት የተመሰረተው ዐሳ በማጥመድ እና የጣና ሐይቅ ዳርቻዎች ላይ ሰብል በማምረት ነው በሐይቁ ዙሪያ የሚበቅለው ሳርም ለከብቶቻቸው ምግብ የጣና ሐይቅ ውሃም ለመጠጥ ልብሳቸውን ለማጠብ እና ገላቸውን ለመታጠብ ይገለገሉበት ነበር አሁን ሁሉም ነገር ነበር እየሆነ የመጣ ይመስላል።ጣና ውሃው ሳይሆን አረሙ ነው እየታየ የመጣው ይህ አረም በኣካባቢው ገበሬዎች አጠራር “ግም ቅጠል” ጣናን ከወረረ ወዲህ ግን ከብቶች የሚበሉት ሳር በማጣታቸው አረሙን በመብላት እየሞቱ ይገኛሉ የዐሳ ምርት እጅጉን እንደቀነሰ ዐሳ አስጋሪዎች ያስረዳሉ። ገበሬዎቹ ታንኳ ተጠቅመው እንደልባቸው በጣና ላይ መንቀሳቀስ ተስኗቸዋል።

የእምቦጭ አረምን መስፋፋት ለመቀነስ ማሽን ብቻ ሳይሆን ሌሎች ልምዶች እንደሚያስፈልጉ በመታሰቡ እንደ ጢንዚዛ ያሉ በባዮሎጂካል ምርምር የማርባት ቪክቶሪያ ሐይቅ ላይ ያለውን ተሞክሮ በመውሰድ ውጤታማ መሆን እንደሚቻልም በመገመቱ የባህርዳር ዩኒቨርሲቲ አረሙን የሚመገብ የጢንዚዛ መንጋ በማርባት የተደረገው ሙከራ ግብ አልመታም። ባህርዳር ዩኒቨርሲቲ በጀት መድቦ ከሙላት ኢንጂነሪንግ ጋር በመተባበር ማሽኖች በመስራት እንዲሁም ጎንደር ዩኒቨርሲቲ በርካታ ሙከራዎች ቢደረጉም ስኬታማ የሆነ አንድም ሙከራ ግን እስካሁን አልተደረገም።በባህላዊ የህክምና ዘዴ አገር በቀል በሆነ መድሀኒት እምቦጭን ለማጥፋት ባህላዊ ህክምና እንደተገኘ የተሰማው ዜናም የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነበር።በሥነ ሕይወት ተፈጥሮው በዘሩ እና በግንዱ የሚራባው ይህ አረም በእጅ በሚነቀልበት ወቅትም ውሃው ላይ ሲንጠባጠብ መልሶ በመተካቱ እና አረሙ ከተነቀለ በኋላ የመድረቅ አቅሙ በጣም ዝቅተኛ ስለሆነ እና ባለበት ተመልሶ በማንሰራራቱ አረሙን ለማጥፋት ከባድ እንደሆነ ታውቋል።በፀረ አረም ኬሚካል በመርጨት አረሙን ለመጥፋት የአማራ ክልል ግብርና ምርምር ኢንስቲቲዩት ያደረገው ሙከራም ከሽፏል። ምክንያቱንም የጣና ሐይቅ እና ሌሎች የውሃ አካላት ጥበቃ እና ልማት ኤጀንሲ ዋና ስራ አስኪያጂ የሆኑት አያሌው ዘውዴ(ዶ/ር) ሲናገሩ ‹‹ የጣና ሐይቅ አካባቢ ነዋሪ ውሃውን ለልብሱ ማጠቢያ ለገላው መታጠቢያ አልፎ አልፎ ለእራሱም ይጠጣዋል ከብቶቹም የሚጠጡት ከዚሁ ከጣና ውሃ ሲሆን በዙሪያው የሚበቅለው ሳር ደግሞ ለከብቶቹ መኖ እንዲሁም የሚየውል በመሆኑ በቀላሉ ኬሚካል መርጨት አልተቻለም›› ብልዋል።

ባለለፈው ሳምንት ጥቅምት ዘጠኝ የጣና ሐይቅን 90 በመቶ እምቦጭ አረምን በሰው ኃይል በመንቀል እና በማሽን የማስወገድ ሥራ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ደመቀ መኮንን የሚመራ የአንድ ወር አገራዊ ዘመቻ ተጀምሯል።ዘመቻው ከጥቅምት ዘጠኝ እስከ ህዳር ዘጠኝ የሚቆይ ነው። ዘመቻውን ያስጀመሩት የውሃ እና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ስለሺ በቀለ (ዶ/ር)ናቸው። ”ህዳሴ ግድብ ያለ አባይ አባይ ደግሞ ያለ ጣና ማሰብ አይቻልም” በሚል መሪ ቃል ነው ዘመቻው የተጀመረው። ለዕቅዱ ማስፈጻሚያ ከፌዴራል መንግስት ከገንዘብ ሚኒስተር ከሁሉም የክልል መንግስታት ከፌድራል ተቋማት ከሚንስትር መስሪያ ቤቶች እንዲሁም ከኢትዮ ያ ዲያስፖራ ትረስት ፈንድ እና ከልማት ተቋማት የሚሸፈን እና ቃል የተገባ ከ92 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት ተይዟል።

በዘመቻው 360 ሽሕ ሰዎች ይሳተፋሉ በዘመቻ ሥራው ከአካባቢው ማኅበረሰብ እና ከሌሎች አካባቢዎች የሚመጡ ግለሰቦች የተቋማት ሠራተኞች በጎ ፈቃደኞች የጉልበት ሠራተኞች እና ሌሎችም እየተሳተፉ ይገኛሉ።በዚህ ዘመቻ አረሙን በእጅ በመንቀል እና በማሽን በመታገዝ ለማቃጠል ታቅዶ ነው እየተሰራ የሚገኘው።ዘመቻው በ2014 አረሙን ሙሉ በሙሉ ለማጥፋት አቅዷል።ነገር ግን ለዚህ ጋዜጣ ቃለምልልስ እስካደረግንበት ረቡዕ ጥቅምት 18 ድረስ ምንም አይነት ገንዘብ ወደ ኤጀንሲው የባንክ ደብተር እንዳልገባ አያሌው(ዶ/ር) ተናግረው ሥራው እየተሰራ ያለው ከዚህ በፊት ቃል ተገብቶ በተሰበሰበ 20 ሚሊዮን ብር እንደሆነ ገልፀዋል።ይህ አገራዊ ዘመቻ ለአንድ ወር ብቻ ተካሂዶ የሚቆም ሳይሆን ለተከታታይ አምስት ዓመታት የሚያሰሩ ዕቅዶች የተያዙበት እንደሆነ ታውቋል።

ከዘጠኝ አመት በላይ ሳይጠፋ የቆየን አረም በአንድ ወር ውስጥ ያውም ሙሉ በሙሉ እንዴት ማጥፋት ይቻላል ብለን ለአያሌው (ዶ/ር) ላነሳንላቸው ጥያቄ ሲመልሱ አረሙን የምናጠፋው 90 በመቶውን ነው ይህ ማለት 10 በመቶውን ሳናስወግድ እንተወዋለን ለማለት ሳይሆን ከዚህ ዘመቻ መጠናቀቅ በኋላ አረሙ ለሚቀጥለው 2014 ተመልሶ ሊበቅል ወይም ሊተካ የሚችለው በዘሩ ምክያት 10 በመቶ ያህሉ ብቻ መሆኑን ለመንገር እንደሆነ አስረድተው በዚህ አንድ ወር ውስጥ ደግሞ በሃይቁ ጥልቀት ምክንያት ሊደረስባቸው የማይቻል ቦታዎች ስለሚኖሩ እንደሆነ አስረድተዋል።

ዶክተሩ አክለውም እምቦጭ ላይ የታየው የመንግስት ሚና ምን እንደነበረ እና ምን መሆን እንዳለበት እና መንግስት ያለቀ ነገር ላይ ሁሌም ለምን አጣብቂኝ ውስጥ እንደሚገባ ለተጠየቁት ጥያቄ‹ ይህ የኔም የሁሉም ሰው ጥያቄ ሲሆን ነገር ግን መጭው ጊዜ ካለፈው ስለሚበልጥ ወደኋላ ጣት ከመጠቋቆም ከመንግስት ወገን ብቻ ሳይሆን ህብረተሰቡ ጋርም ድክመት ስላለ አሁንም ዝም ብለን የበለጠ ዋጋ እንዳንከፍል ከዛሬ መጀመሩ የተሸለ ነው› ብለዋል።

የትራንስፖርት ሚኒስትር ዳግማዊት ሞገስ ከሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ከፍተኛ አመራሮች ጋር በመሆን የእንቦጭ አረምን ለማጥፋት በሚደረገው ሀገራዊ ዘመቻ ላይ ተሳትፈዋል።ሚንስትሯ ከሕዝብ ተወካዮች የከተማ ልማት ኮንስትራክሽን እና ትራንስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አመራር እና አባላት የትራንስፖርት ሚኒስቴር ከፍተኛ አመራር የትራንስፖርት ዘርፍ ተጠሪ ተቋማት ዳይሬክተሮች እና የሁሉም ክልል እና ከተማ አስተዳደር የትራንስፖርት ዘርፍ የሥራ ኃላፊዎች ጋር በመሆን ነው ዘመቻውን የተቀላቀሉት።አያሌው (ዶ/ር) እንዳሉት ከሆነም በዚህ እምቦጭን የማጥፋት ሰፊ አገራዊ ዘመቻ ላይ የተሳተፉ የተፋሰሱ ከፍተኛ ምክር ቤት ሰብሳቢ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ዘመቻውን ከማስጀመር በተጨማሪ በየዕለቱ የደረሰበትን ደረጃ በመከታተል ለዘመቻወ የሰጡትን ትኩረት ሳያደንቁ እንደማያልፉ ተናግረዋል።

በመጀመሪያው ሳምንት በ26 ቀበሌዎች ላይ አረም የመንቀል ስራው ሲከናወን በሐይቁ ጥልቀትና በመንገድ ችግር ምክንያት ያልተጀመረባቸው አካባቢዎች ሳምንት የበለጠ ትኩረት ተሰጥቶ ተሰርቶበታል።

እምቦጭን ከጣና ሃይቅ ለማስወገድ የተጀመረው ዘመቻ በሁሉም ቀበሌዎች ተጀምሯል። የዚህ ዘመቻ አፈጻጸም ከፌደራል እስከ ቀበሌ ድረስ ክትትል እና ግምገማ እየተደረገበት ይገኛል ሁሉም በታቀደው ልክ እየሄደ መሆኑን ዶክተሩ አረጋግጠዋል።ጣናን ከእንቦጭ አረም ነፃ ለማድርግ ለአንድ ወር የተጀመረው ዘመቻም በታሰበው መንገድ እንደቀጠለ በመጀመሪያው ሳንምንት የስራ ክንውን 30 ሺሕ የሚጠጋ የሰው ሃይል ማሰማራት መቻሉንም አብራርተዋል።በቀን ወደ 12 ሺሕ ሰው ወደ ሥራ ለማሰማራት ታቅዶ እስካሁን በቀን ከ11 ሺሕ በላይ ሰዎችን ማሰማራት ተችሏል።43 የማስወገጃ ጣቢያ ባሉት በዚህ ዘመቻ ላይ ከአንድ ወረዳ በስተቀር በሌሎች ወረዳዎች ዕቅዱን እንደሚሳካ ግምት አለ ብለዋል።አያይዘውም ለስራው የሚያስፈልጉ ቁሳቁሶችን ድጋፍ የሚያደርጉ አካላት ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።

አገሪቱ ላይ የተጋረጠው ችግር የእምቦጭ አረም ብቻ ሳይሆን ሌሎች ስነ ምህዳራዊ የሆኑ እንደ ድርቅ በረሃማነት የአምበጣ መንጋ ወረርሽኝ እንዲሁም ከእምቦጭ ጋር የሚመሳሰሉ መጤ እና ተዛማጂ አረሞች ጭምር እንደሆኑ የገለፁት የደን እና የአየር ንብረት ለውጥ ባለሙያው አደፍርስ ወርቁ(ዶ/ር) ናቸው።አሁን ከእምቦጭ በተጨማሪ የገበሬውን ሰብል የሚያጠቁ የወፍ ቆሎ የተባለ አረም እና በአፋር ከልል ደግሞ በሳይንሳዊ አጠራሩ ‘ፓርቲኒየም’ ወይንም በአካባቢው ገበሬዎች አጠራር ”የወያኔ ዛፍ” የተባለ አረም የእርሻ መሬታቸውን ወሮታል ብለዋል። እምቦጭን ስናነሳ ደግሞ ይላሉ እኝህ የደን እና የአየር ንብረት ለውጥ ባለሙያ ከዛሬ 10 እና ከ15 ዓመት በፊት በስምጥ ሸለቆ ሐይቆች ላይ ታይቶ እንደነበረ አስታውሰው አረሙ እስከ አርባምንጭ ደርሶ እንደነበር ተናግረዋል።እምቦጭ በስነ ህይወታዊ ባህሪው ከቦታቦታ ይንቀሳቃል በብዙ መንገድ በፍጥነት አበባ አብቦ ብቻ ሳይሆን በቁራጩ ጭምር ስለሚራባ በቀላሉ ለመቆጣጠር እንደሚከብድ አስረድተዋል።

ነገር ግን ቤቱ እየተቃጠለ ማንም ሰው ቁጭ ብሎ ስለማይመለከት አረሙን ለመከላከል ከሚረዱ በርካታ የመከላከያ መንገዶች ለምሳሌ ማሽኖችን መጠቀም ፀረ አረም ኬሚካሎችን መርጨት በስነ ህይወታዊ መንገድ አረሙን ሊመገቡ የሚችሉ ነፍሳን ማራባት እንዲሁም የጎንዮሽ ጉዳት የሌለውን ግን ደግሞ እጅግ ውጤታማ ያልሆነውን የሰው ጉልበት በመጠቀም እና በማሽኖች እየታገዙ እምቦጭን የመንቀል ስራ ተመልሶ እንደይከሰት እየተከላከሉ መሰራቱ አንዱ አማራጭ ነው ብለዋል አደፍርስ(ዶ/ር)። ባለሙያው በተጨማሪ ‹‹ የሰውን ጉልበት የሚቀንሱ ወይም የሚያግዙ ተጨማሪ ማሽኖች ቢገዙ ወይንም ደግሞ ተበላሽተው የቆሙት ቢጠገኑ በጉልበቱ የሚሰራው የህብረተሰብ ክፍል እነዲሁም የአካባቢው ነዋሪ ገበሬዎች ተስፋ እንዳይቆርጡ ይረዳቸዋል›› ብለዋል።ምክንያቱም እንደ እምቦጭ ያሉ መጤ አረሞች በባህሪያቸው ከእኔ አቅም በላይ ነው የሚል ስነ ልቦናዊ ተፅእኖ ስለሚያሳድሩ ብለዋል።

ስለውጤታማነቱ ላነሳንላቸው ጥያቄም ሲመልሱ እምቦጭንም ሆነ ሌሎች መጤ አረሞችን የመከላከል አቅማችን በጣም ዝቅተኛ እና ወደኋላ የቀረን በመሆናችን በጥናት የተደገፈ እና የተቀናጀ ስራ ውስጥ እስከምንገባ ድረስ ይህ መንገድ ብቸኛው አማራጭ እንደሆነ ተናግረው ውጤት ማምጣት ባንችልም እንኳን ይህንን ሥራ እየሰሩ ያሉትን አካላት በማበረታታት እና የሚመለከተው ባለድርሻ አካል የሙህራኑን ምክረ ሃሳብ ወደ ተግባር ማስኬድ አለበት ብለዋል።ምክንያቱም የእምቦጭ አረም ተፈጥሮ ለማጥፋት እጅግ አስቸጋሪ ስለሆነ እና አረሙ የበቀለው ውሃ ላይ በመሆኑ በማሽን ለመንቀል አስቸጋሪ ነው።በሥነ ሕይወታዊ መንገድ አረሙን ሊመገቡ የሚችሉ እንደ ጢንዚዛ ያሉ ነፍሳን ማራባት ደግሞ አረሙን በልተው ሲጨርሱ ለማስወገድ ካልተቻለ ሰብል እና ሌሎች አስፈላጊ ዕፀዋትን ሊበሉ ስለሚችሉ ፀረ አረም መርጨቱም ሌላ ተጨማሪ የጎንዮሽ ጉዳት ስለሚያስከትል እንዲሁም በቂ የሆነ የሰው ጉልበት ስላለን አሁን ያለው ብቸኛ አማራጭ አረሙን ሰው እጅ መንቀል ብቻ ነው ብለዋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 104 ጥቅምት 21 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

error: Content is protected !!