የእለት ዜና

የሞባይል መገጣጠሚያ ኩባንያዎች ከ16 ወደ 5 ቀነሱ

በአገራችን 16 የሚሆኑ የተንቀሳቃሽ ስልክ መገጣጠሚያ ኩባንያዎች የነበሩ ሲሆን ብዙዎቹ ዘግተው አምስት የሚሆኑት ብቻ በአሁኑ ሰአት በስራ ላይ እንደሚገኙ ታወቀ።

አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው የአይሲቲ ኢቲ ሀርድዌር ቡድን ባለድርሻ የሆኑት አብይ ምንውየለት እንዳሉት አምራች ኩባንያዎቹ ከገበያ የወጡበት ምክንያት የመጀመሪያው እና ዋነኛው ምክንያት ለተንቀሳቃሽ ስልኮች መገጣጠሚያ ግብአቶች በአገር ውስጥ አለመኖራቸው ሲሆን በዚህም ምክንያት ከውጪ አገር ማስገባት ስለሚያስፈልግ ይህንን ለማድረግ የውጭ ምንዛሬ እጥረት ከፍተኛ ተግዳሮት መሆኑን ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

የውጪ ምንዛሬ ችግሩ ከፍተኛ እንደሆነ የተናገሩት አምራች ኩባንያዎቹ የውጭ ምንዛሬ ለማግኘት ከሰባት እስከ ስምንት ወር መጠበቅ እንደሚኖርባቸው እና ሲያገኙ ደግሞ የጠየቁትን ያህል እንደማይሰጣቸውም ከጠየቁት ወደ 40 በመቶ ወይም 30 በመቶ የሚሆነው ብቻ እንደሚሰጣቸው ጠቅሰዋል።

በአንድ አመት አንድ ጊዜ የውጭ ምንዛሬ ተፈቅዶ እቃው እስኪገባ የሚወስደው ጊዜ በጣም ብዙ እንደሆነና ሲገባ ደግሞ ጉምሩክ ላይ ይያዝና ተጨማሪ ግምገማዎች ይወጣባቸውና እቃዎቹ ከተገዙበት ዋጋ በላይ ተጨማሪ ቀረጥ ይከፈላል ሲሉም አክለው ገልጸዋል።

እቃው እስኪገባ ድረስ የሰራተኛ ደሞዝ ይከፈላል የፋብሪካ ወጪ ሌሎች ሎሎችም ወጪ አሉ ስለዚህም በዛ ሁኔታ አምርቶ ደግሞ ገበያ ውስጥ ያለው ዋጋ በኮንትሮባንድ በገቡት ምርቶች ምክንያት ሲቀንስ ደግሞ ጭራሽ ከገበያው ጋር መወዳደር ስለማይቻል ፋብሪካዎቻቸውን ለመዝጋት እንደተገደዱ አዲስ ማለዳ ከአምራቾች ያገኘችው መረጃ ያመላክታል።

በፊት ለሞባይል መገጣጠሚያ የሚሆኑ ጥሬ እቃዎችን ሲናስገባ ቀረጥ የለውም ነበር ያሉት አብይ መንግስት ከባለፈው አመት ጀምሮ ተጨማሪ አምስት በመቶ ቀረጥ የጣለበት ሲሆን ፤በተጓዳኝም የኮንትሮባንድ ንግዱ ደግሞ ጭራሽ ቁጥጥር እየተደረገበት አይደለም እንደውም በአሁኑ ሰአት እየጨመረ ነው ሲሉ ተናግረዋል።
ሁለተኛው እና አሳሳቢው ምክንያት የሆነው ኮንትሮባንድ በአሁኑ ጊዜም ወደ 67 በመቶ የሚሆነውን ገበያ የተቆጣጠረው በኮንትሮባንድ የሚገባ ስልክ እንደሆነም ዐብይ አስታውቀዋል።

እንደ ዐብይ ገለፃ በኮንትሮባንድ እቃዎች ሲገቡ ዋጋ ሰብረው ነው የሚገቡት ይህም የሆነበት ምክንያት በኮንትሮባንድ የሚገቡ ምርቶች ምንም አይነት ግብር አይከፍሉም ቀረጥ አይከፍሉም ከትርፍ አቅርቦት ግብር አይከፍሉም ስለዚህ በኮንትሮባንድ አምጥተው ገበያው ውስጥ ይበትኑታል ብለዋል ።

ኢትዮጵያ ውስጥ የነበሩት ሌሎቹ መገጣጠሚያ ኩባንያዎች ወጥተው ሌላ ሀገር መገጣጠሚያ ኩባንያዎችን ከፍተው በኮንትሮባንድ ኢትዮጵያ ውስጥ እየሸጡ እንዳሉም ዐብይ ተናግረዋል። የኮንትሮባንድ ነጋዴዎች ያለምንም የውጪ ምንዛሬ እጥረት መሸጥ ይችላሉ ስለዚህም እዚህ አገር ላይ ከመገጣጠም ይልቅ ኮንትሮባንድ ማስገባት የተሻለ ነው ሲሉም ቅሬታቸውን ለአዲስ ማለዳ አስታውቀዋል።

እስከዛሬ በኢትዮጵያ ቴሌኮም አገልግሎት 40 ሚሊዮን አካባቢ የሚሆን የደንበዮች ምዝገባ እንዳከናወነና በአሁኑ ሰአትም ኢትዮጵያ አዲስ የደንበኞች ምዝገባ ደረጃ ላይ ስላለች በአመት 50 ሚሊዮን ሞባይል ያስፈልጋታል ነው ያሉት ይሄ ደረጃ ከተስተካከለ ወደ 95 በመቶ ከደረሰ በኋላ ግን ኢትዮጵያ ያለማቋረጥ በአመት 20 እስከ 25 ሚሊዮን የሚሆኑ የሞባይል ቀፎዎች እንደሚያስፈልጋት የህዝብ ቁጥር በሚጨምርበት ጊዜ ደግሞ የሚያስፈልጉት የሞባይል ቀፎዎች ቁጥርም እንደሚጨምርም ነው የተናገሩት።

በጉዳዩ ላይ አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው የብረታ ብረት ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትውት የኮርፖሬት ዳይሬክተር ፊጤ በቀለ የተንቀሳቃሽ ስልኮችን አምራች ኢንዱስትሪው በንቃት እየሰራ እንዳለ ተናግረው፤ ነገር ግን አሁን ዘርፉ መዳከም ትልቅ ሚና ያለው የውጪ ምንዛሬ አጥረት እንደሆነና እጥረቱ ደግሞ በአገር ላይ ያለ እንደሆነ ጠቅሰው ለብዙ ኢንዱስትሪዎች መዳከም ከፍተኛ ሚና እንዳለው አስረድተዋል። ያለቁ ምርቶች ከሚያስገቡ ሰዎች ጋር ዶላር መቀራመትም ለአምራች ኩባንያዎቹ ከባድ እንደሆነ ጠቅሰዋል።

እንደ ዳይሬክተሩ ገለፃ ኮንትሮባንድም በዚህ ዙሪያ ከፍተኛ ችግርን እየፈጠረ ነው ብለዋል ለዚህም በቅርቡ የውይይት መድረኮች እንዳሉና የማሻሻያ ስራ እየተሰራ እንዳለ ገልፀዋል።

የጥሬ ዕቃ እጥረት እንደ አገር አለ ያሉት ዳይሬክተሩ አምራቹ ካለው ዘርፈ ብዙ ጥቅም አንፃር መንግስት ለአምራች ዘርፉ ትልቅ ትኩረት መስጠት እንዳለበትና ኢንዱስትሪውን ማገዝ አገርን ማገዝ እንደሆነም ጠቅሰዋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 104 ጥቅምት 21 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com